>

የአሜሪካ ሀገር ማፍረስ ታሪክ! (ፍቃዱ ሽ.)

የአሜሪካ ሀገር ማፍረስ ታሪክ!

 

(ፍቃዱ ሽ.)

 

 

 

 

በናፓል ቦምብ ጥቃት የተቃጠለችው የቬትናም ህጻን ከወንድሞቿ ጋር በሽሽት ላይ

ጥቂት ምሳሌዎችን እናንሳ፡-

እ.ኤ.አ. 2003 ዓመት ፣ የ9/11(2001 እ.አ.አ.) ሁለቱ የኒዎርክ መንትያ ህንጻዎች ጥቃትን ተከትሎ  አሜሪካ ፣ኢራቅ የኒኩሌር ማብለያ ተቋም እገነባች ነው፤ አሸባሪዎችንም እየረዳች ነው በሚል የሀሰት ውንጀላ ከእንግሊዝ ጋር በመተባበር ሁለተኛውን የባህረ-ሰላጤ ጦርነት አውጃ ኢራቅ ላይ 157800 ወታደሮችን በማዝመት የሳዳም ሁሴንን መንግስት ገርስሳ፣ ሳዳም ሁሴንንም በስቅላት አስቀጥታ፣ ሀገሪቱን የአሸባራዎች፣  የወንበዴዎችና የወረበላዎች መፈንጫ አድርጋ፤ከሶስት ሺህ በላይ የአሜሪካን ወታደሮችን ህይወት ገብራ፣ ሀገሪቱን በጦርነትና በኢኮኖሚ ካደቀቀች በኃላ በ2011 እ.ኤ.አ አብዛኛውን ተወጊ ወታደሮቿ ለቀው እንዲወጡ ስታደርግ፤ በያዝነው ዓመት(2021) መጨረሻ ወደ 2500 ገደማ የሚሆኑትን ወታደሮቿን በሙሉ እንደምታስወጣ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን አሳውቀዋል፡፡

ኢራቅ በአሁኑ ሰዓት በሳዳም ሁሴን ዘመን የነበራት የተሻለ ሰላም እርቋት፣ ኢኮኖሚዋ ደቆ እና የተሻለ የነበረው ማህበራዊ መስተጋብሯ ተመሰቃቅሎ፣የስራ አጡ ቁጥር ከ70 በመቶ በላይ አሻቅቦ የአሸባሪዎች መሸሸጊያን መፈልፈያ ሀገር ሆናለች፡፡

እ.ኤ.አ. በ2011 የሊቢያ ሁለተኛው የእርስበርስ ጦርነት በመባል በሚታወቀው ጦርነት ላይ ከተወሰኑ የኔቶ አባል ሀገራት ጋር በመተባበር በሲቪል ዋሩ ጣልቃ በመግባት ከተዋጊ አይሮፕላን እና ከመርከብ ላይ የሚተኮሱ ሀገር አቋራጭ ክሩዝ ሚሳኤሎችን በገፍ በመተኮስና ከፍተኛ የቦምብ ድብደባ በማድረግ የጋዳፊ መንግስት እንዲወገድ ጋዳፊም በተቃዋሚዎቹ ተይዞ እዲገደል አድርጋ ሊቢያ የሽብርተኞችና የጦር አበጋዞች መፈንጫ እንድትሆን ትልቁን ሚና ተጫውታለች፡፡ ኑሮአቸውን ለማሻሻል በስደት ላይ የነበሩ 30 ኢትዮጵያዊያን ወገኞቻችን በአይሲሲ ቢለዋ በሊቢያ(2015 እ.ኤ.አ) የታረዱት አሜሪካ ሀገሪቱን በጦር ከፈታች በኋላ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ 

ዛሬ ላይ ሊቢያ የራቃትን ሰላም ለመመለስ እና በጦርነት የወደመውን ኢኮኖሚዋን እንዲያገግም ለማድረግ እየተወተረተረች ትገኛለች፡፡

አሜሪካ፣ ሁለቱ የኒዎርክ አለም አቀፍ የገባያ ማዕከል ህጻዎች በአልቃይዳ አጥፍቶ ጠፊዎች በተጠለፉ አይሮፕላኞች በ መስከረም 11/2001 እ.ኤ.አ. ዓመት ወደ አመድነት በተቀየሩ እና ከ3000 ሺህ በላይ ሰዎች በጥቃቱ በሞቱ ማግስት ፤የታሊባን መንግስት በሳውዲ ተወላጁ ፣ ቱጃሩ ኦሳማ ቢን ላደን የሚመራውን የሽብርተኛ ቡድን(አልቃይዳን) ይረዳል በሚል እና ሁለቱንም ለማጥፋትና ለመበቀል አፍጋኒስታን ላይ ጦርነት አውጃ የታሊባንን መንግስት ማሶገድና ከአመታት በኋላ(ግንቦት 02/2011 እ.ኤ.አ. በኦባማ ዘመን) ቢን ላደንን በፓኪስታን መግደል ብትችልም የአፍጋኒስታን ህዝብን ለባሰ ድህነት፣ ለሰላም እጦት እና ለህይወት ምስቅልቅል ዳርጋ አገሪቱን ለቃ ስትወጣ ወደ 20 ዓመት ገደማ በሽምቅ ተዋጊነት ሀገሪቱን ሲያምስ የነበረው የታልባን አማጺያን ቡድን ሰሞኑን በአሜሪካ የተቋቋመውን መንግስት አባሮ ወደ ቤተመንግስት ገብቷል፡፡ አሜሪካም ዜጎቿን ከካቡል ለማውጣት በመሯሯጠች ላይ ነች፡፡

በጎሬበታችን ሶማሊያ የነበረውን የጦር አበጋዞች የእርስ በእርስ ጦርነት ለማስቆም በሚል ሰበብ ኮማንዶዎቿን ወደ ሞቋድሾ በመላክ(እ.ኤ.አ 1993) የጦር አበጋዙን መሀመድ ፋር አዲድን ለመያዝ ብትሞክርም ያልጠበቀችው ጦርነት ገጥሟት ሁለት ብላክ ሀዋክ ሄልኮፕተሮቿን የአዲድ ደጋፊ ሚሊሻዎች መተው በመጣል ከ18 በላይ ወታደሮቿን ገለው አስከሬናቸውን በሞቋድሾ መንገዶች ላይ በገመድ አስረው ከጎተቱ በኃላ ከስድስት ወር በላይ ሳትቆይ ሶማሊያን ለቅ ወጥታለች፡፡

የኮምኒዝም መስፋፋትን ለመግታት ፣የካፒታሊዝም ደጋፊ የነበሩትን ደቡብ ቬትናሞችን ለመደገፍ በሚል ሰበብ የቬትናም ታላቁ ጦርነት ላይ ዋነኛ ተሳታፊ በመሆን በሶቭየት ህብረት ይደገፍ የነበረውን የሆችሚን ቡድን ለማጥፋት ለ19 ዓመታት ያላትን ሁሉ አቅም ተጠቅማ ከ2 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ቬትናማዊያን ሞት ምክንያት ሆና ፤ ከ56 ሺህ በላይ ወታደሮቿን ገብራ፤ ከ70 ቢሊየን ዶላር በላይ ለጦርነቱ ብታውልም በቆራጡ ሆችሚን መሪነት እና በቬትናም ህዝብ አይበገሬነት መክፈል የሚገባቸውን ሁሉ መስዋዕትነት በመክፈል አሜሪካንን በማሸነፍ ሀገራቸው እንደ ኮሪያ ለሁለት እንዳትከፈል በማድረግ ለትውልድ የሚተላለፍ ታሪክ ሰርተዋል፡፡

እኛ ኢትዮጵያኖችም፣ በዚህ ዘመን ያለን ትውልድ፣ ከውስጥም ከውጭም የገጠመንን ፈተና ለማለፍ በአንድነትና በአይበገሬነት በመቆም መክፈል የሚገባንን መስዋዕትነት ሁሉ ከፍለን ጣሊያንን አርበድብደው የሀገራችንን አንድነትና ሉዓላዊነት ያስጠበቁልንን አርበኛ አባቶቻችንን ታሪክ በመድገም ሀገራችንን ከገጠማት ዘርፈ ብዙ ስጋትና ፈተና በማውጣት ወደ ፊት ማስቀጠል ይጠበቅብናል፡፡

Filed in: Amharic