>

ቀይ መስመር....!!! [ዶ|ር ዮሴፍ ወርቅነህ]

ቀይ መስመር….!!!

[ዶ|ር ዮሴፍ ወርቅነህ]

አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ ለአሜሪካዋ ኮንግረስ አባል ካረን ባስ የሰጠውን ማብራሪያ ተከትሎ የምርቃት መዐት ሲዥጎደጎድ አየሁና ማብራሪያውን ለመስማት ሞከርኩ ። አርቲስቱ በሀገሩ ላይ እየደረሰ ያለውን ዐለም አቀፍ ጫና ለመቋቋም የግሉን አስተዋዕፅኦ ለማበርከት የሄደበት ርቀት የሚደነቅ ነው ። ነገር ግን ለማዳም ካረን የሰጠው ማብራሪያ ላይ አደገኛ የሆነ የታሪክ አረዳድ ስህተት ስላለ ይሄን አመለካከት ማረም ያስፈልጋል ።
በመጀመሪያ ደረጃ የህወሀትን አረመኔነት ለማስረዳት ሁለት መቶ አመታት ወደኋላ ተጉዞ የአባቶችን አጥንት መርገጥ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም ። ዐፄ ዮሐንስና ወያኔ ምንም አይነት ግንኙነት ያላቸው አካላት አይደሉም ። በስመ ትግሬ ዘር ማንዘራቸው ሀገር ሲያፈርስ ነው የኖረው ብሎ ራስ ስሑል ሚካኤልን  ማንሳት አንድን ትልቅ ህዝብ ታሪክ አልባ የማድረግ አደገኛ ሙከራ ነው ። ከዚህም በኋላ የአንድ ሀገር ዜጎች ሆነን በጋራ ክፍለዘመናትን እናሳልፋለን ለምንል ህዝቦች እንዲህ አይነት ትርክቶች የአንድነት ካንሰሮች ናቸው ። ዐፄ ምንሊክ ጡት ቆረጡ | እጅ ቆረጡ የሚሉ ለቅሶዎችን የምንቃወመው እኮ አብረው ስለማያኗኑሩን ነው እንጂ የሰው ብሔር እየመረጡ እንከን ለመምዘዝ አይደለም ። እኛም ወደኃላ ተጉዘን ነገስታትን መዝለፍ ከጀመርን ከእዬዬ ብሔርተኛ ፖለቲከኞች በምን ተሻልን ? የስነልቦና ከፍታችንስ የቱጋር ነው ?
በሁለተኛ ደረጃ ዐፄ ቴዎድሮስን በማስገደል ውስጥ በርሱ አማርኛ የ”ከሀዲ ትግሬዎች” እጅ እንዳለበት (ዐፄ ዮሐንስን ለመንካት ነው) ጠቅሶ ዐፄ ምኒሊክ ለሀገር ያበረከቱትን አስተዋዕፅኦ ማሞካሸት ታሪክን ካለማወቅ ይነሳል ። በርግጥ ዐፄ ምኒልክም | ዐፄ ቴዎድሮስም | ቀዳማዊ ሐይለስላሴም ለሀገር አንድነት ከባድ ዋጋ ከፍለዋል ። ነገር ዩሐንስ አራተኛም በሀገር አንድነት ላይ ባበረከቱት ዋጋ የሚታሙ ኢትዮጵያዊ አይደሉም ።
ዐፄ ቴዎድሮስን በማስገደል ሂደት ውስጥ የዐፄ ዮሐንስ እጅ እንዳለበት ባይካድም | ዐፄ ምኒልክም በዚህ የሚሞካሹ መሪ አይደሉም ። ሁለቱም የዐፄ ቴዎድሮስ ተቀናቃኞች (ዳግማዊ ምኒልክና | ዐፄ ዮሐንስ) ጫካ ገብተው ንጉሱን በነፍስ ለማግኘት የሸፈቱ ነገስታት ናቸው ። የነገስታቱም ጦርነት ሀገር ከመሸጥ ጋር ሳይሆን ከፖለቲካ ልዩነት ጋር የተያያዘ ችግር ነው ። ደግሞም በዐፄ ዮሐንስ ሞት ላይም ዐፄ ምኒሊክ ከጣሊያን ጋር የሸረቡት ሴራ ትልቁን ሚና ተጫውቷል ። እርስ በርስ ተጠላልፎ ስልጣን መያዝ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ማንነትና የዘር ግንድ ሳይለይ ዘመናትን ያሳለፈ የታሪካችን አካል ነው ። ስለዚህ በብሔር ለይቶ አንዱን ሀገር ከሀዲ ሌላውን ሀገር አቅኚ አርጎ ማቅረብ ስህተት ነው ። ደግሞም ዐፄ ዮሐንስ ለሀገራቸው ዳር ድንበር መከበር በሰሜን ከግብፅና ጣሊያን በምዕራብ ከደርቡሽ ጋር ለመግጠም መተማ ድረስ ዘምተው ለሀገራቸው አንገታቸውን የሰጡ ሀገር ወዳድ አባት መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል ።
ሶስተኛ የትግራይን ህዝብ በጣሊያን ወረራ ጊዜ ባንዳ ሆኖ ሀገሩን ያስወጋ ብሎ በጅምላ የፈረጀው አፈራረጅ እጅግ በጣም አደገኛ ነው ። ተሰፍሮ ተጠርቶ የማያልቅ የትግራይ ጀግና ደሙን ለእናት ሀገሩ አፍስሷል ። ልጆቹን ገብሯል ። ከማንም ህዝብ ባላነሰ (ምናልባትም በበለጠ) ከባድ ዋጋ ከፍሏል ። የትግራይን ህዝብ እስከአያት ቅድመአያት እየመዘዙ በሀገር ሻጭነት መፈረጅ የእነራስ አሉላ መቃብር ላይ ምራቅ መትፋት ይሆንብናል ።
አራተኛ በአንድ ጎኑ ብቻ በማየት የመንግስት ሚዲያዎችን ጨምሮ እንዲህ አይነት ልዩነትን የሚዘሩ ንግግሮችን እውቅና ሰጥቶ እያወደሱ ለህዝብ ማቅረብ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም ። ዛሬ የገባንበት መካረርና ጊዜያዊ ግጭት እንዳለ ሆኖ ለሺ አመታት ለሀገር ዳር ድንበር መከበር ዋጋ የከፈሉ አባቶችንና ህዝቦችን ስም ማጠልሸት ከባድ ዋጋ ያስከፍለናል ።
አንዳንዴም በእውር ድንብር ስሜታዊ ሙገሳን ማዥጎድጎድ ሀገርን ያፈርሳልና ጥንቃቄ ይደረግ ። ለኢትዮጵያ አንድነትሸ  ዋጋ የከፈሉ አባቶች በሙሉ በደማቅ ቀለም ታሪካቸውን ብንከትብ ክብሩ ለእኛው ነው ። ጨዋ አስተያየታችሁን ብቻ ስጡኝ
[ነጋቲ]
Filed in: Amharic