>

ባልደራስ የከፍተኛ አመራሮቹን የፍርድ ሂደት መጓተት አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ

ባልደራስ የከፍተኛ አመራሮቹን የፍርድ ሂደት መጓተት አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ

 
“የዘገዬ ፍትህ እንደተነፈገ ፍትህ ይቆጠራል”

ከዛሬ ሦስት ዓመታት በፊት ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ ከአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን ሲረከቡ በፓርላማ ውስጥ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ባደረጉት ንግግር ከእንግዲህ “ሳናጣራ አናስርም፤ የሕግ ሥርዓቱም ሥር ነቀል ማሻሻያ ይደረግበታል” የሚል ቃልኪዳን መግባታቸው ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ለሀገሪቱ ሕዝብ ቃል እንደገቧቸው እና ተስፋ ቢስ እንደሆኑት በርካታ ቃልኪዳኖች ይህም ቃል በተግባር ሳይተረጎም ቀርቷል፡፡
በበርካታ ሀገሮች የህግ ሥርዓቱ የዜጎች መሠረታዊ የሆኑ የፖለቲካ፣ የሰብዓዊ እና የንብረት ጥበቃ መብቶች የሚከበሩባቸው፣ በአጠቃላይ የህግ የበላይነት እውን የሚሆንበት ዓይነተኛ ተቋማዊ ሥርዓት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የህግ ሥርዓት  በማይከበርበት ሀገር ስለ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት መናገር አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በሀገራችን ያለው በፖለቲካ ውሳኔ የሚመራው የህግ ሥርዓት እጅግ ከፍተኛ መሻሻሎች ሊደረጉበት የሚገባ ነው፡፡ የህግ ሥርዓት ቁልፍ የሃገር ሰላምና የዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ዋልታ እና ማገር መሆኑ በገዥው ፓርቲ ግንዛቤ ሊያገኝ አልቻለም፡፡
 በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ በገሃድ እያስተዋለ ያለው ፍትህ መጓደሉን እና ፍርድ ቤቶች የፍትህ ቤቶች መሆናቸው ቀርቶ የፖለቲካ ሥርዓቱ መሣሪዎች መሆናቸውን ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች ፍትሃዊ ዳኝነት ከመስጠት ይልቅ ፍትህን በማዛባት እና ታሣሪዎችን በማንገላታት የተካኑ ሁነው ተገኝተዋል፡፡
     በሀገራችን ያለው የፍትህ ሥርዓት አራት ጉድለቶች እንዳሉበት እየታዬ ነው፡፡ እነዚም፡- 
1. በፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ የሚታየው የመጀመሪው ከፍተኛ ጉድለት የፍትህ ሥርዓቱ ከአስፈፃሚው መንግሥታዊ አካል ተፅዕኖ ያልወጣ፣ የፖለቲካ መሣሪያ እና መገልገያ የመሆኑ ችግር ነው፡፡
2. የሃገራችን የህግ ሥርዓት ዓይነተኛ ድክመትና ልዩ መገለጫውበሙያው በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ዳኞች እና አቃቤ ሕጎች በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች አለመመደብ፣ታማኝነታቸው ለህግ ሳይሆን ለሥልጣናቸውመሆኑሲሆን ይህም ሕዝብ በፍትህ ሥርዓቱ ተስፋ እንዲቆርጥ እያደረገው መጥቷል፡፡
3. የፍትህ ሥርዓቱ እንዲሻሻል እና መሠረታዊ ለውጥ እንዲኖረው ማድረግ የሚችሉ የመንግሥት የሕግ አውጭና አስፈፃሚ አካላት ለውጥ እንዲደረግ ያለመፈለጋቸው አንዱ ችግር ሆኗል፡፡
4. የሀገራችን የፍትህ ሥርዓት ሌላው ጉድለቱ በሙሰኝነት የተተበተበ መሆኑ ነው፡፡
የተዘረዘሩት ችግሮች ሳይፈቱ በሃገራችን የፍትህ ሥርዓቱ ተሻሽሏል ብሎ ማለት አይቻልም፡፡ በተለይ ደግሞ የፍትህ ሥርዓቱ የገዢው ፓርቲ ፍላጎት ማስፈፀሚያ ሆኖ መገኘቱ ለሀገራችን ሰላም መታጣት ዓይነተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑ እየታየ ነው፡፡
ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. የሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ አስመልከቶ የተቀሰቀሰውን ሁከትና ግጭት ሰበብ በማድረግ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዘዳንት አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብ ስዩም እና ወ/ሪት አስካል ደምሌ ያለምንም ቅድመ ማጣሪያ ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡የፍትህ ሥርዓቱ እነዚህን የፓርቲያችን አመራሮች በተገቢው ህጋዊ መንገድ ሊያስተናግዳቸው አልቻለም፡፡ ይኸውም አቃቢ ህግ አንድ ጊዜ ምስክሮችን ከመጋረጃ ጀርባ ላሰማ ሲል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ምስክሮቼ በገሃድ የሚመሰክሩ ከሆነ ለዚህ የሚያስፈልገውን በጀት ላሰባስብ፣ … ወዘተ. የሚሉ ሰንካላ ምክንያቶችን በማቅረብ ላለፉት 13 ወራት አላግባብ እያንገላታቸው ይገኛል፡፡ይኸ ድርጊቱ ኦህዲድ መራሹ ብልፅግና ፓርቲ የወላጅ አባቱ የህወሓት አምሳያ ልጅ መሆኑን ይመሰክርበታል፡፡በዚህ አጋጣሚ ፓርቲያችን “የዘገዬ ፍትህ እንደተነፈገ ፍትህ ይቆጠራል” (‹‹Justice delayed is Justice denied››) የተሰኘውን ምርጥ የእንግሊዘኛ ፍትህ ነክ አባባል በመፈክርነት ሊያነሳ መገደዱን መግለጽ እንወዳለን፡፡
 ባልደራስ ከፍተኛ ሀገራዊ ሓላፊነት እንደሚሰማው ፓርቲ አመራሮቻችን በህግ ሊያስጠይቃቸው የሚችል ተግባር ያለመፈፀማቸውን ስለሚያምን፣‹‹በ6ኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ እንዳይሳተፉ በኢትዮጵያ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መከልከላቸው ህጋዊ አይደለም፡፡›› በሚል ክስ ከፍቶ በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች ተሟግቷል፡፡ በኋላም ላይ በሰበር ሰሚ ችሎት ‹‹መወዳደር ይችላሉ›› የሚል ብይን እንዳገኘና አመራሮቹ በእሥር ቤት እያሉም ቢሆን በምርጫው እንዲወዳደሩ ማደረጉ ይታወሳል፡፡
 በመጨረሻም አሁን በያዝነው ሀምሌ ወር አጋማሽ ላይ አቃቢ ሕግ ምስክሮችን ለማቅረብ በተፈቀደለት 5 ቀናት ውስጥ አሰምቶ ጨርሶ ፍርድ ይሰጣቸዋል ብለን ስንጠብቅ፣ የፍትህ ሥርዓቱ የምስክር ማሰማቱን ሂደት እንዲሰናከል አድርጎታል፡፡
ፓርቲያችን ባለፉት ወራት ሀገራችን የገባችበትን ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሂደቱን በትዕግስት ለመከታተል ቢሞክርም በገሀድ እየተፈፀመ ያለው የፍትህ መዛባት ግን መሸከም ከምንችለው በላይ ትከሻችንን እያጎበጠው መጥቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በቂሊንጦ ወህኒ ቤት በሚገኙት በፓርቲያችን ፕሬዘዳንት በአቶ እስክንድር ነጋ እና በአቶ ስንታየሁ ቸኮል ላይ በተለይ ከሀገር አቀፉ ምርጫ በኋላ በእስር አያያዛቸው ላይ እየተፈፀመ ያለው ከባድ ጫና ፓርቲያችንን በከፍተኛ ደረጃ አሳስቦታል፡፡
በተዘረዘሩት ምክንያቶች ፓርቲያችን ለፍትህ መስፈን የሚያደርገውን ሰላማዊ ትግል ወደ ከፍተኛ የሰላማዊ ትግል ደረጃ ለማሸጋገር ወስኗል፡፡ በዚህ የሰላማዊ ትግል፣ የጥሪ ስምሪቱን እንቅስቃሴ የሚያቀናጁ አንድ ግብረ ኃይልና የተለያዩ ኮሚቴዎችን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር እንዲቋቋሙ ለማድረግ ፓርቲያችን በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በየደረጃው የሚቋቋሙት ግብረ ኃይል እና ኮሚቴዎች በቀጣይ የሚካሄደውን ሰላማዊ ትግል በቁርጠኝነት እንደሚመሩ የባልደራስ ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሙሉ እምነት ያለው መሆኑን መግለጽ ይሻል፡፡
በመጨረሻም ከታሣሪ አመራሮቻችን ጎን በመሆን በየፍርድ ቤቱ እና በየእሥር ቤቱ በመመላለስ ተቆርቋሪነታችሁን እና ድጋፋችሁን ላሳያችሁ  የፓርቲያችን አባላትና ደጋፊዎች በሙሉ የድርጅታችን የብሔራዊ ሥራ አሥፈፃሚ ኮሚቴ ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባል፡፡ በውጭ ሀገርም ያላችሁ ወገኖቻችን ለታሠሩት የአመራር አባሎቻችን በተለያዩ መንገዶች ድጋፋችሁን ስላደረጋችሁ ልባዊ ምሥጋናችን ይድረሳችሁ፡፡
የፓርቲያችንን መሪዎች እስራትና የፍርድ ቤት ውሎ አስመልክቶ በተለያዩ ጊዜያት የሕዝብ ዓይንና ጆሮ በመሆን በየጊዜው መረጃዎችን ስታሰራጩ የነበራችሁ የመገናኛ ብዙኃን አካላት ላከናወናችኋቸው ሙያዊ ተግባራት ከልብ እናመሰግናለን፡፡ ወደፊትም በፓርቲያችን የሚተላለፈውን የሰላማዊ ትግል ጥሪ በተለመደው ትብብራችሁ ለኅብረተሰቡ እንድታደርሱልን አደራ እንላለን፡፡
በአመራሮቻችን ላይ በእስር ቤት እየተፈጸመ ያለው የመብት ጥሰት እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሁኔታውን አጣርታችሁ ድምፃችሁን ልታሰሙ ይገባል እንላለን፡፡
በአሁኑ ወቅት ህወሓት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ወደማይፈለግ የእርስ በእርስ ጦርነት በማስገባት የሀገራችንን ህልውና ለማናጋት የጀመረውን እኩይ ድርጊት ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በጽኑ ያወግዛል፡፡
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ 
የብሔራዊ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ሐምሌ 20/2013 
አዲስ አበባ
Filed in: Amharic