>

እሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል! (አምባቸው ዓለሙ - ከወልዲያ)

እሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል!

አምባቸው ዓለሙ (ከወልዲያ)


ከሣምንት በላይ አምጬ የወለድኩትን እጅግ አነስተኛ የመጻፍ ፍላጎት አክብሮ ይህችን ጦማር የሚያነብልኝ አንድ ሰው እንኳን ባገኝ ደስታየ ከፍተኛ ነው፡፡ የተከመረብን አጠቃላይና ሁልአቀፍ ችግራችን መፍትሔው ከመጻፍም ሆነ ከማንበብ በላይ ሆኖብን ተቸግረናል፡፡ ሀገራችንና ሕዝቧ የመጨረሻ ጣር ላይ ናቸው፡፡ ይህ ግን ለብዙዎች ግልጽ አይመስልም፡፡ እንደዘመነ ሦዶም ወገሞራና እንደዘመነ ኖኅ የሚሰማውና የሚታየው ምንም ሳይመስለው ከገባበት ጠማማ መንገድ ባለመውጣት አሼሼ ገዳሜውን የሚያቀልጠው ዜጋ የመብዛቱ ነገር እጅግ ያሳዝናል፤ ያስቆጫልም፡፡

በአሁኑ ወቅት በርካታ ቂጣዎች ጠፍተው፣ በርካታ ሽሎችም ገፍተው በግልጽ የሚታዩበት ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን፡፡ ስንጮኽባቸው ከነበሩ ጉዳዮች ዋና ዋናዎቹ እውን እየሆኑ መጥተው የሚቀረው ትልቁ ሀገራዊ ትዕይንት ነው፡፡ ያም ትዕይንት ከአርማጌዴዎናዊ እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ በኋላ የሚመጣውና ማንም ሊያስቀረው የማይችል፣ ቀድሞ ቃል የተገባልን የሀገራችን ነፃነት ነው፡፡ ትልቅ እውነት ነው – በርግጥም ኢትዮጵያ ሦርያ ወይም ዩጎዝላቪያ አይደለችም፡፡ የሽዎች ዓመታት ተጋምዶና የጥቂት አሠርት ዓመታት ጥልፍልፎሽ እኩል አይበጠስም፡፡ 

መሬት ላይ የምናየው ወቅታዊ ክስተት ምንድን ነው? ብለን እንጠይቅና ጥቂት ዳሰሳ እናድርግ፡፡ 

በአሁኑ ወቅት በግልጽ እያየነው የምንገኘው መሬት ላይ ያለው እውነት በኔ ዕይታ ከዕድሜ አንጻር አባትና ልጅ ሊሆኑ የሚችሉ ሁለት ፀረ-ኢትዮጵያ ሰዎች የተናገሯቸው የሩቅና የቅርብ ዕቅዶች ትግበራ ነው፡፡

  1. ያለንበት ውጥንቅጥ ችግር ኢሣይያስ አፈወርቂ እ.አ.አ. በ1990 ወይ 91 አካባቢ “የኤርትራን ነፃነት ማግኘት ቀላል ነው፡፡ ችግሩ ነፃነቱን በዘላቂነት የማቆየቱ ከባድ ሥራ ነው፡፡ እርሱንም ከኢሕአዴግ ጋር እየሠራንበት ነው” በሚለው ዘመን ተሻጋሪ ሻዕቢያዊ ንግግሩ የሰጠን የ100 ዓመት የቤት ሥራ አካል መሆኑን መርሳት አይገባንም፡፡ እባብ ምንጊዜም እባብ ነው – በወረት ፍቅርም አንታወር፡፡ በየትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው የተነሱበትን ዓላማ ማሳካት ያለና የነበረ የሚኖርም ነው፡፡ እየሣቁ ሲገድሉት እየሣቀ የሚሞት ካለ ግን እርሱ ሀበሻ ብቻ ነው፡፡
  2. ኦነግ/ኦህዲድ የፌዴራል ተብዬውን ሥልጣን ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ አግበስብሶ እጁ ውስጥ ካስገባ በኋላ በኢትዮጵያ ጥላቻ ተኮትኩቶ ያደገው ወጣቱ የሰሞኑ ሙሹራ የኦሮሚያው ፕሬዝደንት ሽመልስ አብዲሣ ለኦሮሞ ልሂቃን በድብቅ ስብሰባ የተናገረውን መርሳት ሀገራዊውን ወቅታዊ ሥዕል እንደመዘንጋት ይቆጠራል፤ ወይም አድር ባይነትና አዴፓነት ነው፡፡ ያ ንግግሩ ተተርጉሞ በሚዲያ ተላልፏል፡፡ ነገር ግን ብዙዎቻችን የተጣባንን ነገር አላውቅም ሆዳችን ከሞላ ለሌላው ነገር ‹ኬረዳሽ› በመሆናችን ትናንትናን ይቅርና ዛሬ ጧትን ማስታወስ አንችልም ወይንም አንፈልግም፡፡ ይህን ባሕርያችንን ደግሞ እነአቢይ በደምብ ያውቁታል፤ ከሚገባውም በላይ ይጠቀሙበታል – “ሾርት ሜሞሪ ያለው ሕዝብ” ብለው በመሳደብ ጭምር ለዚያውም፡፡ ሽመልስ “የአማራን ነገር ለኛ ተውት፡፡ ታገሱን እንጂ በቅርብ ጊዜ ውስጥ አማራን ከነቋንቋው መቀመቅ እንከተዋለን፡፡ በምትኩም ኦሮሙማንና ኦሮምያን በኢትዮጵያ ከርሰ መቃብር ላይ እንዲያብቡ እናደርጋለን፡፡ ለዚህም ስኬት አባይን ተሻግረን በማሳመንም በማምታታትም ብዙ ሥራ ሠርተናል፡፡…” በማለት የተናገረው ትልቅ ማስጠንቀቂያ ሊሆነን በተገባ ነበር፡፡ ግን የተነገረ አይቀርማ! ትንቢት መፈጸሙ ግድ ነዋ!

አሁን ማቄን ጨርቄን የለም፡፡ ያደለብከው በሬ ሲረጋግጥህና በቀንዱ ሲቦሸራርክህ ዝም ብለህ መቀበል ነው፡፡ ምርጫ የለህም፡፡ ምርጫዎችህን ሲያጠቡብህ እንዳላየ አይተህ እያለፍክና “ባክህ ምንም አይመጣም!” እያልክ አዳሜ ስታሾፍና ስታላግጥ በሰው ስቃይም ስትዝናና ከርመሃል፡፡ አዲስ አበባ ዙሪያ በሰንዳፋ፣ በቡራዩና በሰበታ ሲያለማምዱህ የነበረው ዘር ተኮር መከራና ስቃይ በጉራ ፈርዳ፣ በሻሸመኔ፣ በሆሮ ጉድሩ፣ በመተከል፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በሸዋ ሮቢት፣ በአጣዬ፣ በከሚሴ … አቆራርጦ የየጁን መዲና ወልዲያን አልፎ ዛሬ መጠኑንና ቅርጹን በመለወጥ ወደያለህበት ቀየ እየመጣልህ ነው – ዕድሜ “100% ለመረጥከው” አቢይ አህመድ – (ምን ዓይነቱ የድራማ መሬት ላይ ፈጠርከኝ አምላኬ!)፡፡ ትናንትናና ከትናንትና ወዲያ ኮረምና አላማጣ፣ ቆቦና ጋሸና፣ ላሊበለና ሮቢት፣ ጎብዬን ዶሮ-ግብር ሲያለቅሱ አንተ በከበር መልስ ሼሼ ገዳሜ ትል ነበር – አንተም ባትሆን ጓደኛህ፡፡ ዛሬና ምናልባት ነገ ወያኔን ከሁለት ሣምንታት በላይ ብቻውን ተቋቁሞ የተፋለመው የወልዲያ ሕዝብ አቅሙ ዝሎ ቢረታና ትህነግ በአቢይ የኦሮሙማ ሤራ ከወልዲያ ብታልፍ ደሴና ደብረ ብርሃን ለመግባት አንድም ነገር አያግዳትም፡፡ ያኔ የፖለቲካው ሤራ ጫፍ ይደርስና አዲስ አበባም በሁለቱ ሰይጣናት የሸር ጉንጉን ልትተበተብ ትችላለች፡፡ ነገን አናውቅም፡፡ የፖለቲካ ሤራ መጥፎነቱ ወይም ደግነቱ የሤራው አቀናባሪም በሤራው ቀድሞ የሚንደባለልበትና እንጦርጦስ የሚወርድበት ሁኔታ መኖሩ ነው፡፡ ደስ ሲል!

እንደሚባለው የትህነግን ኃይል (የአሁኑን ማለቴ ነው) የአንድ የአማራ ክልል ወረዳ ሕዝብ ሊቋቋመው በቻለ ነበር፡፡ ግን ያን ዓይነቱን ነገር አቢይና የርሱ ደንገጡሮች አጥብቀው ይጠሉታል፡፡ ዛሬ ወያኔን የሚገዳደር ኃይል ነገ ኦነግን ስለሚያስቸግር ያለው ብቸኛ አማራኝ የአማራን ኃይል አሁን እያጠኑ ሞገደኛ ሞገደኛውን መፈረካከስ ነው – ይህ በአቢይ የመቆጣጠርያ ገመድ የተያዘ ጦርነት አማራን መፈተኛ ጦርነት መሆኑ ነው፡፡ ወልዲያ ከተሸነፈች የምትሸነፈው በወያኔ ሣይሆን በአሻጥር ብቻ ነው፡፡ ያም አሻጥር የሚመነጨው ከአቢይ አህመድ፣ ከብአዴንና ከትህነግ ነው፡፡ በመሠረቱ አማራን የዶግ ዐመድ ለማድረግ ሤራው ዛሬ አልተጀመረም፤ የቆዬ ነው፡፡ የአሁኑ የዱሮው ቅጣይ ነው፤ ምናልባትም የመጨረሻው፡፡ የሤራው አካላትም የውስጥና የውጭ መሆናቸው ከጥንትም የነበረ ነው፡፡ የአሁኑ ለየት የሚለው ግን ብአዴን በሚል ስም ከራሱ ከአማራው ወጣ የተባለ ኃይል ለሆድኑና ከአንዲት ኮረብታ አድማስ ለማታልፍ ሥልጣኑ ሲል በአማራ ላይ ታሪክና ትውልድ ይቅር የማይሉት ግፍ እንዲፈጸም ዋነኛ ምክንያት ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ ያሳዝናል፡፡

ሁሉንም ቢያወሩት ዋጋ የለውም፡፡ ምን እንደሚመጣ ይልቁንስ ልንገርህና አእምሮህን አዘጋጅ፡፡ መናኛውና ግልቡ የኦሮሞ ወኪል ነኝ ባይ ሁላ እንደወያኔ በንኖ የሚጠፉበት ጊዜ እየመጣ ነው፡፡ ጉድጓዱን ለራሳቸውም አርቀው እየቆፈሩ ስለመሆናቸው ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ ዛሬ በአማራ ስቃይ የሚስቅ የሚደሰተው ቢበዛም ነገ – እመነኝ – በአንድ ዓመት ውስጥ በሚታይ የሁኔታዎች መለዋወጥ ሳቢያ በዚህ በአማራ ውድመት የሚሣተፉ ወገኖች ሁሉ እነሱ እንደሚጠቀሙበት ቃል ዱቄት ይሆናሉ፡፡ እንኳንስ ከሁነኛ ምንጭ የሰማሁትን አስታውሼ ከራሴው አንደበትም የሚመስለኝን ተናግሬ ያፈርኩበት እንደሌለ በዚህ አጋጣሚ ለተጠራጣሪዎች መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ እስኪ ከሼህ ሁሤን ጂብሪል የማስታውሳቸውን ጥቂት ስንኞች ላስፍር፡- (ከ30 ዓመታት በፊት ካነበብኩት አንድ መጽሐፍ በቃሌ ከያዝኩትና ትዝ ከሚለኝ ነው፡፡)

መን ተለውጦ ጥቅምት ቲደርስ፤

ባስመራ ከተማ ይነፍሳል ነፋስ፤

የዚያነዜ አበሻ ይላል ፍርስርስ፤

ሃምሣ ቀን ይቆያል ሴት ወንዱ ቲያለቅስ፡፡

ያስመራው ጦርነት ትሳስ ቲጀመር፤

ወያኔ ሻቢያ አያገኝም ኸይር፤

መግዛቱንስ ይግዛ የዮሐንስ ዘር፤

ወዲያው ለጥቂት ቀን ይላል ፍንጥርጥር፤

የኋላ የኋላ ሃቲማው አያምር…

…………………..

መቀሌን አየኋት አረሆ በልቷት፤

………………………..

አሥመራ መቀሌ ትሆናለች እርሻ፤

እነዚህ ስንኞች በአንድ ቦታ ላይ የሚገኙ አይደሉም፡፡ በዚያም ላይ የአንዳንዶቹ የላይኛው ወይ የታችኛው ቤት ተረስቶኛል፡፡ መጽሐፊቱን ማን እንደተዋሰኝ ሳላውቅ ጠፍታብኝ እንጂ ብዙ ነገር ትናገራለች፡፡

ችግሩ ትንቢት ሁሉ የመፈጸሚያ ጊዜውን በትክክል ስለማይናገር “ይሄ ነው፤ ያ ነው” በሚል ማወዛገቡ ነው፡፡ አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር “ይሄኛው ትንቢት ተፈጸመ” ወይም “ሊፈጸም ነው” እያልን በከንቱ እንድንወራከብ ክፍተት መፍጠራቸው የብዙ ትንቶቢች የጋራ ባሕርይ ነው፡፡ ግን ብዙዎቹ አይዋሹም፡፡

የሆኖ ሆኖ የሀገራችን ጉዳይ በተለይ በአሁኑ ወቅት ቁልጭ ብለው ከሚታዩ ነገሮች ተነስተን ስለመጪ ክስተቶች ጥቂት ብንናገር እምብዝም አንሳሳትም፡፡

ሦስቱ በሬዎች እየተዳለቁ ነው፡፡ አንደኛው እጅግ ተስፋ ቆርጧል፡፡ ግን የተመታና ኃይልና ወዘናውን ያጣ በመሆኑ በቅርብ ለይቶለት ይወድቃል፡፡ እስኪወድቅ ግን በተለይ በፊት ለፊቱ የሚያገኘውን አበያ በሬ ቁም ስቅሉን ያሳየዋል፡፡ ይህ ቁም ስቅሉን የሚያይ በሬ ተስፋ ቆርጦ የሞት ሞቱን እስኪነሳና የሚያቆመው ነገር እስኪያጣ፣ ሜዳዎችም ሁሉ ለርሱ ምቹ እስኪሆኑለት ድረስ ብዙ ይቆሳስላል፡፡ ካልቆሳሰለ ደግሞ በንዴት ፎግልቶ በመነሳት ለድል አይደርስምና ክፉኛ መጎሳቆሉና መቁሰሉ ለድሉ ስኬት እንደግብኣት የሚቆጠር ነው፡፡ አንደኛው ሌላው በሬ ይህን የደከመ በሬ በሁሉም ነገር በማገዝና ሁሉንም ዓይነት ዕርዳታ በቀጥታና በተዛዋሪ በማድረግ የተወሰነ ርቀት ያስኬደዋል – ምናልባትም እስከመሀል ሰሜን ሸዋ፡፡ ከዚያ ግን ብዙም አያልፍም፡፡ የበሬዎች ብርታት በወፈሩና በቀጠኑ አይደለም፤ ካልተዛባ ምክንያታዊ አስተዳደግም ይጀምራል፡፡

ሦስተኛውና በላይኛው አንቀጽ በመጠኑ የተጠቀሰው በሬ ግዴለሽ ነው፡፡ ሁለቱ በሬዎች በጋራም በተናጠልም ሲወጉት እርባና ያለው መልስ ባለመስጠት ብዙ ይታገሳል – እኩያ በሬዎች “ጓደኛችን ለካንስ ይህን ያህል ፈሪ ነው!” ብለው ክፉኛ እስኪታዘቡት፡፡ ማሸነፍ ብርቁ አይመስልም፡፡ ብዙ ጉልበት አለው፡፡ ግን በጉልበቱ አይኮራም፤ አይኮፈስም፡፡ በጠላትነት የፈረጁት ሁለቱ በሬዎች እንደጦር የሚፈሩትም ለዚህ ነው፡፡

ለማንኛውም “የፈሩት መድረሱ፣ የጠሉት መውረሱ” የሚባለው እውን መሆኑ አይቀርም፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነገሮች በእጅጉ ይገለባበጣሉ፡፡ ያኔ ምድር ቀውጢ ትሆናለች፡፡ በሬዎች ልካቸውን የሚያውቁበትና የሚከባበሩበት ዘመን ይብታል፡፡ አንዱ አሳዳጅ ሌላው ተሳዳጅ ሳይሆን የጋራ መሬታቸውን ሣርና ግጦሽ በፍቅርና በመዋደድ የሚግጡበት ወቅት ይመጣል፡፡ እንደስካሁኑ የሚፈራሩበትና አንዱ ሌላውን እንደኅልውና ሥጋት የሚቆጥርበት ዘመን ይከስማል፡፡ በመሀል ሆነው የሚያጣሏቸውና በውጊያቸው የሚደሰቱም ጥግ ይይዛሉ፡፡ 

ወደተነሳሁበት ልመለስ፡፡ ወንድሞችና እህቶች! አንዳንዴ ተስፋ መቁረጥ ጥሩ ነው፡፡ ተስፋ መቁረጥ ንዴትን ይወልዳል፡፡ ንዴት ቁጭትን ቁጭትም ለትግል መነሳሳትን ይፈጥራል፡፡ የማይናደድ ብዛቱ እንኳን ሸክሙ ነው፡፡ ከዐርባና ሃምሣ ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ ይዘህ ከስድስት ሚሊዮን በወጣ አንበጣና ተርብ እንዲህ መሰቃየት ከአመራር ችግሩ በተጓዳኝ አንዳች አንደርብ ያለም ይመስላል፡፡ ለዚህ ልዩነት አንዱ ሰበብ የመናደድ ውጤት መሆኑ ሊካድ አይገባውምና መናደድንና ተስፋ መቁረጥን አንናቃቸው፤ አንጥላቸውም፡፡ 

እስኪጨምሪበት በበደል ላይ በደል፤

ወተት ይሸፍታል እንኳን ሰው ሲበደል፡፡ የተባለውም ለዚህ ነው፡፡

በደልና ግፍ ሲበዛ ሰውን ከሰውነት አውጥቶ ወደ ዐውሬነት መደብ ይጨምረዋል – ይህ ነገር ባይወደድም አንዳንዴ ለኅልውና ሲባል ይደረጋል፡፡ ይህንን ነው በትግሬዎች እያየን ያለነው አሁን፡፡ ሲባል የምንሰማውን ሀሽሹንና ሌላ ሌላውን የወኔ ማነሳሻ ንጥረ ነገር ትተነው አሁን በትግራይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ አንድን የዚያ አካባቢ ኗሪ ሊያሳብድና አማራን ቀርቶ ኬንያን እንዲወር ሊያስገድድ ቢችል አይፈረድበትም፡፡ የኅልውና ጉዳይ ነው፡፡ በዚህን ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ ሲገኙ ድመትና ውሾችም ጌቶቻቸውን ይጎዳሉ፤ ጥንቸል ዝኆንን ልታሸነፍ ትችላለች፡፡ ይህ ንዴትና ተስፋ መቁረጥ እንዲፈጠር ካደረጉት ውስጥ ዋናው ሕወሓት መሆኑ ቢታወቅም ንዴታቸውንና ቁጣቸውን የሚያበርዱት አማራ ላይ እንዲሆን የተሠራውን ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሤራ ማስታወሱ ግን ተገቢ ነው፡፡ አቢይ አህመድ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሀብት ሙሉ በሙሉ አሁን እየተጠቀመበት የሚገኘው አማራን ለማጥፋት መሆኑ በዚህ አጋጣሚ ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ እንግዲህ አቢይ በኢትዮጵያውያን ላይ እየፈጸመ ያለውን የሚከተሉትን ዋና ዋና ተዛማጅ ቅጣቶች ሳይጨምር ነው፡፡

  1. የከረፋና የጠነባ ከወያኔም የባሰ የዘረኝነት አገዛዝ – የትም ቢሮ ሂድ ሐጎስንና አብረኸትን ተክተው የምታገኛቸው ባለሥልጣናት ደቻሣና ጫልቱ ናቸው – ለሥራው ብቁ ቢሆኑ እኮ ምንም ባልነበረ፤ ግን በዘር ብቻ የተሳሳቡ ደናቁርትና ሙሰኛ ናቸው፡፡ ትምህርቱ ባብዛኛው ከሪፍት ቫሊና ከመሰሎቹ በግዢና በገጸ በረከት የተገኘ ፒኤችዲ ወይንም ኤም ኤና ቢኤ፡፡ እዚህ ላይ አድማስ ዩኒቨርስቲ በሪፍት ቫሊ ከመተካቱ በስተቀር የሥራ ብቃትና ቅልጥፍና አልተሻሻለም፡፡ በዚህም ሥራ ተበደለ፡፡ አገር ቆረቆዘ፡፡ 
  2. ሆን ተብሎ በየቀኑ ሽቅብ የሚወነጨፍ የኑሮ ውድነት፡፡ አቢይ ማንን እያስተዳደረ እንደሆነ እንኳን እኛ እሱም በፍጹም የሚያውቅ አይመስልም፡፡ ኑሮና ደመወዝ  ባቢሎን ሆነው እርሱ በችግኝ ተከላ ይቀልዳል፡፡ አገር በጦርነትና በውስጥ መፈናቀል እየተናጠች የደላው አቢይ በመናፈሻ ምርቃት ይዘባነናል፡፡ ግዴላችሁም የዚህ ሰው ዲኤንኤ ይመርመርና በእውነት የዚህች ምድር አባል መሆኑ ይታወቅልን፡፡ በስቃይ የሚደሰት፣ በሀዘን የሚጨፍር፣ በልቅሶ የሚስቅ ልዩ ፍጡር ነው፡፡ በዚያ ላይ ውሸቱና ማጭበርበሩ አይነሳ፡፡ የበቀደሙን ምርጫ እንኳን እንዴት አድርጎ እንዳጭበረበረ የባልደራስን ጥናታዊ ሪፖርት በማንበብ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ሰው ነው እንግዲህ የደርግ አምስት ብር አሁን ከሽህ ብር በላይ በምትመነዘርበት ዘመን ላይ የበቀደሙን የ20 ብር አንድ ኪሎ ሥጋ ዛሬ እርሱ ሥልጣን በያዘ ማግስት 1000 ብር እንድንገዛ ስንገደድ እየሳቀ “በኔ በ7ኛው ንጉሥ ዘመነ መንግሥት ተመችቷችኋል!” እያለ የሚያላግጥብን፡፡ ርሀቡ ራሱ ከጦርነቱ ብሷል፡፡ በሁሉም አቅጣጫ ነው የተወጠርነው፡፡ አዲስ አበባም በሉት ወልዲያ ኑሮው ተመሳሳይና ማንቁርትን ሰንጎ ወደሞት አፋፍ የሚነዳ ሆኗል፡፡
  3. ቅጥ ያጣው ሙስና፡፡ የትም ቢሮ ሂድ – ያለ ገንዘብ ምንም ጉዳይ አታስፈጽምም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለምን አይሆንም – ጉቦና ሙስና የሀገራችን የሥራ ቢሮዎች ዋና ቁልፍ ነው፡፡ ሲጥ ትላታለህ እንጂ ካለጉቦ የትም ሄደህ ምንም አታገኝም – ከሞት በስተቀር፡፡ እርሱን እግዜር ይስጠው ኃጢኣቷን ካልፈራህና ዋጋውን ከቻልከው ሦስት ሜትር ገመድ ገዝተህ ወደሚቀርብህ ዛፍ መሮጥ ነው፡፡ ኧረ ለመሞትስ ሰውም ሊተባበርህ ይችላል፤ ዛሬ እኮ ሟች የሚያስቀናበት ዘመን ላይ ነው ያለነው፡፡ የምትገርም ሀገር፤ በፍጹም የማላውቃት እየሆነች የምትሄድ ዕንቆልሽ አገር፡፡ ለኔ ብቻ ይሆን ግን?

በተረፈ ግና የጦር ግንባሩን ውሎ በሚመለከት ከፍ ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ስንቅና ትጥቅ መከልከልን ጨምሮ አማራው ወያኔን እንዳይዋጋ ሻጥር መሥራት፣ መከላከያው የጦር መሣሪያንና ስንቅን ለወያኔ እያስረከበ በተለይ የአማራ አካባቢዎችን በሰላም ለትህነግ ማስረከብ፣ ወያኔ ወደ አንድ የአማራ አካባቢ ከመግባቷ አስቀድሞ መብራትንና ስልክን ማጥፋት፣ ወያኔን የሚዋጋ የአማራ ኃይልን በእጅ አዙር መምታትና ማስመታት፣ የጦር ሥልትን በምሥጢር ለወያኔ አሾልኮ ማቀበል ወዘተ. የሚጠቁመው የመናኛውንና የግልቡን ኦሮሙማ ዕቅድ ነው፡፡ ይህ የጅሎች ዕቅድ እንዴት እንደሚፈረካከስና ባለቤቶቹን ይዞ ገደል እንደሚገባ በቅርብ የምናየው ይሆናል፡፡ ይህም የሚሆነው ትግሬን አበሳጭተው ለዚህ ዐውሬነት እንዳበቁት ሁሉ አማራንም አበሳጭተው ተስፋ በሚያስቆርጡበት ወቅት ነው፡፡ አማራ እስካሁን የፈራው ወይም በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ የታገሰው ተስፋ ስላልቆረጠ ነው፡፡ ተስፋ ቆርጦም ስላልተናደደ ነው፤ ቢናደድም የመጨረሻውን ንዴት ከአፎቱ ስላላወጣው ነው፡፡ በከፍተኛ የፈጣሪ ጣልቃ ገብነት እንደምንም ችሎ በጓዳው ያስቀመጠውን ያን የክት ንዴት ሲያወጣው ግን አሥር የመንዝ ሽፍቶች ሊሠሩት የሚችሉትን ጀብድ እንኳን እኔ የሰማይ አእዋፍ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ኦነግና ትህነግ በትብብር እየሠሩት ያለው ደባ ታዲያ አማራን ወደ ኅልውና ጥያቄ እየከተተው ነውና ማጣፊያው ሲያጥራቸው ይታየኛል – የትንቢቱም ፍጻሜ እቅጩን ልንገርህ ያ ዘመን ነው፡፡ 

እንግዲህ ያላወጣሁት ምሥጢር የለም፡፡ እንደምንጊዜውም ሁሉ በል በል የሚለኝ በል ያለኝን እናገራለሁ፤ ለመናገርም አዲስ አይደለሁም፡፡ ስለመጪው ጊዜ ማንም መናገር የሚችለው ብዙ ነገር ፍንትው ብሎ ይታያል፡፡ የኦሮሞዎቹ ጄኔራሎችና የአቢይ ተደብቆ አማራን ማስጨረስ የሚያስከትለውን መዘዝ መጠቆም በራሱ ለነቢይነት ደረጃ የማይበቃ የተራ ዜጋ ትክክለኛ ግምት ነው፡፡ የሚሠሩት የጭቡ ሥራ ሁሉ ግልጽ ነው፡፡ 

በፊታችን ብዙ ዕልቂት መኖሩን መናገር ለቀባሪ እንደማርዳት ነውና ይቅርብኝ፡፡ ሬሣን የሚያነሳና የሚቀብር ሰው እስኪታጣ ድረስ መሬት በሙታን አስከሬን ትሸፈናለች – አቢይ የመጣው ይህን አሰቃቂ ተውኔት በስኬት ተወጥቶ ከኢሉሚናቲዎች የተዘጋጀለትን የሲዖል አክሊል ለመቀበል ነው – ካላወቀ ንገሩት፤ ግን ያውቀዋል፡፡ ከዚያኛው ዓለም ይልቅ የዚህኛው በልጦበት ነው እንዲህ ፍዳውን የሚያየው፤ ከጠሊቃኑ ጋራ በኖቤል ተፈራርሟልና ከርሱ ምንም አትጠብቁ፡፡ በጸሎት ይለዝባል እንዳንል ደግሞ አንድም ጳጳስ ወይም አንድም ቀሲስ የለም፤ ሁላችንም በደራው የዓለም የሥጋ ገበያ እየፈነጨን ከፈጣሪ ጋር ያለንን ኔትወርክ ንጹሕና ጸሎታችን ሥሙር እንዳይሆን አድርገናል፡፡ ሁላችንም ጠፍተናል፡፡ ቢሆንም …. ቢሆንም …. አንድም ቢሆን ሻል የሚል ገዳማዊ ካለ ለርሱ ሲል ጌታችን መራራቱ አይቀርምና መጪውን የደም ጎርፍ ቀለል ያደርግልን ይሆናል፡፡ ለኦነግ ልብ ይስጠውና ከተሳሳተ የህልም ዓለም ያውጣው — ይህ በራሱ መቅሰፍቱን በግማሽ ይቀንሰዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህች ዓለም አላፊ ጠፊ ናት፡፡ ላለቀ ዓለም ብለን በነገድና በቋንቋ ጎራ ለይተን እስከዚህን ድረስ ጨካኞች መሆናችን የሰማይን በሮች እንደሚዘጋብን አውቀን በጊዜ ሰው ብንሆን ሁላችንም ተጠቃሚዎች እንሆናለንና ከየተከረቸምንበት ምናባዊ ዓለማት በአፋጣኝ እንውጣ፡፡ አንተ ደግሞ ለምን እንደዚህ ትረግመኛለህ — የተሰማኝንና እውነት መስሎ የታየኝን ተናገርኩ እንጂ ላስከፋህ ፈልጌ አይደለም፤ ባይሆን በዚህ መልክ ላልመለስ ቃል ልግባልህ፡፡ ባልኩት ነገር በጣም ቅር ከተሰኘህ ደግሞ ይቅርታ፡፡ በል በቸር ያገናኘን፡፡….

Filed in: Amharic