>

ውድ ወንድሜ ታማኝ በየነ፤  አህያውን ፈርተህ ዳውላውን? (መስፍን አረጋ)

ውድ ወንድሜ ታማኝ በየነ፤  አህያውን ፈርተህ ዳውላውን?

  1. ውድ ወንድሜ ታማኝ በየነ፣ ወያኔ አረጋዊ እናትህን ማጎሳቆሉ ከፍተኛ ቁጭት ውስጥ ሊከት የሚገባው አንተን ወይም የቅርብ ዘመዶችህን ብቻ ሳይሆን አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ነው፡፡  ለአማራ ሕዝብ ደግሞ ሞት ብቻ ሳይሆን የቁም ሞት ነው፡፡ 
  2. ነገር ግን፣ ወያኔ አረጋዊ እናትህን በማጎሳቆሉ ሊወቀስ አይችልም፣  ምክኒያቱም ያደረገው የባሕሪውን ነውና፡፡  የአሲል ዕባብ የተፈጥሮ ባሕሪ ሲያቃጡበት መጥመልመል፣ ሲዞሩለት መንደፍ ስለሆነ፣ ጥፋተኛው ወይም ስህተተኛው ተነዳፊው ግለሰብ እንጅ ነዳፊው ዕባብ አይደለም፡፡  ወያኔ የተፈጠረው ደግሞ ምቹ አጋጣሚ እየጠበቀ የአማራን ሕዝብ በመንደፍ ከአጋም እንደተጠጋ ቁልቋል ዘላለም ለማስለቀስ ብቻና ብቻ ነው፡፡  ስለዚህም የአማራ ሕዝብ ይህን የደደቢት ዕባብ እተፈጠረበት እደደቢት ድረስ ሂዶ ራስ፣ ራሱን ቀጥቅጦ ካልገደለውና መቸም እንደማይነሳ ካላረጋገጠ በስተቀር እንዳለቀሰ ይኖራታል፡፡
  3. ስለዚህም ወንድሜ ታማኝ በየነ፣ መውቀስ ያለብህ ውድ እናትህን የነደፋቸውን ዕባብ ሳይሆን፣ እንዲነድፋቸው ያመቻቸውን ሰው ነው፡፡  ያ ሰው ደግሞ ስሙን በክፉ ላለማንሳት እጅጉን የምትጠነቀቅለት ኦቦ ዐብይ አሕመድ ነው፡፡  ሰምተኸኛል ወንድሜ ታማኝ?  እናትህን ያስነደፋቸው ኦነጋዊው ዐብይ አሕመድ ነው፡፡     
  4. ስለዚህም ወንድሜ ታማኝ፣ ዕባቡን በጀርባው ተሸክሞ፣ እያንከባከበ እናትህ ደጃፍ ድረስ ያመጣውን አህያውን ዐብይ አሕመድን እንጅ፣  ዳውላውን ወያኔን አትኮንን፡፡  ወያኔንማ ያማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ጣዕረ ሞት ውስጥ ከተውት ነበር፣ ዐብይ አሕመድ በፍጥነት እንዲያንሰራራ አደረገው እንጅ፡፡  
  5. እስኪ ልጠይቅህ ወንድሜ ታማኝ፡፡  ዳውላውን ወያኔን ያለ የሌለ ውርጅብኝ እያወረድክበት፣ አህያውን ዐብይ አሕመድን ለማውገዝ ቅረቶ ለመተቸት እንኳን የምታቅማማው ለምንድን ነው?  ዐብይ አሕመድን ለመተቸት እንኳን የማትፈልገው፣ ዐብይ አሕመድ ባለፉት ሦስት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ የፈጸመውና ያስፈጸመው ወንጀል፣ ወያኔ በሃያ ሰባት ዓመታት ባማራ ሕዝብ ላይ ከፈጸመውና ካስፈጸመው ወንጀል በብዛትም ባሰቃቂነትም አያሌ እጥፍ እንደሚበልጥ ጠፍቶህ እንዳልሆነ በርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ዐብይ አሕመድን ለመተቸት እንኳን የማትፈልገው፣ እንደ አንዳርጋቸው ጽጌና ብርሃኑ ነጋ የሰሜን ጠል ፖለቲካ አቀንቃኝ ስለሆንክ እንዳልሆነ ደግሞ የረዥም ዘመን የትግል ታሪክህ በግልጽ ይመሰክራል፡፡ ዐብይ አሕመድ ለመተቸት እንኳን የማትፈለገው፣ በጥቅም ተገዝተህ ነው ለማለት ደግሞ በጣም ይቸግራል፣ ምንም እንኳን እግር ሂዶ፣ ሂዶ ጭቃ መግባቱ ያለ፣ የነበረና የሚኖር ቢሆንም፡፡  
  6. ስለዚህም ዐብይ አሕመድን ለማውገዝ ቀርቶ ለመተቸት የማትፈልገው ስለምትፈራው ነው ማለት ነው፡፡   ነገር ግን፣ ዐብይ አሕመድን የምትፈራው ለምንድን ነው?  አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ብርሃኑ ነጋና መሰሎቻቸው ሁርንጭላወች ስለሆኑ አህያውን ቢፈሩ አይፈረድባቸውም፡፡  አንተ ታማኝ በየነ ግን አህያውን የምትፈራው ለምንድን ነው?  
  7. አህያውን የምትፈራው ባንድ ወቀት አህያው አጠገብ ተደፍተህ ስለነበረ ከሆነ በጣም ተሳስተሃል፡፡  ያን ቀን የተደፋኸው ኢትዮጵያ እግር ሥር እንጅ አህያ ኮቴ ሥር አልነበርም፡፡  እርግጥ ነው፣ አህያው አህያ ስለሆነ፣ የወደቅከው እሱ እግር ሥር ሊመስለውና ሊበሻቀጥብህ ይችላል፡፡  እሱ ኮቴ ሥር አለመደፋትህን ግን አህያ ያልሆነ ሁሉ ያውቀዋል፡፡  ስለዚህም በዚህ በኩል አሳብ ሊገባህ አይገባም፡፡   
  8. አማራን በመግደል ኢትዮጵያን መግደል የሚቻለው በኦነግ፣ በወያኔ፣ በዐረብ ወይም በነጭ ኃይል ሳይሆን አማራን መስሎ አማራን በማደንዘዝ ብቻና ብቻ ነው፡፡  ይህን እውነታ በደንብ የተረዱ ዐብይ አሕመድና ለማ መገርሳ በቀመሙት አማራን የማደንዘዣ መርዝ ደንዝዘህ የነበርከው አንተ ታማኝ በየነ ብቻ ሳትሆን ሁላችንም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያኖች ነበርን፡፡  ዐብይ አሕመድን ስናይ፣ እናይ የነበረው የምንመኛትን ኢትዮጵያን ስለነበር፣ እግሩ ሥር ከመውደቅ አልፈን ደረታችንን ለጥይት ልንሰጥለት ሙሉ ፈቃደኞች ነበርን፡፡   አብይ አሕመድ ግን ክብር የማይወድለት አህያ ስለሆነ፣ የኢትዮጵያን አልጋ ትቶ የኦነግን ዐመድ መረጠ፡፡  እኛም ዐብይ አሕመድ፣ ዐብይ አሕመድ፣ ያህያ ሥጋ ባልጋ ሲሉት ባመድ በማለት ክብረቢስነቱን ነገርነው፡፡

በዲስኩሩ አክብረን ብናወጣው ላይጌ

በምግባሩ ዘቅጦ ወረደ እታችጌ

ተነስ አይባልም ክብረቢስ ባለጌ፡፡

  1. እኔን ራሴን መስፍን አረጋን ብንወስድ፣ በዐብይ አሕመድና በለማ መገርሳ መርዝ ተመርዠ አቅሌን በማጣት ሙሉው ከክፍሎቹ ድምር ይበልጣል (the whole is greater than the sum of its parts) የሚለውን መሠረት አድርጌ የሚከተለውን መወድስ እስከመግጠም ደርሸ ነበር፡፡ 

ጎጠኛ ማይም ነው ደንቆሮ የማያቅ

ከክፍሎቹ ድምር ሙሉው እንደሚልቅ፡፡

ይህንን እውነታ ሲገልጥ አሳምሮ

መደመር ብሎታል ዐብይ ዘአጋሮ፡፡

የሥሁልን ሽንሽን ቴድሮስ እንደሰፋ

የመለስን ክልል ዐብይ አህመድ ያስፋ፡፡

  1. ዐብይ አሕመድ ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚያደርጋቸው ንግግሮች ሁሉ ምጸቶች (irony) እንደሆኑና፣ በዐብይ አሕመድ ቋንቋ መደመር ማለት መቀነስ ማለት እንደሆነ ስገነዘብ ግን፣ ዐብይ አሕመድን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ለመቀነስ በምችለው ሁሉ ለመታገል ቆርጨ ተነሳሁ፡፡  

ዐብይ አህመድ አሊ የኦነጉ ኦቦ

አፉና ምግበሩ ሐራምባና ቆቦ፡፡

ያብይ አህመድ ስሌት፣ ኦነጋዊ ቀመር

በተግባር ቀንሶ፣ በወሬ መደመር፡፡ 

  1. ዐብይ አሕመድን ስመለከት፣ የምመለከተው የምመኛትን ኢትዮጵያን እንደልነበር፣  አሁን ላይ ግን ይህን ሰው ስመለከት የምመለከተው፣ አገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ መቸም አይታው የማታውቀው እጅግ ሲበዛ አጭበርባሪ፣ በዚያ ላይ ደግሞ እጅግ ሲበዛ አረመኔ የሆነ ኦነጋዊ ግለሰብ ነው፡፡  ዐብይ አሕመድን ስመለከት ባይነ ሕሊናየ ላይ የሚመጡብኝ፣ ወለጋ ውስጥ ቤት ተዘግቶባቸው እናቴ፣ አባቴ እያሉ እያለቀሱ በአቶን እሳት የተንጨረጨሩት የአማራ ሕፃናት፣ አሩሲ ውስጥ ሬሳቸው በሞተር ሳይክል የተገተተው አማሮች፣ ሻሸመኔ ላይ እንደ ዱላ የተጨፈረባቸው ከአማራ አስከሬኖች የተቆረጡ እጆችና እግሮች፣ አጣየ ላይ የተዘረከቱት የአማራ ማሕጸኖች፣ እንዲሁም መተከል ላይ ደማቸው እንደ ጠጅ የተጠጣው፣ ሥጋቸው እንደ ብርንዶ የተበላው የአማራ ሽሎች ናቸው፡፡  ይበልጥ ቆሽቴን የሚያደብነው ደግሞ እነዚህ ሁሉ አሰቃቂ ወንጀሎች በተፈጸሙ ማግሰቱ ዐብይ አሕመድ በሰፊው የአማራ ሕዝብ ላይ የሚያፌዘው ማፌዝ ነው፡፡ የአማራን ሞት ከዝንብ ሞት እንደሚቆጥረው ለማሳየት ሲል ብቻ፣ በአማራወች ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ እስኪፈጸም ድረስ ሥራየ ብለ ይጠብቅና፣ በነገታው አዳባባይ ወጥቶ አበባ ይተክላል፣ ወይም ደግሞ በፌስቡክና በትዊተር ስለ አበባ ውበት ይደሰኩራል፡፡  የአማራን ሕዝብ ያቆስልና፣ ማቁሰሉ ስለማያረካው በቁስሉ ላይ እንጨት ይሰድበታል፡፡    
  2. ዐብይ አህመድ የጭቆናን ምንነት በቅጡ ሊረዳ በማይችልበት ለጋ እድሜው “ያማራ ጨቋኞችን” ለመታገል ጫካ ገብቶ የወያኔን ጡት እየጠባ ባማራ ጥላቻ ተመርዞና ተሰቅዞ ያደገ፣ አማራን በማጥፋት አማራዊ ናት የሚላትን ጦቢያን አፈራርሶ በሷ መቃብር ላይ የኦሮሞ አጼጌ (Oromo empire) ለመመሥረት ቆርጦ የተነሳ፣ በዚያ ላይ ደግሞ በማንነቱ ምክኒያት በሥርሰደድ (chronic) የስነልቦና በሽታ የሚሰቃይ ኦነጋዊ አውሬ ነው፡፡  ስለዚህም፣ የአማራ ሕዝብ ለሕልውናው ሲል ይህን ኦነጋዊ አውሬ መንቀል አለበት፡፡  መንቀል ያለበት ደግሞ ሁለተኛ እንዳይበቅል ከሥሩ መንግሎ ነው፡፡   
  3. ስለዚህም ወንድሜ ታማኝ በየነ፣ ባንድ ወቅት ከሥሩ ወድቄ ነበር ብለህ ዐብይ አሕመድን አትፍራው፡፡  ምን ማለት እንዳለብህ ላንተ ለመናገር ባልደፍርም፣ ብትለው ደስ የሚለኝ ግን የሚከተለውን ነው፡፡  በዲስኩርህ ደንዝዠ የኢትዮጵያ መሲህ መስለኸኝ ከእግርህ ሥር ወድቄ ነበር፡፡  አሁን ግን የኢትዮጵያ መላከሞት መሆንህን ከተግባርህ ስለተረዳሁ፣ ለኢትዮጵያ ሥል ከሥርህ እንደወደኩ ለኢትዮጵያ ስል ከሥርህ እመነግልሃለሁ በለው፡፡  ልትመነግለው ከፈለክ ደግሞ፣ ወያኔን ለመመንገል ከፍተኛ ሚና እንደተጫወትክ፣ ዐብይን ለመመንገል ከፍተኛ ሚና የመጫወት እምቅ ችሎታ እንዳለህ ነጋሪ አያስፈልግህም፡፡  ዐብይ አሕመዳውያን ደግሞ ከዐብይ አሕመድ ሥር ወድቀኻል በማለት ሞራልህን ለመስበር የሚሞክሩት፣ ዐብይ አሕመድን መንግለህ ለመጣል ማድረግ የምትችለውን ወሳኝ አስተዋጽኦ አሳምረው ስለሚያውቁና እንደጦር ስለሚፈሩት ነው፡፡
  4. ባሁኑ ወቅት የአማራ ሕዝብ ትልቁ ጠላት ዐብይ አሕመድ እንጅ ወያኔ አይደለም፡፡  ወያኔ ማለት በዐብይ አሕመድ ላይ የተጫነ ዳውላ ማለት ስለሆነ፣ አህያው ከተወገደ ዳውላው የትም አይደርስም፡፡  የአማራ ሕዘብ ከዐብይ አሕመድ አፍዝ አደንግዝ ከተላቀቀ፣ ወያኔና ኦነግ እዳቸው ገብስ ነው፡፡   

 

መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic