>

የወቅቱን የሃገራችንን የፖለቲካ እና ወታደራዊ ሁኔታ በማስመልከት ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ !

የወቅቱን የሃገራችንን የፖለቲካ እና ወታደራዊ ሁኔታ በማስመልከት ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ !
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በእርስ በርስ ጦርነት ፣ በርሃብ፣ የነገድ ፖለቲካ ባስከተላቸው ቀውሶች፣ በፍትህ እጦት፣ በኑሮ ውድነት፣ ወዘተ… እና በሌሎችም አሳዛኝና አስከፊ ሁኔታዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ከገጠሟት እጅግ አስከፊና አሳዛኝ ወቅቶች መሃከል ይህ አሁን ያለንበት  እንደ አንዱ ሊቆጠር ይችላል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
ምዕራባውያን ሀገራት ከረጅም ጊዜያት አንስቶ ኢትዮጵያን በእነሱ ተጽዕኖ ሥር ለማድረግ ‹‹አማራን ማዳከም ይገባል›› የሚል ዕምነት እንዳላቸው ከተለያዩ የታሪክ መዛግብት እና በገሀድም ከሚፈጽሟቸው ተግባሮቻቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ህወሃትና ኦነግ የሚያራምዱት  ፀረ ኢትዮጵያ አቋም እና ‹‹አማራ ጨቋኝ ብሔር ነው›› የሚለው የሀሰት ትርክት አስተሳሰባቸውን የወረሱት ከምዕራብ ቅኝ ገዥዎችና በአካባቢው ካሉ ታሪካዊ ፀረ- ኢትዮጵያ ኃይሎች ነው፡፡
በእነዚህ ፅንፈኛ ብሄርተኞች የሚቀነቀነው ፀረ-አማራ የፖለቲካ ዘይቤ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በኸርማን    ኮኸን እና በአቶ መለስ ዜናዊ አሁን ደግሞ  በውጭ ጉዳይ ሚንስትር ብሊከን እና በዶ/ር ደብረፅዮን ጥምረት የተከሰተ ቢሆንም፣ አጀማመሩ የቆየ ታሪክ ያለው ነው፡፡ የፀረ-አማራ/አበሾች ትርክት የተጀመረው ከዛሬ ሦስት መቶ አርባ ድስት ዓመት በፊት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1667 ዓ.ም ነው፡፡ ግራኝ መሀመድ በቱርኮች በመታገዝ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥታዊ መንግሥት ላይ በከፈተው ጦርነት አፄ ልብነ ድንግልን በኋላም አፄ ገላውዲዎስን ለመርዳት መጥተው የነበሩ ፓርቹጊዞች ከጦርነቱ በኋላ ወደ ሃገራቸው ከመመለሳቸው በፊት ዓድዋ አጠገብ በምትገኝ ፍሪሞና በተሰኘች ቦታ የኢየሱሳውያን (ጀዝዊት) ካቶሊክ ሚሲዮን ከፍተው ነበር፡፡ በአፄ ሱስኒዮስ ዘመነ መንግሥት እነዚህ የፓርቹጊዝ ሚሲዮናውያን የንጉሡ አማካሪ በመሆን ንጉሡን ሃይማኖታቸውን  አስቀይረው  ካቶሊክ አድርገዋቸው ነበር፡፡  በዚህ ምክንያት በንጉሡ ነገሥቱ ጦር እና የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን  አማኞች ባሰማሩት የገበሬ ጦር መካከል ሦስት ዓመታት የፈጀ ብርቱ የእርስ በእርስ ጦርነት ተካሄደ፡፡  በጦርነቱም ብዙ ህዝብ አለቀ፡፡ በወቅቱ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ማሸነፍ እንደማይችል የተረዱት አጼ ሱስኒዎስ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትን በአዋጅ አፅንተው፣ ዙፋኑን ለልጃቸው ለፋሲለደስ  አስረክበው፣ እሳቸው በካቶሊክ እምነታቸው እንደፀኑ፣ ጣና ገዳም ገብተው ሞቱ፡፡ ልጃቸው አፄ ፋሲለደስ ወደ ካቶሊክ እምነት የተቀየሩትን  ፈጅተው፣ ከአውሮፓ የመጡ የካቶሊክ ሰባክያንን ከኢትዮጵያ አባረሩ፡፡ ሁለተኛም ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመለሱ ምፅዋን ይቆጣጠሩ ከነበሩት ቱርኮች ጋር ስምምነት አደረጉ፡፡
    የወቅቱ የአውሮፓ ኃያላን ሀገሮች በኢትዮጵያ ላይ ቂም መያዝ የጀመሩት በእምነት ማስፋፋት ሽፋን ሃገር  ለማሰስ የላኳቸው ሚሊዮናዊያን ከሰሜን ኢትዮጵያ እንዲባረሩ ከተደረገበት ከ1667 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡
ይህ የአጼ ፋሲለደስ ድርጊት ከዛን ጊዜ ጀምሮ በሚሲዮናዊነት ሸፋን  ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ምዕራባውያን የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊዎች የብቀላ ብዕራቸውን አማራ ወይም አበሻ በሚሉት ማህበረሰብ ላይ እንዲያነሱ አደረጋቸው፡፡ ፖርቺጊዞች ‹‹ኢትዮጵያውያንን ልናግዝ ብንመጣ የእኛን ሃይማኖት ለመቀበል ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም፤ አበሾች ነገዳዊ ጠንካራ ሃገራዊ አመለካከት ያላቸው በመሆኑ በአፍሪካ ላይ ልናስፋፋ ለምንፈልገው የቅኝ ግዛት  የሚንበረከኩ አይደሉም›› የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ።
 የፖርቹጊዝ ሚሲዮናውያን በ16ኛ መቶ ክፍለ ዘመን የዘሩትን ይህን የፀረ አማራ አስተምህሮ በ18ኛ መቶ ክፍለ ዘመን የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ እንግዳ በመሆን ወደ ሸዋ የመጡት የጀርመን ፕሮቲስታንት ሚሲዮናዊያን ክራፍ እና አይዝንበርግ በይበልጥ አስፋፉት፡፡ አማራውንና ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን በማጥላላት ኦሮምያ የተሰኘ ስያሜ በመፍጠር ለኦሮሞ ፅንፈኛ ብሄርተኝነት የርዕዮተ ዓለም መሠረት ጣሉ፡፡
  በዚያው በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አማርኛ ተናጋሪ የነበሩ የወሎ የኦሮሞ ዝርያ ያላቸው ርዕስ – መሳፍንቶች የጎንደርን ቤተ መንግሥትን ሲቆጣጠሩ በኢትዮጵያ ታሪክ ዘመነ መሳፍንት በመባል የሚታወቀው የታሪክ ወቅት ተጀመረ፡፡ በዚያ የታሪክ ዘመን የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት በእጅጉ የተዳከመበት የአካባቢ መሳፍንት እርስ በእርስ በመፋለም የሃገሪቱን ገበሬ በብዛት በጦርነት እና በርሃብ እንዲያልቅ ያደረጉበት እና በሃገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ውድመት ያደረሱበት ወቅት ነበር፡፡
ዘመነ መሳፍንት በመባል በሚታወቀው የታሪክ ወቅት ከአውሮፓ የተለያዩ ሀገሮች ሚሲዮናዊ ሰባክያን እና ኢትዮጵያን የማጥናት ተልዕኮ የያዙ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የየአካባቢ ገዥዎች የመስፋፋት ፍላጎት በመደገፍ፣ በወቅቱ ለነበሩ ዋና ዋና የጦር አበጋዞች የጦር መሳሪያ እና የውጭ ግንኙነት ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡   በዚህም በኢትዮጵያ ይካሄድ የነበረውን የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይበርድ እና ለእርስ በእርስ እልቂቱ መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ  አድርገዋል፡፡ እነዚህ ምዕራባዊያን ሃገር  አሳሾች ወደ ሃገሮቻቸው ከተመለሱ በኋላ የጻፏቸው መጣጥፎች እና መጻሕፍት አማሮች/አበሾች ለምዕራብ ኃይሎች የማይመቹ መሆኑን የሚያስረግጡ ነበሩ፡፡
  በኢትዮጵያ የዘመነ መሳፍንት ጊዜ እንዲያበቃ፣ የኢትዮጵያ አንድነት እና ሉዓላዊነት  እንዲመለስ በማድረግ ረገድ  አጼ ቴዎድሮስ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ከእንግሊዝ ጋር በተጋጩበት ጊዜ፣ እንግሊዞች የአፄ ቴዎድሮስን ጦር ለማሸነፍ የተጠቀሙባቸው ከአጼ ቴዎድሮስ በኋላ ከፍተኛ ሠራዊት የነበራቸውን የላስታውን ዋግሹም ጉበዜ ወይም አጼ ተክለጊዮርጊስን ሳይሆን፣ የትግሬውን ካሳ ምርጫ    (አጼ ዮሃንስን) እና በወሎ ወርቂትን እና መስታወትን ነበር፡፡ ዋግሹም ጎበዜ የእንግሊዙ ጀነራል ናፒዬር ሊያገኛቸው እና የመቅደላን የጦር አምባ ሊያስረክባቸው ፈልጎ መልዕክት ቢልክባቸው  እሳቸው  መልዕክተኛቸውን በመላክ የመቅደላን የጦር አምባ ለመረከብ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን መግለጻቸዉ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡
አጼ ቴዎድሮስ ለእንግሊዝ ጦር እጄን አልሰጥም ብለው እራሳቸውን ካጠፉ  በኋላ  ዋግሹም ጎበዜ በኋላ አጼ ተክለጊዮርጊስ በሚል ስመ-መንግስት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መሆናቸውን አውጀው ነበር፡፡ ይሁንና ለናፕዬር ጦር ቀለብ በማቅረብና መንገድ በመምራት የረዱት ካሣ ምርጫ ናፕየር ኢትዮጵያን ለቆ ሲወጣ ባስረከባቸው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ በመታገዝ፣ ከሳቸው አነስተኛ ቁርጥ ከነበረው የትግሬ ሠራዊት እጅግ የበዛ ቁጥር የነበረውን በአጼ ተክለጊዮርጊስ የሚመራ የላስታ አማራ ሠራዊት በማሸነፍ  አጼ ዮሐንስ አራተኛ ተብለው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሊሆኑ በቁ፡፡ እንግሊዝ ለምታራምደው የቅኝ ግዛት እና አፍሪካውያንን በመከፋፈል የማዳከም ፓሊሲ አማሮች የተመቹ አይደሉም የሚል ጭብጥ የያዙት ከአጼ ተክለጊዮርጊስ ጋር የነበራቸውን ያልስመረ ግንኙነት መነሻ  በማድረግ ነው፡፡
  በትግራይ ጫካ የተመሠረተው ህወሓት የካቲት 1968 ዓ.ም  ባዘጋጀው ማኒፌስቶ የአማራን ጥላቻ መነሻ ያደረገው በአጼ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ትግራይ በኢትዮጵያ ላይ የነበራት የፖለቲካ የበላይነት ሊቀጥል አለመቻሉን በቁጭት በማንሳት ነው፡፡ ህወሃት የትግራይ ሥልጣን በአማራ በተለይም በአጼ ምኒሊክ በሚመራው በሸዋ አማራ ሥርወ መንግሥት በሸፍጥ ተነጥቋል ብሎ ያምናል፡፡ እንደ ህወሃት አመለካከት ከአጼ ዮሐንስ በኋላ ዙፋኑ ወደ አጼ ዮሐንስ ልጆች መተላለፍ ሲገባው፣ በአጼ ምኒለክ የሸዋ መኳንንት እጅ እንደተያዘ መቆየቱን፣ የአማራው ሥርወ መንግሥት በትግራይ ብሔረሰብ ላይ የብሔር ጭቆና ሊያሰፍን የቻለበት ምክንያት እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል፡፡
ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ አስባ ፍላጎቷ በአፄ ምንሊክ የበሰለ የጦር አደረጃጀት፣ ስልት እና የዲፕሎማሲ ጥበብ የበላይነት በአድዋ ላይ እንደከሸፈ ይታወቃል፡፡ ይህ ክንውን አውሮፓውያን አፍሪካንና ኢሲያን በቅኝ አገዛዝ ለመቀራመት ባሰፈሰፉበት ጊዜ የተከናወነ በመሆኑ፣ በነፃነት ተምሳሌነቱ የአውሮፓውያን ቅን ገዥዎች ትልም በማሰናከል ረገድ አርአያነቱ በእጅጉ የጎላ ነበር፡፡ አርዓያነቱ በዓለም ላይ ላለው የጥቁር ዘር ብቻ ሳይሆን ለእሲያ ህዝቦች ጭምርም ስለነበረ፣ አውሮፓውያን ኢትዮጵያን ለማዳከም ከተቻለ ደግሞ ለማፍረስ የሚቻለው አማራ የሚሉትን ማኅበረሰብ በማዳከም ነው የሚል ስትራቲጂያቸውን አጥብቀው ለመያዝ ተገደዱ፡፡
በኋላም በአጼ ኃይለ ሥላሴ እና በወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ዘመነ መንግሥታት ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ንቅናቄዎችን በመደገፍ ቅኝ አገዛዝ ከአፍሪካ ጨርሶ እንዲነቀል በማድረግ፣ ነፃ የወጡ የአፍሪካ ሃገሮች የአፍሪካ አንድነት ደርጅትን እንዲመሠርቱ በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያ የተጫወተችው ሚና አቻ የሌለው ነበር፡፡ ይህ ሚናዋ የምዕራባውያን ኃያላን ሀገሮች በኢትዮጵያ ቂም እንዲቋጥሩባት አድርጓል፡፡ አጋጣሚውን ባገኙ ቁጥር ኢትዮጵያ የምትዳከምበትን ሁኔታ ከመፍጠር ወደ ኋላ የማይሉት ለአፍሪካ ነፃነት አርዓያ መሆኗ በአካባቢው ያለውን ጥቅማቸውን ይጎዳብናል ብለው ስለሚገምቱ ነው፡፡
በ1928 ዓ.ም. ፋሺሽት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ከመውረሯ ጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ በኢዲስ አበባ ተቀምጦ በከተማዋ ይኖሩ  ለነበሩ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ዲፕሎማቶች የህግ አማካሪ እና ጠበቃ በመሆን ሲያገለግል የነበረ  ባሮን ሮማን ፕሮቸስካ የተባለ ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው ለጣሊያን ፋሽሽዝም ውግንና የነበረው የፖላንድ ትውልድ ያለው ጀርመናዊ የናዚ የብዕር ሰው ሲሆን፣ የአማራ ማህበረሰብን የሚያጥላላ “Abysinia-The Powder Barrel” (አቢሲኒያ- የባሩድ በርሜል) የሚል መፅሐፍ ጽፏል፡፡ ይኸ የናዚ አስተምህሮ አራማጅ ሰው ‹‹ኢትዮጵያውያንን በአውሮፓውያን ተፅዕኖ ሥር ለማድረግ መቆጣጠር የሚቻለው አማራውን ማዳከም ሲቻል ብቻ ነው፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ ሌሎች የሃገሪቱን ማኅበረሰቦች በአማራው ላይ እንዲነሳሱ በማድረግ ነው››  የሚል አመለካከቱን በአውሮፓ በሚታተሙ ጋዜጦች ላይ እያወጣ፣  ጣሊያን በኢትዮጵያ ያላትን ፍላጎት እንግሊዝና ፈረንሳይ እንዲደግፉ  ሲቀሰቅስ የነበረ ሰው ነው፡፡ ይኸ ሰው እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 1934 ዓ.ም. ‹‹በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የሃገር ውስጥ እና የውጭ ደህንነት ላይ አደጋ የጋረጠ፣ የማይፈልግ ወይም ተቀባይት የሌለው ሰው ነው /Persona non- grata/›› ተብሎ ከሀገር ተባረረ፡፡
ፀረ- አማራ ትርክት የኤርትራ ነፃ አውጭ ግንባሮች፣ ህወሓትና ኦነግ የወረሱት ከሮማን ፕሮቸስካ እና በኋላም የእሱን አስተምህሮ በተጨባጭ ከተረጎመው ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ከወረረው የኢጣሊያ ፋሽሽት መንግሥት ነው፡፡ በአምስቱ የፋሽሽት ኢጣሊያ ወረራ ዘመን ጣልያኖች የኢትዮጵያ የተለያዩ ማኅበረሰቦች በአማራው ላይ ጥላቻ እንዲኖራቸው በአደባባይ ይቀሰቅሱ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡
ከአብዮቱ በኋላ በ1969 ዓ.ም. ሶማሌ ኢትዮጵያን ልትወር የቻለቸው በአሜሪካ እና በምዕራብ ሀገሮች አይዞሽ ባይነት መሆኑ በወቅቱ በአደባባይ ተገልጿል፡፡ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ለጦር መሳሪያ ግዥ ቀደም ሲል ክፍያ ከተቀበለች በኋላ ለመላክ ፍቃደኛ ሆና ባለመገኘቷ እና ይህን መረጃ ለሱማሌ በማስተላለፏ፣ ሱማሌ ኢትዮጵያን ለመውረር የደፈረችው በዚህ የአሜሪካ ድጋፍ በመበረታቷ ነበር፡፡ በኋላም በ1983 ዓ.ም በአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ እና በኸርማን ኮኸን እና በአቶ መለስ ዜናዊ ስምምነት ህወሓት/ ኢህአደግ የኢትየጵያን ሃገረ- መንግስት ሥልጣን እንዲረከብ ተደረገ።
በ2010 ዓ.ም. ህወሓት ህዝባዊ ተቃውሞ ሲያይልበት መቀሌ ሂዶ የፅሞና ጊዜ በመውሰድ እንዲመሽግ፣ በምትኩ ኦህዴድ/ብልጽግና ሥልጣን እንዲረከብ መደረጉ ከአሜሪካ ጫና ውጭ እንዳልነበር አሁን ግልፅ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ወደ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የተደረገው ሰላማዊ የሥልጣን ርክክብ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት አግኝቶ የነበረው፣ በአሜሪካ መሪነት መላ ምዕራባውን ሃገሮች እንዲቀበሉት በመደረጉ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን እንደያዙ ወዲያውኑ ከኤርትራ ጋር የፈጠሩትን ሰላማዊ ግንኙነት ሽፋን በማድረግ ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሸልማት በኖርዌይ አማካይነት እንዲበረከትላቸው የተደረገው ምዕራባውያን ሀገሮች ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ አመራር ይሁንታ መስጠታቸውን ለማስረገጥ ነበር፡፡
ነገር ግን ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያውያንን ሰብአዊ መብት የረገጠ፣ የሃገሪቱን ሀብት የዘረፈ፣ ተዋደውና ተከባብረው ይኖሩ የነበሩትን ኢትዮጵያውያንነ በሀሰት ትርክት ያለያየና ሌሎችም በደሎችን ሲፈጽም የነበረ ህወሓትን ተጠያቂ አላደረጉም፡፡ በሀገርና በወገን ላይ የመብት ረገጣ ሲፈጽሙ የነበሩ የህወሓት አባላትንም ለፍርድ አላቀረቡም፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የህወሓት ባለስልጣናት ትግራይ በመሄድ ኢትዮጵያን ለመውጋት በስንቅና ትጥቅ ሲደራጁ፣ ማንአህሉኝነታቸውን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲያሳዩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን  በመንግሥታቸው በኩል ይህን የሚመክት በቂ ዝግጅት እና ትኩረት እንዲሰጥ አላደረጉም፡፡ በዚህ ምክንያትም አሁን በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት የብዙዎችን ህይወት የቀጠፈ፣ ቤት ንብረትን ያወደመ እና በርካቶችን ለመፈናቀል የዳረገ ሆኗል፡፡ በአሁን ወቅት በሀገሪቱ እየተስፋፋ ላለው ጦርነት  ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ ሓላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ጊዜው ሲደርስ ተጠያቂ ከመሆን የሚያመልጡ አይሆንም፡፡
የብልፅግና መንግስት ወደ ቻይና የማጋደል አካሄዱን፣ እንዲገታ ፣ የአባይን ግድብ የውሃ ሙሌት በተመለከተ የመካከለኛ ምስራቅ ቁልፍ አጋሯ ከሆነችውን ግብፅ ጋር ስምምነት ላይ ሳይደረስ እንዳይሞላ የሚለው የአሜሪካ አቋም በህወሓት ከኢትዮጵያ ፖለቲካ አለመገለል ላይ የተንጠለጥለ ነበረ። ይህ ደግሞ አሜሪካ ህውሃትን በኢትዮጵያ አንገት ላይ የተጠመጠመ ሸምቀቆ አርጋ ለመጠቀም የወጠነችው ፓሊሲ መሆኑን ለመገንዘብ አዳጋች አይሆንም፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የኤርትራን፣ ኢትዮጵያንና የሱማሌ መንግሥታትን ትብብር አሜሪካኖች አልወደዱትም፡፡  ስለሆነም ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ እንዲወጡ እና የአማራ ልዩ ኃይል ከያዛቸው ወልቃይትና የራያ አካባቢዎች እንዲወጣ በብርቱ ወተወቱ፡፡ አልሆን ሲል የፋይናንስ እቀባና በባለሥልጣናት ላይ የጉዞ ክልከላ እንዲጣል አደረጉ፡፡ ጦርነቱ እንደ አጀማመሩ እየቀጠለ ከሄደ፣ የውስጥ ወኪላቸው ህወሓት ጨርሶ ሊጠፋ ይችል ይሆናል ብለው ሰጉ። በመሆኑም የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግሥት ‹‹ረሃብን የጦርነት ስልት እንዲሆን አድርጓል›› በሚል ጠቅላይ ሚኒስተሩን በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ሊቀርቡ እንደሚችሉ ዛቱ፡፡ ትግራይን ለቆ ለመውጣት ቁልፍ ምክንያት የሆነው የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት እናቀርባለን የሚለው የአሜሪካኖች ዛቻ ከፍተኛ መደናገጥን በማስከተሉ ነው እንጅ ለትግራይ ገበሬ በማዘን እንዳልሆነ ለመረዳት አያስቸግርም፡፡
የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግሥት ለዚህ የአሜሪካ ፍላጎት በመንበርከክ ከምርጫው በኋላ ትግራይን ሙሉ ለሙሉ ለቆ እንደሚወጣ የውስጥ ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ በስምምነቱ መሠረትም ምርጫው ባለቀ በሳምንቱ ትግራይ ሙሉ በሙሉ እንደተለቀቀ ተገለጸ፡፡ ‹‹ዱቄት ሆኖ ተበትኗል፡፡ ከባድ መሣሪያ እንዳይኖረው ተደርጓል፡፡ ወዘተ.›› የተባለው ሃሰት ሁኖ ተገኘ፡፡ ህውሓት የታጥቀዉ ታንክ፣ መድፍ፣ ሞርታርና ቢኤም መከላከያ አግባብ ባልሆነ ሁኔታና በጥድፊያ ከትግራይ ለቆ ሲወጣ የተተወለት መሆኑ የተሰወረ አይደለም፡፡
በአሜሪካ እና በአውሮፓ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጫና ክፉኛ የተደናገጠው የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግሥት ትግራይን ለቆ መውጣቱ የግድ የመሆኑ ሁኔታ ደግሞ ከኦሮሞ ብልፅግና አማራን የማዳከም የፖለቲካ ፍላጎት ጋር የተገጣጠመ፣ “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ የመጣልን” ዕድል ስለፈጠረለት፣ አጋጣሚው ለኦህዴድ መራሹ ብልጽግና የሚጠላ አልሆነም።
ላለፉት ሦስት ዓመታት የኦሮሞ ብልፅግና ከህወሓት ይልቅ የሚፈራው የአማራውን ልዩ ኃይል መደራጀት እንደነበር ለብዙዎች የተደበቀ አይደለም፡፡ ከላይ እንደገለጽነው  ህውሓት ሦስት ዓመት ሙሉ በልዩ ኃይል ሥልጠና እየተጠናከረ እና በመሣሪያ እየታጠቀ እንደነበር ቢታወቅም፣ በመንግሥት በኩል ግን እንዳልታየ በማለፍ  ዋና አቅጣጫውን የአማራ ክልል በልዩ ኃይል ሥልጠና እንዳይገፋ ማተኮር ላይ አድርጓል፡፡ በተቃራኒው ግን የአማራ ልዩ ኃይል ሥልጠና ላይ ትኩረት የሰጡትን የክልሉን የፖለቲካ እና የፀጥታ መሪዎች እስከ ማስወገድም ተደርሷል፡፡
በኦህዴድ ብልፅግና እውቅና እና ድጋፍ አማራው ከቤኒሻንጉል እና ከወለጋ ርህራሄ በሌለው አሰቃቂ ሁኔታ ሲገደልና በስፋት ሲፈናቀል ቆየ፤ መገደሉና መፈናቀሉ አሁንም አላባራም፡፡   የኦህዴድ መራሹ የብልጽግና መንግሥት በኦነግ ሸኔ ላይ ጥብቅ እርምጃ ወስዶ ጥቃቱን ማስቆም ሲገባው አላደረገም፡፡ ይህም ሀገሪቱን እየመራ ያለውን የብልጽግና መንግሥት በህግ ፊት ተጠያቂ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
አሁን ደግሞ ጦርነቱ ከትግራይ ወጥቶ በአማራ ክልል ውስጥ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በራያ አላማጣ ግንባር የመከላከያ ሠራዊት በመንግሥት ትዕዛዝ ለህወሓት ቁልፍ የወታደራዊ ቦታዎችን ለቆ እንዲወጣና እንዲያፈገፍግ  ተደርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ የአማራው ልዩ ኃይል እና ሚሊሻያ በከባድ መስዋዕትነት የያዛቸውን ቦታዎች እንዲለቅ፣ በአንዳንድ ቦታዎችም ‹‹በስህተት ነው›› እየተባለ የመከላከያ ሠራዊት የከባድ መሣሪያ ጥይት በላዩ ላይ እንዲዎርድበት መደረጉ የበርካታ መገናኛ ብዙኃንን ሽፋን አግኝቷል፡፡ ህወሓት ያለ ተከላካይ ጦርነቱን በአማራ ክልል እንዲያስፋፋና የአማራው ክልል የህውሓትን ወራሪ ለመመከት በሚያደርገው ከባድ ተጋድሎ በሰው ኃይልም ሆነ በአካባቢ ሃብት ላይ ከፍተኛ ጉዳይ ደርሶበት እንዲዳከም፣ በሂደትም ለኦሮሙማ ፍላጎት ደንቃራ እንዳይሆን ለማድረግ መታሰቡ በተግባር  እየታየ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን የደረሰችበት እጅግ አስጊ የሆነ የህልውና አደጋ ላይ እንዴት ልትደርስ ቻለች?
ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ በትግራይ ውስጥ ከተከፈተው ጦርነት እና በጦርነቱ ህወሓት የመንግሥትን የመከላከያ ኃይል ከትግራይ ለማስወጣት ከመቻሉ ጋር ብቻ አያይዞ ማየት ስህተት ይሆናል፡፡ ውድቀቱ የተጀመረው ከጦርነቱ በፊት ነው፡፡
• ሲጀመር በኦሮሞ ብልግጽግና እና በህወሓት መካከል የስልጣን ሽኩቻ እንጂ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት የለም፡፡ ሁለቱም አገር እያፈራረሰ ላለው ህገ-መንግስት ዘብ የቆሙ የነገድ ፖለቲካ አራማጆች ናቸው፡፡
• ሁለቱም ኢትዮጵያን በየተራ በመፈራረቅ በአምባገነናዊ አገዛዝ ሥር አድርጎ ለመግዛት እንጅ ሃገሪቱን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሽጋገር ቅንጣት ያህል ፍላጎት እንደሌላቸዉ ተግባሮቻቸው በበቂ ሁኔታ መስክረዋል፡፡
ህወሓት ለሃያ ሰባት ዓመታት ሲፈጽመው የነበረው የአንባገነናዊ አገዛዝ የታወቀ እና ፀሃይ የሞቀው የማያከራክር ጉዳይ ነው፡፡ በኦሮሞ ብልፅግና መሪነት ባለፉት ሦስት ዓመታት ተደረጉ የተባሉ የተቋማት ማሻሻያዎች (በመከላከያ፣ በፖሊስ፣ በፍትህ ሥርዓት፣ በምርጫ ቦርድ ወዘተ….) የማስመሰል እንጂ እውነት እንዳልነበሩ በአሁኑ ጊዜ የማያጠራጥሩ እና የማያወዛገቡ እውነታዎች መሆናቸው ግልጽ ሆኗል፡፡
• የጦርነቱን አመራር በተመለከተ በሃገር መከላከያ ኃይል ላይ ከጥቅምት 24 ያልተናነሰ ጉዳት እንዲደርስበት የተደረገው የተናጠል ተኩስ አቁም በሚል ፈሊጥ ቆራጥ ወታደራዊ አመራር ለመስጠት ባለመቻሉ ነው፡፡ ቆራጥ አመራር  ደግሞ የሚመነጨው ለኢትዮጵያ  አንድነት እና ሉአላዊነት በአፍ ሳይሆን በተግባር የሚገለጽና የማይታጠፍ የፖለቲካ ዓላማ ሲኖር ነው፡፡   ጦርነት የፖለቲካ ዓላማን  ከግብ ለማድረስ ጥቅም ላይ የሚውል ስልት ነው፡፡ የጦርነት ድል ከትክከለኛ የጦር ስትራቴጂና ስልት የሚመነጭ ሲሆን አገርን ከመፈራረስ እና ከህልውና አደጋ ለመታደግ የሚያስችል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጦርነት ለመምራት በኢትዮጵያ አንድነት እና ሉኣላዊነት ሙሉ እምነት ያለው ከመሆን በተጨማሪ ሕይወትንም እስከመስጠት ቁርጠኝነትን ይፈልጋል፡፡ ይሁንና የብልጽግና አመራር  በሚከተለው የነገድ ፖለቲካ እና የሥልጣን ተረኝነት  ፖለሲ ምክንያት አገሪቱ ይህን ዓይነት ቆራጥ አመራር ለማግኘት አልታደለችም፡፡
• ሃገርን እየጎዳ እና ህዝብ እራሱን ከጥቃት እና ከውርደት እንዳይታደግ እያዘናጋው ያለው መንግሥታዊ ውሸት ከፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎች የግል ባህርይ ወደ መንግስታዊ ፓሊሲነት መሸጋገሩ ህዝቡ ጉድ እስኪል ድረስ ገሃድ ወጥቷል፡፡
• በአሁኑ ወቅት ሃገራችን ኢትዮጵያ እጅግ አደገኛ ወደሆነ የህልውና አደጋ ላይ እንድትወድቅ የተደረገችው ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም.  ጀምሮ ከህወሓት ጋር በተከፈተው ጦርነት የብልፅግና ፓርቲ ለመንግሥት የሚሰጠው የፖለቲካ፣ የወታደራዊ እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አመራር ብልሹ እና የወረደ መሆኑ ሁሉም የታዘበዉ ጉዳይ ሆኗል፡፡
•ባለፉት ሦስት ዓመታት በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ሲመራ የቆየው ገዥ ፓርቲ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ መስኮች ሲመራባቸው የቆዩት ፓሊሲዎች በሥልጣን ተረኝነት መንፈስ የተቃኙና የተተበተቡ ናቸው፡፡ ብልፅግና የሚያራምደው ፖሊሲ ከሃገራዊ ራዕይ ይልቅ የተረኝነት መንፈስ የተጠናወተው በመሆኑ ብቃት ያለው ሃገራዊ አመራር ለማስፈን አልቻለም፡፡ የኦሕዲድ መራሹ ብልፅግና ትግራይን ለቆ በመውጣቱ ያጋጠመው ሽንፈት ፓርቲው ባለፉት ሦስት ዓመታት ያራመደው  ፓሊሲ ውድቀት ድምር ውጤት ነው፡፡
• የኦሮሙማ ጽንፈኛ ብሔረተኞች ፖለቲካዊ ግብ ከተቻለ በኦሮሞ ብልጽግና አማካይነት የያዙትን የመንግሥት ሥልጣን በመጠቀም፣ ኢትዮጵያን በኦሮሞ አምሳያ ለመቅረጽ ሲሆን፣  ይህ ካልተቻለ ደግሞ ነፃ ኦሮሚያን መመሥረት መሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሚፈጽሟቸው ተግባሮቻቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡ የነፃ ኦሮሚያ መንግሥት ሊመሠረት የሚችለው ደግሞ በቅድሚያ ትግራይ ከኢትዮጵያ የምትገነጠልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ሲቻል ነው፡፡ ህወሓት የሻዕቢያን ወታደራዊ እና ድርጅታዊ ብቃት በመፍራት ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል በማድረግ ብቸኛ ሓላፊነቱን እንደወሰደ ሁሉ ‹‹ታሪክ ራሱን ይደግማል›› እንደሚባለው፣  ኦህዴድ/ብልጽግናም  አጥብቆ  የሚፈራውን ህወሓት ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ለማራቅ ትግራይን ከቀረችው ኢትዮጵያ ለመገንጠል መንገድ እየጠረገ ይሆን? መልሱን ጊዜና የወደፊት ክንውን ይመልሱልናል፡፡
አሁን ምን ይደረግ ?
1. ከአጭር ጊዜ ዕይታ አንፃር የተናጠል የተኩስ ማቆም የተሰኘው አካሄድ የተሳሳተ ነው፡፡ ምክንያቱም የአማራው እና የአፋር ክልሎች ሦስት ዓመት ሙሉ ሲጠናከር በቆየ የህወሓት ሠራዊት እንዲጠቁ ከማድረግ ውጭ የፈየደው ነገር የለምና፡፡ መከላከያው የሃገርን ህልውና የመታደግ ተቀዳሚ ሚና ሊኖረው ሲገባ፣ የአማራና የአፋር ክልሎች ልዩ  ኃይሎች እና ሕዝባዊ ሚሊሻዎች ለብቻቸው ይህን የሃገር ህልውና የመከላከል ሚና ከወር በላይ ለብቻቸው እንዲጋፈጡ መደረጉ አግባብነት የሌለው ውሳኔ ነበር፡: ከጥቂት ቀናት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ስም የተገለጸው የመከላከያ ሠራዊቱ ጦርነቱን እንዲቀላቀል የሚጠይቀው መግለጫ የረፈደ ከመሆኑ በቀር አግባብነት ያለው ነው፡፡  የመከላከያ ኃይሉ ህዝቡ  ለሃገር ህልውና የሚያደርገውን ተጋድሎ ተቀላቅሎ እና በዚህ አቋሙ ፀንቶ መስዋዕትነት ለመክፈል ከቆረጠና ይህንም በተግባር ካሳዬ ስሙን ያድሳል፤ በክብርም ይዘከራል፡፡
2. አሁን ሀገራችን ለደረሰችበት የመዋረድ እና የመናቅ መጥፎ እጣ ምክንያቶቹ ቆራጥነት በሌላው፣ ሃገርን ሳይሆን ሥልጣንን ካስቀደመና፣ ተጠያቂነትን በእጅጉ ከፈራ መንግሥታዊ አመራር ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑ ለመላ የሃገሪቱ ህዝብ ግልጽ ሆኗል፡፡  ሃገሪቱም ሆነ ሕዝቡ እየከፈሉ ያሉት ከባድ እና አስፈላጊ ያልሆነ መስዋዕትነት በመንግሥታዊ የአመራር ብቃት ማነስ ሳቢያ በመሆኑ ተጠያቂነትን ማስከተሉ የግድ ነው፡፡ ይሁንና ተጠያቂነትን አሁን ሀገሪቱ ባለችበት ሁኔታ ለማንሳት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ሃገሪቱ ይህን ጥያቄ ለማንሳት በተመቻቸ ሁኔታ ላይ አይደለችምና፡፡ ግምገማውና ተጠያቂነቱ ሃገር ሲረጋጋ የሚደረስበት ይሆናል፡፡
የሃገሪቱ የፖለቲካ እና የወታደራዊ መሪዎች ለሃገርም ባይሆን ለራሳቸው ሲሉ ሥልጣናቸውን እንደያዙ በቃል በመሸንገል ሳይሆን፣ በተግባር በሚገለጽ ከጎጠኝነት እና ከውጭ ኃይሎች ተንበርካኪነት የፀዳ አመራር ለመስጠት ቁርጠኝነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡
3. ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ዘመናት በአንድነት በመቆም የውጭ ወራሪን ድባቅ በመምታት ለኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ቀጣይነት በታማኝነት የሚታገሉ መሆናቸውን በተግባር አስመስክረዋል፡፡ ስለሆነም ለዘለቄታው የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ሊከበር የሚችለው ከሁሉም አካባቢዎች በተወጣጡ ማኅበረሰቦችና ኢትዮጵያን በሚያስቀድሙ የፖለቲካ ኃይሎች ትብብር መሆኑን መገንዘብና መተማመን ያስፈልጋል፡፡
4. ህወሓትና ኦነግ እንዲሁም ሌሎች የኦሮሙማ ኃይሎች የትግል ጥምረት እየፈጠሩ ነው፡፡ ይህንን የፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ጥምረት ማክሸፍ የሚቻለው የተለያዩ ማኅበረሰቦች ሕዝባዊ ኃይሎች ኢትዮጵያን ከሚያስቀድሙ ከሌሎች  የፖለቲካ ኃይሎች ጋር የትግል ትብብር መፍጠር ሲቻል ነው፡፡
የኢትዮጵያን እውነተኛ ትንሣዔ ለማብሰር  እንደአማራ፣ አፋር፣ ሱማሌ፣ . . .  የመሳሰሉት ሕዝባዊ ኃይሎች  ከሌሎች ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ኃይሎች ትብብር ጋር ጠንካራ ራ አደረጃጀት በመፍጠር ኢትዮጵያን ለመበታተን በተነሱት ላይ የበረታ ክንድ በማሳረፍ የማያዳግም ትምህርት መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡
ህዝባዊ ኃይሎቹና የሌሎች ኢትዮጵውያን ኃይሎች የፖለቲካ ትብብር የራሳቸውን የአደረጃት ነፃነት በጠበቀ መልኩ፣ ሃገርን ለማዳን ሲባል ከመንግሥት ጋር ትግሉን በማቀናጀት መሥራቱ ሃገሪቱ ከገጠማት እጅግ ከባድ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ችግር በአሽናፊነት ለመውጣት የሚያስችል  የፖለቲካ ስልት ነው፡፡
ኢትዮጵያ አንድነቷ ተከብሮ ለዘላለም ትኑር!!!                                                                                                                                                     ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ
ነሃሴ 10 ቀን 2013 ዓ.ም.                                                                             አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ
Filed in: Amharic