>

እጅግ ከከፉ አጋንንት መካከል ምርጫ አያስፈልግም፤ የትግል ቅደም ተከተል እንጂ!! (ከይኄይስ እውነቱ)

እጅግ ከከፉ አጋንንት መካከል ምርጫ አያስፈልግም፤ የትግል ቅደም ተከተል እንጂ!!

ከይኄይስ እውነቱ


ኢትዮጵያ አገራችን ባለፈው ግማሽ ምእት ዓመት መንበሯ የአጋንንት መንፈስ ተጣብቶት በመንፈሳዊው ሕይወት መኖራቸውን ከምናምናቸው አጋንንት የከፉ ሥጋ የለበሱና የሰው ደም የተጠሙ አጋንንት በአገዛዝነት እየተፈራረቁ አገራችንን ለጥፋት ሕዝባችንን ለማያባራ እልቂትና መከራ እየዳረጉ ይገኛሉ፡፡ ‹ብልግና› የተባለው ካልዓይ ኢሕአዴግ ከግብር አባቱ ከቀዳማዊው ኢሕአዴግ (ሕወሓት) እንደተማረው አስቀድሞ የተባለ ዕቁብ የሆነውን የውሸት ‹ምርጫ› አደርጋለሁ ካለበት ዋዜማ ጀምሮ የኢትዮጵያንና የሕዝቧን ጉዳይ አቅም የፈቀደውን ከማድረግ ጋር የመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ካልተጨመረበት እንደማይፈታ በማመን ከመጻፍም ታቅቤ በጽሞና ለመከታተል ወስኜ ነበር፡፡ በጦርነቱም በኑሮ ውድነቱም ልብን የሚያደማ አእምሮን ረፍት የሚነሳ ነገር በር አንኳኩቶ እየመጣ ተቸግሬ ጤናዬን ጨርሶ ከማጣ ለመተንፈስ አሰብሁ፡፡ 

ተደጋግሞ እንደተነገረው ጦርነት አገርን መምራት ብቃቱም ችሎታውም የሌላቸው ጨካኝ አምባገነኖች አገዛዝ ውጤት ነው፡፡ ጦርነት፣ ሥርዓተ አልበኝነት፣ የአስተዳደር በደልና የፍትሕ እጦት፣ ይህንንም ተከትሎ የሚመጣው የኑሮ ውድነት የአገዛዝ መገለጫ/መለያ ነው፡፡ ሽብር ፈጣሪዎችን በማሠማራት ሰላማዊ ሕዝብን ዕረፍት መንሳት፤ ከዚህም አልፎ በንጹሐን ላይ ፍጅት መፈጸም፣ ማፈናቀልና ማጉላላት፣ የፖለቲካ ግድያዎችን መፈጸም ሌላው የአገዛዝ ሥርዓት ባሕርይና መገለጫ ነው፡፡ በወለጋ፣ በጎጃሙ መተከል፣ ወያኔ ‹ኦሮሚያ› ብሎ በፈጠረው የኢትዮጵያ ግዛት ላለፉት ሦስት ዓመታት የታየው ይኸው አገዛዙ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልኩ ድጋፍ ሲሰጠው የነበረ የሽብር ተግባር ነው፡፡ 

በተለይም ጦርነት የአገዛዝ መገለጫነቱ ከሁለት ባንዱ መልኩ የሚታይ ነው፡፡ በአገዛዝ ብልሹነት የተማረረ ሕዝብ ጀርባውን ሲሰጠው የሕዝብን እምነት አገኛለሁ መስሎት ናላውን በሚያዞረው ሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚደክምበት ማጭበርበሪያ ስልትነቱ አንዱ ሲሆን፤ አፍጦ አግጦ የመጣን የሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት አፍን ማስዘጊያና የትኩረት አቅጣጫን ማስቀየሪያ መንገድ አድርጎ መውሰዱ ሌላው ነው፡፡ ጦርነቱም የሚከሠተው ብሔራዊ ችግሮችን በዕውቀት፣ በጥበብና በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት ባለመፈለግና ብቃት በማጣት ምክንያት ተገዶ የሚገባበት አንደኛው መልኩ ሲሆን፤ በዚህም መልኩ ካልተከሠተ አገዛዞች ለሥልጣንና ጥቅማቸው እናተርፍበታለን ብለው ካሰቡ በራሳቸው ፈጥረው የሚገቡበት ነው፡፡ የወያኔና የሻእቢያን ጦርነት ልብ ይሏል፡፡ ላገር አንድነትና ሉዐላዊነት፣ ለሕዝብ ደኅንነትና ጥቅም ተብሎ የተደረገ ጦርነት አልነበረም፡፡ ሆኖም በመቶ ሺዎች የሚቈጠሩ ቤተዘመዳሞች በከንቱ እምሽክ ያሉበት አስከፊ ጦርነት ነበር፡፡ 

የወያኔ ውላጅ የሆነው የኦሕዴድ (ብልግና) አገዛዝም የገባበት ጦርነት በመቶ ሺዎች ኢትዮጵያውያን ተማግደው በሥልጣን ላይ ለመቈየት የሚያስችለውን መንገድ ሂሳብ የሚሠራበት የግፍ ‹ጨዋታ› እንጂ የአገር ህልውናን የሕዝብ ደኅንነትን እሳቤ ያደረገ ነው የሚል ቅዠት የለኝም፡፡ አሁን የጦርነት ገፈት ቀማሹ ሕዝብም የተረዳው ይመስለኛል፡፡ ወያኔ ኢሕአዴግ የሚል ማጭበርበሪያ ፈጥሮ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ይህ አጋንንታዊ ድርጅት ከነ አሽከሮቹ (በተለይም ብአዴን የሚባለው መዳኛ የሌለው ደዌ) እና ‹አጋሮቹ› ጋር ፈርሶ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት (አባላቱ ከማናቸውም የፖለቲካ ማኅበር ተሳትፎ ለተወሰኑ ዓመታት እንዲገለሉ ካልተደረገ በቀር) እንዲወጣ ካልተደረገ የኢትዮጵያ አገራዊ ህልውና እና የሕዝብ አብሮነት በማይጠገን ሁናቴ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ስጮኽና ስጽፍ ከርሜአለሁ፡፡ አገርን ለማዳን ሲባል ሕዝብ ከሚጠላው አገዛዝ ጋር ሊቆም የሚቻለው ቢያንስ ከጐሣ ወይም ማንነት ፖለቲካ፣ አገር አጥፊና ስታሊናው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም፣ ‹ክልል› ከተባለና የአንድ አገር ሕዝብን ባይተዋር ከሚያደርግ መዋቅር፣ ለዚህም ሕጋዊ መደላድልን ከፈጠረና አገርን ለማፍረስ ከተዘጋጀ የጐሠኞች ማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› ጋር ፍቺ ሲፈጽም ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ አገር አፍራሹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግንባር ቀደም ጠላቱ የሆነው ወያኔ ሕወሓት ብቻ ሳይሆን የሱ ፍጡር የሆነውና በጉልበትና በውሸት ‹ምርጫ› የኢትዮጵያ መንበረ መንግሥት ላይ የተቀመጠው ኦሕዴድ ‹ብልግና› የተባለውና በሎሌነት ያደሩለት ኃይሎች ጭምር ናቸው፡፡ 

ላለፉት በርካታ ዓመታት ብሔራዊ መግባባት፣ በሠለጠነ መንገድ በንግግር ችግሮችን መፍታት፣ ብሔራዊ ዕርቅና የሽግግር ፍትሕ እያልን ጮኸናል፡፡ ወያኔም ሆነ ወራሹ ኦሕዴድ/‹ብልግና› ለዚህ ጆሮ እንደሌላቸው ደጋግመው በተግባር አሳይተውናል፡፡ በዚህም ሁለቱም አጥፊ ኃይሎች መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡ በእኔ ትሁት እምነት በቀዳማዊውና በካልዓዩ ኢሕአዴግ መካከል ልዩነት የለም፡፡ አሁን አብዛኛው ሕዝባችን እንደተረዳው የነሱ ግጭት የሥልጣን ብቻ ነው፡፡ የጐሣ/ማንነት ፖለቲካን፣ ‹ክልል› የተባለ የሐሰት ፌዴራላዊ መዋቅርን፣ ከሥሩ የተበላሸ የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓትን፣ ፀረ አብሮነት የሆነውን እና አገር አፍራሹን የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› እና ይህንን መሠረት አድርጎ ባገር ላይ የሠለጠነውን የንቅዘት ሥርዓት ወዘተ. በሚመለከት እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ልዩነት የላቸውም፡፡ ስለሆነም ሥልጣን ላይ ያለው አካል ከወያኔ ጋር እንዲደራደር የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈቃድ አልሰጠውም፡፡ የሞራል ብቃቱም የለውም፡፡ እኔ በግሌ ወያኔ ከኢትዮጵያ ምድረ ገጽ መጥፋት አለበት የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ እውነተኛ ጦርነት ከተካሄደና የምንከፍለውም መሥዋዕትነት ባግባቡ ከሆነ ከባድ አይመስለኝም፡፡ ከሠላሳ ዓመት በኋላ የዚህን አጋንንታዊ ድርጅት ባሕርይ መረዳት ካቃተን ችግሩ ያለው እኛ ጋር ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ባለው አጥፊ ኃይልና ‹አሽከሮቹ› አማካይነት በሚፈጸም ደባና አሻጥር (ሳቦታዥ) የተተበተበ ጦርነት በመሆኑ እንጂ እስካሁን የተከፈለው መሥዋዕትነት ወያኔን አይደለም ውላጆቹንም ለማጥፋት ከበቂ በላይ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሕዝባችን ምን ያህል ተረድቶ እንደሆነ አላውቅም እንጂ ሥልጣን ላይ ያለው አካል እና ከወያኔ ጋር ለመፋለም ራሱን ለመሥዋዕትነት ያዘጋጀው ሕዝባዊ ኃይል ዓላማና ፍላጎት በጭራሽ የማይገናኝ ነው፡፡

የአጋንንት በጎ የላቸውምና በተለምዶ እንደሚባለው ክፋቱ ያነሰውን ጋኔን እንምረጥ የምንልበት ጊዜ ላይ አይደለም ያለነው፡፡ ከአንድ የገማ ኵሬ የተቀዱ ጉዶችን ነው ኢትዮጵያ የተሸከመችው፡፡ ባንድ በኩል ‹መንግሥት› ነኝ የሚለው አካል በቀጥታና በተዘዋዋሪ ባሠማራቸው የጥፋት ኃይሎች በወለጋና በጎጃሙ መተከል ዜጎችን በነገድ ማንነታቸውና በእምነታቸው ለይቶ ጭፍጨፋውንና ማፈናቀሉን አላቆመም፡፡ በሌላ ወገን ይኸው የዱርዬዎች መንጋ የአገር ህልውና አደጋ ላይ ወድቋልና ለውትድርና ምልመላና ለመከላከያ ዕርዳታ አድርጉ ብሎ ለሚገላቸውና ለሚያፈናቅላቸው ዜጎች ጥሪ ያደርጋል፡፡ ወገን! ምን ዓይነት እንቆቅልሽ ውስጥ ነው የገባንው፡፡ ለዚህም ነው አገራችን በሁለት የአጋንንት ኃይሎች የእንግርግሪት ተይዛለች የምንለው፡፡ ለዚህም ነው ከዜጎች ጥረት ባልተናነሳ ሁላችን እንደየ እምነታችን የመለኮትን ጣልቃ ገብነትና ቸርነት የምንማፀነው፡፡ ለዚህም ነው ርእሰ መጽሐፉ እንደሚለን እንደነዚህ ዓይነቶቹን አጋንንት ለማጥፋት በግዙፍ መሣሪያ ብቻ ሳይሆን የጾምና ጸሎት ኃይል የሚያስፈልገን፡፡ 

በማጠቃለያ ሳላነሳ የማላልፈው ጉዳይ የኑሮ ውድነቱን ጉዳይ ነው፡፡ በገጠር ብቻ ሳይሆን በመዲናችን አዲስ አበባ የሚታየውንና ቃላት የማይገልጹት የኑሮ ውድነት እና ያስከተለው ረሃብ እየከፋ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሰው ሠራሽ የኑሮ ውድነትም የአገዛዞች አንዱ መለያ ባሕርያቸው ነው፡፡ አንድም የአመራር ውድቀታቸው ማሳያ፣ በሌላም በኩል ሕዝብ እነሱ ከሌሉ የኑሮ ዋስትና እንደሌለው በማስመሰል ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛላቸው የሚጠቀሙበት የጭካኔ ስልት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ሕዝብን ማደኅየት ያልተጻፈ ፖሊሲያቸው ነው፡፡ ደርግም፣ ወያኔም ሆነ ውላጁ ‹ብልግና› ይህንን ግፍ ፈጽመዋል አሁንም ቀጥሏል፡፡ ዛሬ በመናገሻ ከተማችን ሸዋ ዳቦ እየተባለ በሚጠራው የንግድ መደብር የአንድ ገብስ ዳቦ ዋጋ (ግራሙ ተቀንሶ) 7 ብር ገብቷል፡፡ አንድ ሊትር ዘይት 150 ብር ገብቷል፡፡ መሠረታዊ የምንላቸውን የምግብ አቅርቦትና ዋጋ ዝርዝር እናቅርብ ብንል ለማመን የሚያዳግት ነው፡፡ ‹‹እልል!!¡¡? የምሥራች!!¡¡? አትሉም?››፡፡ ሕይወታችንን ለማቆየት ቢያንስ አንዲት ጥረሾ (ቂጣ) ገምጠን ወይም ጥሬ ቈርጥመን ውኃ ተጎንጭተን ማደር አለብን፡፡ በ21ኛው መቶ ክ/ዘመን በጉልበት የሠለጠኑባት የኢትዮጵያ አገዛዞች ከዚህም አውርደውናል፡፡ 

በመጨረሻም ኢሕአዴግ በሚባለው የኢትዮጵያ ነቀርሳ ላይ የጨዋ ግዝትና ርግማን እንዳደርግ አንባቢያንን ከይቅርታ ጋር በትህትና እጠይቃለሁ፡፡

በኢትዮጵያ አንድነት፣ በማይሸራረፍ የግዛት ሉዐላዊነት፣ በሕዝቧ አብሮነት፣ ኢትዮጵያዊነት በሚባለው ብሔራዊ ማንነት፣ በጋራ በተሸመነ ባህሏና ታሪኳ፣ በጋራ በዳበረ ሥጋዊና መንፈሳዊ እሴቶቿ፣ ቀደመት አበውና እመው በፈጸሙት ደማቅና አኩሪ በሆነው ፀረ-ቅኝ ግዛትና ፀረ-ፋሺስት ተጋድሎ ባቈዩልን ነፃ አገር፣ ያለፈ ክፉ ጠባሳ ካለም ለመለያያ÷ ጥላቻና ንትርክ ሳይሆን ለትምህርትና ለእርምት ተጠቅመንበት ለወደፊት እንደ አንድ ሕዝብ አገራችንን አስከብረን እኛም በእኩልነት÷ በነፃነት÷ በሕግ የበላይነት የምንከብርበት አገር ለመገንባት የምንችልበት ዕድሉም÷ፈቃዱም÷ችሎታውም÷ዐቅሙም እንዳለን ጽኑ እምነት ያለን ኢትዮጵያውያን፤

ቀድሞ በአሸባሪው ወያኔ አሁን ራሱን ‹ብልግና› ብሎ በሚጠራው ኦሕዴድ የሚመራውንና ኢሕአዴግ  የሚባለውን ከይሲ ድርጅት ከነ አሽከሮቹ (በተለይም ዘላለማዊ ባርነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነው የኢትዮጵያ ማፈሪያ ብአዴን) እና አጋሮቹ በፍጹም ላለመተባበርና በጭራሽ ላለማመን ቃል እንግባ፡፡ ይህ አጋንንታዊ ስብስብ አስተሳሰቡ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ በዚህም አስተሳሰብና ርዕዮተ ዓለም ላይ ተመሥርቶ የአገርን አንድነትና የሕዝብን አብሮነት ለማጥፋት የዘረጋው መዋቅር ሁሉ የተረገመ ይሁን!!! ከዚህ ቆሻሻ ድርጅት ጋር የሚተባበር ግለሰብ፣ ቡድንም ሆነ ድርጅት የተረገመ ይሁን፤ የኢትዮጵያ አምላክ በጎ ቀንን አያሳየው፡፡

Filed in: Amharic