የንቅናቄያችን ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላና ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ የሱፍ ኢብራሂም በዛሬው ዕለት ከአሜሪካ መንግስት የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ረዳት ልዩ መልዕክተኛ ሚ/ር ፔይተን ኖፍ (Payton Knopf) እና የአሜሪካ ኤምባሲ የፖለቲካ አማካሪ ሚስ ኢሎና ኮይል (Ilona Coyle) ጋር በሸራተን አዲስ ውይይት አደረጉ።
በውይይቱም በርካታ አንኳር ሀራዊና ቀጠናዊ ጉዳዬች የተነሱ ሲሆን የተሻለ የጋራ ምልከታ የተያዘባቸውና መግባባት ላይ የተደረሰባቸው መሆኑን ሊቀመናብርቱ ገልፀዋል።
ሊቀመናብርቱ የህወሀት ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ በከፈተው የወረራ ጦርነት ምክንያት እየደረሰ ያለው ሰብአዊ ቀውስ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በመግለፅ የአሜሪካ መንግስት አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
አጠቃላይ ሁኔታዎችን በተመለከተ የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ገለልተኛና በተጨባጭ መረጃዎች ላይ ሊመሰረት ይገባል የሚል ምክረሀሳብ በሊቀመናብርቱ የቀረበ ሲሆን በተለይም የህወሀትን ፀብ አጫሪነትና የሽብር ተግባራት በዝርዝር በማንሳት ሽብርተኛው ድርጅትና አመራሮቹ በህግ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።
አሁን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በተመለከተ ጉዳዩ የኢትዬጵያ መንግስት ብቻ ሳይሆን እንደሀገር የኢትዬጰያ አንድነትና ህልውና ጋር የተያያዘ በመሆኑ የመላ ኢትዬጵያውያን አጀንዳ መሆኑን መቀበል እንደሚገባ ሊቀመናብርቱ አሳስበዋል። የኢትዬጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት በተመለከተም አብን ፍፁም የማይዛነፍ አቋም እንደሚያራምድ በግልፅ አስረድተዋል። በሀገራዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቀጣይ ውይይቶችን ለማድረግ ተስማምተዋል።
ድል ለኢትዮጵያችን!