>

ጎባጣው ትዳሬ ...!!! (በእውቀቱ ስዩም)

ጎባጣው ትዳሬ …!!!

በእውቀቱ ስዩም


በየሳምንቱ ቅዳሜ አንድ መርህ አለኝ ፤ ያገርቤትም ሆነ የውጭ አገር  ፖለቲካ ዜና  እጦማለሁ፤ ኪነጥበብና ማህበራዊ ጉዳይ ላይ እጣድና ነፍሴን አለመልማታለሁ፤ በዚህ መሰረት ፥ ቅድም ዩቲዩብ  ላይ ስርመሰመስ ቆየሁ ::

በቀደም አንድ የሞሮኮ ዜጋ የሆነ ዘፋኝ “ ሊጋባው በየነ” የሚለውን ዘፈን በራሱ ቃና ዘፍኖ አስደምሞኝ ነበር ፤ ዛሬ ደግሞ  ሸገር ውስጥ  በስደተኝነት የሚኖር ሶርያዊ ዘፋኝ  “ ለዚህ ለዚህማ ምናለኝ አገሬ “ የሚለውን የጌቴ አንላይን ዘፈን ዘፍኖ አስለቀሰኝ   ::

ወደ ፌስቡክ ተመለስኩ፤ ባለፈው አንዱ “ ላጤ” የሚለውን ግሩፕ እንድቀላቀል መጥርያ  ልኮልኝ ነበር  ፤ ያለሁበትን ተጨባጭ  ሁኔታ ለመሰለል ፈልጎ ይመስለኛል፤ እኔም ግሩፑን ቀስ ብየ በለሆሳስ እየተራመድኩ  ሰለልኩት፤ ፍቅር የተራቡ ” ሆርኒ”  ወጣቶች የተደራጁበት ቡድን መሆኑን ደረስኩበት፤ ብዙም ሳይቆይ አንዲት ወይዘሮ  ‘ በትዳራችን ጉዳይ እንመካከር “ የሚል ግሩፕ ላይ እንድሳተፍ መጥርያ ሰደደችልኝ  ፤ ይሄ ግሩፕ የመጨረሻ  ተመቸኝ፤የመጀመርያም ተመቸኝ :: አብዛኞቹ  የግሩፑ አባላት ፥ የፍቅር ታሪካቸውን ተርከው ፤  በትዳራቸው ላይ የገጠማቸውን ችግር ዘርዝረው፥ ካንባቢ ምክርና መፍትሄ ያማትራሉ፤ እንሆ  እኔም ተሞክሮየን ለማካፈል ወሰንኩ ፥

በውቄ እባላለሁ፤  ከባለቤቴ ጋራ የተገናኘነው ባጋጣሚ ነው፤ በጊዜው  እሷ ሚስ ኢትዯጵያ ተብላ በቁንጅና ስትመረጥ እኔ አወዳደሪው ነበርኩ::  የመጀመርያዎቹ ሀያ  አመታት የትዳር ቆይታችን  ጎረቤት የሚያስቀና ነበር  ::    ከቢሮ ስመጣ  በደስታ በፈገግታና በውዝዋዜ  ትቀበለኛለች፤ ኮቴን አውልቃ ወደላውንደሪው  አፍ  እየጨመረች    “ ምሳ እስኪደርስ ፤   ክትፎ በቆጮ  እየቀማመስክ ቆይ “ ትለኛለች::   ከምሳ በሁዋላ ሶፋው ሳፋ እሲከመስል ድረስ ፍቅር እንሰራለን፤

በዙም ሳይቆይ   ጸነሰች ፤ ከዘጠኝ ወራት ላልበለጠ ጊዜ በርግዝና ቆየች ::  ያለ ብዙ ምጥ    ወንድ ልጅ ተገላገለች፤ ልጃችንም ያለ ብዙ ለቅሶ ተገረዘ !  ልጃቸን   በተወለደ በአንድ አመቱ  ዶንኪቲዩብ   ላይ እየቀረበ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠቃሚ  ምክር መለገስ እና አቅጣጫ ማስቀመጥ ጀመረ::  ሰባት አመት ሲሞላው ካሮጌ ቅጥቅጥ  ሚኒባስ ሂሊኮፍተር ሰራ ::  አሁን ካዲስ አበባ ብሾፍቱ  ራይድ እየሰራበት  ይገኛል ::

ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ባለቤቱ ጸባይ መቀየር ጀመረ:: የገቢ ምንጯና ለኔ ያላት ፍቅር በፍጥነት  እየጨመረ ሄደ፤   ለልደቴ  ፍልውሃ ያለውን ፓርክ ገዝታ በስጦታ አበረከተችልኝ ::

በዚህ አይነት ሁሉን የሚያስቀና ትዳር ውስጥ እየኖርን እጅግ  የሚያሳዝን ነገር ተከሰተ፤ ሄቲ ውስጥ የመሬት መንቀጥቀጥ ደረሰ  ! ታሊባን አፍጋኒስታን መልሶ ተቆጣጠረ፤  ይህ ግን በፍቅራችን ላይ የፈጠረው አሉታዊ ተጽኖ አልነበረውም ::

አንባቢ ሆይ !! ትዳራችን ፈረሰ የሚለውን ለመስማት፥ ምክርና ከንፈር መጠጣ ለማዋጣት   ሰፍ ብለህ እየጠበቅህ ነውን ? በቃ ሼም የለህም?   ለምን የሟርተኞችና   የክፉ ታሪክ ናፋቂዎች ግሩፕ አታቋቁምም ?

Filed in: Amharic