>

የቁማርተኞች ኢትዮጵያ ትለፈኝ....!!!   (  ጎዳና ያእቆብ)

የቁማርተኞች ኢትዮጵያ ትለፈኝ….!!!

    ጎዳና ያእቆብ

ስልጣን በኃይል በማባበል/ማታለል (flattery/fraud) እና በማሳመን (persuasion) ይያዛል:: ህዋሃት ድሮም ይሁን አሁን በhard እንደሚመጣ ጎረምሳ ነው:: ጉልበትን እንደብቸኛ አማራጭ የወሰደና በማባበልና በማሽኮርመም ብቻ ለመደገፍ ፍቃደኛ የሆነውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመረዳትና <<በሬ ሆይ ሳሩን አይተህ ገደሉን ሳታይ>> የሚለውን አካሄድ ያልተረዱና መረዳትም ያልፈለጉ ይመስላሉ:: የአብይ አህመድ መንግስት ግን ማባበልና ማታለል እና ማደናገርን መርህ አድርጎ የተነሳና የኢትዮጵያዊያን በተለይም የኢትዮጵያኒስቶች ስነ ልቦናን ጠንቅቆ የተረዳ ይመስላል::
ይኼ አካሄዱ በአጋጣሚ በስሜት የመጣ ሳይሆን ስልታዊ ነው:: ለምሳሌ እርካብና መንበር የተሰኘው መፅሀፉ ላይ (ገፅ 36) ላይ << መቼም ሥልጣን ዝም ብሎ አይገኝም:: መሃሉ ላይ መውጣትና መውረድ: መውደቅና መነሳት ይኖራል:: የተሳካለት ባለሟል ግን #ሥልጣን የመያዝ ፍላጎት እንዳለው #ሳያሳብቅ ጥሩ #ተዋናይ በመሆን በትረ ሥልጣንን መጨበጥ የቻለ ነው::>> ሲል #የመተወን #የማታለል እና #የማማለል ስልቱን በራሱ አንደበት ገልፆልናልና አጭበርባሪነቱን ሲነግረን እንመነው::
አድር ባዮችን እንዴት ወደራስ ጎራ መክተት እንደሚቻልና እንደሚያስፈልግ በገፅ 38 ላይ <<ሰዎች ራስ #ወዳድ ናቸውና #በጥቅም ሂድባቸው>> ብሎናል:: ምን ያህል ግምገማው ትክክል እንደሆነ አሁን በተግባር የምናየው ነው:: ከሰማይ የገዘፉና እጅግ በጣም ስናከብራቸው እና ስንሳሳላቸው የነበሩ ሰዎች ሁሉ ተሰብስበው እንዴት ሆዳቸውንና ጥቅማቸውን እሽሩሩ እንዳለ የምናውቀው ሀቅ ነው::
ቀውስ ፈጥሮ ቀውስ አስተዳድሮ ብቸኛ መፍትሄ ሆኖ የመውጣትን አድፈላጊነት በተመለከተ << በተለይም ወዳጅና ጠላት የሚለየው በችግር ቀን ነው ብሎ የሚያምነው ህዝባችን ልብ ውስጥ #ከነእድፍ #ተደላድሎ ለመቀመጥ በችግር ጊዜ መድረስን የመሰለ ጥሩ አጋጣሚ አይገኝም::. መንግስት በሚገዛቸው ህዝቦች ላይ የሞራል የፓለቲካና የአይዲዮሎጂ የበላይነት እንዲኖረው ያስችለዋል>> ይለናል:: #ከነእድፍ የሚለው #ይሰመርልኝ:: አብይ አህመድ #እድፉን #አራግፎ እና በሀሪውን አርቆ ለቦታው የሚመጥን ስነምግባር መያዝ ሳይሆን #ከነእድፌ #እንዴት #እቀመጣለሁ የሚል አካሄድ እንዳለው ግልፅ ማሳያ ነው:: አዳነች አበቤ ኃፍረቷን ሁሉ ትታ ተረኛ ሳንሆን አገልጋይ ነን ስትል ህዝብን ምን ያህል እንደሚንቁና አገዛዝን አመራር አድርገው ሊያሳምኑን እና ሊያደናግሩን እየሞከሩ ነውና እስቲ የአብይ አህመድን ግጥም እናስታውሳቸው::
የእውነት ለመምራት….የስኬት ተምሳሌት – እንዲሆን መምራትህ ውል እንዲይዝ ሥሩ መምራት እና  መግዛት አይጥፋህ ድንበሩ::ለምትመራው ጀማ ራሥህን ካልሰጠህ #ስስቱን በመተው”እኔ” ያለ ቀን ነው  መሪ #የሚሞተው:: የመምራት ኃይልህን… በቅንነት ያዘው በጥበብ አፅድለው ምክንያቱም… ተመሪ ውስጥ ነው የመሪ እድሜ ያለው::.   እርካብና መንበር (ገፅ 77)
አብይ አህመድ ውስጥ ስንት አብይ አህመዶች አሉ ለሚለው ከተለዋዋጭ ባህሪው ለሚነሱ ጥያቄዎች ቢያንስ ከአንድ በላይ እንደሆኑ ( እኔ ቢያንስ ሶስት አብይ አህመዶች አሉ [1) ኦሮሙማ የምትባል እጅግ በጣም የሚወዳት ሚስት ያለው [2] ኢትዮጵያ የምትባል ምናልባት ሊወዳት የሚችል ግን መቼም ሚስቱን  ትቶ ሚስቱን ፈቶ የማያገባት ውሽማ ያለው [3] በአፍቅሮተ ራስ የተነደፈውና ከሰባት አመቱ ጀምሮ ንግስና ወይም ሞት የሚለው አብይ አህመዶች አሉ ብዬ ባምንም የአብይ አህመድን አብይ አህመዶች ከአንደበቱ እንስማ::) <<አንዳንዴ ደግሞ መስፍኑ #የተለበጠ ማንነት ሊኖረው ይገባል:: ሰዎች የሚያውቁት #የላዩን ብቻ ሲሆን አስፈላጊ የሆነ ጊዜ ግን ሁለተኛውንና #ድብቁ #ማንነት ይገለጣል:: በመልካሙ ጊዜ ህዝብን በፍቅር መያዝ አስፈላጊ ነው:: ፍላጎታቸውን በመፈፀም የልብ ትርታቸውንም በማዳመጥ ደስ የሚያሰኛቸውን ነገር በማድረግ በህዝብ ልቦና ውስጥ ተደላድሎ መቀመጥ ይቻላል:: ነገር ግን ይህ አካሄድ አንዳንዴ ችግር አያጣውም:: ታዲያ የአመፅና የመክዳት ምልክት የታየ ጊዜ #በሁለተኛውና #በተለበጠው #ማንነት #መገለጥ ተገቢ ይሆናል:: አስተማሪነት ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣትና ተግባራዊ በማድረግ በፍቅር ወቅት #መልአክ በአመፅ ጊዜ ግን #ሰይጣን ሊሆን እንድሚችል ማሳወቅ አለበት:: ማንም ውሃ እና እሳት አብረው ቀርበውለት እጁን ወደ እሳቱ መክተትን ምርጫው አያደርግም:: #ያንቀላፋ ሰይጣንን ቀስቅሶ በራሱ ላይችግርን ማምጣት የሚሻ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም:: ቢኖር እንኳን የሚተባበረው ሲለሚያጣ ብቻውን ይቀራል::>> ሲል በገፅ 36 ላይ የተከፋፈለ ማንነቱን አሳውቆናል::
ስለዚህ እንዲህ አይነት ያንቀላፉ ሰይጣኖች (ሲያንቀላፉ ላለፉት ሶስት አመታት የሰሩት ሰይጣን የሚያስቀና እኩይ ተግባር መገለፅ ከሆነ ሲነቁ ምን እንደሚሆኑ ፈጣሪ አያሳየን!) እና ቁማርተኞች የሚያስተምሩኝ የሚያሳስቡኝ ኢትዮጵያዊነት የለም:: ሊኖርም አይችልም::
ኢትዮጵያዬ ሲሉ <<ያልወለድኩት ልጅ ሲለኝ አባባ አፌን አለኝ ዳባዳባ>> እንዲሉ ነው የሆነብኝ:: ዶ/ር ዲማ ነገዎ የሚሰንኩኝ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ትብራብኝ:: እኔ በልቤ ያለችውን ታሪክ ጠገብ እድሜ ጠገብ የሆነውን ታላቂቷን ኢትዮጵያ ይዤ እኖራለሁ:: ዘክራለሁ:: አከብራለሁ:: አነግሳለሁ:: ከቁማርተኞች ከአስመሳዮችና ከአድር ባዮች ጋር የምቆምላትም የምዘምርላትም ኢትዮጵያ የለችኝም::
Filed in: Amharic