>

አብርሃም ገብረ መድሕንን እስከማውቀው....!!! (ሰለሞን ደሜ)

አብርሃም ገብረ መድሕንን እስከማውቀው….!!!

ሰለሞን ደሜ

 

*…. የትናንቱ ኤርትራዊ የዛሬው ትግራዋይ
የትናንቱ አርቲስት የዛሬው ታጋይ አብርሃም ገብረ መድህንን በፍቃዱ ላደረላቸው ጌቶቹ ማገዶ ለቃሚ ሆኖ ላየው ግራ መጋባትንም አግርሞትንም ያጭራል…!
       አብርሃም የተወለደው ኤርትራ ምፅዋ /ባፀ/ ነው ። ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት በ1982 መጨረሻ ምፅዋ በሻዕቢያ ሲያዝ ከቤተሰቡ ጋር ተፈናቅለው አሥመራ በመጡ ጊዜ ነው ። ገና ለወጣትነት ሳይደርስ ። በጊዜው አባቱ አቶ ገብረመድህን የወደብ ሾፌር ነበሩ ። /እዚህ ላይ በአንድ ኢንተረቪው ትግራይ አድዋ ነው የተወለድኩት የለውን አስተውሱልኝማ/
        ጊዜ ተለውጦ ድጋሚ ያገኘሁትና መልካምም አሣዛኝም ገጠመኞችን ያሳለፍነው ከኤርትራ ተፈናቅለን ከመጣንበት ከ1983 ክረምት ጀምሮ ኢህአዴግን ጠጋ ጠጋ ማለት እስከጀመረበት 1991_92 ድረስ ነው ።/ እርግጥ እኔ ቀጥታ ሳይሆን በሱዳን ዞሬ ነው የመጣሁት ።/
          በዚህ ወቅት ጃንሜዳ ከነበረው የተፈናቃይ ማረፊያ ጀምሮ እኛ ቤት በመከራየት አብርሃምና ቤተሰቡ በተለየ ሁኔታ የቀበሌ ቤት በማግኘት ወደ ጎፋ ሠፈር ለመክተም በቃን ። የምንኖርባቸው ቤቶች ከቤተሠብ ብዛት አንፃር ይጠብቡን ሥለነበር በባለቤቴ ወንድም የመኪና ወንበር ማደሻ /ታፒሴሪ/ ወስጥ አብርሃምና ሁለቱ ወንድሞቹ/ተክሊትና ዘርዑ/ ጨምሮ ሌሎችም ተጣብበን እናድር ነበር ። ቆየት ብሎ አብርሃም ጎፋ ማዞሪያ አካባቢ ባር ሶሎዳ በሚባል ጭፈራ ቤት የመሐሙድንና የተክለ ተሥፋዝጊ ዘፈኖችን በመዝፈን እየተዋጣለት ሄደ እኔና አንድ ወዳጃችን የቤቱ ደምበኛም የአብርሃም ጋርድም የሚወዳድቅ ሽልማት ሰብሳቢ ሆነን ከረምን ። ከዚያ አብርሃም በቀበሌ ወጣት ማሕበር በኩል ወደ ኢህአዴግ ሲጠጋጋ የቀረነው ለወያኔ በነበረን ጥላቻ የተነሳ መራራቁ ግድ ሆነ ።
         ለሦስተኛ ጊዜ የተገናኘነው አብርሃም እጅግ ዝነኛና ሃብታም ሆኖ በቤት መኪና እኔ ደግሞ እንግዳ ልቀበል አየር መንገድ የተገናኘን ጊዜ ነው ። እንዴ አብርሽ ሠላም ነህ ብዬ ሥጠጋ ዞር ብሎ “እንዴ ሰለሙን አለኻ ዲኻ” ብሎ ቆም እንኳ ሳይል መሥታወቱን ዘግቶ በአስደነገጠኝ ጊዜ ነው ።
          ለአራተኛ ጊዜ የተገናኘነው እኔ በልጅነቴ እንጦጦ ለእናቴ እንጀራ መጋገሪያ ማገዶ ሥለቅም አንደነበረው በፍቃዱ ለአደረላቸው ጌቶቹ ማገዶ ሲለቅም በዚህ ፎቶ ነው ።
Filed in: Amharic