>

ሻለቃ ደራርቱና ዶ/ር አሸብር ወደ ቶኪዮ የወሰዷት ኢትዮጵያ! የትኛዋ ሀገርን ታክላለች፤ እኛን ትመስላለች? (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)

ሻለቃ ደራርቱና ዶ/ር አሸብር ወደ ቶኪዮ የወሰዷት ኢትዮጵያ! የትኛዋ ሀገርን ታክላለች፤ እኛን ትመስላለች?

(ዶ/ር  በድሉ ዋቅጅራ)

.ለመንግስት (በጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ደረጃ)፣ ለባህል ሚንስቴር፣ . . . ለሚመለከተው ሁሉ! 
 
ግላዊ ምስል . . .
ደራርቱን ስለሀገር ፍቅሯ አላማትም፡፡ ገና ሳውቃት . . . . ባርሴሎና ላይ አረንጓዴና ቀይ ለብሳ ስትሮጥ ጀምሮ. . .  እግሯ ላይ፣ ፊቷ ላይ የተግተረተሩ ስሮቿ ላይ፣ የሀገሯ ብሄራዊ መዝሙር ሲዘመር ያጠለቀችው ወርቅ ላይ እንባ እያዘነቡ ከሰንደቋ ጋር ሽቅብ የተሰቀሉ አይኗቿ ላይ አይቸዋለሁ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሀገር ምልክት ትመስለኛለች፡፡
.
በአንጻሩ ዶ/ር አሸብርን ያወቅኩት የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆኖ ነው፡፡ ያ ዘመን እግር ኳሳችን በችግር የታመሰበት፣ ፌዴሬሽኑ በቡድን ተከፋፍሎ የተሸበረበት ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰውዬው በሄደበት ስሙን እየመሰለ፣ ይኸው ኦሎምፒ ላይ ደረሰ፡፡ እና እሷ ሀገርን እሱ ስሙን ይመስሉኛል፡፡
.
ለሚመለከተው ሁሉ! 
የኦሎምፒክ ጉዳይ የሀገር ጉዳይ ነው፡፡ ይህን የሚያውቅ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ሊቀመንበር፣ በጥቂት የስፖር አይነቶች የሚወዳደሩ ጥቂት ስፖርተኞችን ይዞ፣ (ያውም በሶስት ጊዜ ተካፋፍለው እየሄዱ) 5 የኦሎምፒክ ኮሚቴ አመራሮች፣ 10 የኦሎምፒክ ኮሚቴ ስራ አስፈጻሚዎች (3ቱ የታገዱ)፣ 7 የመንግስት አመራሮች፣ በከፍተኛ ውሎ አበል ይዞ አይጓዝም፡፡ እነዚህ ሰዎች ከመክፈቻው በፊት ቶኪዮ እንደመግባታቸው፣ በመክፈቻው ላይ ሀገራቸውን ወክለው ቢሆን፣ ትልቅ ውለታና ክብር ነበር፡፡ ግን አላደረጉም ለእነሱ ኦሎምፒክ ገበያ እንጂ ሀገር አልሆነም፡፡
.
አትሌት ገዛኸን አበራን የተናገረውን በቴሌቪዥን ተመልክቻለሁ፤ ሰንደቅ ይዞ የተሰለፈውን የውሀ ዋና ተወዳዳሪ በስልክ አነጋግሬያለሁ፡፡ የውሀ ዋና ተወዳዳሪውና በስፍራው የነበረች የኦሎምፒክ ኮሚቴው “የሂሳብ ሰራተኛ” ባንዲራውን ይዘው ገብተዋል፡፡
.
በኦሎምፒክ ኮሚቴውና በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል የነበረው አለመግባባት የተቋጨው ቶኪዮ ሜዳ ላይ ቢሆንም፣ የሰነበተ ነው፡፡ …. ግለሰቦች በሀገር ስም በሚያገኙት ስልጣን የግል ፍላጎታቸውን ማርካት በፖለቲካችንና በመንግስት ሹመኞች ያማረረን ሳያንስ፣ ያለንን አዎንታዊ የሀገር መልክ ሲመርዘው ዝም ብለን መመልከት የለብንም፡፡
.
የባህል ሚንስቴር፣ መንግስት (በጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ደረጃ)፣ . . . ሌሎችን የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን መርምረው የእርምት እርምጃ መውሰድና ውሳኔውን ለህዝብ ማቅረብ አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ በዚህ ኦሎምፒክ በተነሳው ውዝግብ መመረጥ ሲገባቸው ያልተመረጡ፣ ተመርጠው ያልተወዳደሩ አትሌቶቻችን፣ በሚቀጥለው ኦሎምፒክ እንደ ‹‹የባህሬኗ›› ቃልኪዳን በሌላ ሰንደቅ አላማ ስር እንደምናያቸው መጠራጠር የለብንም፡፡ . . . ይህ እንዳይሆን እርምጃ መወሰድ ያለበት ዛሬ ነው!
Filed in: Amharic