>

የእስክንድር ጉዳይ....!!! (አበበ ገላው)

የእስክንድር ጉዳይ….!!!

አበበ ገላው

 

*…. ከእስክንድር ጋር የሃሳብ ልዩነት ቢኖረኝም በእርሱም ላይ ይሁን በትግል አጋሮቹ ላይ የቀረበው ክስ አሳፋሪም አስተዛዛቢም እንደሆነ ደጋግሜ ገልጫለሁ።
የዘመነ ህወሃት ማክተምን ተከትሎ እስክንድር  ከእስር ተፈቶ ቤተሰቡንና ደጋፊዎቹን ለማየት ወደ አሜሪካ በመምጣቱ ጊዜ ወስደን በተለያዩ ጉዳዮች በሰፊው ለመወያየት አጋጣሚ አግኝተን ነበር። ምንም እንኳ እስክንድር ካመነበት ዘነፍ እንደማይል ድሮም ጠንቅቄ ባውቅም የወዳጅ ምክር ነበረኝ።
እስር ቤት በሰው ላይ የሚያሳድረው አካላዊና አዕምሯዊ ጉዳት ቀላል ባለመሆኑ ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ ከቤተቡ ጋር በቂ እረፍት እንዲያደርግ የተለያዩ እድሎችንና አማራጮችን ላቀርብለት ሞከርኩ። በእርግጥ አልተቀበለውም። ሌላው ከጋዜጠኝነቱና የመብት ተሟጋችነት ባሻገር የፖለቲካ ፓርቲ የትግል አማራጭ ካለው የሃገራችን ያልሰከነ ተጨባጭ አውነታ አንጻር ብዙም የሚያዋጣ ስልት ነው የሚል እምነት እንደሌለኝ ገለጽኩለት። እርሱም በወቅቱ የፖለቲካ ፓርቲ መስርቶ አመራር የመሆን እቅድ ስላልነበረው እዚህ ላይ የሃሳብ ልዩነት አልነበረንም። በአለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖና ተሰሚነት እንደነበረው ጋዜጠኛ ሌላኛው አማራጭ የነበረውን ችግርና ተግዳሮት ጠንቅቆ ይረዳ ነበር።
ይሁንና በስተመጨረሻ እስክንድር ያመነውን አደረገ።  ባላቀደው መንገድ የባልዳራስ መስራችና መሪ ሆነ። በድጋሚ ለዘጠነኛ ጊዜ የህሊና እስረኛ ሆነ።  ከእስክንድር ጋር የሃሳብ ልዩነት ቢኖረኝም በእርሱም ላይ ይሁን በትግል አጋሮቹ ላይ የቀረበው ክስ አሳፋሪም አስተዛዛቢም እንደሆነ ደጋግሜ ገልጫለሁ።
በእርግጥ እስክንድር የእኔንም ይሁን የሌሎች ወዳጆቹን ምክር ሰምቶ እረፍት ወስዶና በአግባቡ አገግሞ የተዋጣለት ጋዜጠኛ እንደመሆኑ ከሙያው ሳይርቅና የአለም አቀፉን ህብረተሰብ ድጋፍ እንደያዘ ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ የበለጠ ውጤታማ ይሆን ነበር የሚል እምነት አለኝ።
ሌላው የባልደራስ አባላትና ደጋፊዎቻ ከሌሎች በበለጠ እስክንድርን ጨምሮ መሪያዎቻቸው እንዳይረሱና እንዲፈቱ የመታገል ዋናው ሃላፊት የእነርሱ ነው። የአላማ አንድነት የፖለቲካ ፓርቲ መሰረት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። መሪዎቹ የታሰሩበት የፖለቲካ ፓርቲ ሙሉ ቁመና ሊኖረው አይችልም። ምንም ቢዘገይ አሁንም ከማንም በላይ እውነት ነጻ ያወጣዋል!
Filed in: Amharic