>

« የጋራ ጠላትን በጋራ የመፋለም ጥምረት» በሚል  መርህ ህወሀትና ሸኔ ተጣመሩ...!!! D W

« የጋራ ጠላትን በጋራ የመፋለም ጥምረት» በሚል  መርህ ህወሀትና ሸኔ ተጣመሩ…!!!
D W

 

የኢትዮጵያ መንግስት በአሸባሪነት የፈረጀው  ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር በማለት ራሱን የሚጠራው እና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ኃይል ከትግራይ ኃይሎች ጋር ወታደራዊ ጥምረት መፍጠሩን አስታወቀ። በሀገሪቱ አሁን ያለው ብቸኛ መፍትሔ « ይህንን መንግስት ማስወገድ ነው» ለዚህም ከትግራይ ኃይሎች ጋር ጥምረት ፈጥረናል ሲሉ የኦሮሞ ነጻነት ጦር አዛዥ ኩምሳ ዲሪባ ለአሶሽየትድ ፕረስ ነግረዋል።
ጥምረቱ በትግራይ ኃይሎች ሃሳብ አመንጪነት ከጥቂት ሳምንታት በፊት መፈጸሙንም ጨምረው ገልጸዋል። «ጥምረቱ የጋራ ጠላትን በጋራ መፋለም » በሚል መርህ በተለይ ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ ከስምምነት መደረሱንም አመልክተዋል። በወታደራዊ ስምምነቱ መሰረት ወታደራዊ መረጃዎችን መቀባበል መጀመራቸውን የገለጹት የታጣቂ ቡድኑ መሪ ለጊዜው ጎን ለጎን ሆነው መዋጋት አለመጀመራቸውን እና ምናልባትም «ያንን የምናደርግበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል» ብለዋል።
ከወታደራዊ ጥምረቱ ጎን ለጎን ከሌሎች የፖለቲካ አጋሮች ጋር ንግግር መጀመራቸውንም ለአሶሽየትድ ፕረስ የነገሩት ኩምሳ ዲሪባ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድን መንግስት የሚቀናቀኑ እና አጋር መሆን የሚሹ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገሪቱ እንዳሉም ጠቁመዋል።
በጉዳዩ ላይ የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳይ እና ከጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት የተሰጠ ምላሽ እንደሌለ የዜና ምንጩ አክሎ ጠቅሷል። ይሁንና ህወሓት፣ቡድኑን ጨምሮ በኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን አቅም አላቸው ካላቸው ቡድኖች ጋር ጋር እየተወያየ መሆኑን ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
«ኢትዮጵያን አሁን ካለበት ቀውስ ለማዳን አቅም ካላቸው ኃይሎች ጋር መተባበር እንዳለብን እናምናለን። ከዛ ጋር የተያያዙ የጀመርናቸው ውይይቶች አሉ። የዛ አካል OLF ሠራዊትም በኢትዮጵያ ውስጥ ስራ እየሰራ ያለ በኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን አቅም ካላቸው ወገኖች አንዱ ስለሆነ ከኛጋም የጀመርነው ውይይት አለ ከዛ በላይ ብዙ መናገር አልችልም።» ብለዋል። ራሱን  የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድኑ በኢትዮጵያ በህዝብ ብዛት ትልቁን ቁጥር የሚወስደውን ኦሮሚያ ክልል ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ለማጎናጸፍ እንደሚታገል ሲገልጽ ቆይቷል።
Filed in: Amharic