>
5:31 pm - Friday November 13, 2809

ይድረስ በኦሮሙማ የሽብርተኝነት ወንጀል ለተከሰስከው 'የቀበሮ ጉድጓድ መልዕክተኛው መሪዬ!" (ኤርምያስ ለገሰ)

ይድረስ በኦሮሙማ የሽብርተኝነት ወንጀል ለተከሰስከው ‘የቀበሮ ጉድጓድ መልዕክተኛው መሪዬ!”
                      ከኤርምያስ ለገሰ
                     ጷግሜ 5 ቀን 2012 ዓ.ም.
                      የአዲስ አመት ዋዜማ

   


           የደብዳቤው መታሰቢያ: ለአሹ ቀበና!

መሪዬ እስክንድር፣
እንኳን ለኢትዮጵያ አዲሱ አመት በአምላክ ፍቃድ አደረሰህ። በሰላም አደረሰህ ማለት የተሳነኝ በሁለት ምክንያቶች ነው። ዛሬ በአንተና የትግል አጋሮችህ ላይ የቀረበውን የሽብርተኝነት ክስ መጪው አመት ጨለማው የማይገፍበት ሆኖ ስለተሰማኝ ነው። እንዲሁም ወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ተስፋ የሚሰጥ ሳይሆን ከድጡ ወደ ማጡ የምንጓዝበት ሆኖ ስላገኘሁት ነው። እስቲ ሁለቱንም ምክንያቶችን ዘርዘር አድርጌ ላቅርብ።
ወንድሜ እስክንድር፣
በአንተና በጓደኞችህ ላይ የቀረበውን የሽብርተኝነት ክስ የተመለከቱ በርካታ ኢትዮጲያውያን በክስ አቅራቢዎች ላይ ተሳልቀውባቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ እኔ ከህዝቡ ጠብቄ የነበረው ንዴትና ቁጣ ነበር። ለካስ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም አዲስአበቤ የዚህን መንግስትና መሪዎችን ባህሪ ጠንቅቆ መረዳት ከቻለ ቆይቷል። የኢትዮጵያ ህዝብ ቀድሞ ከሄደ ቆይቷል። በተለይ አዲስአበቤ እንቅልፉን ጨርሶ ወፍ በተንጫጫ ቁጥር “ደሞ ዛሬ ቲአትረኛው ንጉስ ምን እስክሪፕት ጽፎ ሊተውን ይሆን?” ብሎ መነጋገር ከጀመረ ውሎ አድሯል። የቲአትሩን አጋፋሪዎችም ጠንቅቆ አውቋቸዋል።
በእኔ በኩል ግን ክሱን ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዚህ ደረጃ ቁልቁል ይወርዳሉ ብዬ ማሰብ በፍጹም አልቻልኩም። እስክንድር ነጋ ” የእከሌ ገበሬ እንጂ የእከሌ ቄስ የለም”፤ ” እከሌ ወደመጣበት ማዳጋስካር እንመልሰዋለን” ፤ የእከሌና የእንቶኔ ብሔር ንብረት መውደም አለበት” የሚል መፈክር ጽፎ ህዝብ ከህዝብ ሊያጋጭ ነበር በሚል ክስ እንዴት አልገረም። መቼም “እከሌና እንቶኔ” የሚለውን አባባል የተጠቀምኩት እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግስታቸው ብሔረሰቦቹን መጠራት በማይፈልጉበት በመጥራት ወርጄ ላለመሳደብ ነው። ከእነ ተረቱስ ቢሆን ” ከሰደበኝ መልሶ የነገረኝ” ይባል የለ።
እዚህ ላይ ሌላም እጅግ የገረመኝን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና መንግስታቸው ሁለት ክሶች ልጨምር። አንደኛው እስክንድር ነጋ አመጽ ሲያስተባብር የነበረው በፓሊስ ሬዲዬ መገናኛ ነበር ይላል። እጅግ በጣም ያስቃል። ያስገርማል።
ሁለተኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአቃቤ ህግ ካባ ውስጥ ተሸሽገው ያቀረቡት ክስ ነው። ይህ በአንተና ጓዶችህ ላይ የቀረበው  የሽብርተኝነት ክስ እንዲህ ይላል፣
” ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት እና የፓለቲካ አመራሮችን በግድያ የሚያስወግድ ገዳይ የሽብር ቡድን ከአዲስ አበባና አማራ ክልል መልምሎ በአማራ ክልል ሞጣ ከተማ ውስጥ በማሰልጠንና ተልዕኮ በመስጠት ፤ ባልደራስ ስልጣን ሲይዝ ስልጣን እንደሚሰጣቸው ቃል በመግባት ቤተ-እምነቶችን በማቃጠል እና የመንግስት አመራሮችን በመግደል አዲስ አበባ ውስጥ ብጥብጥ በመፍጠር የፓለቲካ ርዕዮተ አለማቸውን ለማራመድ በመስማማትና በማደም ሕዝብን በማሸበር እና ስልጣን በኃይል ለመያዝ አስቦ በመንቀሳቀስ” ይላል።
ወንድሜ እስክንድር ፣
መቼም! የመንግስት ስልጣን ላይ ተቀምጦ ማን የሽብር ቡድን ሲያደራጅ እንደነበር ብዙ ርቀት ሳይኬድ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት ላይ በቀላሉ የሚገኝ ነው።
 መቼም! ኦነግን የመሰለ ፀረ-ኢትዮጲያዊ የሽብር ቡድን ማን መረጃ እያሾለከ ሲሰጥ እንደነበር አሁንም ሩቅ መሔድ ሳይገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የቀደምት ንግግሮች ፈተሽተሽ ማድረግ ነው።
መቼም! አማራ ክልል ሞጣ ከተማ ለምን ተመረጠች የሚለውን ለአስማጭና አደናጋሪ የፓለቲካ ቁማርተኞች ትተነው የአማራ ክልል ፓሊስ አዛዥ ምን ነው? ከግንቦት 7 የህቡዕ አመራር ተገልብጦ የክልሉ ፓሊስ አዛዥ ሊሆን ቻለ ብለን የጊዜ ይገልጠዋል ጥያቄ አንስተን እንለፍ።
         ***
ወንድሜ እስክንድር
ከላይ እንደጠቀስኩት ወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱም በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀስ ሆኗል። ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበት የህልውና አደጋ የማያሳስበው ዜጋ ያለ አይመስልም።በብዙዎች እንደሚገለፀው የኢትዮጵያ የፓለቲካ ሁኔታ ላለፉት ሁለት አመታት አንደ አርታሌ ሙቀት ባለው እሳት ላይ እንደተጣደ ባልጩት መንተክተኩን ቀጥሏል።
የአገሪቱን አንድ ትውልድና ኢኮኖሚ አንክቶ ወደበላው የጦርነት ሁኔታና እርስ በራስ ፍጅት ዘመን ልንመለስ ይሆን? የሚል ጥያቄ በመነሳት ላይ ነው። በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያለውን የፀረ-ኢትዮጲያ የአክራሪዎች ቅስቀሳ ስንመረምር በተለይም “ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ!” የሚለውን ስንሰማ ተስፉችን ይጨልማል። ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ወቅታዊ የአገሪቱ ጥያቄ ኢትዮጵያ እንደ አንድ አገርና ሕዝብ የመኖር ያለመኖር ጥያቄ ሆኗል።
ዛሬ በኢትዮጵያ የሚሰማው ሮሮና ጩኸት በአለም አቀፍ የሚዲያዎችና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አማካይነት የሚቀርበውም ዘገባ የዘርና ሀይማኖት ተኮር ጄኖሳይድ መፈፀሙን ሆኗል። በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲ የሚመራው የኦሮሙማ አስተዳደር የደም መሬት ከሆነ ውሎ አድሯል። የኦሮሞ ፖለቲከኞች የዘር ማጥፋት ዝግጅት እና አፈጻጸም የአለማቀፉን ወንጀለኛ ፍርድቤት መስፈርት አሟልቶ መፈጸሙን መግባባት ላይ እየተደረሰ ነው። ከወደ ኒዎርክ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመረጃ ምንጮቻችን እንዳረጋገጥነው ድርጅቱ በኦሮሙማ የተፈፀመውን ጄኖሳይድ ጉዳዩን ክትትል ከሚያደርጉ አካላት ጋር በአካል የመረጃ ልውውጥ ማድረግ ጀምሯል። ይሄ የአንተ ልፋት በከንቱ ሳይቀር ፍሬ እያፈራ በመሆኑ በዚህ አጋጣሚ እንኳን ደስ አለህ ማለት እፈልጋለሁ።
            ***
ወንድሜ እስክንድር፣
አሁን ያለንበት ወቅትና ዘመን ወደ አምባገነናዊ ሰባተኛ ንጉስነት እየወሰደን መሆኑ ግላጭ እየወጣ መጥቷል። በአገራችን ህጋዊም ሆነ ባህላዊ አሰራር ደግሞ “ንጉስ አይከሰስ፤ ሰማይ አይታረስ” ይባላል። ንጉስ በፈለገና ባሰኘው ጊዜ የፈለገውን ያስራል፣ የፈለገውን ያስደበድባል፣ የፈለገውን ይፈታል። የፈለገውን በሽብርተኛነት ይከሳል።
የንጉሱ ዋነኛ አማካሪዎች ደግሞ በአገራቸው ደስተኛ ማህበረሰብ መፍጠር የቻሉት፣ ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስት ያላቸው፣ በየጊዜው በሚካሄድ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጡት ወዲ አፈወርቂ ናቸው። የኤርትራው የህይወት ዘመን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ! በዚህም ምክንያት ሰሞኑን በሰባተኛው ንጉስ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፕሬዝዳንት የሆነውን እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎች የፓርቲው አመራርና አባላትን አስደንጋጭ በሆነ ሽብርተኝነት መክሰሱ ተጠባቂ ነበር።
                      ***
ወንድሜ እስክንድር
ሰሞኑን በተለይም የአዲሱ አመት ዋዜማ ላይ ሆኜ አእምሮዬን የስንግ ይዞ ፋታ ከነሳኝ ውስጥ “የቀበሮ ጉድጓድ መልዕክተኛው ለምን በግፍ ታሰረ?” የሚለው ሆኗል። “ለምን ለሰማይ ለምድሩ የከበደ የሽብርተኝነት ክስ ዳግም ሊቀርብበት ቻለ?” የሚለው ጥያቄ ሆኗል።
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ይህን ደብዳቤዬን ለሚያነቡና ለሚያዳምጡ ወገኖች ይሄ ” የቀበሮ ጉድጓድ መልዕክተኛ” የሚለው አገላለጥ ትንሽ ግር ሊላቸው ስለሚችል ታሪካዊ አመጣጡን ትንሽ ላብራራው።
እንዲህ ነበር የሆነው፣ 
አንተም እንደምታስታውሰው ቀኑ የህዳር ወር የሁለተኛ ሳምንት ቅዳሜ 2019 ዓ.ም. የዋለበት ነበር። በእለቱ አንድ ከኢትዮጵያ የሚመጣ ጥቁር እንግዳ ለመቀበል ዝግጅት ያደረግንበት ነበር። እንግዳውም አንተ መሪያችን እስክንድር ነጋ ነበርክ። ታዲያ! አንተን የምንቀበለው ቨርጂኒያ በሚገኘው የዳላስ ኤርፓርት በመሆኑና ከመኖሪያ ቤቴ ራቅ ስለሚል በጠዋት መነሳት ነበረብኝ። ወደ ኤርፓርቱ ተሰባስቦ ለመሄድ ደግሞ ከአዲስአበቤው አሹ ቀበና ጋር ቀጥሮ ይዣለሁ። አሹ ጀግና ነበር። አሹ ትላንት በሚደግፈው ፓርቲ በመታለሉ ምክንያት በእልህና ቁጭት የአዲስ አበባን ንቅናቄ የሚደግፍ ነበር።
እናም ከአሹ ቀበናና የፈረንሳይ ልጆች እንደ አምባሳደራቸው የሚቆጥሩት ቦክሰኛው ወንድማችን ጋር ሆነን ዳላስ ኤርፓርት ሔድን። ከሰአታት በኃላ ሰውነቱ ገርጠት ያለና በቁመቱ ዘንግ ያለ ሰው ከአውሮፕላን ወርዶ ወደተሰበሰብነው ሰው መጣ። ሁሉም ተነስቶ ሞቅ ባለ ጭብጨባና በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ተቀበለው። እንግዳው ከሁሉም ጋር ሰላምታ ከተለዋወጠ በኃላ እንዲህ የሚል መልዕክት አስተላለፈ።
“ወገኖቼ! በሰማይ ጋሪ ውቅያኖስ ተሻግሬ በመምጣት በድጋሚ ስላገኘኃችው በቅድሚያ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ ። በማስከተል ከቀበሮ ጉድጓድ ይዤ የመጣሁት መልዕክት የሚያስጨንቅ እንጂ ብስራት አይደለም። በዚህም አዝናለሁ። ይቅርታም እጠይቃለሁ። አገራችን ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ናት! ቶሎ ልንደርስላት ይገባል” የሚል ነበር። ይህ የቀበሮ ጉድጓድ መልዕክተኛ መሪያችን እስክንድር ነጋ ነበር።
አሹ ቀበና ዛሬ በህይወት የለም። የዘመኑ ቀሳፊ ወረርሽኝ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ከነጠቀን ብርቅዬ ኢትዮጵያዊ አሹ የመጀመሪያው ነበር። መሪዬ እስክንድር! ለአዲስ አበባና አዲስአበቤ ተቆርቋሪ የነበረው አሹ ቀበና ያለጊዜው ከመሬት በታች በመዋሉ የተሰማህን ጥልቅ ሀዘን አጫውተኸኝ እንደ ነበርን አልዘነጋውም። አሹ አዲስ አበባ መቼም ቢሆን አትረሳህም። አዲስአበቤም በየጊዜው ይዘክርሃል። ለጊዜው ይሄ ደብዳቤ ማስታወሻህ ይሁን።
     ( ክፍል ሁለት ይቀጥላል…)

ልክ የዛሬ አመት ይህን ብለን ነበር
Filed in: Amharic