>

በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የተሸረበው  የእጅ አዙር ጦርነት ሁነኛ መፍትሔ ካልተበጀለት ለኢትዮጵያ አደጋን ሊጋብዝ ይቻለዋል ማን ነው ተወቃሹ ? ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የተሸረበው  የእጅ አዙር ጦርነት ሁነኛ መፍትሔ ካልተበጀለት ለኢትዮጵያ አደጋን ሊጋብዝ ይቻለዋል!….ማን ነው ተወቃሹ ?

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)


ምክንያታዊ የሆነ ሰው እንደሚታዘበው በታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት ኢትዮጵያ ላይ ያላቋረጠው የግብጽ፣ ሱዳን እና የምእራባውያን ትችት፣ የአሸባሪው ወያኔ ወረራ በምእራባውያን ዐይን ችላ መባሉ፣የሱዳን አለ አግባብ የሆነው የድንበር ወረራ፣ ምእራባውያን የ2021 (እ.ኤ.አ.) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ውድድር ትክክል እና ፍትሃዊ ያልሆነ፣ ለአንድ ገዢ ቡድና ያደላ ነበር  ወዘተ ዘወተ ማለታቸው ድብቅ፣ በማስክ የተሸፈነ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም የታለመ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ቀንዲል እንዲቀለቀል ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የመነጨ አልነበረም፡፡ የምእራባውያን መንግስታት በአብዛኛው ( ሁሉንም በደምሳሳው ማሳጣት ከባድ ይማስለኛል፡፡ በአፍሪካም ሆነ ኢትዮጵያ ምድርላይ ዴሞክራሲ እንዲጎመራ ቢያንስ በግለሰብ ደራጃ ህሊና የፈጠረባቸው እና ሞራል ያላቸው እንደነ አናጎሜዝ የመሰሉና እውነተኛ የዲሞክራሲ ተቋማትና የተማሩ ሰዎች አይጠፉም) ግራም ነፈሰ ቀኝ በኢትዮጵያ የምእራባውያን ዋነኛ ፍላጎት በአፍሪካው ቀንድ፣ በቀይ ባህር ኮሪደር እና በናይል ወንዝ አኳያ ያላቸውን ድብቅ ፍላጎት ለሟሟላት የታለመና የታቀደ ነበር፡፡ ሁለተኛው ድብቁ ፍላጎታቸው ደግሞ በእጃ ዙር ጦርነት ለመካፈል እንዲያመቻቸው፣የሳይበር ጉዳት ለማድረስ፣ህገወጥ የጦር ማሳሪያ ለማሰተላለፍ እንዲረዳቸው፣ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እንዲስፋፋ ባላቸው ድብቅ አጀንዳ ወዘተ ወዘተ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ላይ የጥቃት ሰበዛቸውን የመዘዙት፡፡ ለምስኪኑ የኢትዮጵያ ህዝብ መቼም ቢሆን የሚደማ ልብ ኖሯቸው አያውቅም፡፡ እዬ እዬ ሲዳላ ነው፡፡ በእኔ የግል አስተያየት ( የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በስፋት እንዲሄዱበት በዚህ አጋጣሚ እጋዛለሁ) የጥቁር ገበያን መስፋፋት ችላ የሚሉት የኢትዮጵያ ህዝብ በመንግስት ሀላፊዎች ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ ለማድረግ ነው፡፡

It is intended to camouflage dominance over the Horn of Africa, the Red Sea corridor, and the Nile River

በእኔ የግል ግምገማ መሰረት ከላይ ለመጠቃቀስ የሞከርኳቸውና ሌሎች በምአራባውያን የሚሸረቡ  የፖለቲካ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሴራዎች ሁሉ የታቀዱት፡-

  • ኢትዮጵያን ለማዳከም፣ከተቻለም ኢትዮጵያን ለመከፋፈል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የተዘጋጀለትን የሞት ድግስ ፈጥኖ እንዳይረዳ በተለያዩ ዘዴዎች ያጠምዱታል፡፡ በሃይለኛው ፕሮፓጋንዳቸውና በሆሊዉድ ምርጥ ፊልሞቻቸው አመሃኝነት የአነርሱ የስነ ልቦና ተገዢ ለማድረግ በብዙ ባጅተዋል፡፡
  • ማናቸውም ግለሰብ በተለይም የአፍረካውን ቀንድ እና የመካከለኛው ምስራቅ የጂኦፖለቲካ ጉዳይ በቅጡ ለሚያውቅ ግለሰብ የኢኮኖሚ አሻጥር እና የውክልና ጦርነት የግብጽ የንግድ ምልክት እንደሆነ አስረጅ አያስፈልገውም፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ሁሉ መቼም ግዜ ቢሆን ይህን መዘንጋት አይኖርባቸውም፡፡

በዛሬው አስተያየቴ ላይ ኢትዮጵያ በውስጥና ከውጭ ሀይሎች ሊደርስባት ስለሚችለው ጥቃት ዳሰሳ ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡ በዛሬው ጽሁፌ ላይ ኢትዮጵያውያንን፣የእነርሱን ወዳጆች እና አለም አቀፉ ህብረተሰብ አንድ ጥያቄ መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ ይሄውም አሸባሪውና አረመኔው የወያኔ ዘረኛ ቡድን ኢትዮጵያን እያጠቃ ያለውን ብቻውን ነው ወይ ? የሚለው ነው፡፡ የኢትዮጵያ የውስጥ ጠላቶች ባለፉት አመታት ኢትዮጵያን ያደሙት ብቻቸውን አይደለም፡፡ ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያን እያደሙ የሚገኙት ብቻቸውን አይደለም፡፡

ለምንድን ነው ግብጽ፣ ሱዳንና ሌሎች አጋሮቻቸው ኢትዮጵያውያን ከወደቁበት በፍጥነት እንዳያገግሙ ሴራቸውን የሚጎነጉኑት ?

ኢትዮጵያ ዛሬ ለምትግኝበት ውስብስብ ችግር ውስጥ እንድትዶል የዳረጋት መሰረታዊ ምክንያት ምን ይሆን ? ለዚህ መልሱ በርካታ ሊሆን ይችላል፡፡ እስቲ በየአካባቢችሁ ተወያዩበትና መልሱን ለማግኘት ሞክሩ፡፡ በእኔ በኩል በኢትዮጵያ ታሪክ አኳያ፣የዳር ድንበር ጉዳይ፣ሉአላዊነት ጉዳይ፣የህገመንግስት እና የጎሳ ፖለቲካ አስፈላጊነት ወይም አላስፈላጊነት በተመለከተ ቢያንስ ላለመስማመት መስማማት መንፈሳዊ ወኔ ስለከዳን በችግር አረንቋ ውስጥ እንደተዘፈቅን ይሰማኛል፡፡ ይህ የእኔ የግል አስተያየት ነው ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የተጠቀሱት ሀገራት በዋነኛነት ሴራቸውን የሚጎነጉኑት አንድነታችን እንዲላላ ፣ከወደቅንበት እንዳንነሳ ለማድረግ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ የውስጥ ጠላት የሆነው አሸባሪው የወያኔ ቡድን ለኢትዮጵያ የሚደማ ልብ የለውም፡፡ ሰብዓዊነት ስሜት አልፈጠረበትም፡፡ እንደሚታወቀው ለወያኔ የዘረኛ ቡድን ዲሞክራሲያዊነት ተፈጥሮአዊ ባህሪው አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ ከተደቀነባት ብሔራዊ አደጋ እንድትፈወስ ወይም እንድትተርፍ ከተፈለገ የኢትዮጵያ አንድነት በጽኑ አለት ላይ መቆም አለበት፡፡ የሰብዓዊ መብቶች መከበር አለባቸው፡፡ 

ለኢትዮጵያ አንድነት መሰረታዊ ችግር ወይም የችግሮች ሁሉ ችግር የሆነው ህገመንግስቱ መሆኑን መረዳት እና መቀበል ለኢትዮጵያ ውስጣዊ ሰላም ይበጃል ብዬ አስባለሁ፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ህገመንግስት ሰላም ለማግኘት ይከብዳታል፡፡

ከግብጽና ሱዳን ጋር አጋር ለመሆን የተዘጋጁት ወይም አጋር ነን የሚሉት የአሸባሪው የወያኔ ቡድን ፊትአውራሪዎች ሀገርን የሸጡ ባንዳዎች ናቸው ተብሎ ቢጻፍ ስህተት አይመስለኝም፡፡

በቅርብ ግዜ ውስጥ ከእንግሊዙ የዜና አውታር ቢቢሲ ቴሌቪዥን እውቅ ጋዜጠኛ ስቴፈን ሳከር the BBC’s Stephen Sackur (Hard Talk) ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት የአሸባሪው ወያኔ ቡድን የፕሮፓጋንዳ ማሺነሪ አፈቀላጤ በሰጡት አስተያየት ለኢትዮጵያ አንድነት ምንም አይነት ስሜት እንደሌላቸው አሳይተዋል፡፡የጥላቻ መርዝ ነበር የረጩት፡፡ ይህ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የሚዘራውን የጥላቻ መርዝ የሚያስተጋቡለት የግብጽ እና የሱዳን የዜና አውታሮች እንዲሁም የምእራቡ አለም መገናኛ ብዙሃን ሰፊ ሽፋን ይሰጡታል፡፡

ለአብነት ያህል የተባበረችው አሜሪካ የውጭ ተራድኦ ድርጅት አስተዳዳሪ ሚስስ ሳማንታ ፓወር ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ሴትየዋ ከኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በኋላ በጭፍን ይደግፉት የነበረውን የአሸባሪውን ቡድን ወያኔ በተመለከተ ያላቸውን አቋም እንደገና ለመመርመር እድሉን ያገኛሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

ሳማንታ የወያኔ ቡድን ወደ ኋላ መመለስ እንደማይፈልግ ሙሉበሙሉ የሚረዱ ይመስለኛል፡፡ ወያኔ ወደ ኋላ የሚመለስ አይደለም፡፡ ከስህተቱ በፍጹም መታረም አይችልም፡፡ ወያኔ ወረራውን በአፋር እና አማራ ክልሎች አስፋፍቶት ይገኛል፡፡ ወያኔ ሰላማዊ ዜጎችን በግፍ የሚጨፈጭፍ አረመኔ ድርጅት ነው፡፡ ይህ የለየለት የኢትዮጵያ ጠላት እና ዘረኛ ድርጅት በአፋር ክልል 107 ህጻናት እና 40 ኢትዮጵያዊ እናቶችን በግፍ ጨፍጭፏል፡፡ በቅርቡ ነሐሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ደግሞ ከ300 በላይ ኢትዮጵያዊ የአማራ ተወላጆች በወለጋ ምድር በኦነግ ሸኔ አሸባ ቡድን አባላት በግፍ እንደተገደሉ ከመገናኛ ብዙሃን ተሰምቷል፡፡ በእውነቱ ያሳዝናል፣ህሊናን ያደማል፣ ሆድንም ይበጠብጣል፡፡

የወያኔ አሸባሪ ቡድን በአማራ ክልል የጦር ወንጀል እንደፈጸመ የሚያሳዩ የመገናኛ ዘገባዎች በርካታ ናቸው፡፡( ለአብነት ያህል በደቡብ ጎንደር በታሪካዊቷ ከተማ ደብረማርቆስ ከተማ የአንድ ቤተሰብ አባል የነበሩ 5 ሰዎችን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን ዜጎችን ጨፍጭፏል)፣መንደሮችን አቃጥሏል፣ በመቶ ሚሊዮኖች የሚያወጡ ንብረቶች ተሰርቀዋል፡፡ ወይም ወድመዋል፡፡

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ነሐሴ 20 2021 ሳማንታ በሰጡት አስተያየት ወይም ትእዛዝ የአማራ ክልላዊ መስተዳድር ከትግራይ ክልል ለቆ እንዲወጣ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የአማራ ሀይል በትግራይ ምድር አልነበረም፡፡ ምናልባት ሳማንታ ‹‹ ምእራብ ትግራይ ›› ለማለት ፈልገው  የኢትዮጵያን ታሪክ መልሰው እንዲያነቡ እጋብዛቸዋለሁ፡፡ ይህ ምድር የትግራይ አካል ሆኖ አያውቀም፡፡ እነርሱ ‹‹ ምእራብ ትግራይ›› የሚሉት ‹‹ ወልቃይት›› የቤጌምድር አካል ነው፡፡

ሌላው አስገራሚውና አሳዛኙ ሁነት ደግሞ የአሜሪካ የውጭ ተራድኦ ድርጅት አስተዳዳሪ የሆኑት ሳማንታ የወያኔ አሸባሪ ቡድን በማይካድራ ከተማ የፈጸመውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ትንፍሽ ለማለት አልፈለጉም፡፡ በሳማንታ ቃላት ውስጥ ፍትህ አለችን ? መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ትቼዋለሁ፡፡

እውቀት ሳይኖረው እውቀት እንዳለው የሚያሰመስለው አረመኔው ጌታቸው ረዳ በየጊዜው ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ላይ መዘባበቱ ሲታሰብ በእውነቱ ያሳዝናል፡፡ ይህ ያለ ምክንያት አልነበረም የሆነው፡፡ በነገራችን ላይ የአሸባሪው የወያኔ ቡድን የፕሮፓጋንዳ ማሽን የሚረዳው ከኢትዮጵያ ደሃ ህዝብ በተዘረፈ ብር ነው፡፡ ይህ ቡድን በሚዘራው ዶላር ልብወለድ የሆኑ ነገሮች ወደ እውነት ለማስመሰል ተጠቅሞባታል፡፡ ይህ እኩይ ቡድን የውጭ ሀይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብተው እንዲፈተፍቱ ጥርጊያ መንገድ ከፍቶላቸዋል፡፡ አያያዟን አይተው ጭብጦዋን ቀሟት የሚለው ተረት ለኢትዮጵያ የሚስማማ ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ሁሉ የውስጥ ችግራችንን በሰለጠነ መንገድፈተን ወደ አንድነት፣ወደ ህብረት መምጣት አለብን፡፡ በምንም አይነት መልኩ ለውጭ ጣልቃ ገብነት የሚረዱ ቀዳዳዎችን መድፈን አለበት፡፡ ጎበዝ ኢትዮጵያ በየወሩ ፣በየግዜው የተባበሩት መንግስታት የመወያያ ርእስ ስትሆን ሊያሳስበን ሊያስጨንቀን ይገባል፡፡ አንድ ነገር ማስተዋል ያለብን ጉዳይ ምእራባውያን ከሁሉ ነገር በፊት የሚያስቀድሙት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ነው፡፡ እነኚህ ሀይሎች ነጻ የኢኮኖሚ ርእዮት አለምን የሚደግፉ ናቸው፡፡ በአንድ ሀገር ኢንቨስት ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ ምንአልባትም ሉአላዊነትን በአስጠበቀ መልኩ ከምእራባውያን ጋር የኢኮኖሚ ትብብር ማድረጉ መልካም ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ምእራባውያን የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅም ሊያስጠብቅልን ይችላል በሚል ስሌት የወያኔን አሸባሪ ቡድን ደግፈው መቆማቸው በምንም አይነት ተቀባይነት ያለው አይመስለኝም፡፡ የአንድን ሀገር ብሔራዊ ባንክ ቤት ቅርንጫፍ ጽ/ቤትን የሲቪሎችን ንብረት የሚያወድም እኩይ ድርጅት ለምእራባውያን ዘለቄታ ጥቅም የሚያስገኝ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አይችልም፡፡ ጸረ ኢትዮጵያ ድርጅት የሆነው የወያኔ ቡድን በነውር የሚኮራ ነው፡፡ ይህ ድርጅት ነውረኛ፣ዋሾ እና ቀጣፊ ነው፡፡ ስለሆነም ይህን ድርጅት መደገፍ ዛሬም ባይሆን ነገ ተነገወዲያ በታሪክ ያስጠይቃል፡፡

በአሜሪካ የሚመራው የብይነ መንግስታቱ ድርጅት ልዩ ወኪል እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 18 2021 ባወጣው መግለጫ በትግራይ ምድር በአሸባሪው የወያኔ ቡድን አባላት የተፈጸሙ ሰቆቃዎችን በተመለከተ ምንም አይነት መረጃ የለኝም በሚል አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት የፈጸሙትን ግፍ ሊደብቁላቸው ሞክረዋል፡፡ ያሳዝናል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ የሚከተለውን ጥያቄ  የአለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ለሆኑት ሲኤንኤን፣ቢቢሲ፣ እንዲሁም አለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ለአብነት ያህል አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣አለም አቀፍ የግጭት ማእከል ወዘተ ወዘተ ያቀርባል፡፡ ይኀውም  የሀሰት መረጃ፣የውሸት ዜና  ለአለም አታሰራጩ የሚለውን ነው፡፡ 

የወያኔ አሸባሪ ቡድን ሞራል የሌለው የማይድን ካንሰር መሆኑን ብዙዎች የፖለቲካ ተንታኞችና ትንታግ ጋዜጠኞች በብዙ የሄዱበት ጉዳይ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያን ሀብት ሀገር በመዝረፍ የራሳቸውን የግል ህይወት  እና የቤተሰባቸውን ህይወት ያሻሻሉት፣ ሀብት በሀብት ላይ የጨመሩት ለምልአተ የትግራይ ህዝብ ያመጡለት የማህበራዊ ህይወት እድገት አልነበረም፡፡ ዛሬ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት ያላሳለሰ ጥረት ፣በአለም አቀፍ ረጂዎች ደግነትና የአለም ባንክ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በመታቀፍ፣ ነው ህይወቱን ያቆየው፡፡ ስለሆነም ወያኔ ፣ሞራል የለውም፣ሰብዓዊነት የለውም፣ የትግራይ ህዝብ በውጭ እርዳታ ስር እንዲቆይ የሚያደርግ ቡድን ሰብዓዊነት ስሜት ያልፈጠረበት ነው፡፡

ልጅህን በፎጣ ጠቅልለህ አትጣለው (Do not “throw the baby with the bath towel.” )

ከዶክተር አብይ መንግስት አስተዳደር ጋር በአንዳንድ የፖሊሲ አካሄድ አኳያ የማልስማማባቸው ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ከሰብዓዊ ስሜት አኳያ ጥያቄ ውስጥ የሚዶል አይመስለኝም፡፡ በሌላ አነጋገር አቶ ጌታቸው ረዳ እና የተባበረችው አሜሪካ የውጭ ተራድኦ አስተዳዳሪ ሚስስ ሳማንታ የኢትዮጵያ መንግስት ለትግራይ ተፈናቃዮች የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ ደንቃራ ፈጥሯል፣ በትግራይ ተወላጅ ወንድሞቻችን ላይ ለተፈጸመው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሁሉ ተጠያቂው የኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ነው እያሉ በየግዜው ለተለያዩ የአለም መገናኛ ብዙሃን የሚሰጡት መግለጫ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ በህሊና ሚዛን ላይ ተቀምጠን ስንመዝነው በሰሜን ኢትዮጵያ ይሄ ሁሉ ምስቅልቅል እንዲፈጠር በዋነኛነት ምክንያት የሆነው የወያኔ አሸባሪ ቡድን ነው፡፡ ይህ አሸባሪ ቡድን የኢትዮጵያን ድንበር ይጠብቅ በነበረው የሰሜን እዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመሰንዘር የጦር ወንጀል የፈጸመ እኩይ ድርጅት ነው፡፡ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በማበር ኢትዮጵያን ለማድማት በይፋ፣በአደባባይ ተንቀሰቅሷል፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈጽሟል፡፡ በትግራይ፣አማራ እና አፋር ክልሎች በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለመፈጸማቸው ምንም ክርክር የሚያጭር አይመስለኝም፡፡ በተለይ በትግራይ ለተፈጸሙት አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሁሉ የኢትዮጵያን መንግስት ብቻ ተጠያቂ የሚያደርጉት እነ ሳማንታ እና የምእራቡ አለም የሕሊና ሚዛናቸውን የተጠቀሙ አይመስለኝም፡፡ በእኔ በኩል ማስረጃ ስለሌኝ በያንዳንዱ በተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ የምለው የለኝም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በትግራይ ምድር ለደረሰው አሳዛኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በዋነኝነት ተጠያቂው ይህ አሸባሪ ቡድን ነው የሚል የግል አስተያየት አለኝ፡፡ ምክንያቱም የጦርነት ቋያ እንዲነድ በመጀመሪያ እሳት የለኮሰው የወያኔ አሸባሪ ቡድን በመሆኑ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአፋር እና አማራ ክልል በንጹሃን ዜጎች ላይ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል፡፡ በነገራችን ላይ የምእራቡ አለም እና በእነርሱ ቁጥጥር ስር የወደቁ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን፣የፖለቲካ መሪዎቻቸውና የአለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች መሪዎቻቸው እንደሚዋሹት ሁሉ ውሸት ባህል ሆኗል፡፡ ኢሰብዓዊነት፣ሰብዓዊነት ሆኗል፡፡ በዚች አለም ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽሙ ተመስጋኝ፣ተወዳሽ እየሆኑ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህል በምእራቡ አለም በተለይም በተባበረችው አሜሪካ ፕሬዜዴንት ግብጽና ሱዳን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የመከራ ዶፍ ያዘነበውና በማዝነብ ላይ የሚገኘው የህውሃት አሸባሪ ቡድን ከወቀሳ ይልቅ ውዳሴ ቀርቦለታል፡፡

በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ ለሰብዓዊነት የሚቆረቆሩ፣ለሰብዓዊነት ዋጋ የቆሙ፣ለሀገር ድንበር ክብር የሚፋለሙ እና ለሉአላዊነት የሚሰሩ ፍትሃዊ ባልሆነ ሁኔታ በምእራባውያን ሀይሎች  ይተቻሉ፡፡ ምን አይነት የግርንቢጥ አለም ውስጥ እንደምንገኝ ልብ ልንል ይገባል፡፡ የወያኔ ዘረኛ ቡድን የፈጸማቸው መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገቢርም በነቢብም በርካታ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ምእራባውያን የሚሰማ ጆሮ፣የሚያይ አይን የላቸውም፡፡ ሰምተው እንዳልሱ፣አይተው እንዳላዩ መሆን ግብራቸው ከሆነ ዘለገ ያለ ግዜያት ተቆጥረዋል፡፡ በነገራችን ላይ ከማያይ አይንና ከማያስማ ጆሮ በስተጀርበሳ የተደበቀ ትልቅ አጀንዳ አላቸው፡፡ ይሔውም የወያኔ አሸባሪ ቡድን የውጭ ሀይል ( የምእራባውያንም ሆነ የእነርሱ ደጋፊ ሆኑ ሀገራት) ታማኝ አገልጋይ እንዲሆን ካላቸው አቅድ ይመነጫል፡፡

በሁለቱ ሀይሎች ማለትም በኢትዮጵያ መንግስትና አሸባሪው የወያኔ ቡድን ለማለት ነው፡፡ ከአሰብዓዊነት፣ እና ኢሰብዓዊነት አኳያ ያላቸውን ልዩነት ለማወዳደር ይረዳኝ ዘንድ እንደሚከተለው የግል ምልከታዬን ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

1.የትግራይ አሸናፊ ቡድን አጀንዳ የትግራይ ኤሊቶች አጀንዳ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አጀንዳ ግን የኢትዮጵውያኖች አጀንዳ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የኢትዮጵያ አጀንዳ የቆመው ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን ነው፡፡( እርግጥ ነው ከኢትዮጵያ ተጻራሪ አቋም ያላቸው ግለሰቦችና በመንግስት መዋቅር ውስጥ በተለያዩ ሀላፊነት ላይ የተቀመጡ አንዳንድ የከንቱ ከንቱዎች እንዳሉ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ይሰማል፡፡

  1. የወያኑ አሸባሪ ቡድን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ተቋማት ያፈረሰ ቡድን ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በተቃራኒው እንደገና በማዋቀር ላይ ይገኛል፡፡ የወያኔ አሸባሪ ቡድን ራሱን እንደ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊ በፍጹም ቆጥሮ አያውቅም፡፡ ኢትዮጵያ ትፈረስ እያለ በአደባባይ የፎከረ ድርጅት ነው፡፡ (It encourages “Down! Down Ethiopia ) ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ ሲሉ ለመሞት እንደ ተርብ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የወያኔ አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሲል ወደ ሱዳን ልኡካኑን ልኳል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የኢትዮጵያን ጠቅላይ ሚነስትር ዶክተር አብይን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ መንግስታት ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ለማግባባትና ለመምከር ወደ ኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገራት ልከዋል፡፡

3.የወያኔ አገዛዝ ስልጣን ላይ በነበረበት ግዜም ሆነ ከስልጣኑ ተሸቀንጥሮ ከወደቀ  እና ወደ አሸባሪነት ግብሩ ከተመለሰ በኋላ እጅግ ግዙፍ እርዳታ ከምእራቡ አለም ተቀብሏል፡፡ ምክንያቱም ታማኝነቱ ስለተረጋገጠ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ፈጣኑና ቀላሉ የሀብት ማማ ላይ ፣ውጫ የሆነው ሌብነት፣ሙስና ወዘተ በረጂዎቹ ምእራበውያን አልተተቸም፡፡ በአለም የገንዘብ ድርጅት ውስጥ ከሁለት አስርተ አመታት በላይ በምርምርና ጥናት ያገለገሉት ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ በአንድ የጥናት መጽሐፋቸው ላይ እንደጠቀሱት ከሆነ ማእከላዊ መንግስት የስልጣን ዘመናቸው ግዜ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ መዝብረዋል፡፡

  1. ኢትዮጵያን በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳት የሚገኘው የጎሳ ፖለቲካ መርዝ የተቀመመው በዋነኝነት በወያኔ አሸባሪ ቡድን ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንን ከፋፍሎ ለመግዛት ያቆመው የጎሳ ፖለቲካ አሁን ድረስ ሰራሄ መፍትሔ አልተገኘለትም፡፡ እርግጥ ነው ብሔራዊ ስሜት እንደገና መልሶ እንዲያንሰራራ የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ እርምጃዎችን መውሰዱ እሙን ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የጎሳ ፖለቲካ በሌላ የፖለቲካ አካሄድ ስለመቀየሩ ገና ከኢትዮጵያ መንግስት በይፋ አልተነገረም፡፡ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ሳይቀር በሰለጠነ መንገድ፣በኢትዮጵያ ህዝብ ምልአተ ይሁንታ መቼ እንደሚሻሻል ወይም እንደሚቀየር ገና የታወቀ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ በጎሳ ፖለቲካ ምክንያት አፍጦ የመጣ አደጋ ውስጥ ልትዶል እንደምትችል የሚያከራክር አይደለም፡፡ ጠባቦችና ጎሰኞች ለኢትዮጵያ ተስፋ ሳይሆኑ ችግሮች ናቸው፡፡

5.የወያኔ ቡድን ጋዜጠኞች፣የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና አባላቶቻቸው፣የሲቪል ማህበር መሪዎችን እንደ ወንጀለኛ ከመቁጠሩ ባሻግር ሀገራቸውን ጥለው ወደ ባእድ ሀገር እንዲሰደዱ አድርጎ ነበር፡፡ አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ ሀገር ውስጥ ገብተው በሀገሪቱ የፖለቲካ ጨዋታ ላይ እንዲካፈሉ ጋብዞ እንደነበር የሚያከራክር አይደለም፡፡ከተጋበዙት የፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል ከኦነግ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የወጣው የኦነግ ሸኔ ቡድን ዛሬ ከአሸባሪው የህውሃት ቡድን ጋር የትግል አንድነት መስርቻለሁ ማለቱ የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡

  1. የወያኔ አሸባሪ ቡድን በጋምቤላ፣አማራ ክልል የጎሳ ማጽዳት ወንጀል የፈጸመ ድርጅት ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በሶማሌ ክልል በኦሮሚ ክልሎች መሃከል የነበረው ግጭት ዛሬ የለም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በአፋር ክልልና ሶማሊያ ክልሎች መሃከል አልፎ አልፎ አልፎ በድንበር ይገባኛል ምክንቶች የተነሳ ግጭቶች ይከሰታሉ፡፡ በኦሮሚያ ክልል በተለይም በወለጋ አራቱም አቅጣጫዎች፣በቤኒሻንጉል ክልል በአማራ ተወላጆች ላይ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ግድያን ጨምሮ ፣በኢትዮጵያዊ የአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸመው ግፍ እንዲቆም የኢትዮጵያ መንግስት ታሪካዊ ሃለፊነት አለበት፡፡ ድርጊቱ በማንም ይፈጸም የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎቹን በህይወት የመኖር መብት ለማስከበር በታሪክ ፊት ቆሟል፡፡ የግፍ ጽዋው ሞልቶ አየፈሰሰ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በኢትዮጵያዊ የአማራ ተወላጆች ላይ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ ከእብድ ውሻ በከፉ አረመኔዎች የሚፈጸመውን ግፍ በፍጥነት ማስቆም ያለበት ይመስለኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት ወድቋል በማለት ጀርባችንን መስጠት ያለብን አይመስለኝም፡፡ ልጃችንን በፎጣ ጠቅልለን እንደማንጥለው ሁሉ የኢትዮጵያን መንግስት በህሊና እና የሞራል ሚዛን ላይ ቆመን ማገዝ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ከስሜት ደጋፊነት ባሻግር ከጥፋቱ እንዲማር በእውነት መሰረት ላይ ቆመን መምከር የዜግነት ግዴታችን ይመስለኛል፡፡ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣እንዲሁም የህግ የበላይነት እንዲከበሩ በብዙ መባጀት አለብን የሚለው ሌላው መልእክቴ ነው፡፡
  2. የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ መንግስት ጋር ባደረገው የሰላም ስምምነት ምክንያት፣ኢትዮጵያ በቀይ ባህር በኩል የባህር በር ለማግኘት በር የተከፈተላት ይመስላል፡፡ በወያኔ እኩይ ሴራ የፈረሰው የኢትዮጵያ የባህር ሀይል እንደገና ሊመሰረት ነው መባሉ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ እንደ መልካም ዜና ይቆጠራል፡፡

8.ባለፉት አስር ወራቶች ብቻ የወያኔ አሸባሪ ቡድን ባማይካድራ የጦር ወንጀለ4 እና የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል፡፡ በእኔ በኩል ብዙ ማይካድራዎችን ተከታትያለሁ፡፡ በቅርብ ግዜ ውስጥ 107 ህጻናትን ጨምሮ በአፋር ክልል ከ42 በላይ ንጹሃን ዜጎች ሴቶች እህቶቻችን በወያኔ አረመኔ ቡድን በከባድ መሳሪያ በግፍ ተገድለዋል፡፡ በአማራ ክልል ሴት እህቶቻችን ተደፍረዋል፣ እጅግ ግዙፍ የሕዝብና የመንግስት ሀብት ተዘርፏል የተረፈው ወድሟል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪል ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻችን ተገድለዋል፡፡ የወያኔ አሸባሪ ቡድን ከአለም አቀፍ ህግ በተጻራሪ በመቆም ህጻናትን በጦር ሜዳ በማሰለፍ በሰብዓዊ ጋሻነት ተጠቅሞባቸዋል፡፡ TPLF deployed Tigrean children as human shields and fodders of brutality. በርካታ የፖለቲካ ተንታኞችና የጦር ስልት አዋቂዎች በኢትዮጵያ መንግስት የአንድ ወገን ተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ ተችተውታል፡፡ እውን እንዲህ አይነት የትግራይ ገበሬ በክረምት እርሻ ላይ እንዲቆይ በሚል የአንድ ወገን ተኩስ ማቆም ውሳኔ ከሰብዓዊ ስሜት ያፈነገጠ ነውን ? መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ትቼዋላሁ፡፡

9.የኢትዮጵያ መንግስት የአንድ ወገን የተኩስ ማቆም ውሳኔ ካደረገ በኋላ የወያኔ አሸባሪ ቡድን ወረራ በማድረግ የጦርነት አውዱን አስፍቶታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ወረራውን ለመቀልበስ የሚያድረገው ፍልሚያ ምክንያታዊ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በሌላ በኩል ቱርክን ከመሰሉ ሀገራት የሚያደርገው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያስመሰግን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ከቱርክ ጋር የነበረውን ታሪካዊ ግንኙነትና በአሁኑ ዘመን ያለውን የቱርክን ሁነኛ ፍላጎት በቅጡ መመርመር ከኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ አዋቂዎችና የመንግስት መሪዎች እንደሚጠበቅ ማስታወሱ አይከፋም፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ የወያኔ አሸባሪ ቡድን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ አሁን ድረስ ባለመፈለጉ ከሰብዓዊ ስሜት አኳያ የከሸፈ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለሰላም ያላቸው ፍላጎት የሞተ ነው፡፡

10.በሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለሰ ዜናዊ ተነሳሽነት የተጀመረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በታሪክ የራሱ ስፍራ አለው ብዬ አስባለሁ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የወያኔ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎችና አፋሽ አጎንባሾቻቸው የመዘበሩት የሀገር ሀብት ደግሞ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በአጭሩ የዚህን ታላቅ ፕሮዤ የሙስና ምንጭ አድርገውት ነበር፡፡ ለአብነት ያህል በሜቴክ ከፍተኛ ሃላፊዎች የተፈጸመው ምዝበራ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር የተዘገበ መራር ሀቅ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ በሙስና እስከ ጭንቅላታቸው ድረስ ተዘፍቀው የነበሩትን የዚህ ታላቅ ፕሮዤ የስራ ሃላፊዎች የኢትዮጵያ መንግስት ከቦታቸው እንዲነሱ ከማድረጉ ባሻግር በፍትህ አደባባይ እንዲቆሙ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ዛሬ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስራ እየተጣደፈ ከመገኘቱ ባሻግር፣ለሁለት ግዜያት ያህል ወደ ግድቡ የውሃ ሙሊት ስራ ተከናውኗል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የኢትዮጵያ መንግስት ከግብጽና ሱዳን ጋር የግድቡን ግንባታ በተመለከተ ከሱዳንና ግብጽ መንግስታት ጋር በሚያደርጋቸው ውይይትና ድርድሮች ግዜ የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ እንደነበር የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ ግብጽ፣ሱዳን እና አጋሮቻቸው ሃብታም ሀገራትና የመሃከለኛው ምስራቅ የነዳጅ ሀብት ባለጸጋ ሸሪኮቻቸው በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አኳያ ደስተኛ አይደሉም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ በችጋር የሚሰቃዩ ዜጎቿን ወደ ተሻለ የኑሮ ደረጃ በማውጣት፣ በእድገት ጎዳና ትገሰግሳለች በሚል ምክንያት ነው፡፡ ወይም የባላይነታችን ሊያከትመለት ይችላል በሚል ይሆናል፡፡ This is because they believe that their hegemony will evaporate into thin air.

ወያኔና የፌክ ምርጫው

1.ሌላው ወያኔ በታሪክ ከሚወቀስባቸው ተግባራቱ መሃከል አንድም ግዜ እውነተኛ የምርጫ ውድድር ማካሄድ ሳይችል መቅረቱ ነበር፡፡ በ1997 ዓ.ም. በሩን ገርበብ አድርጎ ዴሞክራያዊ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ድምጹን ቢነፍገውም ቅሉ ውጤቱን አልቀበልም በማለት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ወደ እስር ቤት ወርውሮ ስልጣኑን ሙሉበሙሉ ተቆጣጥሮት ነበር፡፡ በአጭሩ በወያኔ ይመራ የነበረው ኢህአዲግ ያለ ነጻ ምርጫ ኢትዮጵያን ለሶስት አስርተ አመታት ቀጥቅጦ ገዝቷል፡፡

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2015 በተካሄደው የምርጫ ውድድር ስርዓቱ 100 ፐርሰንት የፓርላማ መቀመጫ መውሰዱ ይታወሳል፡፡ ይህንኑ የምርጫ ውድድር በተመለከተ አንድ <<Electoral Integrity Project, a panel of scholars and experts on election integrity ›› የተሰኘ የአዋቂዎች ስብስብ ይህን የፌዝ ምርጫ በተመለከተ የሚከተለውን ትዝብቱን በጥናት ወረቀቱ ላይ አስፍሮ ነበር፡፡

  • የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ወከባና እንግልት ገጥሟቸው ነበር
  • የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት አልነበረም
  • የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽዋል
  • በእነኚህ ምሁራን የጥናት ግምገማ እና መመዘኛ መሰረት የተካሄደው ምርጫ ሀገራት ካካሄዱት የምርጫ ውድድሮች ሁሉ የከፋ ነው፡፡

በነገራችን ላይ ይህንኑ የፌዝ ምርጫ የተባበረችው አሜሪካ ፕሬዜዴንት የነበሩት ባራክ ኦባማ ማወደሳቸውን የምናስታውስ ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የወያኔ የውርብ ወዳጅ የነበሩት አንዲት የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ለባራክ ኦባማ መልእክት በማስተላለፋቸው እንደነበር ከፖለቲካ አዋቂዎች ጽሁፍ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በግዜው የሠብዓዊ መብት ተመልካች ድርጅት ባወጣው ምርጫው ጭቆና የታየበትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመበት  ሲል ነበር የኮነነው፡፡

  1. ከላይ ከጠቀሱት በተቃራኒው እንደ ጎርጎሮሲያኑኑ አቆጣጠር ሰኔ 2021 በኢትዮጵያ ተካሂዲ የነበረው የምርጫ ውድድር በብዙ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የተካሄደ ነበር፡፡ ለአብነት ያህል የሚከተሉትን መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡

– የኮቪዲ በሽታ ወረርሽኝ

– በትግራይ ክልል ውስጥ የነበረው ጦርነት

– የሱዳን ጠብ ያለሽ በዳቦ እና የኢትዮጵያን ድንበር መያዝ

– በታላቁ የአባይ ግድብ ዙሪያ የሚደረገው የሶስትዮሹ ድርድር ( በኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ መሃከል የሚደረገው ድርድር) ውጥረት የነገሰበት መሆኑ

– በተባበረችው አሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት ይደረግ የነበረው ጫና መጨመሩ ወዘተ ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡

ከላይ በተጠቀሱት  እና ሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ይህ የምርጫ ውድድር ሙሉነሙሉ የተሳካ ነበር ብሎ ምስክርነት የሚሰጥ ምክንያታዊ ሰውና ድርጅት ያለ አይመስለኝም፡፡ በግዜው፡-

  • የሎጂስክ፣ የጸጥታ ችግር ( በብዙ አካባቢዎች ነበር)፣ኮቪዲ ወረርሽኝ እና ሌሎች ችግሮች ታይተው ነበር፡፡ እንደ ባለፉት አመታት ሁሉ በፖለቲካ ፓርቲ አባላት ላይ የከፋ ወከባ ባይከሰትም፣ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ቢጠናቀቅም አልፎ አልፎ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን፣የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እጥረት፣ከምርጫ ጋር የተያያዙ ህገ ወጥ ድርጊቶች መፈጸማቸውን የሚያሳዩ የዜና ዘገባዎችን መስማቴን አስታውሳለሁ፡፡

የህግ ባለሙያ  በሆኑት ወ/ሮ ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው  የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ወደ 53 የሚጠጉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መዝግቦ ህጋዊ እውቅና እንደሰጠ፣ ከእነኚህ ውስጥ 46ቱ እጩ ተመራጮችን ማቅረባቸውን፣ 17ቱ በብሔራዊ ደረጃ፣29ኙ በክልል ደረጃ የምርጫ እጩ ተወዳዳሪዎችን አቅርበው ነበር፡፡

በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ውስጥ የተካሄደው የምርጫ ውድድር የተሞላ አልነበረም፡፡ ይህ በመሬት ላይ የታየ እውነት ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የኦሮሞ ብሐየራዊ ኮንግረነስ ፓርቲ እና የወያኔ አጋር የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በምርጫው ላይ አንካፈልም በማለታቸው እንደሆነ ከመገናኛ ብዙሃን ተሰምቷል፡፡ በእኔ በኩል ሁለቱም ፓርቲዎች በምርጫ ውድድር ሲካፈሉ ማየት ምኞቴ ነው፡፡ ሆኖም በምርጫው አለመካፈል ሰብዓዊ መብታቸው ቢሆንም እርምጃቸው ግን ለኢትዮጵያ የሚበጃት አይመስለኝም፡፡ 

በመጨረሻም ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራቲክ ጎዳና እንዳትራመድ የወያኔ- ኢህአዲግ አገዛዝ የዘጋውን ጎዳና ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር መክፈት አለባቸው የሚለውን ሃሳብ ሳቀርብ በአክብሮት ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ የውጭ ሀይሎችን ፍላጎት ለማስፈጸም ሲል ወደ  ሽብር ተግባር የገባውን የወያኔ ቡድን ወረራ ለመመከት ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአንድነት መሰለፍ አለባቸው ባይ ነኝ፡፡ በተልእኮ በሚካሄዱ ግጭቶች እና ጦርነት ምክንያት የሰብዓዊ መብቶች እንዳይገፈፉ መከላከልም የመንግስት ተግባራት ብቻ ሳይሆነ የሁላችንም የዜጎች ሀላፊነት መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

 ከላይ ከተጠቀሰው እውነታ ተጻራሪ በሆነ መልኩ የፕሬዜዴንት ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ጣልቃ ለመግባትና ግፊት ለማድረግ ጥረቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ ይህ ግን ተቀባይነት የለውም፡፡

 ከጥቂት የምእራባውያን የዜና አውታሮች እና የህትመት ውጤቶች በቀር ጦርነቱን በተመለከተ የተሳሳቱ የዜና ዘገባዎችን ማቅረብ የተለመደ ተግባራቸው ሲሆን፣ የምእራቡ አለም የወያኔ አሸባሪ ቡድን  የፈጸመውን የሙስና እና ጭካኔ ተግባር ለማውገዝ አልቻሉም፡፡ ወይም ከሞራል አኳያ ወድቋል፡፡በመጨረሻም  ከኢትዮጵያ አኳያ ያላቸውን ፖሊሲ የፕሬዜዴነት ባይደን አስተዳደር የአፍሪካ ፖሊሲ ቲም( ቡድን) እና የምእራቡ አለም ፍጹም ቸልተኝነትና አደገኛነት የሚስተዋልበት ስለሆነ ዳግም እንዲመረምሩት፣እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከመቼውም ግዜ በላይ አንድነታችንን ማጠንከር እንዳለብን፣ ለአንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎች ደግሞ በእጅ አዙር ሊያጣሉን ሊያጋጩን በመፈለግ ውስብስብ ሴራ ከሚጎነጉኑ ታሪካዊ ጠላቶቻችን በመራቅ ወይም የእነርሱ መሳሪያ ላለመሆን ሁለት ሶስት ግዜ ቁጭ ብለን እንድናስብ በማስታወስ እሰናበታለሁ፡፡

‹‹ ኢትዮጵያ እደዊሃ ሃበ እግዜአብሔር ››

Filed in: Amharic