>

ወታደራዊው ፍርድ ቤት በሀገር ክህደት የተከሰሱ 48 ግለሰቦች ላይ የቅጣት ውሳኔ አሳለፈ...!!! አዜአ

ወታደራዊው ፍርድ ቤት በሀገር ክህደት የተከሰሱ 48 ግለሰቦች ላይ የቅጣት ውሳኔ አሳለፈ…!!!
አዜአ

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር መከላከያ ሰራዊት የደቡብ ዕዝ ቀዳማዊ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ከአሸባሪው ህወሓት ጋር አብረው አገርን በመክዳት ወንጀል የተከሰሱ 48 የዕዙ አባላትን ከሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወር እስከ 18 ዓመት ከስምንት ወር በሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወሰነ።
ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው ዛሬ በዋለው ችሎት በ47 መዝገቦች የተከሰሱ እስከ ሌተናል ኮሎኔል ማዕረግ ድረስ ባላቸው ግለሰቦች ላይ ጭምር ነው።
በዚህ መሰረትም፡-
1ኛ. ግደይ ገብረዮሐንስ 18 ዓመት ከሶስት ወር ፅኑ እሰራት
2ኛ. ሹምዬ ወልደብርሀን 17 ዓመት ፅኑ እስራት
3ኛ. ገብረኪዳን ወልደማርያም 18 ዓመት ፅኑ እስራት
4ኛ. ሀብቱ አበራ ግደይ 17 ዓመት ፅኑ እስራት
5ኛ. ወንድም ገብረዋህድ 18 ዓመት ከሶስት ወር ፅኑ እስራት
6ኛ. ካሱ ብርሀነ ተወልደ 18 ዓመት ፅኑ እስራት
7ኛ. ሹመንዲ ትርፌ 18 ዓመት ከስምንት ወር ፅኑ እስራት
8ኛ. ገብረሳሙኤል ወላይ 14 ዓመት ከሁለት ወር ፅኑ እስራት
9ኛ. አደም ያደታ ስድስት ዓመት ፅኑ እስራት
10ኛ. ኪኒሶ መኮንን አምስት ዓመት ፅኑ እስራት
11ኛ. ላዕከ ክፍሌ 13 ዓመት ከአንድ ወር ፅኑ እስራት
12ኛ. ብርሀነ ወላይ 10 ዓመት ፅኑ እስራት
13ኛ. ወልዳይ ብርሀኔ አምስት ዓመት ከአምስት ወር ፅኑ እስራት
14ኛ. ሀዱሽ ገብረመድህን 13 ዓመት ከሁለት ወር ፅኑ እስራት
15ኛ. ብርሀኔ ገብረወልድ 17 ዓመት ፅኑ እስራት
16ኛ. አብርሀም ጉበቦ ሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወር ፅኑ እስራት ሲወሰንባቸው፤ በቀሪዎቹም ላይ እንደየጥፋታቸው መጠን የቅጣት ወሳኔ ተላልፎባቸዋል።
ዓቃቢ -ሕግ በተከሳሾቹ ላይ የሰው ምስክርና ማስረጃ አስደግፎ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል በዕዙ ውስጥ ያሉ የሰራዊቱ አባላት በመከላከያና በመንግስት ላይ እንዲያምፁ ማነሳሳት፣ አባላት ከሰራዊቱ እንዲኮበልሉና የአሸባሪውን ህወሃት ታጣቂ ቡድን እንዲቀላቀሉ የተለያዩ ጥረቶችን ማድረጋቸው ይገኙበታል።
በተለይ ከአሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ አመራሮች ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነት በማድረግና የወገንን ጦር ለጠላት ጥቃት አሳልፎ መስጠት፣ የመከላከያ ሰራዊቱ የጦር መሳሪያዎች አገልግሎት እንዳይሰጡ ማበላሸት እንዲሁም በንግግር የአሸባሪውን ህወሃት ፕሮፓጋንዳ በሰራዊቱ ውስጥ መንዛታቸውም በክስ መዝገቡ ተብራርቷል።
የደቡብ ዕዝ ፍትህ ቡድን መሪ ሻለቃ ፀሐይ ምንዳ በሰጡት መግለጫ፤ “በዕዙ ውስጥ የነበሩና የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ግለሰቦች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከህወሐት ጋር በማበር፣ በግንባር ከከፈተብን ጦርነት በላይ በሰራዊቱና አገር ላይ ትልቅ ጥፋት ለማድረስ ተንቀሳቅሰዋል” ብለዋል።
ህወሃት በሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በዜጎች ላይ አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ሲፈጽም መቆየቱን አስታውሰው፤ “የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ሰዎች ምንም እንኳን በአገር ላይ ከባድ ወንጀል የፈፀሙ ቢሆንም የሕግ የበላይነትን መሠረት አድርገን በተጨባጭ ማስረጃ አስደግፈን በሕግ እንዲቀጡ አድርገናል” ሲሉ ገልጸዋል።
“ተጠርጣሪዎቹ ከጥቅምት 24ቱ ጥቃት በፊትም ከአሸባሪዎቹ ህወሐትና ሸኔ ጋር ሲሰሩ ነበር” ያሉት ሻለቃ ፀሐይ፤ በተለይ የሸኔን ታጣቂዎች ለመደምሰስ ሲካሄዱ በነበሩ ኦፕሬሽኖች ላይ ከጠላት ጋር መረጃ በመለዋወጥ ሰራዊቱን ሲያስመቱ የነበሩ የጦር አመራሮች እንደነበሩ አስረድተዋል።
ተከሳሾቹን ለፍርድ ለማቅረብ በነበረው የማስረጃ ማሰባሰብ ከፍተኛ የአገር ፍቅር ያላቸው የዕዙ አባላት መረጃ ከመስጠት ችሎት ቆሞ ምስክር እስከመሆን ድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን መጥቀሳቸውን ዘግቧል።
Filed in: Amharic