>
5:13 pm - Wednesday April 20, 1442

የውሸት ፀሐይ ሲጠልቅ የሤረኞች ወጥመድ ይበጠሳል! (ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ)

የውሸት ፀሐይ ሲጠልቅ የሤረኞች ወጥመድ ይበጠሳል!

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ



ሁልጊዜም ከመንጋቱ በፊት ድቅድቅ ጨለማ ይሆናል። በምሽትና በንጋት ሽግግር ውስጥ ያላለፈ ሀገርና ትውልድ የለም። ብርቱው ጨለማ የንጋቱ ጸዳል አብሳሪ ስለሆነ፣ መቼም ቢሆን “ይኼ ምሽት እንደ ጨለመ ቢቀርስ?” ወይንም ‘ንጋት ባይመጣስ?’ ብለን አንሠጋም።ንጋቱ አይቀሬ ነውና አስደንጋጩ ጨለማ በማለዳው የብርሃን ጸዳል ይዋጣል። የአዲሱ ቀን ጎሕ ሲቀድድ አስፈሪዎቹ አውሬዎች ወደየጎሬያቸው መግባታቸው፣ የሌሊቱም ቁር ለቀኑ ሙቀት ሥፍራ መልቀቁ አይቀሬ ነው። በቀን የተሰወሩት ከዋክብትም ቢሆኑ ከመቼውም ይልቅ ደምቀውና ጎልተው የሚታዩት ጨለማው ሲበረታና ሌሊቱ ከመንጋቱ በፊት ነው።
በሕይወት ጉዟችንም ከጠበቅነው የተስፋ ንጋት ቀድሞ ጨለማ የሚመስል ፈተና ከፊታችን እንደ ጅብራ ሊደነቀር ይችላል። ፈተናው አዲስ እየመሰለን የስሜት መረበሽ ያጋጥመናል። በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በአስተዳደርና በሌሎች ማኅበራዊ ሂደቶች ሁሉ፣ ተግዳሮትና ፈተና ውስጥ ገብተን ራሳችንን እናገኛለን። ግለሰቦችና ቤተሰቦች፣ መንግሥታትና ሀገራት በጥፋት ሥጋት የህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብተው በአጣብቂኝ ውስጥ ያልፋሉ። ጥያቄው ‘ይህ ጊዜ ያልፋል ወይስ አያልፍም?’ ሳይሆን ‘እንዴት ይታለፋል?’ ነው? ይህ ችግርና ተግዳሮት በጨለማው ውስጥ ደምቀውና አሸናፊ ሆነው ብዙዎችን አስከትለው ለሚወጡ ከዋክብት የድምቀትና የጀግንነት እድልም ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በቀደምት ታሪኳ ብዙ ክረምትና በጋዎችን፣ ጨለማና ብርሃንን ያፈራረቁ ውጣ ውረዶችንና እንቅፋቶችን አሳልፋለች። በገባችበት የክረምት አረንቋና የውድቅት ሌሊት የፈተና ሰዓት የቁርጥ ቀን ልጆችዋ “በክፉዎች ሤራ ተጠልፋ ትወድቅ ይሆን?” የሚል ሥጋት ቢገባቸውም፣ እጃቸውን አጣጥፈው ከመቀመጥ ይልቅ በተስፋ ጽናት በሕይወታቸው ተወራርደው ችግሯን ተጋፍጠውላታል። ጠላቶቿን ለማሳፈር አንገታቸውን ለሰይፍ፣ ደረታቸውን ለጥይት ሰጥተዋል።
በዚህም እንደ ጨለማ የበረቱት ጠላቶችዋ ሲወድቁ፣ እሷ አንገቷን ቀና አድርጋለች።
ብዙ የዓለም ሀገራትም እኛ ዛሬ የምናልፍበት በሤራ የመጠለፍ አደጋና የመበታተን ሥጋት፣ በአንድ ወይንም በሌላ ዘመን ገጥሟቸው ያውቃል። እንደ ዩጎዝላቪያና ሶሪያ፣ ሶማልያና ሊቢያ ያሉ ሀገራት በሥጋታቸው ተጠልፈው ወድቀዋል። እንደ ጀርመንና ጃፓን፣ ኮርያና ቬየትናም ያሉት ሀገራት ደግሞ በተመሳሳይ ቀውስ ውስጥ አልፈው፣ ፈተናቸውን ፊት ለፊት ተጋፍጠው፣ ለጋራ ድል በአንድነት ሠርተው፣ ለስኬት ከበቁ ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳሉ።
እነዚህ ሀገራት ዛሬ በኢኮኖሚ ዐቅማቸውና በዘመናዊ የፖለቲካ አስተዳደራቸው፣ በቴክኖሎጂ ምጥቀታቸውና በማኅበራዊ ዕሴታቸው እጅግ ዘመናዊ ከሚባሉት ሀገራት መካከል የሚመደቡ ሆነዋል። አስቀያሚና ፈታኙን ቀውስ አይተው ተሻግረውታል። የገጠሟቸውን እንቅፋቶች እንደ መስፈንጠሪያ ነጥብ እየተጠቀሙ አሁን ካሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
ለምሳሌ ጀርመን በሁለተኛው ጦርነት ማግሥት ወድቃና ተንኮታኩታ ነበር። ምሥራቅና ምዕራብ ጀርመን እየተባለች ለሁለት ተከፍላ ለመቆየት ተገድዳለች። ጊዜው ቢረዝምም በመጨረሻ ሕዝቦቿ ተባብረው የለያቸውን የድንጋይና የርዕዮተ ዓለም ግንብ አፍርሰውታል፡፡ በ1860 አካባቢ ደም አፋሳሽ በሆነው የርስ በርስ ጦርነት ገብታ ሁለት ከመከፈል ለጥቂት የተረፈችው አሜሪካ ራሷ ከደረሰባት ጥፋትና የመበታተን አደጋ የዳነችው በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የልጆቿን ሕይወት ዋጋ ከፍላ ነው።
በድህነት ላይ የእርስ በእርስ ጦርነትና የውጭ ጣልቃ ገብነት ክፉኛ ፈትኗት ሳትረታና ሳትፈታ በድል ያለፈችው የደቡብ ኮርያ ታሪክ ከሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በእጅጉ ተዛማጅ ነው። ዛሬ እኛ እያለፍን በምንገኝበት መንገድ ውስጥ ያለፉ፤ ችግርና እንቅፋት የሩቅ ሳይሆን የቅርብ ጊዜ ትዝታቸው የሆኑ፣ ሌሎች ሀገራትም ቁጥራቸው ጥቂት አይደሉም።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ያልገጠሟት ፈተናዎች፣ ያላለፈችበት ተግዳሮቶች የሉም። ሁሉንም የቀለበሰችውና ድል አድርጋ የወጣችው በአንድነት፣ በብልሐትና በመደመር ነው። ከውጭ የመጣ አደጋም ሆነ ከውስጥ የተነሳባት ፈተና፣ የቱንም ያህል የበረታ ቢሆን ልጆቿ በኅብረት ሲቆሙ ከዐቅማቸው በላይ ሆኖ አያውቅም።
በሌላ በኩል ደግሞ “እኔ ከሞትኩ” ባዮች፣ ለግል ጥቅም ሲሉ እናታቸውን በሚሸጡና ሀገራቸውን አሳልፈው በሚሰጡ፣ ጠላት እንደፈለገው በሚጋልባቸው ከንቱ ልጆችዋ ምክንያት ኢትዮጵያ ከአንዴም ብዙ ጊዜ ብርቱ ፈተና ውስጥ ገብታለች።
ዛሬም ኢትዮጵያ በደኅናው ቀን እፍታዋን ያጎረሰችው፣ የማጀቷን ምርጥ በልቶ የጠገበው የጁንታው ኃይል፣ ሀገርን ለጠላት አሳልፎ ለመስጠት ዐይኑን የማያሽ ውስጥ ዐዋቂ ባንዳ በመሆኑ ምክንያት ፈተናው ጠንክሮብን ይሆናል። በአንድነት ከቆምንና ተደምረን ከተጋን ግን ይኽን ፈተና አሸንፈን፣ ችግሩን ወደ ዕድል፣ ዕድሉንም ወደ ታላቅ ድል ለውጠን፣ ሀገራችንን ወደ አየንላት የሰላምና የብልጽግና ከፍታ ማማ ላይ እንደምናደርሳት ለአፍታም ልንጠራጠር አይገባም።
ለዘመናት በሀገራችን የሰራ አካል ውስጥ ተሰግስጎ የኖረው ሕወሓት አለ፡፡ የህ ቡድን ራሱን እያፋፋ፣ ኢትዮጵያን በአንጀት – በደም ሥርዋ ሰርጎ ሲጣባ – ሲመርዛት ኖሯል፡፡ አሸባሪው ሕወሐት አሁን ተጠራርጎ ሊወጣ አፋፍ ደርሶና ጣዕረ ሞት ይዞት በመንፈራገጥ ላይ ይገኛል። እድሜውን ለማራዘም የመጨረሻ መፍጨርጨርና የሞት ሽረት ትግል ላይ ነው። የአልሞት ባይ አትርሱኝ መወራጨቱ በዝቷል። ከግብአተ መቃብሩ በፊት ልትወጣ ያለች ነፍሱ እስካለች ድረስ መንፈራገጡና የሰላም ደንቃራ መሆኑ አይቀርም። ክፉ መርዙን ተክሎ ጥገኝነቱን ከመሠረተበት የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተነቅሎና ተጠራርጎ እስኪወጣ ድረስ ደዌ ነውና ሕመሙን ችለን፣ የማሻሪያ መድኃኒት እየወሰድን እንቆያለን።
“ኮሶ ሊያሽር ይመራል” እንደሚባለው፣ የማያዳግም ፀረ ሽብር መድኃኒቱ የጎን ጉዳት የሆነውን ምሬትና ሕመም ታግሠን ከቆየን፣ ሕወሓትም ሆነ ማንኛውም እናቱን ለመሸጥ የሚደራደር ኃይል የሀገራችን ክፉ ትዝታ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ ላይኖረው በቅርቡ ለዘለዓለሙ ይሰናበታል።ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በብዙ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አሻጥሮች ውስጥ አልፈናል። ዛሬ በዲፕሎማሲያችን ላይ የሚታየው ከፍተኛ መንገራገጭ ከሦስትና ከአራት ዓመታት በፊት በሁሉም ዘርፎች ላይ የሚታይ የየዕለት ስቃያችን ነበረ።
በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊው ዘርፍ፣ በአስተዳደር፣ በሕግ ሥርዓቱ፣ በጸጥታና ደኅንነት ሥርዓቱ፣ ከክልል እስከ ወረዳ በሁሉም ቦታ ይሄ ቀውስ ነበር። በእነዚህ ቦታዎች ሁሉ ፈውስ እስኪገኝ ስቃይ ነበር፤ ሕመም ነበር። ስለዚህ አሁንም በዲፕሎማሲያችን ውስጥ ቀውስ ውስጥ ገባን ብለን መበርገግ አይገባም። ጠላት ሁሌም በማስፈራራትና በፕሮፓጋንዳ ቀድሞ ሊያሸንፈን ሲጥር ተሸንፈን አንጠብቀው።
የምንዋጋው ኃይል ዋነኛ ትጥቁ ውሸት ነው። ማኅበራዊ ትስስርን ጨምሮ በየሚዲያው አንድ ውሸት በተኮሰ ቁጥር የምትበረግጉ ሰዎች ባለማወቅ የጁንታው ተባባሪዎች እየሆናችሁ እንደሆነ ዕወቁ።ሰው አንድና ሁለት ጊዜ ይሸወድ ይሆናል፤ ባለፉት ብዙ ዓመታት የተሸወዳችሁት ሳያንስ ዛሬም በፕሮፓጋንዳው በመደንበር፣ የሀገራችሁን ጥቅም ከማሳጣት በዘለለ ምንም የሚፈይድላችሁ ነገር የለም። በተለይ ጥቃቅን ነጥቦችን በመገጣጠም የሤራ ትንታኔ ለመስጠት የምትነሡ ሰዎች፣ ሤራ በመተንተን የምሁርነት ጊዜው አልፏል። አሁን የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ተገቢው ቦታ ላይ መሰለፍ የሚጠይቅበት ጊዜ ላይ ነን። የኢትዮጵያ ጠላቶች ድሮ በድብቅ የሚያደርጉትን አሁን በግልጽ በሁለት ግንባሮች ላይ ጦርነት ከፍተዋል፤ በጦር ግንባር እና በዲፕሎማሲ ግንባር። ስለዚህ የኢትዮጵያ ህልውና ግድ የሚለው ሁሉ ከሤራ ትንታኔና ከአጉል መበርገግ ወጥቶ ሁለቱን ግንባሮች በይፋ ይቀላቀል።
ጁንታው ቀሩኝ የሚላቸውን የክፋት ካርዶች ሁሉ ተጠቅሞ ሊያሸብረን፣ ሊያበጣብጠንና ሊለያየን የሚችለውን ድንጋይ ፈንቅሏል። በገንዘብ ኃይል ሕዝባችን ላይ እሳት እየለኮሰና እርስ በእርስ እያጋጨ እሱ በምቾት እሳት ሲሞቅና ሕዝባችን ላይ ሲሳለቅ ነበር። የሽብር ነጋሪቱን እየጎሰመ ጀሌዎቹን አስከትሎ ዘምቷል። አሁን በተቃራኒው ተሳዳጅና የሞት ሽረት ሩጫ ውስጥ ነው። ጀንበሩ እየጠለቀች ነው። በሞት ሽረት ሩጫ ውስጥ የቀበረውንና የቀረውን የመጨረሻ ጥይቶቹን እየተኮሰ ነው።
ከመጨረሻዎቹ ምሽጎቹ የጣር ድምጹንና የተስፋ መቁረጥ ቀረርቶውን ስሙልኝ ብሎ ነጋ ጠባ ያላዝናል።የሀገራችንን እጅ ለመጠምዘዝ የሚፈልገው የምዕራቡ ዓለም ዲፕሎማሲና የሚዲያ ጩኸትም የጁንታውን ድምጽ በማስተጋባት ደጀን ሊሆን ጥረቱን ቀጥሏል። ተባብረን ጫናውን ለመቋቋምና ለመመከት ከቆረጥን ይኼ ኃይል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያልቅለታል።
ዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት “ሰጥቶ በመቀበል” መርሕ የሚመራ የፖለቲካ ዳንስ ነው። በትክክለኛ የግንኙነት መሥመር በተቃኘ ዲፕሎማሲ በዋናነት ተጠቃሚ የምትሆነው ሀገራችን ለመሆኗ ምንም ጥርጥር የለውም። በተቃራኒው የሀገራችንን ጥቅምና ሉዓላዊነታችንን አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ የሚቃኝ ግንኙነት ለጊዜው ፋታ የሚሰጥ ቢመስልም ዘላቂ ጉዳቱ አመዛኝ ነው። ይኼን ለማስተከለል መንግሥት የበኩሉን እያደረገ ነው፤ ወደፊትም አቋሙን አጽንቶ ይቀጥላል።
በዚህ አንጻር መታወቅ ያለበት አንድ ቁልፍ ሐቅ አለ፡፡ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ላይ ዋነኛ ተጽዕኖ የሚፈጠረው በመደበኛው መንገድ ብቻ አይደለም። ለምሳሌ የምዕራቡ ዓለም ጫና ሊያደርጉባቸው በሚፈልጓቸው ሀገራት ላይ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን በመጠቀም መጠነ ሰፊ ልዩ ልዩ ዘመቻዎችን እንደሚያደርጉ የአደባባይ እውነት ነው። ዛሬም ሆነ ትናንት የሚደርስብንን ጫና “አይሆንም” ማለት ስንጀምር አፍራሽና ስም አጠልሺ የሆኑ የሚዲያና የመረጃ ዘመቻዎች ይከፈቱብናል። እነርሱ ትልልቅ ዐቅምና ሽፋን አላቸው፣ የዓለም ሕዝብ የተሳሳተ ምስል እንዲኖረው የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ የሚዲያ መሣሪያዎችና የዳበረ ኃይል በበቂ አላቸው።
ስለዚህም በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የሚዲያና የዲፕሎማሲ ጫና ለመመከት ሁሉም ሀገር ወዳድ ወገን መረባረብ ይጠበቅበታል። ተደምረን ያለንን የተጽዕኖ በርና ዕድል ሁሉ በመጠቀም የተከፈተብንን ዘመቻ መመከት አለብን።በማኅበራዊና በዋናው ሚዲያ፣ በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር፣ በግልና በጋራ፣ በተናጠልና በመናበብ ሀገራችንን የሚጎዱ የውሸት ዜናዎች መቃወምና ማምከን ያስፈልጋል። እውነት በትክክልና በበቂ ከተነገረች ውሸትን ታሸንፋለች፤ እናም ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ እውነት ዘብ በመሆን ሐቃችን እንዲያሸንፍ ማድረግ አለበት።
በዚህ አስፈላጊ ወቅት ሁሉም ሀገር ወዳድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ እንዲቆም እናት ሀገሩ ጥሪ ታቀርብለታለች።እስካሁንም ጥቂት የማይባሉ የሀገር ልጆች ቀደም ብለው ትግሉን በመቀላቀል ለሀገራችን ብርቱ ፍልሚያ በማድረግ ላይ ናቸው። እነዚህ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ጀግኖች፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ እስከዛሬ አንድነቷንና ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የቆየችው በልጆቿ ብርቱ ጥረትና ትብብር እንጂ፣ እጅን አጣጥፎ በመቀመጥና ወሬ በመሰለቅ እንዳልሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ።
ወደ ሌላ ሰው ጣት ከመቀሰር ይልቅ “ሀገሬ የገጠማትን ችግር ለመመከት ከእኔ ምን ይጠበቃል?” በሚል መንፈስ ጠዋትና ማታ ሳይታክቱ ይፋለማሉ። በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ቢኖሩ፣ የሀገራችንን ችግር በመጋፈጥ ያገኟትን ዕድል ወደ ድል ለመለወጥ ነጋ ጠባ በመዋደቅ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ከማበርከት አልቦዘኑም። ኢትዮጵያም ለሚያደርጉት ትግል ታመሰግናቸዋለች።
በተመሳሳይ ጥሪዋን ተቀብለው በዱር በገደሉ የሕይወት መሥዋዕትን በመክፈል የሀገራችንን ህልውና ለማስጠበቅ ተጋድሎ የሚያደርጉ ብርቅዬ ኢትዮጵያውያንንም ታሪክ ለዘላለም ይዘክራቸዋል። እነዚህ ሁሉ ሀገር በጨለመባት በዚህ ሌሊት የአንድነት ደማቅ ኮከቦቿና የነጻነት ፋና ወጊዎቿ ናቸው።
የውሸት ፀሐይ ሲጠልቅ የሤረኞች ወጥመድ መበጠሱ፣ እውነትም አንገቷን ቀና አድርጋ መታየቷ አይቀርም። ጨለማው ይነጋል፤ ክረምቱም ያልፋል፤ ይኼም ፈተና ሰብሮን ሳይሆን አጠንክሮን በድል ይጠናቀቃል። ያለን አማራጭ ወደ ፊት፣ ወደ ብልጽግና፣ ወደ ነጻነትና ወደ ሰላም መገስገስ ነው። ካለፈው ትውልድ የተረከብናትን ሀገር የተሻለችና የተመረጠች አድርገን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ በጋራ እንነሣ። ጠላት ወደ ወጥመዳችን እየገባ ነው፡፡ የማሸነፍ ዐቅማችን ተደራጅቶና ተጠናክሮ እየወጣ ነው፡፡ ቃል እንደ ገባነው እጅን በአፍ የሚያስጭን ገድል መፈጸማችንን የምናበሥርበት ጊዜው ቅርብ ነው፡፡የያዝነው የኢትዮጵያን አምላክ ነው፤ የምንታገለው ለኢትዮጵያ ነው፣ የሚዋጋው የኢትዮጵያ ጦር ነው፡፡ በመጨረሻም ታሪክ እንደሚነግረን አሸናፊዋ ኢትዮጵያ ናት፡፡መሆን ይችላል፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ነሐሴ 9፣ 2013 ዓ.ም
Filed in: Amharic