>
5:21 pm - Tuesday July 21, 8448

ከታቦር ተራራ አትቅር ... (ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ)

ከታቦር ተራራ አትቅር …

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
የወንጌላውያን ትሕትና ይደንቃል ፣ ማቴዎስ ማርቆስ ሉቃስ ስለ ደብረ ታቦር ሲጽፉ ዮሐንስ አልጻፈም። ዮሐንስ ተመርጦ የተገኘበትን ታሪክ “ተመርጬ” ብሎ አልጻፈም። የቀሩት ወንጌላውያን ደግሞ “እኛ የሌለንበትን ነገር አንጽፍም” አላሉም። አንድ ወንጌል እየሰበኩ የሚፎካከሩ ፣ የአንድ ቤት ጣሪያ እየሠሩ ቆርቆሮ የሚሻሙ የእኛ ዘመን አገልጋዮች አልነበሩምና እነርሱ  ያልተመረጡበትን ታሪክ ለመናገር ተሯሯጡ። እኛን የማያካትት ክብር ፣ እኛን የማይጨምር ድግስ ጉዳይ ሲነሣ ለማይጥመን ፣ እኛ የሌለንበትን ፎቶ እንኳን ለማየት የማንፈልግ ፣ በእኛ በኩል ያለፈን ነገር ብቻ የምናራግብ ፣ የሌለንበትን ነገር ጥሩም ቢሆን እንኳን ለምናጣጥል “በእኔ በቀር ባዮች” ትምህርቱ ድንቅ ነው።
ሌላ ማሳያም አለ ማቴዎስ ወንጌላዊው  ስለ ራሱ ታሪክ ሲጽፍ “ማቴዎስ የተባለ ቀራጭ በመቅረጫው ተቀምጦ” ብሎ በኃጢአት ከተዘፈቀበት ሥራ ላይ ወደ ክርስትና እንደተጠራ በግልጽ ሲጽፍ ሌሎቹ ወንጌላውያን ግን በሐዋርያት ዝርዝር ላይ ማቴዎስ ያሉትን ሰው ስለ ቀድሞ የቀራጭነት ሥራው ሲጽፉ ግን  ሌዊ የሚል ተለዋጭ ስሙን ተጠቅመዋል። ትሑቱ ማቴዎስ ግን በሌሎች ወንጌላውያን የተሸሸገ የቀድሞ የኃጢአት አኗኗሩን ለእግዚአብሔር ይቅር ባይነት ማሳያ እንዲሆን ስለፈለገ ጭራሽ በሐዋርያት የስም ዝርዝር ላይ “ቀራጩ ማቴዎስ” ብሎ ራሱን ጠርቷል።
የሚገርመው ከቀራጭነት ከተጠራ በኋላ በቤቱ  ታላቅ ድግስ ደግሶ ጌታችንን ከኃጢአተኞች ጓደኞቹ ጋር የተቀበለ መሆኑን በሌሎች ወንጌላውያን ሲጽፉ ማቴዎስ ግን ቀራጭነቱን አጉልቶ እንዳልጻፈ ሁሉ የግብዣው ነገር ደጋሹ እርሱ መሆኑን አድበስብሶ በመጻፍ አልፎታል።
★    ★   ★
ቅዱስ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው” አለ።  “ለእኛ” መልካም ነው የሚለው ቃል ድንቅ  ነው። በእግዚአብሔር ቤት መኖራችን መልካምነቱና ጥቅሙ ለእኛ ነው እንጂ ለእግዚአብሔር አይደለም። የማንጠቅም ባሪያዎቹ ስሙን በአሕዛብ ዘንድ ከማሰደብ በቀር ለእርሱ ምን እንጠቅመዋለን። ለዚህም ነው ቅዱስ ባስልዮስ “ጌታ ሆይ የአንተ አምላክነት ለእኔ ያስፈልገኛል እንጂ የእኔ ፍጡርነት ለአንተ አያስፈልግህም” ያለው።
ስለዚህ ጴጥሮስ “ለእኛ መልካም ነው” አለ።
“ብትወድስ ሦስት ዳስ እንሥራ” አለ ፣ ጌታ ካልወደደ እንኳን ሦስት አንድ ዳስ መሥራት አይቻልም ፣ እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ” ስለዚህ “ብትወድስ” አለ።
የዋሁ ጴጥሮስ ለእኔ ልሥራ አላለም ፣ የሐዲስ ኪዳን ሐዋርያ ነኝ ብሎ የብሉይ ኪዳን ነቢያትን ከማክበር ወደ ኋላ አላለም። “አንተ ዓለት ነህ በዚህች ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ” በተባለ ማግስት ለነቢያቱ ድንኳን ሊቀልስ የጠየቀ ከጴጥሮስ በቀር ማን አለ?
ከእግዚአብሔር አብ ግን “አትሙት” እስከማለት ለደረሰው ለነጴጥሮስ ንግግር “የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት” የሚል ትእዛዝ መጣ። ሃሳቡ ድንቅ ቢሆንም ቃሉን ሳይሰሙ ዳስ መሥራት መጀመር አይቻልም።
 በዚያ ላይ ጌታ የመጣው በደብረ ታቦር ድንኳን አስጥሎ ሊኖር ሳይሆን በቀራንዮ በተሰቀለበት በመስቀሉ ካስማ በደሙ ድንኳን ተክሎ ሊያስጠልለን ነው። ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ “ጴጥሮስ ሆይ ለአንተ የፊቱን ብርሃን እያየህ በዚህ መኖር መልካም ነው ፣ እኛ ግን የምንድነው በተራራው ሲኖር ሳይሆን ወርዶ ፊቱን በጥፊ ሲመታ ነው” ብሎታል።
ጴጥሮስ የዋሁ “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ” ላለው ለክርስቶስ ድንኳን ሊቀልስ ጠየቀ። በሰማይ “በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ድንኳን” ላለችው ሊቀ ካህናት ድንኳን ሊሠራ ለመነ። እዚህ አለ ሲሉት እዚያ ለሚገኘው ፣ በመንፈስ እየተነጠቀ አድራሻውን ለመወሰን ያስቸግር ለነበረው ኤልያስ እንዲቀመጥ ተስፋ አድርጎ ድንኳን ልሥራ አለ። እጅግ የተዋበችና በወርቅ በሐር ያጌጠችን የኦሪት ድንኳን ለሠራው ሙሴ ዓሣ አጥማጁ ጴጥሮስ ድንኳን ልሥራለት አለ። ሐዋርያት ነቢያቱን ሊያስተናግዱ የለመኑባት ደብረ ታቦር ፣  ሐዋርያት ነቢያቱን ለጌታ ቀኝ አዝማች ግራዝማች አድርገው በድንኳን አስቀምጠው እነርሱ እንደ ሎሌ ከደጅ ሊኖሩ የጠየቁ እነ ጴጥሮስ እንደምን ይደንቃሉ? ጴጥሮስ ሆይ አሁን በሰማይ ድንኳኖች ውስጥ እያገለገልህ ይሆንን? ደብረ ታቦርን አይተህ በደስታ “እንኑር” ያልከው ጴጥሮስ ሆይ የገነት ደስታ ስታይ ምን ተሰምቶህ  ይሆን?
በእሳት ድንኳን ለመኖር ተስፋ የምናደርግ  “በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል” የተባልን እኛስ ምንኛ የታደልን ነን?
★   ★   ★
በታቦር ተራራ ላይ የጌታችን ልብስ እንደ ፀሐይ አበራ ፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ከፀሐይም በላይ ነው ፣ ፀሐይ አይቶ የወደቀ የለም የጌታችንን ልብስ ሲያዩ ግን የወደቁት ያበራው ከዚያ በላይ ስለሆነ ነው” ይላል።
ከጌታችን በዚያ ተራራ ከሙሴና ኤልያስ ጋር ነበረ። ሙሴ እንደምናውቀው ጽላቱን ተቀብሎ ሲወርድ ሕዝቡ “እባክህን ተሸፈንልን” ብለውት ፊቱን በመጎናጸፊያው ሸፍኖ ነበር። የሙሴ አምላክ ክርስቶስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ሲወድቁ አይቶ በልብሱ እንዳይሸፈን ያበራው ፊቱ ብቻ ሳይሆን ልብሱም ነበር።
” አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ” ማር 9: 3
የሚለው ቃል ምንኛ የሚደንቅ ነው።  በምድር ላይ ያለ አጣቢ ቢፈትግ ቢታገል የዚያን ያህል ሊያነጻው የማይችለው ነጭ እንዴት ያለ ነው? መቼም ሁላችን የምናውቀው ነጭ ነገር ሁሉ በምድር ላይ ባለ አጣቢ የታጠበ ስለሆነ እንዲህ ነው ማለት አንችልም። ብቻ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በምድር ያሉ አጣቢዎች ከሚያነጡት በላይ ልብስን ማንጣት ይችላል።
ይህ ቃል በኃጢአት እድፍ ልብሳችን ላደፈ ሁሉ መጽናኛችን ነው።
መቼም የምድር አጣቢዎች አቅማቸው ውስን ነው።
 ቆሽሸን ያዩን ሰዎች ብንታጠብም አያምኑንም ፣ ቢያጥቡልንም በኅሊናቸው የሚያስቀሩብን ቆሻሻ አለ።
በሰው ዓይን አንዴ ቆሽሸህ አትገኝ እንጂ ከተገኘህ መቼም ነጭ አትሆንም። አንተ ግን የደብረ ታቦሩ ብርሃን መድኃኔ ዓለምን ብቻ  “እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ” በለው  “ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች። ” ብሎ በገባው ቃል መሠረት ነጭ ያደርግሃል።
 እርሱ ወዳለባት የቅድስት ቤተክርስቲያን ተራራ በንስሓ ከደረስክና በታቦር ያበራውን ብርሃኑን ካበራልህ ነጭ ትሆናለህ። ከዚያ “አጣቢ የማያነጻውን ያህል ትነጻለህ” ከአብ የባሕርይ ልጅ ከብርሃኑ ፀዳል ስትቀርብ አንተም በጥምቀት ያገኘኸው የጸጋ ልጅነትህ ያንጸባርቃል።  ነጭ በሆንህ ጊዜ የሚያዩህ ሁሉ “በበጉ ደም ልብስህ መታጠቡን”ና ነጭ መሆኑን አይተው ይደነግጣሉ ፣  ሊሰሙህ ያልወደዱ ሁሉ ለባሕርይ ልጁ “የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት” ብሎ እንዳዘዘለት ለአንተም ጆሮ እንዲሠጡህ ያደርግልሃል።
አንተ ብቻ ከደብረ ታቦር አትቅር ፣   ካልሞትህ እንደ ኤልያስ ፈጥነህ ና ፣  በበደል ከሞትክም እንደሙሴ ተነሥተህ ና። ብቻ ወደ ደብረ ታቦር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለመምጣት ተስፋ አትቁረጥ ፣  እንደ ሙሴ ትሞታለህ እንጂ ምድረ ርስትን አታይም ብትባል ፣ እንደ ኤልያስ ትኖራለህ እንጂ ሞትን አታይም ብትባል ብቻ አንተ ከደብረ ታቦር አትቅር።
ደብረ ታቦር  – ለንደን ፣ ብሪታንያ
Filed in: Amharic