የወረረን ‹‹የተበተነው ዱቄት›› ሳይሆን ዱቄት ሲሰፈርለት የነበረው ነው…!!!
አሳዬ ደርቤ
አገራችን ኢትዮጵያ ህውሓት የተባለ ብርቱ ጠላትና ብልጽግና የሚባል ልግመኛ መንግሥት ያላት አገር ናት፡፡ ከእለታት ባንዱ ቀን ታዲያ ይህ ብርቱ ጠላት ሰሜን እዝን አጥቅቶ መንግሥትን የሚያስቆጣ ተግባር ፈጸመ፡፡
ይሄም ክህደት ያንገበገበው መንግሥት በማልመጥ ፈንታ ቁርጥ የሆነ ውሳኔ አሳልፎ እዚህ ግባ የማይባል ጦሩን በድሮን እና በጦር አውሮፕላን አግዞ ዘመናዊ ጦር መሳሪያና እጅግ የተደራጀ ሠራዊት ባለቤት የነበረውን ጸረ አገር ድርጅት በጣጥሶ መቀሌን ተቆጣጠረ፡፡
የተደራጀውን ሠራዊትም የተበተነ ዱቄት አደረገው፡፡
በዚህም ድል የተዘናጋው መንግሥት ፊቱን ወደ መናፈሻና ወደ ችግኝ ልማት ሲያዛውር የተበተነው ዱቄት ግን ቆላ ተንቤን ላይ ተሰባስቦ ዱቄትና ስንዴ የሚጓጓዝለትን ሕዝብ ሲያደራጅ ሰንብቶ ሕዛባዊ ሠራዊት መገንባት ቻለ፡፡
የፌደራሉ መንግሥት ከመቶ ቢሊዮን ብር ጋር የትግራይን ጉዳይ ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርና ላዘመተው መከላከያ ሠራዊት አስረክቦ ፊቱን ወደ ምርጫው ባዞረበት ሰዓት ትሕነግ ከጊዜያዊ አስተዳደሩና ከሠራዊቱ አመራሮች መሃከል የተወሰኑትን በገንዘብ አስከድቶ ወደ ክልሉ በተላከው መቶ ቢሊዮን ብር ሕዝባዊ ጦር ገነባ፡፡
ብቸኛ ትኩረቱን ምርጫው ላይ ያደረገውና በፌደራል መንግሥቱ ሪሞት የሚንቀሳቀሰው የአማራ ክልል መንግሥት ደግሞ ትሕነግን ለመመከት የሚያስችል ጦር ሊገነባ ቀርቶ በወሎና በሰሜን ሸዋ አቅጣጫ ሰርጎ የገባውን የኦነግ ጦር እንኳን ማስቆም የቻለው አጣዬ ከጠፋች በኋላ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከመቀሌ በተባረረባቸው ስምንት ወራቶች ቁስሉን እየላሰና በተሸናፊ መንፈስ የአዞ እንባውን እያለቀሰ ሕዝባዊ ጦር መገንባትና ጦር መሳሪያ ማስገባት የቻለው የትሕነግ አሸባሪም የምርጫው ሰሞን ይሄን ሃይሉን በመጠቀም ሁለተኛውን ጥቃት በሠራዊታችን ላይ መድገም ቻለ፡፡ ከጥቃቱ የተረፈው ሠራዊትም ሕዝብ ጋር መታኮስ ከባድ በመሆኑ ደጀን ፍለጋ ወደ ራያና ቆቦ አካባቢዎች አፈገፈገ፡፡ የጦር ሜዳውም ወደ አፋርና አማራ ክልል ተዛወረ፡፡
ስለሆነም ባሁኑ ሰዓት ከክልሉም አልፎ አፋር እና አማራን መውረር የቻለው ‹‹የተበተነ ዱቄት›› የተባለው የቀድሞው የትሕነግ ሠራዊት ሳይሆን ስንዴና ዱቄት ሲላክለት ከነበረው ሕዝብ መሃከል የተውጣጣ አዲስ ሕዝባዊ ሠራዊት ነው፡፡
የሚገርመው ነገር ታዲያ ጥቅምት ላይ ሰሜን እዝን ወግቶ በቅራቅርና በራያ በኩል ወረራ የጀመረው የትሕነግ ሠራዊት ኢትዮጵያ ባደራጀችው ሠራዊት በአጭር ጊዜ ውስጥ ድባቅ እንደተመታው ሁሉ ይህ ወራሪ ሃይልም ኢትዮጵያ ካላት ሃይል ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
ሆኖም ግን ይሄን ሕጻናትን ሳይቀር ያሳተፈ ወራሪ ጦር በአጭር ጊዜ ውስጥ መቅበር የሚቻለው ድንገተኛ ወረራ ለተፈጸመባቸው የሁለት ክልል ሕዝቦች ዘመቻውን በማስረከብ ፈንታ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ወጣት የሚያሳትፍ የክተት አዋጅ ተግባራዊ በማድረግ ቢሆንም ለፌደራል መንግሥቱ ጥሪ ግን ምላሽ የሰጡት እነዚሁ ሁለት ክልሎች ሆነዋል፡፡
በመሆኑም ‹‹ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ አንጦሮጦስ ድረስ እጓዛለሁ›› ለሚለው ሃይል ሁሉም ክልሎች ተግባራዊ ምላሽ አለመስጠታቸው፣ ወጣት ያላቸው ክልሎች አማራና አፋር ብቻ መሆናቸው፣ ወደ ማሰልጠኛ የገቡ ወጣቶች አለመመረቃቸው፣ የጦር ጀቶቻችን እንቅስቃሴ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ውስን መሆኑ… በሦስት ቀን ሥልጠና ወረራ የፈጸመው አሸባሪ ሃይል ለፌደራሉ መንግሥት አስጊ ባይሆንም በርካታ ከተሞችን በመዝረፍ እራሱንና ክልሉን እንዲያጠናክር እረድቶታል፡፡
ስለዚህ የጋራ ጠላታችንን አሸንፈን የጋራ አገራችንን ማትረፍ ካለብን የመንግሥትን ጥንካሬ እያወሳን ከማወደስ ባለፈ ድክመቱንም መንቀስ ያለብን ይመስለኛል፡፡
‹‹ችግርህ የአቅም እጦት ሳይሆን ያለህን አቅም አለመጠቀምህ ነውና ብዙ ከተሞች ከመውደማቸው በፊት ቅደማቸው›› ማለት ግድ ይለናል፡፡
አገራችን ድል ማድረጓ እርግጥ ቢሆንም አሸናፊነቱ ከብዙ ውድመት በኋላ እንዳይሆን ‹‹በፌስቡክ ላቀረብከው አገራዊ ጥሪ ስንት ክልሎች ምላሽ ሰጡ?›› ብለን መጠየቅ ግድ ይለናል፡፡