>

ክፉኛ እንዳትሸነፍ፣ ሕዝብና ሀገርህን እንዳታዋርድ ከርስትህ አትንቀል፤ ከስፍራህን  ንቅንቅ አትበል...!!! (ጌታቸው ሽፈራው)

ክፉኛ እንዳትሸነፍ፣ ሕዝብና ሀገርህን እንዳታዋርድ ከርስትህ አትንቀል፤ ከስፍራህን  ንቅንቅ አትበል…!!!

ጌታቸው ሽፈራው

 

ከቦታህ ንቅንቅ እንዳትል! የፀጥታ ኃይሉ አንተን የመጠበቅ ግዴታ አለበት። ዝም ብሎ ከለቀቀ ወንጀል እየሰራ ነው።  የሀገር ክህደት ነው! ያሳስራል፣ ያስረሽነዋል።
ትህነግ  በወረራቸው የቅርብ ርቀት ያሉ ቦታዎች  ጥቃት ሰግተው የሸሹ አሉ። በአንፃሩ ግን ትህነግ በአማራ ከተሞች ሰርጎ ገብ ኃይል አሰማርቷል። በ2008 ዓ/ም በተለያዩ የአማራ ከተሞች በደሕንነት ስራ ተሰማርተው የነበሩና ከትግሉ በኋላ የሸሹ ወደአማራ ክልል ከተሞች እየተመለሱ ነው። ብዙ ሰው ተይዞበታል። አንተ ገና ትህነግ ያልያዘው ቦታ ላይ በውዥንብር ስትወጣ የትህነግ ኃይል ራሱን ቀይሮ ወደ ዋና ዋና ከተሞችህ ይገባህ። ይህ ውርደት ነው!
በእርግጥ ትህነግ በወረረባቸው አካባቢዎች ሰው የሚሸሸው ዘር ጨፍጫፊነቱን ስለሚያውቅ ነው። እንደ ማይካድራ ያሉ ጭፍጨፋዎች ይፈፅማል ከሚል ስጋት ነው። ግን የት ነው የሚኬደው? አዲስ አበባ ድረስ ብትሸሽለት ይመጣል። ሌላው ቀርቶ ሱዳን ድረስ ሄደው እያጠቁ ነው። ሱዳን ውስጥ የሚገኙ ስደተኛ ካምፕ የሚገኙ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ተፈናቃዮችን የትህነግ ስደተኞች ለማጥቃት ሞክረዋል። የትም ብትሄድ እነሱ ከማጥቃት አይመለሱም። መፍትሄው ከቦታ ንቅንቅ አለማለት ነው። ቀየህ ከየትኛውም ቦታ የተሻለ የምታውቀው ነው። ስትለቀው  ጠላት ዘርፎት ይሄዳል። ጥለሃቸው የሄድካቸውን ወገኖች ይገድላል።  ቦታውን ለቅቆ ከመጣው ይልቅ አንተ የማሸነፍ መአት እድል አለህ። ትግራይ ውስጥ ሕዝብ ነው መከላከያውን ቤት ውስጥ ሆኖ ያጠቃው።  አካባቢህን የሚከላከል የፀጥታ ኃይል የአንተን ደጀንነት ይጠብቃል። አንተ ቀየህን ለቀህ ከሌላ አካባቢ የመጣ የፀጥታ ኃይል የአንተን ጋራ ሸንተረር ወጥቶ ወርዶ ሊጠብቅልህ አይችልም። መሳርያ ስለያዘ ብቻ አይደፍርም። አንተ ስትሸሽ እሱም ሊሸሽ ይችላል። አንተ ሸሽተህ፣ ሌላውም ሸሽቶ ሕዝብንና ሀገርን ታዋርዳለህ!
አንተ ከቦታህ ንቅንቅ ካላልክ ታሸንፋለህ። የራስክን ትጠብቃለህ። የሚሸሽ ካለ ታስቆማለህ።
መከላከያ በለው ልዩ ኃይል በለው ሚሊሻ አንተን ሊጠብቅ ነው በቦታው የተገኘው!  መጀመርያ ደጀን መሆን ነው። ደጀን እየሆንከው ያለ አግባብ እንቀሳቀሳለሁ የሚለውን፣ ተበታትኖ የሚወጣ ቢኖር “የት ትሄዳለህ?” ብለህ የመያዝ መብትም ግዴታም አለህ። ያለ አግባብ ከግንባር መሸሸት ወንጀል ነው። ቀላል ወንጀል ሳይሆን በወታደራዊ ሕግ ያስረሽናል። የሚያስረሽን ወንጀል እያየህ ዝም ብለህ አታልፈውም። ከተመለሰ ታግዘዋለህ። እሄዳለሁ ካለ ግን የወንጀሉን ዋጋ እንዲያገኝ ማድረግ ነው። ስለሆነም ሴራ የሚሰራ ቢኖር እጁን ይዘህ እስር ቤት የሚገባበት መንገድ መፈለግ መብትህ ነው።  ግዴታም አለብህ። ሰብሰብ ብለህ ሕግን ማስከበር ነው። በየአካባቢው ተደራጅቶ ጠላትንም ወዳጅንም መጠበቅ ያስፈልጋል። ጦሩ በደንብ ከተመራ አይሸሽም። የሚሸሽ ቢኖር ግን እንዲታሰር ብታደርገው ውለታ እንደዋልክለት ይቆጠራል። በሕጉ መሰረት ቀጥታ እርምጃ ነው የሚወሰድበት! መሳርያ ያዝክ አልያዝክ አንተም ንቅንቅ ሳትል፣ እሱም እንዳይነቃነቅ በማድረግ መታገል ነው። ትህነግ የእሱ ደጀን በሌለበት የአንተ ትልልቅ ከተማ ሰርጎ ገብቶ እየሰለለ፣ ወሬ እያስወራ፣ አንተ በወሬ አካባቢህን ለቀህ ከወጣህ የራስህ ችግርም ነው።
የፖለቲካ አመራሩ ከአንተ በላይ ግዴታ አለበት። ሕዝብን ማረጋጋት፣ የፀጥታ ኃይሉን ማስተባበርና ማገዝ ግዴታ አለበት። ይህን መስራት ሲገባው የሽብር ወሬ የሚያስወራ፣ ጭራሽ ልሸሽ የሚል ከሆነ ወንጀሉ ከፍ ያለ ነው። የሀገር ክህደት ነው። ሀገርን እበትናለሁ ለሚል አሸባሪ ክፍት ቦታ መስጠት ነው፣ለጠላት ማገዝ ነው፣ መተባበር ነው። አውቆትም ይሁን ሳያውቀው። ስለሆነም አመራሩ ኃላፊነቱን ካልተወጣ ወደ እስር ቤት እንዲገባ መሰራት አለበት። ወሬ አስወርቶ፣ እሸሻለሁ ብሎ ከተማው ሲረጋጋ ተመልሶ ስልጣን ላይ ሊቀመጥ አይችልም። የክልሉ መንግስትም በመሰል አመራር ላይ ቆምጨጭ ያለ እርምጃ መውሰድ አለበት። ስልጣኑን መልቀቅ ብቻ አይደለም። ስልጣን ለቆ እስር ቤት መግባት አለበት!
ብቻ አንተ ከቦታህ ንቅንቅ አትበል። ብትለቅ ትህነግ የትም ይከተልሃል። የአንተን ቦታ እንዳይዝ ቦታህን ይዘህ መቆየት አለብህ። አንተ አርዓያ ካልሆንክ አንተ ለቀህ የገባህበት ሌላ ከተማ ነዋሪም እንዳንተው ይለቃል። ወደሌላ ከተማ መልቀቅህ ነው። ለቅቆ መውጣት የሚቆመው አንተ ይህን ሽንፈት ስታስቆም  ነው።  ከራስህ ይጀምራል። ትህነግ ከአዲስ አበባ ጀምሮ በርካታ ከተሞች ላይ ሰርጎ ገብ አስገብቷል። ከትግራይም ከሱዳንም ከሌላም ቦታ መጥተው ያንተ ከተማ ላይ ሲሰርጉ አንተ ከለቀክ ችግር ተፈጥሯል ማለት ነው። ከቦታህ ንቅንቅ እንዳትል!
Filed in: Amharic