ጋዜጠኛ መአዛ መሃመድ
*…. ባለጌዎችን በጨዋነት ሌቦችን በሀቀኝነት ጯሂዎችን በትህትና አሸንፎ – ፖለቲካ የሴረኞች የአድርባዮች እና የአስመሳዮች ብቻ መጠራቀሚያ አለመሆኑ ያሳየን – እስክንድር ነጋ
ሰለ እስክንድር ሳስብ ዕውነታው እንዲህ ነው !
ምክንያቱም በእስክንድር አልበገር ባይነት ያገጠጠ አድር ባይነታቸውን ስለሚያዩት ፣ በእስክንድር ጀግንነት ውስጥ የበዛ ድክመታቸው ልቆ ስለሚታያቸው ፣ በእስክንድር ዕምነት ውስጥ የነሱ ቃል አባይነት ባዶነታቸውን ስለሚነግራቸው ፣ በእስክንድር ንፅህና ውስጥ የእነሱ ጉድፍ ስለሚያሳክካቸው፤ ሴራቸውን ቀድሞ ተረድቶ ስለ አጋለጠባቸው ይታሰር ይሉታል። እብድ ይሉታል።ታከለ ዑማን አምነው እስክንድርን የፍትህ ስርዓቱ መፈተሻ እንዲሆን ፈርደውበታል።
ሆኖም ግን እስክንድር የተናገራቸው ዕውነታዎች በሙሉ አይናቸውን አፍጥጠው መጥተው ዛሬ እየኖርናቸው ነው።
እስክንድርን ስለምን አምባገነኖች ይፈሩታል? ስለምንስ ይጠሉታል?” ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሆን ዘንድ ሦስት መሠረታዊ ዕውነታዎች ማየቱ በቂ ነው።
የመጀመሪያ ጉዳይ ከሃዲዎች ሁልጊዜ የደበቁትን ማንነታቸውንና ገመናቸውን ፍፁም ሰላማዊ እና ጨዋነት በተሞላበት መንገድ ስለሚያሳይባቸው ነው።
ሁለተኛው ጉዳይ እስክንድር የሚሠራውን ሁሉ ጠንቅቆ በማወቁ ነው። እያንዳንዷ ድርጊቱ ፍፁም ዕውቀት በተሞላበትና በተጠና መንገድ የምትከወን ናት። ስህትት የሚባል ነገር እርሱን አያውቀውም።
ሦስትኛውና የመጨረሻው ጉዳይ በእስክንድር ትህትና ፣ መልካምነትና ታዛዥነት ምክንያት የሚጋለጠው ተረኝነታቸውና አምባገነንነታቸው በመሆኑ ነው።
እስክንድርን የማውቀው ዛሬ አይደለም። ትላንት ህወሓት ኢህዴግ በሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት እስርቤት ሆኖ ነው። ሁል ጊዜም እስክንድር በነፃነቱ ስትመጣ ነብር ይሆናል። ይቆጣል። ፍፁም ከሚታወቅበት ሰላማዊነቱና ትህትናው ይቀየራል።
ያኔ “ጦርነት እንከፍትብሃለን” ተብሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊት ለፊት ሲነገር እንዲህ ብሎ ነበር መልስ የሰጠው “ንጉሥ ሆይ ኃይል የእግዚአብሔር ነው።” እናም አሁንም እንላለን ኃይል የእግዚአብሔር ነው። እስክንድርን ፍቱት። እስክንድር የሚያስፈልገን ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችን ብቻ አይደለም። የሚያስፈልገን ለፖለቲካው ብቻ አይደለም።
የእስክንድር አይነት ቅን ሰዎች በልበ ሙሉነት በፖለቲካችን ውስጥ እየተንቀሳቀሱ መኖር እንደሚችሉ ፣ ፖለቲካ የሴረኞች ፣ የተንኮለኞችና የአድር ባዮች ብቻ እንዳልሆነች ማሳያ ምልክታችን እስክንድር ነው እና እስክንድር ፍቱልን።