>

አቢይ አህመድን ያመነ እና ጉም የዘገነ ... (ሸንቁጥ አየለ)

አቢይ አህመድን ያመነ እና ጉም የዘገነ …

ሸንቁጥ አየለ

መቼም ብአዴን አማራ ሲያልቅ ቆሞ አማራ መቃብር ላይ መጨፈር ፡ ትናንት ለወያኔ ዛሬ ለኦህዴድ ስልጣን መጠናከር እንቅጥቅጦሽ መምታት ልማዱ ነዉ።ስለ ህዝቡ ረሃብና ስደት ሞት ግን ግድም አይሰጠዉም።
ኦህዴድ ቢሆን ኖሮ እንኳን የራሴ የሚለዉን ጎሳዉን በረሃብ ሊያስጨርስ ይቅርና መሃል አዲስ አበባ ሚሊዮን ቤት ሰርቶ ስራ አዘጋጅቶ ያሰፍራቸዉ ነበር። ብአዴን ያማራ ህዝብ ደም አይከረፋዉም። ቢያንስ በጦርነት ከቀያቸዉ የተፈናቀሉት በርሃብ ሲያልቁ በቆሎ መግቦ ህይወት ማትረፍ አልቻለም።
 ከብአዴን ጎን ተሰልፎ የሚራወጠዉ አክቲቪስትና ተቃዋሚም ጠዋት ለአቢይ ሲዘፍን ይቆይና ከሰዓት ደግሞ አቢይ ከዳን ብሎ ያለቅሳል። በማግስቱ ደግሞ የአቢይ የጦር ኣማካሪ ይመስል ሚዲያ ላይ ወጥቶ ይተረተራል።
 የአማራ ህዝብ ግን በወያኔ ዘመንም ሆነ በከሃዱያኑ ኦህዴዳዉያን ዘመን በበድኑ ብአዴን እጅና እግሩ ታስሮ መቀለጃ ሆኗል።ወያኔን  በቀናት ዉስጥ መደምሰስ የሚችል ጉልበት እና ወኔ ያለዉ ህዝብ አንዴ ዱላ ይዘህ ተዋጋ ሌላ ጊዜ ጦርነቱ ወደ አማራ ክልል መሃል አካባቢዎች መሳብ በሚል ነፈዝ ስትራቴ ሚሊዮኖች ይፈናቀላሉ ሚሊዮኖች ያልቃሉ።
 ሚሊዮኖች ሲያልቁ አቢይን ለማስደሰት የአማራ አክቲቪስትና ፖለቲከኝ መሳሪያ ተሸክሞ ፎቶ ይፖስታል። አጠቃላይ የጦርነቱን ሂደት የሚቆጣጠረዉ ግን አቢይ እና ኦህዴድ ነዉ። ብኣዴን ለመለመላቸዉ እንኳን ጦር ማቅረብ ተስኖት ዱላ ይዘህ ወደ ጦር ግንባር ግባ ይላል።
ስለዘፈንክ ወይም እጭፈራ መሃል ገብተህ ስላስካካህ የሀይሉን ሚስጢር ተቆጣጥረህዋል ማለት አይደለም። በተለይ ተቃዋሚ የአማራ ፖለቲከኞች የሀይሉ ሚዛን ላይ ምንድን ነዉ ሚናችሁ?
 የሀይሉን ሚዛን የምትቆጣጠሩት ከሆነ ህዝብ ተከዳ እያላችሁ ከምታለቅሱ ለምን የአማራ አካባቢ እና መከላከያ ከተከላካይነት ወደ ደምሳሽነት እንዲሻገር የአጥቂነት ስልት እንዲኖር አታደርጉም?
 እዉነታዉ ምንም አቅምና  የዉሳኔ ሰጭነት ሚና እንዲሁም የሀይል ሚዛኑን የመቆጣጠር ስልት ስላልሰራችሁ ነዉ። አቢይን አምኖ ዝላይ ከብአዴን ተጠግቶ ስትራቴጂ ነደፋ ቆም ብላችሁ ልታስቡበት ይገባል።
ጠዋት እየፎከራችሁ አቢይና ብአዴንን በማወደስ ህዝብ እያደናገራችሁ ከሰዓት ደግሞ አቢይ ህዝባችንን ከዳዉ እያላችሁ እንዴት ትዘልቁታላችሁ?
በዚህ ሁሉ መሃል ግን የዋሁ ህዝብ እጅግ መራራ ዋጋ እየከፈለ ነዉ። ኢትዮጵያን የምታህል ሀገር በርሃብ ለሚረግፍ ህዝብ በቆሎ ማቅረብ አይከብዳትም ነበር። ችግሩ ያለዉ አማራዉ የሚቆጣለት ወኪል ስለሌለዉ ነዉ።
 በወዲያኛዉ ጽንፍ የትግራይን ህዝብ በገፍ አንቆ  በጦርነትም በከፋ ርሃብም እያስጨረሰ ያለዉ ወያኔ ቢያንስ ስለ ትግራይ ህዝብ እርሃብ ጮክ ብሎ ለአለም ማህበረሰብ ያስረዳል ይሰብካል። የትግራይ ህዝብ ሞትና መከራ ግን ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የኦህዴድ ከሃዲያን አማራ እና ትግሬን ጦርነት አጋጥመን እርስ በርሱ አጫረስነዉ እያሉ ያናፋሉ። የዋሁና ምስኪኑ ኢትዮጵያዊ በማያዉቀዉ እና በማይጠቀምበት ጦርነት ይጠበሳል።ህዉሃት እላዩ ላይ የሰፈረዉ ሰይጣን አሁንም አማራን አጥፋ እያለ ያስጓራዋል እና ቀን ከሌት የሚያነበንበዉ ያንኑ አምሳ አመታት ያነበነበዉን ጸረ ኢትዮጵያ ጸረ አማራ እና ጸረ ተዋህዶ ፍልስፍናዉን ነዉ።
በአጠቃላይ ግን የካንሰር አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ላይ አምጥተዉ የተከሉት ያንሰራፉት ህዉሃት ኦህዴድ ብአዴን ለአማራዉም ለትግሬዉም በአጠቃላይ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መቅሰፍት ናቸዉና ህዝባችንን እየጨረሱት እና እያስጨረሱት ነዉ።የጎሳ ፖለቲካ የሰበአዊነት ጸርም ጠንቅም ነዉ።
Filed in: Amharic