>

በጋዜጠኛ ጌጥዬ ያለው እስር ላይ እግድ ተጠየቀ...!!! (ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ )

በጋዜጠኛ ጌጥዬ ያለው እስር ላይ እግድ ተጠየቀ…!!!

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ 


የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የጸረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የእነ እስክንድር ነጋን የክስ መዝገብ ላይ በሐምሌ 29/ 2013 ዓ.ም ከነበረው ቀጠሮ አዘጋገብ ጋር በተያያዘ ጋዜጠኛ ጌጥዬ ያለውን ችሎት በመድፈር ጥፋተኛ ተብሎ በ4 ወር እስራት እንዲቀጣ ከፍተኛ ፍርድቤት ባለፈው ሳምንት መወሰኑ የሚታወስ ነው ።

ውሳኔውን ተከትሎ ለባለፉት አራት ቀናት በፖሊስ ጣቢያ እንዲቆይ ከተደረገ በኋላ ፤ ነሐሴ 18 ቀን 2013 ዓ.ም ጠዋት ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተወስዷል ። ይሁን እንጂ ፤ በጋዜጠኛ ጌጥዬ ያለው ላይ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠው የቅጣት ውሳኔ ውድቅ እንዲሆን በጠበቆች አማካኝነት ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ቀርቧል።

በይግባኙ ላይ ከፍተኛ ፍርድቤቱ በጋዜጠኝነት ዘገባው ወንጀል ተፈፅሟል ብሎ ካመነ በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መሠረት ለሚመለከተው አካል ምርመራ እንዲጣራ ከማዘዝ ባለፈ መቅጣት የህግ መሠረት የለውም ። ፍርድ ቤቱ ጋዜጠኛው አደገኛ መሆኑን ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በገንዘብ ቅጣት ማለፍ ሲገባው እስራት ቅጣት ማስተላለፉ ተገቢ አይደለም በማለት በእስራቱ ላይ ይግባኝ ተጠይቋል ። መደበኛ ፍርድ ቤት ዝግ ስለሆነ ይግባኙ ታይቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ እስሩ እንዲታገድ አቤቱታ ቀርቦ መዝገቡ ለነገ ሐሙስ ነሃሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም ተቀጥሯል።

Filed in: Amharic