>

ፍትህ ለእስክንድርና ለባልደረቦቹ....!!! (ደረጄ ከበደ)

ፍትህ ለእስክንድርና ለባልደረቦቹ….!!!

ደረጄ ከበደ

በእስክንድር ነጋ ላይ የተመሰረተው ክስ ከቶ አንዳችም እውነትነት  የለውም። ዶ/ር አብይ አህመድ የሰውን ቆዳ ከነህይወቱ በገፈፉ ወንጀለኞች ላይ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ እንደነእስክንድር ነጋ ዓይነቶችን ንፁሃንን ማጥቃታቸው ለምን ይሆን?
እስክንድር ነጋ እንኳንስ ወጣቱን በገንዘብ ለአመፅ ሊያነሳሳ ይቅርና ጨዋነት ያልተላበሰ አነጋገር እንኳን ከአንደበቱ የማይወጣ፣ ከዴሞክራሲ እና ከፍትሕ ጥያቄ ውጭ ምንም አጀንዳ የሌለው  እውነተኛ የሕዝብ ልጅ መሆኑን ህይወቱ አስመስክሯል። በዚህ ክቡር ኢትዮጵያዊ ላይ ዓይን ያወጣ ሀሰት መናገር ትልቅ ጥፋት ነው። ንፁሀንን በሃሰት መወንጀል ጊዜው ሲደርስ ማስጠየቁ አይቀርም። እስክንድርን  የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት በሃሰት አስሯል። ይህ ተግባር እጅግ ያሳፍራል።
ዶ/ር አብይ አህመድ እና አቶ ታከለ ኡማ ቤቱን እያስፈረሱ በኮሮና ወረርሽኝ  ሜዳ ለወረወሩት ዜጋ ደራሽ ነው እስክንድር። ሓላፊነት የጎደለው ክፉ አስተዳደር ሜዳ ላይ ያፈሰሳቸው የትላንት ባለቤቶችና ባለተስፋዎች ዛሬ አስፓልት ላይ ግራ ተጋብተው በገዛ ሃገራቸው ሲጎሳቆሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ እና ሹሞቻቸው ዝንብ የጎዱ ያህል እንኳን  አልተሰማቸውም። በሞቀ ቤታቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ኑሮሯቸውን እንደወትሮው ያለሃሳብ ይኖራሉ። እስክንድር ግን ያንን ዝም ብሎ የማየት ድንዳኔ አልፈጠረበትም። እሱ ለተገፉት የሚጮህ፣ ዕድሜውን ሁሉ በእስርና በስቃይ ያሳለፈ ጨዋ ኢትዮጵያዊ ነው። የአቢይ መንግስት ስንት ጊዜ ይህንን ምግባረ ሰናይ ሰው አንገላታው? የሞአ አንበሳ ዘእምነገደ የኢትዮጵያን የአንበሳ ሃውልት በአረምና በቆሻሻ መሃል አዲስ አበባ ጥለውት እስክንድርና ባልደረቦቹ  ሲያፀዱ  ፖሊሶች ልክ ወንጀል እንደፈፀሙ ዓይነት ፖሊስ ጣቢያ ወሰዷቸው። ይህን ጉድ ምን ይሉታል? ይሄ ነው የዴሞክራሲና የመደመር ገፅታው::
መንግሥት የጣላቸውን፣ ያጎሳቆላቸውን፣ መኖራቸውን የረሳቸውን ዜጎች እስክንድር በማሰቡ የጠቅላይ ሚንስትሩ መንግሥት ምን አስቆጣው? ለምንስ ‹‹ከባለደራስ ጋር ግልጽ ጦርነት እንከፍታለን›› አሰኘው? ዜጎችን መንከባከብን ለምን ከእስክንድርና ከባልደረቦቹ አይማርም? ሰው ራሱ በጎ ማድረግ ካልቻለ ሌላው ቢቀር ሌሎች በጎ ሲያደርጉ መንገድ ባለመያዝ መተባበር እኮ ትልቅነት ነው። ሃጥአን የፃድቃን ጠረን እንደሚያስጨንቃቸው ሁሉ እስክንድርን በበጎ ተግባሩ ማየት ብዙ ሆድ አደር ፖሊቲከኞች ከህሊናቸው ጋር እንዲጋፈጡ የሚያደርግ መስተዋት ስለሚሆንባቸው  አይወዱትም።
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች እነስንታየሁ ቸኮልና እነአስቴር ስዩም የመሪያቸው የእስክንድር ደቀመዝሙሮች በምግባር የታነፁ እና ስለዴሞክራሲ ዋጋ የከፈሉ ናቸው። ዴሞክራሲ አለ የምንለው እንደስንታየሁ ቸኮል እና እስክንድር ነጋ ዓይነት ዜጎች ያላቸውን የፖሊቲካ አቋም ያለምንም ገደብ ለማስተላልፍ መድረክ ሲያገኙ፣ መግለጫ ለመስጠት ከየሆቴሉ በመንግሥት የእጅ አዙር ክልከላና እቀባ ሳይባረሩ፣ በመንግሥት በታጀበ ቄሮ ሳይዋከቡ መናገርና መፃፍ ሲችሉ ብቻ ነው። እስክንድር በታከለ ኡማ ሴራ አዳራሽ ሁሉ እንዲዘጋበት ተደርጎ አስፓልት ዳር መግለጫ ሲሰጥ ማየት እጅግ ያሳዝናል። እስክንድር በአደገበት ከተማ ስቴዲዮም ገብቶ የኳስ ጨዋታ እንኳን እንዳያይ በአቢይ ፖሊሶች ተከልክሏል።
እስክንድር ነጋ ተነፍጎት የቆየው የመናገርና የመሰብሰብ ነፃነት ለጀዋር መሃመድ እና ለአጃቢዎቹ ነበር የተሰጠው። እናም ጠቅላይ ሚንሥትሩ ለፈቀዱት የመንቀሳቀስ መብት ይሰጣሉ፤ ላልፈቀዱትና ለሚፎካከራቸው ግን ወዮለት ነው ነገሩ?  ይህ ነው እንግዲህ የብልፅግና ፓርቲና የመሪው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዴሞክራሲ። የሚፎካከራቸውን አፍ መዝጋት፣ ማዋከብ፣ መደብደብ፣ ጨለማ ቤት ማሰር፣ . . . ያለምንም ምክንያት የታሰሩ የተቃራኒ ፓርቲ አባላትን የቀጠሮ ልዋጭ ለ20 ለ 30 ጊዜ በመስጠት ታሳሪዎችን ያለምንም በደል ለወራት በእስር ማሰቃየት፣ ይህ ነው የአብይ ዴሞክራሲ?
 የሰኔውን የአማራ ክልል አመራሮች ግድያ ተከትሎ በጉዳዩ ምንም እጃቸው የሌለበትን ነገር ግን የገዥውን ፓርቲ  የሚቃወሙትን የተለያዩ በተለይ የአማራ መብት ተሟጋቾችን በእስር ቤት አጉሮ በቀነ ቀጠሮ ብዙ ወራቶች ሲያሰቃያቸው መክረሙ የቅርብ ጊዜ ክፉ ትዝታ ነው። አሁንም በእስር ያሉ አሉ። አብይ የሚያስሩት ለስልጣናቸው የሚያስፈራቸውን ተፎካካሮዎችን  እንጅ ነፍሰ ገዳዮችንና ባንክ ሰባሪዎችን አይደለም፤ ይህንን በተደጋጋሚ አይተናል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹አስረን አናጣራም፣ አጣርተን እናስራለን›› አሉ በሥልጣን ወንበር ላይ የተቀመጡ ሰሞን። ያ አባባል ዓመትም አልቆየ ሰዎች ያለምክንያት እየታሰሩ መንግሥትም ‹‹መረጃ ልፈልግ›› በሚል ሳቢያ ወንጀል አልባ እስረኞችን ለዘመናት በማንገላታት ላይ ናቸው።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አሁን የምንጠይቅዎት ያለምክንያት የታሰሩት ንፁሃንን በአስቸኳይ እንዲፈቱ ነው።እስክንድር ነጋ ላይ የተደረደሩት ክሶች የተፈበረኩ እንደሆኑ ወዳጆች ብቻ ሳይሆኑ ጠላቶቹም ያውቃሉና መንግሥት ሆይ ትክክለኛውን ነገር አድረግ። እስክንድር ነጋን ከባልደረቦቹ ከስንታየሁ ቸኮል፣ ከአስቴር ስዩም እና ከአስካለ ደምሌ ጋር በነፃ አሰናብት። ከ200 ቀናት በላይ ያሉበትን የማናውቀውን የታገቱትን የአማራ ተማሪዎችንም ያሉበትን ሁኔታ ለህዝብ በግልፅ አስታውቅ።
Filed in: Amharic