>
5:33 pm - Wednesday December 5, 8170

በአዲስ አመት አልመኝም፤ ተስፋ አደርጋለሁ...!!!  (በድሉ ዋቅጅራ)

በአዲስ አመት አልመኝም፤ ተስፋ አደርጋለሁ…!!!

 (በድሉ ዋቅጅራ)

ስኬትን ዝናብ ሳደርገው ምኞት ነጭ፣ ተስፋ ጥቁር ደመና ይመስሉኛል፡፡ ነጭ ደመና ከመዝነቡ ቀድሞ መጥቆር፣ ምኞትም ስኬት ለመሆን ቀድሞ ተስፋ መሆን አለበት፡፡ ከምኞት ይልቅ የተስፋ ደመና ግብራችንን መሰረት ያደርጋል፡፡ አልቦ-ግብር ምኞት ሊኖር ይችላል፡፡ ቀቢጸ ተስፋ ካልሆነ በቀር ተስፋ ያለ አንዳች ግብር አይወጠንም፡፡ ጥሩ ምር የማግኘት ተስፋ ያለው ገበሬ ዘርቷል፡፡ ብዙ ለማትረፍ ተስፋ ያደረገ ሸቃጭ ገበያ ወጥቷል፡፡ ጠላቱን ደምስሶ፣ ወገኑንና ሀገሩን መታደግ ተስፋ የሚያደርግ ወታደር፣ ምሽግ ውስጥ ያደፈጠ፣ ጣቱን ቃታ ላይ ያስቀመጠ ነው፤ ቢያንስ ማሰልጠኛ ገብቷል፡፡ . . .  ለዚህ ነው ከአዲስ አመት ምኞት የአዲስ አመት ተስፋ መምረጤ፡፡
እና ተስፋ አደርጋለሁ!
2013 አ.ም. ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የተፈተንንበት አመት ነበር፡፡ ትህነግ የከፈተውን ጦርነት ጦርነት ማለት አይቻልም፡፡ ከአጀማመሩ አንስቶ በታጠቁ ሀይሎች መካከል የተከናወነ አልነበረም፡፡ የገዛ ሀገርን በተኛበት በመጨፍጨፍ የተጀመረ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ በየከተማውና መንደሩ እልቂት ተፈጽሟል፡፡ ጦርነት በሌለበት ቃጠሎ፣ ዝርፊያ፣ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መውደም፣ የሴቶች መደፈር፣ ከሁሉም በላይ እስካሁን የትግራይ ህጻናት ለጦርነት እየተማገዱ ነው፡፡ የአማራ ገበሬ ሳር የሚግጡ ከብቶቹን በጥይት አጥቷል፡፡ . . .  ከጦርነቱም ውጭ ዜጎች በብሄራቸው እየተመረጡ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፡፡ በአጠቃላይ ምናልባትም በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከደረሱ ጭካኔዎች ቢወዳደር የከፋ ሊሆን የሚችል ጥቃት ወገን በወገኑ ላይ ፈጽሟል፡፡
. . . . .  የእኔ የአዲስ ተስፋ፣ ይህ ጦርነት በድል ተቋጭቶ፣ የአማራና የትግራይ ገበሬ ጠመንጃውን ጥሎ እርፍ የሚጨብጥበት፣ የትግራይ ህጻናት ትምህርት ቤት የሚውሉበት፣ በሁለቱ ህዝቦች፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን መካከል ያለው ኢትዮጵያዊ መከባበርና ወዳጅነት የተጫነውን የብሄር ፖለቲካ ብስባሽ እያራገፈ ማንሰራራት የሚጀምርበት እንደሚሆን ነው፡፡
2013 የፈተና አመት ቢሆንም፣ የዜጎችን ልብ የሚያሞቁ ተግባራት ተከናውነውበታል፡፡ ከእነዚህ መካከል የህዳሴውን የሁለተኛ ዙር ሙሌት ማከናወናችንና ሊውጠን ደርሶ የነበረውን የውጭ ሀይሎች ተጽእኖ በመቋቋም የተደረገብንን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ መቀልበስ መቻላችን ነው፡፡  . . .  ከዚህ አንጽር መጪው አመት የህዳሴውን የሁለት ተርባይን ፍሬ የምንመገብበት፣ የግድቡን ስራ ያለ እረፍት የምናከናውንበት እንደሚሆን ተስፋ አለኝ፡፡ ከዚህም በላይ መጪው አመት፣ የውጭ ሀብታምና ባለጠመንጃ ሀገሮች የዘረጉብንን የሴጣን እጆች አሰብስበን፣ ሉአላዊነታችን ለድርድር የማይቀር መሆኑን እንዲያስታውሱ የምናስገድድበት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ምንም እንኳን ከችግሮች ባይጻዳም፣ በ2013 ኢትዮጵያ በዜጎች፣ በተወዳዳሪ ፓርቲዎች፣ ከውጭ ውድቀታችንን በሚመኙ ወገኖች ሳይቀር የተሸለ የተባለ ምርጫ አከናውናለች፡፡ በዚህም መሰረት በአዲሱ አመት የመጀመሪያ ወር አሸናፊው የብልጽግና ፓርቲ መንግስት ይመሰርታል፡፡ . . .  አዲሱ መንግስት በምርጫ የታየው የተሻለነት የሚንጸባረቅበት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የካቢኔ አባላት የብሄር ውክልናንና የጾታ ተዋጽኦን ለመጠበቅ ሲባል ብቻ በውክልና የማይሾሙ፣ ለግብራዊ እድገት እንጂ ለገጽታ ግንባታ ያልታለሙ፣ ወገናቸውንና ሀገራቸውን የሚያስቀድሙ፣ የሙያ ብቃትና የስራ ልምድ ያካበቱ እንደሚሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡  . .  . . በዚህም፣ ባለስልጣናት ተግተው የሚያገለግሉበት እንጂ ዘርፈው የማይከብሩበት፣ ዜጎች የተሻለ አገልግሎት የሚያገኙበት አመት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ! . . . . ከሁሉም በላይ እነዚህና ሌሎች የአዲስ አመት ተስፋዎቼ እውን ይሆኑ ዘንድ፣ አዲሱን መንግስት የሚመሰርተው የብልጽግና ፓርቲ ሀሳቤን ተግባራዊ ያደርገዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ!
ለመላው ኢትዮጵያውያን መልካል አዲስ አመት!
Filed in: Amharic