>

‹‹መስከረም ለኢትዮጵያውያን ልዩ የተስፋ ምልክት የሆነው በምክንያት ነው›› ( መጋቤ ሀዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ የስነፈለክ ተመራማሪ)

‹‹መስከረም ለኢትዮጵያውያን ልዩ የተስፋ ምልክት የሆነው በምክንያት ነው›› –
መጋቤ ሀዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ የስነፈለክ ተመራማሪ


(ኢ ፕ ድ )

አዲስ አበባ፡- መስከረም ለኢትዮጵያውያን ልዩ የተስፋ ምልክት ተደርጎ የሚወሰደው በምክንያት እንደሆነ የጥንታውያት መዛግብትና ስነ ፈለክ ተመራማሪ፤የትርጓሜ መጻህፍት መምህር ዶክተር ሮዳስ ታደሰ አስታወቁ።

መጋቤ ሀዲስ ዶክተር ሮዳስ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ መስከረም ለኢትዮጵያውያን ልዩ የተስፋ ምልክት ነው። ይህ ለመሆኑም አበው በብሂላቸው ‹‹ በሰኔ ዝናቡን ወደ እኔ፤ በሐምሌ ልኑር እንዳመሌ›› በማለት በሰኔ ወር የገባው የክረምት ወቅት እየበረታ ሰማዩ በመብረቅ ብልጭታና በነጐድጓድ ድምፅ የሚታጀብበት፤ ከላይ የዝናብ ዶፍ ከሥር ጐርፍ የሚጨምርበት፤ አልፎ ተርፎም በረዶ የሚዘንብበት የጨለማ፣ የጭጋግ፣ የደመና፣ የጉም ጊዜ ያስታውሳሉ። መስከረም ሲሆን ደግሞ ‹‹በመስከረም ስፍራው ሁሉ ለምለም›› ብለው ይዘጉታል።

መስከረም አስፈሪው የሰኔ፣ የሐምሌ፣ የነሐሴ ወራት አልፎ የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ሲሆን የበረደውን የምታሞቀው፣ የጨለመውን የምታስለቅቀው፣ የተሰወረውን የምትገልጠው፣ የረጠበውን የምታደርቀው ፀሐይ ከወራት ደመና ወጥታ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ብርሃኗን መፈንጠቅ ትጀምራለች። ስለሆነም ብርሀን ወጣልን ሲሉ ለየት አድርገው ያከብሩታል። በተመሳሳይ አበባዎችን በየጋራው በየሸንተረሩ ፈክተው መአዛን ሲመግቡን፤ ንቦችም አበባዎችን ቀሥመው ጣፋጭ ማራቸውን ሲሰጡን፤ እንስሳቶችም ሜዳው ላይ እየቦረቁ የእለት ምግባቸውን ሲመገቡ የሚታይበት ጊዜ በመሆኑም ከብዙ ነገር አረፍን ሲሉ እንደሚያከብሩትም አብራርተዋል።

መስከረም ወር በጣም ለኢትዮጵያዊያን ልዩ የተስፋ ምልክት የሚሆንበት ሌላው ምክንያት ኢትዮጵያ ከሦስት ሺህ ዓመት በፊት ሽቶና ሰው ሰራሽ አበባ ታመርት እንደነበር የሚመሰክርላትና የሥልጣኔዋ እድገት ምን ላይ እንደነበረ የሚያስረዳላት ነው። ለዚህም ማሳያው ንግስት ሳባ ሰለሞን ጋር ስትሄድ ሽቶና እርሱን ለመፈተን ይዛቸው የሄደቻቸው አበቦች የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መሆናቸው በግልጽ ተቀምጠዋልና ነው። አሁንም ያንን ዘመን ስናስታውስ እኛም ማድረግ እንደምንችል የሚመራን ታሪክ ያለን ህዝቦች መሆናችንን የሚነግረን ነውና ልዩ ምልክታችን ተደርጎ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን መስከረምን የአዲስ ዓመታቸው መጀመሪያ ያደረጉበት ሌላ ምክንያት መስከረም ዓለም የተፈጠረበት ቀን በመሆኑ ነው የሚሉት መጋቤ ሀዲስ ዶክተር ሮዳስ፤ ይህ ወር ለግብጻዊያን ሳይቀር ለአዲስ ዓመታቸው ምልክት ነበረ። ምክንያቱም ደማቋ ኮከብን ሳይረስን በልዕልና የሚያዩበትና የኮከቧ በመስከረም 1 መውጣትን ተከትለው ራሳቸውን ከአባይ ጎርፍ ይታደጉታል ብለዋልም።

መስከረም የመተካከል ወር እንደሆነም የሚገልጹት መጋቤ ሀዲስ ዶክተር ሮዳስ፤ ጥንታዊው መጽሐፍ ስንክሳር ‹‹የተባረከ የመስከረም ወር የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመታት ወሮች ራስ ነው። የቀኑ ሰዓትም ከሌሊቱ ሰዓት የተስተካከለ አሥራ ሁለት ነው። ከዚህ በኋላ እያነሰ ይሄዳል›› በማለት የመፀው እኩሌ የሚደረግበት ወር እንደሆነ አስቀምጦታል። በዓመት ውስጥ ቀንና ሌሊት እኩል የሚሆኑባቸው ጊዜያቶች መሆናቸውን ያስረዳል። ስለሆነም በኢትዮጵያ ውስጥ ቀኑም ሌሊቱም ደስታን የሚፈጥሩበት ስለሆነ ልዩ ተደርጎ እንደሚከበር አብራርተዋል።

እንደ መጋቤ ሀዲስ ዶክተር ሮዳስ ገለጻ፤ በኢትዮጵያውያን መስከረም ወር ፀሐይ ልክ የምድር ወገብ ላይ ሆና ቀኑና ሌሊቱ እኩል የምታደርግበት ጊዜ ነው። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ፀሐይ ልክ በምሥራቅ ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ ወጥታ በምዕራብ ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ እንድትጠልቅ ያደርጋታል። ስለዚህም ልዩ የተስፋ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

Filed in: Amharic