>

<<ጥላሁን ገሰሰ ያረፈ ቀን>> (ኤርሚያስ ለገሰ)

<<ጥላሁን ገሰሰ ያረፈ ቀን>>

ኤርሚያስ ለገሰ


…በረኸትን ለጊዜው ተሰናብተን ወጣን። ቢሮዬ ስደርስ ስለ ራሱ ማሰብ ጀመርኩ።የበረኸት  አስተዳደግ ምን እንደሚመስል ወደ ኃላ በመሔድ ቃኘሁት። ስብእናው በምን መልኩ እንደተገነባ አሰላሰልኩ። ዘለአለሙን ተንኮልና ቂም አዝሎ እንዲዞር ምክንያቱ ምን እንደሆነ በሳይንሳዊ መንገድ ተመለከትኩ።
.
በቅርብ እንዳየሁት ከሆነ የበረኸት የቂም ቁስል ለዘመናት ተዳፍኖ የኖረ ነው። የተለያየ ጊዜያቶችን እየጠበቀም ያመረቅዛል። በዚህ ወቅት እየጠበቀ በሚያመረቅዝ ቁስል እድሜ ልኩን ይሰቃያል። ዛሬም ባላሰበውና ባልጠበቀው ስልጣን ላይ ሆኖ ያሻውን እያደረገ ከስቃዩ ነፃ መሆን አልቻለም። እንዲያውም እድሜው በገፋ ቁጥር ለባሰና ለከፋ ቂም በቀል ራሱን የሚያዘጋጅ ሰው ሆነ።
.
ይህን የበረኸት ጠባይ ከአስተዳደጉ ጋር አጣምሮ ማየት ያስፈልጋል። ከበረሃ ጀምሮ በቅርብ የሚያውቁት የጫካ ጓደኞቹ በረኸትን በተበቃይነት፣ በማድባትና ዋሾነት ይጠቅሱታል። ወደ ጫካ የገባ የመጀመሪያ ሰሞን የትግራይ ነፃ አውጪን የመበቀል ከፍተኛ ፍላጐት ነበረው። በተለይ ኢህአፓ ውስጥ በነበረ ሰአት የተበቃይነት ስሜቱ መንፈሱን እየረበሸው በደህና ተኝቶ ማደር የማይችልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር።
.
በረኸት ተወልዶ ያደገው በጐንደር ከተማ ነው። አባቱ ገብረህይወት እና እናቱ ወይዘሮ ሓዳስ ይባላሉ። አቶ ገብረህይወት በእጅ ሙያ የሚተዳደሩ በመሆናቸው በድፍን የጐንደር ሕዝብ ይታወቃሉ። የበረኸት ቤተሰቦች የትውልድ ሐረግ የሚመዘዘው ከኤርትራ በመሆኑ በተወሰነ መልኩ የመጤነት ስሜት ይታይበት ነበር። በተጨማሪም በወቅቱ የህብረተሰብ የእድገት ደረጃ የእጅ ሙያተኞች በማህበረሰቡ ውስጥ የሚሰጣቸው ደረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ በበረኸት ቤተሰቦች ዘንድ የበታችነት ስሜት የተጋረደበት ነበር። ይህም ሆኖ አባቱ ገብረህይወት በጐንደር ሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ ነበሩ። ቆርቆሮ ሲያፈስ ተፈልገው የሚጠሩት እሳቸው ናቸው። የወራጅና ማገር እንጨት መምረጥ ሲፈለግ የቅድሚያ ምርጫ እሳቸው ናቸው። በአናጢነትና በግምበኝነት ብዙዎችን ያስከነዳሉ። ያለማጋነን አቶ ገብረህይወት ለጠራቸው ሁሉ “ አቤት” በማለት ቅን ታዛዥና አገልጋይ ሆነው ያለፉ ሰው ናቸው።
***
በረኸት ከልጅነቱ ጀምሮ ጓደኞቹን በማቄል የታወቀ ነው። ስሉጥ ነው። አንድ ነገር አይቶ ለማብራራት ካየበት ሰአት እጥፍ ይፈጅበታል። ለአንደበት የሚጥሙ ወጐችን በማምጣት አብሮ አደጐቹን አፍ ያስከፍት ነበር። በዚህ ምክንያት ውዳሴ ፈላጊነት ከወጣትነቱ ጊዜ ጀምሮ አዳበረ። ይህም ሁሉን ነገር አውቃለሁ የማለት በሽታ እንዲጠናወተው በር ከፈተ።
.
በሌላ በኩል በረኸት ትምህርት ጠል ነበር። በዚህ ምክንያት በመደበኛ ትምህርት ከአስራ አንደኛ ክፍል ማለፍ አልቻለም። ለጨዋታና ወግ ፈጣን የነበረው አእምሮው ለአስኳላ ህይወቱ አልጠቀመውም። ፓስተር ባደግ እግዜር ይስጠውና ከ11ኛ ክፍል አስወንጭፎ “ የተቋም አመራር” ማስትሬት ሸልሞታል።
.
በፓርላማ ለሹመት ሲቀርብ አቶ ኃይለማርያም በለበጣ ፈገግታ ታጅቦ “ ከግሪንውቺ ዩንቨርስቲ በኦርጋናይዜሽናል ሊደርሺፕ ማስትሬት ዲግሪ” በማለት አሞግሶታል። የዛሬን አያድርገውና። ታዲያ የዚያ የፓርላማ ሹመት እለት ልዩ ድምቀት የሰጡት አንጋፋው አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ነበሩ። አቶ ቡልቻ አንገታቸውን አጐንብሰው “ እንዴት የኢህአዴግ ቁልፍና የተማረ ሰው በጽህፈት ቤት ደረጃ ዝቅ ብሎ ይሰራል” በማለት ሸንጐውን አስቀውታል። መቼም አቶ ቡልቻ የኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ያነገው ድብቅ ስልጣን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥሎ መሆኑን ሳይረዱት ቀርተው አይደለም።
***
የበረኸት የልጅነቱ ህይወት ስንመለስ ካሳሁን ገብረህይወት ለሚባለው ታላቅ ወንድሙ ከፍተኛ አድናቆት ነበረው። በፓለቲካ አመለካከትም ተጽእኖ አሳድሮበታል። የኢህአፓ አባል የነበረው ካሳሁን በረኸትን ወረቀት በመበተን እና መልእክት በማድረስ ያሰማራው ስለነበር በሂደቱ ግንዛቤ ነበረው። የኢህአፓን አካሄድ ለማወቅ አግዞታል።
.
ቀን ቀናትን ወልዶ የፓለቲካ ግለቱ ሲሟሟቅ አንድ መጥፎ መርዶ በአቶ ገብረህይወት ቤት ተሰማ። ካሳሁን ገብረህይወት መሰዋቱ ተሰማ። የገደሉት ደግሞ የትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት ( ህውሓት) መሆኑ በሰፊው ተነገረ። ህውሓቶች ወንድሙ ላይ ወሰዱት የተባለው እርምጃ በረኸትን አበሳጨ። በልቡ ውስጥ የቂም በቀል እንዲቀመጥ አደረገ። የወንድሙን ገዳዬች የተባሉትን ለመበቀል ውሳኔ አሳረፈ።
.
የበረኸት በረሃ የመግባትና የመቆየት አልፋና ኦሜጋው ይሄ ነው።ቂም በቀል። የብሔር፣ መደብ ጭቆና እየተባለ የተሰበከውን ተረት ተረት የት አይቶት። ከጐንደር እግሩን ሳይነቅል የመደብ ጭቆናን በየትኛው መነፅር ተመለከተው። ጥራዝ ነጠቅ በሆነ መልኩ ሰምቶት ሊሆን ይችላል። ይሄ ለጥያቄ የሚገባ አይደለም።
.
በዘርፉ ሙያተኞች እንደሚገለጠው መጥፎ ባህሪ ያላቸው ሰዎች ክፉ ለመሆን የቻሉበት የራሳቸው መነሻ ምክንያት አላቸው። የበረኸትም መጥፎነት ካለፈው ገጠመኙ ጋር የተያያዘ ነው። ህውሓቶች ወንድሙን እንደገደሉበት በሰፊው መነገሩ የፈጠረበት የሕሊና ቁስል ሊፈወስ አልቻለም። ውስጡ በጥላቻ፣ በምቀኝነትና በጥርጣሬ ባህሪ እንዲሞላ መሰረታዊ መነሻው ይሄ ነው። ከሃዲና ማተበ ቢስ እንዲሆን እንዳደረገው እምነት ተይዞበታል።
.
በረኸት ህውሓት አደረሰብኝ ብሎ የሚያምነውን በደል ለመወጣት በርካታ ጥረቶች አድርጓል። ይህን ውስጣዊ ቁጭቱን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለመግለጥ ሞክሯል። ህውሓትን በተመለከተ የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም ጠባይ የሚያሳየው በዚህ ምክንያት ይመስላል። ታዲያ አንዳንድ የህውሓት ባለስልጣናት ይሔን ስለሚያውቁ እንደ ጉም ጅብ አተኩረው ይከታተላሉ። ስብሃት ነጋና አርከበ እቁባይ በአይነ ቁራኛ ከሚመለከቱት የህውሓት ሰዎች ዋነኞቹ ናቸው።
     ***
በረኸት በብዙ የኢህአዴግ ካድሬዎች ዘንድ ሁለት ቅፅል ስሞች አሉት። በፕሮፐጋንዳው ዘርፍ ያሉ ካድሬዎች “የኢህአዴግ ዶክተር ጆሴፍ ጐብልስ” ይሉታል። ይህንን ስለሚያውቅ አንዳንድ ጊዜ በጥራዝ ነጠቅነት ከቃረማቸው የዶክተር ጐብልስ አስተምሮቶች ነቅሶ በማውጣት ይጠቀምባቸዋል። የንግግርና የትንተና ችሎታዉ የሚቃኘውም በዚህ የጮሌነት ባህሪው በመነሳት ነው። ከአንደበቱ ውስጥ “ ውሸት ሲደጋገም እውነት ሊመስል ይችላል” የሚለውን የዶክተር ጐብልስ አሳብ የሁልግዜም አፉን ማሟሻ የሚያደርገው ነው።
.
እርግጥ በቀጥታ “ ውሸትን ደጋግመን እውነት እናድርገው” ሲል ሰምቼ አላውቅም። የሒትለሩን የፕሮፐጋንዳ ኃላፊ ዶክተር ገብልስ ስም ሲጠራ አልሰማሁም። ያልሰማሁትን ሰማሁ አልልም። ነገር ግን በየቀኑም ይሁን በሚሰጠው የካድሬ ስልጠና ላይ “ እውነት በእጃችን እያለ እንዴት ደጋግመን መናገር ያቅተናል?” በሚል መልኩ ያቀርባል። እናም ጥያቄ ሆኖ መቅረብ ያለበት “የበረኸት እውነት ምንድነው?” የሚለው ይሆናል። በርግጥም የበረኸት “ እውነት” ምንድነው? ይዘቱ ምን ይመስላል?
.
ተደጋግሞ መገለፅ ያለባቸው የበረኸት እውነቶች በራሱ መፅሀፍ ላይ በድፍረት የተገለፁ ናቸው። የቅድሚያው በአቶ መለስ ቆራጥ መሪነት ኢትዬጲያ ከማሽቆልቆል ወጥታ ሽቅብ ዳገቱን በመውጣት የአፍሪካ ነብር መሆኗ ነው። አቶ መለስ ኢትዬጲያ ካሸለበችበት ረጅም እንቅልፍ ቀስቅሶ በምስራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ባለከባድ ሚዛን አገር እንድትሆን ማድረጉ ነው።አንድ በሉልኝ።
.
የበረከት እውነት የኢትዬጲያ ከተሞች በመለስ ራዕይ ትንሳኤያቸው መበሰሩ ነው። የበረከት እውነት አገራችን ኢትዬጲያ በሚያስጐመዥ ሁኔታ ውስጥ በመገኘቷ ህዝቧ ሁለንተናዊ ለውጥ ውስጥ መግባቱ ነው። የኢትዬጲያ ህዝብ በሚያየው ለውጥ በመደሰቱ ምክንያት ፍላጐቱ እየጨመረ መሄዱ ነው። በመላው ኢትዬጲያ ህንፃዎች ማታ ማታ ተዘርተው እንደ እንጉዳይ ጠዋት የበቀሉ የሚመስሉ አስጐምዥ ሁኔታ ላይ ነን።ሁለት በሉልኝ።
.
የኢህአዴግ ገድል በተወሳበት መጽሐፉ እንደተገለፀው የበረከት እውነት የህውሓት አመራሮችና ባለሟሎቻቸው ለኢትዬጲያ ህዝብ የተለየ ፍቅር፣ አክብሮትና የፀና ወገናዊነት ያላቸው መሆኑ ነው። አመራሮቹ ሕዝብ ሲበደል አይወዱም። በሕዝብ ላይ የሚፈፀም ግፍና በደልም አምርረው ይጠላሉ። ከባድ መስዋትነት ቢጠይቅም ባይጠይቅም የሚጠሉትን ግፍና በደል በፅናት ይታገላሉ። ለኢትዬጲያ ህዝብ ሲሉ የመስዋእትነት ፅዋ የሚጐናፀፋ ናቸው።ሦስት!
.
የበረከት እውነት የህውሓት አመራሮችና ባለሟሎች ስልጣንን ለህዝብ ጥቅም እንጂ ለራስ ጥቅም ማካበቻ ማድረግ የለብንም ብለው በፅናት ያመኑና ይህንንም ወደ ተግባር ለመቀየር ያለመሰልቸት የሰሩ ናቸው። ስልጣንን የሃብት መቀራመቻ ሳይሆን አገር መለወጫ መሳሪያ በማድረግ በኢትዬጲያ እጅግ በጣም ፍትሐዊ ሊባል የሚችል ፈጣን እድገት እንዲመጣ ለማድረግ የበቁ ናቸው።
.
እንግዲህ የበረከት እውነቶች ከብዙ በጥቂቱ ከላይ የተገለፁትን ይመስላሉ። ሳንሰለች ደጋግመን ማስተጋባት አለብን በማለት የሚናገራቸው የእሱ ሃቆች ከላይ የተገለጡትን ነው። በዚህ እምነት የተነዳው በረኸትና ተከታዬቹ የሚያቀርበው የራሱ እውነታ እሱኑ እያደነዘዘ በራሱ እንዲኩራራ አደረገው። ራሱ በፈጠረው ፕሮፐጋንዳ እስረኛ ሆነ። ከማንም በቀደመ የፕሮፐጋንዳው ሰለባ እሱ ሆነ። ሐቁ ግን ሌላ ነበር። ተቃራኒው።
.
በሌላ በኩል በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት እና ካድሬዎች ደግሞ ጓድ በረከትን  “የመለስ ማኪያቬሊ” ይሉታል። እንደ እሱ አይነት የለየለት ኩሸታም በኢትዬጲያ የመንግስታዊ ስርአት ውስጥ ተፈጥሮ እንደማያውቅ ይመሰክራሉ። እንደ በረኸት ጭካኔን ደግነት፣ ካንሰርን ጉንፋን፣ ቁልቁለትን ዳገት፣ ረሃብን ጥጋብ፣ ሀዘንን ደስታ አድርጐ የሚገልፅ እንደሌለ እምነታቸው ነው። ተንኮል፣ ሴራና ሻጥር “ የአድዋ ቤተሰባዊ ገዥ መደብ” መመሪያ እንዲሆን ያደረገው ስብሃት ነጋ እንኳን ከበረኸት ብዙ እንደሚማር በአደባባይ የሚመሰክረው ነው።
.
“ከበረኸት እውነታ” ወጥተን አጠገቡ የነበርን ሰዎች በቅርበት የተመለከትነው የሰውየው ፐርሰናሊቲ ብዙ ሊባልለት ይችላል። በውስጡ አዝሎት የሚኖረው ክፋት ዝም ብሎ የመጣ አይደለም።
.
የሆነው ሆኖ በሄድኩበት ሁሉ የበረከትን ጉዳይ በአስተውሎት ስመለከተው የሚታወሰኝ የማኪያቬሊ አባባል አለ።  “በስልጣን ላይ ለመቆየት ዋናው ነገር ወደ ግብህ የምትደርስበት ስልት ሳይሆን ግብህ ነው። በመሆኑም የሞራል እስረኛ ሳትሆን በተመቸው ስልት እየተጠቀምክ ወደ ግብህ አምራ!” በማለት የገለፀው።
.
( ይህ መጣጥፍ  ” ጥላሁን ያረፈ ቀን” ከሚለው መጽሐፌ ገፅ 175 -184 ውስጥ ተቆርጦ የተወሰደ ነው።)

Filed in: Amharic