>

እናየው ይሆን ይህን ቀን አልፈን?!? (በእውቀቱ ስዩም)

እናየው ይሆን ይህን ቀን አልፈን?!?

(በእውቀቱ ስዩም)

በጦር መርታት ነው፤ የሁሉም ተስፋው
የሰላም ዋጋ መቸ ታሰበ?
አብሮ ለመኖር መላው የጠፋው
አብሮ ለመሞት ተሰባሰበ::
እንዳውሬ መኖር ፤እንደ ሰው ለብሶ
እብዱን ስንፈራው ፤ ጭምቱ ብሶ
“ውረድ እንውረድ” የሁሉም ዘፈን
እናየው ይሆን ፤ ይሕን ቀን አልፈን ?
የሞት ፈረስ ነው፥ አንደኛው ላንዱ
የሁሉም ክንዱ-
-ለማነቅ ተግቶ ፤ ለማቀፍ ዛለ
“ አንተኛው ታገስ፤ አንተም ተመለስ “
የሚል የታለ?
እንደ ጥጥ ሸክም ፤ ሽበት ቀለለ
መስቀል ጨረቃው አልተከበረ
ማርጀት ነው እንጂ መሸምገል ቀረ : :
Filed in: Amharic