>

ሰላምን እሻት፤ ተከተላትም...!!! (ጴጥሮሳውያን የቤተክርስቲያን መብትና ክብር አስጠባቂ)

ሰላምን እሻት፤ ተከተላትም…!!!

ጴጥሮሳውያን የቤተክርስቲያን መብትና ክብር አስጠባቂ

 


 

በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ጦርና የጦርን ወሬ መስማት ከጀመርን ስምንት ወራት ተቆጠሩ። ሰላም የማስከበር ዘመቻ ተብሎ የተጀመረው ውጊያ በውጪ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ወደለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲያመራ ሲሠራ ቆይቶ አሁን ካለበት ደረጃ ደርሷል። በተለይም ለሰላም ማስከበር ዘመቻ የሔደው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት  ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ ሌላ ዐይነት መልክ ያለው ጦርነት ተጀምሯል። በዚህ ጊዜ ውስጥ በውጊያው ውስጥ ቀጥተኛ ሱታፌ የነበራቸውን ብቻ ሳይሆን በውጊያው ቀጠና ውስጥ የነበሩ በርካታ ንጹሐን ኢትዮጵያውያንን አጥተናል። አሁን የተጀመረው ጦርነት ማንንም አሸናፊ የማያደርግ፣ ነገም በታሪክ ፊት የማንኮራበት፣ ኢትዮጵያዊ ማንነትን የሚያጠለሽ፣ በውጪ ጠላት ላይ የውስጥ ሥጋት የሚጨምር፣ ብዙዎቹ ቃሉን ባይወዱትም “የወንድማማቾች ጦርነት” ነው። ትናንት ከኤርትራ ጋር በነበረው ጦርነት ኤርትራና ኢትዮጵያ በጠላትነት ተፈራርጀው ብዙ ጥፋት ደርሷል። ዛሬ የትናንቱን ቁስል ረስተን ሰላም በመፍጠራችን የኤርትራ ወንድም ሕዝብ፣ የኢትዮጵያ ወንድም ሕዝብ መባባል ጀመርን። አትራፊው መንገድ ሰላም ነው። በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ከሰባ ሺ በላይ እህት ወንድሞቻችን ገብረናል። ከዚህ ሁሉ ዕልቂት በኋላ የተጣላንበትን አፈር ባለቤት ለመወሰን በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰይመናል። ጦርነቱ ሺዎችን ከመብላቱ ውጪ ለሁለቱም አገራት ያመጣው አንዳችም ረብ ወይም ጥቅም ያበረከተው ገጸ በረከት የለም። ዛሬም እየሆነ ያለው ይኸው ነው – ታሪክ ራሱን እየደገመ።
“ታሪክ የሚጠቅመው ሰው ከታሪክ እንዲማር ነበር፤ ነገር ግን ታሪክ ራሱ የሚነግረን ሰው ከታሪክ አለመማሩን ነው” የሚለው በእኛ እየተፈጸመብን ይመስላል። ጦርነትን የሚወዱት አይዋጉም፤ የሚዋጉት ደግሞ በአንጻሩ አይወዱትም። ጦርነትን የማይፈልጉት የጦርነቱ ሰላባ ይሆናሉ፤ የጦርነቱ ጠንሳሾች በሌሎች ሞት ጥቅማቸውን ያስከብራሉ። የጦርነት መጥፎ ገጽታው ይኸው ነው። በጦርነት ወቅት ጦርነቱም ውስጥ ያሉ ወታደሮች ይሁኑ በጦርነቱ ቀጠና አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ይሞታሉ፤ ይቆስላሉ፤ ይንገላታሉ፤ ከቀያቸው ይፈናቀላሉ፤ ብዙ የመከራ ዶፍ ይወርድባቸዋል። እንደ አገርም ትልቅ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ይፈጠራል። ይህ የጦርነት መሠረታዊ መገለጫው ስለሆነ ወደ እኛ አገር ሲመጣ መልኩ ሊለወጥ አይችልም። እስካሁን ብዙዎችን አጥተናል። በውጪ አካላት ሴራ በጥላቻ ዐይን የምንተያይ ሆነናል። ነገር ግን የሰላም ዐይናችንን ብንገልጥ አንድ አገር፣ አንድ ሕዝብ ነን። በአንዳችን ሞት ሌላችን ሐሴት አናደርግም። ወንድማችንን ገድለን ጠላት እንደመለሰ ጀግና በድል አንዘምርም። የሚያዘምር ድል የሚገኘው በጋራ በማሸነፍ እንጂ አንዳችን አንዳችንን በመጥለፍ አይደለም። ስለሆነም ከጦርነት በመለስ ያሉ አማራጮችን ማማተር ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ነን ብለን እናምናለን።
በዚህ ሁሉ መሐል በጦርነት የሞቱ ወንድሞቻችንን አስከሬን እየለጠፉ “ዛሬ ሺ ገደልን” እያሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ንግድ የሚያጧጡፉ ወገኖች አሉ። እውነት ይህ ድርጊት ስንኳ ኢትዮጵያዊ ከሆነ ሰው ከማንም የሚጠበቅ አይደለም። እናት እኮ የልጇን ሞት ሳታይ በመሞቷ የታደለች ናት ተብሎ የሚነገርላት፣ የልጇን አስከሬን አይደለም እንቅልፉን ማየት የሚያስፈራት ናት። ማን ወልዶን፣ የት አድገን ነው የእንዲህ ዐይነት የሚያሳፍር ሰብእና ባለቤት የሆንነው? በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ጠላት ተሸንፎ አርበኞች ወደ አዲስ አበባ ሲገቡ በደም ፍላት እንዳይገድሏቸው ብለው ጣሊያናውያንን የሚደብቁ ኢትዮጵውያን ነበሩ። ከዚህ የሞራል ልዕልና ወርደን ዛሬ በወንድማችን አስከሬን የምንሳለቅበት ምክንያት ምን ይሆን? ከላይ የተጠቀሰው ዐይነት የሞራል ልዕልናና መንፈሳዊነት ባይኖረን ስንኳ ከኢትዮጵዊ ሰብአዊነት ውኃልክ መውረድ የለብንም።
ይህ ጦርነት እንዲቀጥል የሚፈልጉ፣ ከጦርነቱ ትርፍ እናገኛለን ብለው የሚያስቡ ወገኖች ከዚህ የቁም ቅዠታቸው መንቃትና ወደ ራሳቸው መመለስ ይገባቸዋል። ያለ በደላቸው አካባቢያቸው የጦርነት ቀጠና ስለሆነ ብቻ መከራ እየተቀበሉ ያሉ ወገኖች ሥቃይ ሊያመንና ሊሰማን ይገባል። “መንገድና ነገር ካልተውት አያልቅም” እንደሚባለው በማይጠቅምና ካልተውነው በማያባራ ጦርነት ምክንያት በቀጣይ የሚደርሰውን ጥፋት በማሰብ ሰው የሆንበትንና ሰው የሚያደርገንን ግብር እንፈጽም። በዙሪያችን ያለውን ጠላት ብንስማማ የምናገኘውን በረከት አተኩረን በመመልከት ከግላዊ ትምክህት እንውጣ። አንዳንችን ለሌላችን ለመኖራችን ምክንያት እንጂ የህልውና ስጋት መሆን የለብንም። ሀገር ለማጥፋት፣ ሃይማኖት ለማስካድ ከመጡት ከእውነተኞች ጠላቶቻችን ጋር ባደረግነው ተጋድሎ ሞታችን ነጻነታችንን፣ አኩሪ ታሪካችንን፣ ኢትዮጵያዊ መልካችንን አትርፎልናል። እነዚህ አካላት ለእኛ መልካም የሚሹ አይደሉምና ፊት ለፊት መጥተው ገጥመው ሲሸነፉ በእጅ አዙር ኢትዮጵያን ለመበታተንና ለማዳከም ይታትራሉ። ለምተን እንዳናድግ፣ ሰላም ሆነን አንድነታችን እንዳይጠናከር በወንድማማቾች መካከል ጠብ በመዝራት የቁም ቅዠት የሆነ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሕልማቸውን ለማሳካት እየተሯሯጡ ነው። እንዲህ ዐይነቱን የጠላት ሴራ ማክሸፍ የሚቻለው ደግሞ ለሰላም ዘብ በመቆምና አገራዊ አንድነትን በማጠናከር ነው።
ለኢትዮጵያም ለኤርትራም አንዳች ትርፍ ባላመጣው የሁለቱ አገራት ጦርነት ከግራም ከቀኝም የወገኖቻችን ሕይወት በመቅጠፍ አቅማችን እንዲዳከም ካደረጉ በኋላ ራሳቸው ሽማግሌ አድርገው በመሰየም የግል ጥቅማቸውን ለማስከበር ተጠቅመውበታል። የዛሬውም ከዚያ ያለፈ አይሆንም። በአንድ በኩል የጦርነት ነጋሪት በመጎሰም በሌላ በኩል ደግሞ የሰላም ሽማግሌ በመምሰል የተለመደ ድራማቸውን ቀጥለዋል። ኢትዮጵያ የማንንም ሽምግልና አትፈልግም። ለራሷ አይደለም ለዓለሙ የሚተርፍ አኩሪ የሽምግልና እሴት ያላት አገር ናት። በህልውናችን ላይ የተጋረጡ ጠላቶችን በአንድነታችን ድል እንደነሣናቸው፣ በመካካለችን ጠብ ለመዝራት የሚደክሙ የቀበሮ በሕታውያንን በሰላምና በወንድማማችነት ፍቅር ልናሳፍራቸው ይገባል። ይህ ጦርነት ጠላቶቻችን በመራናቸው የሞት መንገድ ሔዱልን ብለው ደስታ ፌሽታ ከሚያደርጉብን፣ አቅማችንን በማዳከም ትንኮሳ መፈጸም ለሚፈልጉ አካላት ከማመቻቸት፣ የኢትዮጵያን ዕድገትና ወደ ቀደመ ክብሯ መመለስ ለማይፈልጉ አካላት እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር ያሻቸው ለማድረግ ምቹ ዕድልን ከሚፈጥር በቀር እንደ አገር ለኢትዮጵያ እንደ ክልል ለትግራይ የሚያመጣው በጎ ነገር የለም። እስካሁን ክቡር የሰው ሕይወት ጠፍቷል። ከተቀጠፈው ክቡር የሰው ልጅ ሕይወት በተጨማሪ የደረሰው የኢኮኖሚ ኪሳራ ቀላል አይደለም። በብዙ ቢሊዮን የሚገመት መሠረተ ልማት ወድሟል። ስለሆነም ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ እውነተኛ የሰላም መፍትሔ እንዲመጣ በሁለቱም ወገን ያሉ አካላት ቆም ብለው በማሰብ፣ የአገር መጠበቂያ መሣሪያ እንጂ የጥፋት ምንጭ ከመሆን በመራቅ፣ ከጦርነት በመለስ ያሉ የሰላም መንገዶችን እንዲያዩ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ለአገር ሰላም የሚሠሩ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ እንጠይቃለን።
Filed in: Amharic