>

"አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ"!! በታምራት ላይኔ  የቡና ስርዓት ንጹሀን ወደ ወህኒ...!!! (ዳንኤል ገዛህኝ)

ክፍል 2
አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ”!!
በታምራት ላይኔ  የቡና ስርዓት ንጹሀን ወደ ወህኒ…!!!
ዳንኤል ገዛህኝ

 

ወደ ወረዳ 14 እስር ቤት ከተመለስኩ በሁዋላ ወታደር ውብ እሸት መርማሪዬ የአስር ሺህ ብር ዋስ አዘጋጅ አለኝ። ይሁን እንጂ ፍርድ ቤት ግን የፈቀደልኝ ዋስትና በቂ ዋስ ነበር። ይህም ማለት መታወቂያ ያለው ማንኛውም ሰው ሊያስፈታኝ ይችላል። የተጠየቅኩትን ዋስትና መልእክት ወደ ሙያ ጓደኛዎቼ ላኩኝ ። ወድያው የቃልኪዳን መጽሄት አሳታሚ እና ማኔጄኒንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ኤልያስ ጉዲሳ አሁን አውስትራሊያ ይገኛል፣ የፈታሽ ጋዜጣ አሳታሚ ዘርይሁን ዳምጠው ሌሎችም ዘነጋሁዋቸው የሚያስፋልገውን ፎርማሊቲ አሟልተው ሊያስፈቱኝ ቀረቡ።
በእለቱ ተረኛ ጠባቂ የነበረው ወታደር አምባዬ ወደ መርማሪ ቢሮ ይዞኝ እንዲቀርብ ሲነገረው ከእስር ቤት ክፍል ጠርቶ ካስወጣኝ በሁዋላ ጸያፍ ስድብ ሰደበኝ ። እንደዛ ማለት አትችልም በማለቴ ብቻ ወገቤን በታጠቀው መሳርያ ሰደፍ መታኝ ። ተንገዳግጄ ቆምኩኝ ለመናገር ለቃላት አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ሌላ አንድ ወታደር ተጨምሮ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጸመብኝ። ወታደር አምባዬ ክብሬን  ዝቅ የሚያደርግ ስድብ ሰድቦኛል በሚል ሰበብ መልሶ ወደ እስር ቤት አስገባኝ። እናም ክስ እንደሚመሰረትብኝ ተነግሮኝ ጥቂት ተጨማሪ የእስር ቀናት ቆይቼ ከእስር በዋስትና ተለቀቅኩ። ከዚያ በሁዋላ ጋዜጣችን ገመና በህትመት አልቀጠለችም። ወድያው ነፍሱን ይማረው፣ አፈሩን ገለባ ያድርግለት እና በጋዜጠኛ ከተማ ሀ/ማርያም አሳታሚነት ህትመት በጀመረችው ራይት ጋዜጣ ላይ መስራት ጀመርኩ። እሷም ብዙ አልቆየችም ወደቃልኪዳን መጽሄት እና ጋዜጣ ላይ እየሰራሁ ሁለት ያህል አመታት ግድም እንደቆየሁ በመሀል አሁን የማልጠቅሳቸው የተለያዩ የፕሬስ ክሶች ነበሩ። ለጥቆ በ1993 ከእለታት በአንዱ ቀን። መደበኛ ስራዬን ከጓደኛዎቼ ጋር ስሰራ አምሽቼ ወደ ቤት ስገባ አንድ ውመልእክት ጠበቀኝ። መርማሪዎች ከወረዳ 14 መጥተው መልእክት ትተውልሀል ነገ ጠዋት የማትገኝ ከሆነ አዛውንቷን አክስቴን እንደሚያስሯት አስጠንቅቀው መሄዳቸው ተነገረኝ።
አላንገራገርኩም ሁልጊዜም እንደሚሆነው በሰአቱ እንደምገኝ ለራሴ ቃል ገብቼ አደርኩ።
ወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከፍተኛ አመጽ የሚያሰሙበት ነበረ እና በየእስር ቤቱ በርካታ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚጋዙበት ነበር። ወረዳ 14 ስደርስ ከአራት ኪሎ እስከ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ድረስ ከፍተኛ አመጽ እና ረብሻ እየተካሄደ ነው ።
ወረዳ 14 ግቢ አይታይም በሩ ላይ ወደ አራት ኪሎ በሚዘልቀው መንገድ በስተቀኝ አራት አውቶብሶች ተደርድረዋል።
ወደ ፓሊስ ጣቢያው ግቢ ስዘልቅ ግቢው በሰው ተሞልቶዋል። በተለይ የተማሪ ዩኒፎርም የለበሱ የኤለመንተሪ ወንድና ሴት ተማሪዎች ግቢውን አጨናንቀውታል። እንደምንም ወደ ውስጥ ለማለፍ ብሞክርም ጠባቂዎች ውደ ውስጥ መግባት እንደማልችል ከማስፈራርያ ጋር ነገሩኝ። እኔ ደግሞ ተፈልጌ መምጣቴን ተናግሬ የአዲስዋን መርማሪዬን ስም አሳውቄ የእስዋን ቢሮ ጠየቅኩ። እስር ቤት…ፓሊስ ጣቢያ በዚያ መልኩ ሲሞላ አይቼ አላውቅም።ሲበዛ ወጣት እስረኞች በግቢው ተጠቅጥቀዋል። እንደምንም መርማሪዬን አገኘሁዋት ቀደም ሲል መርማሪዬ የነበረው ወታደር ውብእሸት በግምገማ መባረሩን ሰምቻለሁ። መርማሪዋ ወደ ውስጥ እንዳያስገቡኝ ለጠባቂዎች አስጠንቅቃ ተረኛው ቀበቶ አስፈቶ በኪሴ ያለውን ተረክቦ  ለብቻዬ ከወደ አንድ ጥግ አስቀመጠኝ። መደበኛ እስር ቤቱም ግቢውም ሞልቶ ተጨናንቆዋል። የተሰጠኝ ቦታ ባዶ መሬት ላይ ጸሀይ እየወረደብኝ እስከ እኩለ ቀን ድረስ ዋልኩ። ነፍስዋን ይማረው እና የፈረደባት አዛውንትዋ አክስቴ ምግብ እና መኝታ አቀበለችኝ። ማምሻውን ወደ መርማሪዎች ቢሮ ተዛውሬ አግዳሚ ወንበር ላይ እንዳድር ተደረግኩኝ።
ሌሊቱን ከደረቅ አግዳሚ ወንበር ላይ ስገላበጥ አድሬ ጠዋት መርማሪዬ መጥታ እቃህን ያዝ ብላ ስታበቃ ሁለት እጆቼ ላይ ካቴና አጠለቀችልኝ። ካለኝ ልምድ አንጻር የፓሊሶች ካቴና እጅ በተንቀሳቀሰ ቁጥር እየጠበበ..እየጠበቀ እጅን ያሰለስላል። ከካቴናው የሚተርፈውን የእጅ ክፍል ያሳብጣል።
መርማሪዬ የትራንስፖርት ገንዘብም እንዳዘጋጅ አሳሰበችኝ። አልተከራከርኩም ግን በካቴና ተጠፍሬ ከሰዎች ጋር ከምጋፋ በሚለው በአራት ኪሎ ላዳ ተሳፍረን ልደታ ደረስን። የራሴንም የአሳሪዬንም ሂሳብ እኔው ከፍዬ…
ልደታ ፍርድ ቤት እንደደረስን አንበሳ ቤት ከምትባለው ፍርግርግ ጥቂት አቆይታኝ መርማሪዬ ከችሎቱ ጀርባ ወደ ፊትለፊቱ መግቢያ ስታመጣኝ በቅጡ ያላየሁት ሰው “ለእኛ ካቴና ለእኛ ሰንስለት” ሲል ጆሮዬ ጥልቅ አለ…የመይሳው ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ወንድወሰን መኮንን እና አብሮት የነበረው የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች ማህበር ስራ አስፈጻሚ አሁን ላስቬጋስ የሚገኘው የህብር ሬድዮ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሀብታሙ አሰፋ ነበሩ። ሰላምታ ተለዋውጠን መንፈሴን አበረታተው ችሎቴን ጠይቀውኝ ተለየሁዋቸው። ከመርማርዬ ጋር ወደ ችሎቱ አዳራሽ ገብተን እስረኛ ከሚቀመጥበት ስፍራ እንድቀመጥ ታዘዝኩኝ። ጥቂት ቆይቶ ፓሊስ ጣቢያ የተውኩትን መኝታና ጥቂት የሚነበቡ ጋዜጦች ይዞ ጓደኛዬ ጋዜጠኛ ብንያም ታገሰ ከችሎቱ ደረሰ ። በአንገት ሰላምታ ተለዋወጥን። የችሎቱ አዳራሽ እየሞላ በእስረኛ እና ከአፍ እስከ ገደፍ በታጠቁ ወታደሮች እየተሞላ ሄደ።
የታሰርኩበት ካቴና እጄን በጣም አጥብቆኛል ህመሙን መቋቋም አልቻልኩም ። ይህ ሁሉ እነ ታምራት ላይኔ በመዘበሩት የቡና ስርቆት ነው። ይቀጥላል።
Filed in: Amharic