>

 ዐብይ አሕመድ ያሜሪቃን ማዕቀብ ተቃወመ ፤ በውነት? (መስፍን አረጋ)

 ዐብይ አሕመድ ያሜሪቃን ማዕቀብ ተቃወመ ፤ በውነት? 

መስፍን አረጋ


“ዐብይ አሕመድ ያሜሪቃን ማዕቀብ በመቃወም ግልጽ ደብዳቤ ጻፈ” አሉ፣ የአብይ አሕመድ ሚዲያወች ኢሳትና ዜና ቲዩብ በሰበር ዜናቸው፡፡  ሳይደግስ አይጣላም እንደሚባለው፣ ዐብይ አሕመድ ባንድ በኩል በየዕለቱ እያደማን፣ በሌላ በኩል ግን በየዕለቱ ያስደምመናል፡፡  በርግጥም ግለሰቡ የተዋጣለት ምርጥ ባልተኛ (comedian) ነው፡፡  ያሁኗ ደግሞ ከምርጥ ቧልቶቹ ውስጥ ዋናዋ ባትሆን እንኳን፣ ከዋናወቹ ውስጥ አንዷ ናት፡፡  

አሜሪቃና ኢትዮጵያ በማናቸውም ቀንና ሰዓት በአካልም በርቀትም ለመነጋገርና ለመወያየት መንገዶችን ሁሉ ክፍት ያደረጉ ጓደኛማች (friendly) አገሮች ናቸው፡፡  ይህ ማለት ደግሞ አሜሪቃ ኢትዮጵያን የተመለከተ ማናቸውንም ርምጃ (በተለይም ደግሞ ማዕቀብን የመሰለ ብርቱ ርምጃ) የምትወስደው፣ ከኢትዮጵያ መሪ ጋር ብርቱ ወይይትና ምክክር ካደረገችና በተወሰነ ደረጃ ስምምነት ላይ ከደረሰች በኋላ ነው ማለት ነው፡፡  ይህ ማለት ደግሞ የዮሐንስ ባይደን መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል የዛተበትን መግለጫ ያወጣው የዐብይ አሕመድን ሙሉ እሽታ ካገኘ በኋላ  ነው ማለት ነው፡፡   

ያሜሪቃ መንግሥት የዛቻ መግለጫ ብቸኛ ዓላማ፣ ማዕቀብ እያስገመገመ መሆኑን ለማስጠንቀቅ ሳይሆን፣ ከወያኔ ጋር ባስቸኳይና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተወያዩ የሚባለውን ሐሳብ በጽኑ ይቃወማሉ ብሎ የሚያስባቸውን ባለስልጣኖች በማዕቀብ ማስፈራሪያ ለማስፈራረት ብቻና ብቻ ነው፡፡  እነዚህ ባለስልጣኖች ደግሞ የአማራ ክልልን ከሚወክሉት ውስጥ የተወሰኑት እንደሆኑ ግልጽ ነው፡፡ 

የዐብይ አሕመድ ግልጽ ደብዳቤ ብቸኛ ዓላማ ደግሞ ከባይደን መንግሥት ጋር በመመሳጠር በኢትዮጵያ ላይ ከጀርባ የሚፈጽመውን ደባ፣ ከኢትዮጵያውያን (በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያዊነታቸው ከማይደራደሩት አማሮች) ለመሰወርና ለኢትዮጵያ ጥቅም የሚታገል ለማስመሰል ብቻና ብቻ ነው፡፡  ለነገሩማ የማስመሰል መልዕክቱን ለኢትዮጵያውያን (በተለይም ደግሞ ውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን) በስፋት ለማስተላለፍ ካልሆነ በስተቀር፣ ካሜሪቃ መንግሥት ጋር ለመነጋገር የሚያስችሉ የበለጠ ፍቱን የሆኑ አያሌ መንገዶች እያሉለት፣ ግልጽ ደብዳቤ መጻፍ ለምን ፈለገ?  ግልጽ ደብዳቤ እንዲጻፍ የግድ ከፈለገ ደግሞ፣ ግልጽ ደብዳቤ እሱ ለተቀመጠበት ቦታ እንደማይመጥንና ለኢትዮጵያ አሳፋሪ እንደሆነ እያወቀ በሱ ስም እንዲወጣ ለምን አደረገ?  የበለጠ አግባብነት የሚኖረው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስም ቢወጣ አልነበረም ወይ? 

   እኒህን ሁሉ በጽሞና ያጤነ ሰው፣ ያሜሪቃ መንግሥት በአማራ ባለስልጣኖችና ታዋቂ አማሮች ላይ ለመጣል ባወጣው የማዕቀብ ዛቻ ላይ ዐብይ አሕመድ ወሳኝ ሚና እንደተጫወተ ምንም ጥርጥር አይኖረውም፡፡  ማዕቀቡ ሊያነጣጥርባቸው የሚገባቸውን የአማራ ባለስልጣኖችና ታዋቂ ግለሰቦች ዝርዝር ዐብይ አሕመድ አስቀድሞ አዘጋጅቶ አስቀድሞ ወደ ዋሽንግተን የላከው ቢሆን ደግሞ፣ ምንም አያስገርምም፡፡   

ስለዚህም ትልቁ ጥያቄ የሚከተለው ነው፡፡  ዐብይ አሕመድ የገዛ ራሱ መንግሥት ዐባል የሆኑትን የአማራ ባለስልጣኖች ኃያሉ ያሜሪቃ መንግሥት ማዕቀብ ሊጥልባችሁ ነው በሚል የማዕቀብ ዛቻ ለማስፈራራት የፈለገበት ምክኒያት ምንድን ነው?  ዐብይ አሕመድ ከዚህ ዛቻ የሚያተርፈው ምንድን ነው?

   ዐብይ ዐሕመድ በኢትዮጵያ መንበረ ሥልጣን ላይ ከተቀመጠባት ዕለት ጀምሮ የወሰዳቸው ርምጃወች ሁሉም በግልጽ የሚያመለክቱት፣ ግለሰቡ የኢትዮጵያ መሪ ሳይሆን የኦሮሙማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ (chief executive) ወይም ደግሞ ሰባተኛው ሉባ መሆኑን ነው፡፡  የኦሮሙማ ዓላማ ደግሞ በጦቢያ ፍርስራሽ ላይ ያሁኒቷን ጦቢያን አብዛኞቹን ክፍሎች እንዲሁም ከጎረቤት አገሮች የተወሰኑ ክፍሎችን የሚያጠቃል የኦሮሞ አጼጌ (Oromo empire) መመሥረት ነው፡፡  

ዐብይ አህመድ የኦሮሙማ ሕልሙን ማሳካት የሚቸለው ግን የሐብሻ ክልሎች የሚባሉትን ትግራይና አማራን በተደለሉ (convinced) ወይም በተታለሉ (confused) የኦሮሙማ ሎሌወች (puppets) የሚመሩ ገባሪ ክልሎች (vassal regions) ካደረጋቸው ብቻና ብቻ ነው፡፡  ይህን በማድረግ ረገድ ደግሞ በቂ ርቀት የተጓዘ ይምስላል፣ ወይም ደግሞ ተጉዣለሁ ብሎ የሚያምን ይመስላል፡፡  

በመጀመርያ፣ የወያኔ ወንጀለኞችን ከሕግ ፊት ማቅረብ በሚል ሰበብ ትግራይን አፈራረሳት፡፡  ቀጠለና ደግሞ የጽሞና ጊዜ መስጠት በሚል ሰበብ እነዚህን ወንጀለኞች በአማራ ክልል ላይ መረን በመልቀቅ የአማራን ክልል እንዲያፈራርሱ ማመቻቸት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ እገዛ አደረገላቸው፡፡  አሁን ላይ ደግሞ እነዚህ ሁለት ክልሎች የኦሮምን አጼጌ (oromo empire) የመመሥረቱን ሂደት ማክሸፍ ቀርት ማደናቀፍ በማይችሉበት ደረጃ እጅጉን ስለተዳከሙ፣ ክልሎቹ አሁን ያሉበትን ደካማ ሁኔታ (status quo) በአሜሪቃ መንግሥት በሚመራ፣ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በሚካሄድ አስቸኳይ ድርድር አማካኝነት ሕጋዊነት ሊሰጠው ፈለገ፡፡  

የአማራ ክልል አመራሮችና ታዋቂ ግለሰቦች፣ ወያኔ ክልላችንን ወርሮ፣ ሕዝባችንን እየጨፈጨፈና ንብረታቸንን እየዘረፈ ከወያኔ ጋር አንደራደርም ብለው አሻፈረኝ ቢሉ ደግሞ፣  እንዲህ ካላችሁማ በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሳችሁ ሄግ ትቀርባላቸው በሚል ማስፈራርያ ሊያሽቆጠቁጣቸው ይሞክራል፡፡ ባንተው በራስህ ክልል ላይ ከፍተኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ያስፈጸመው አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዘር ማጥፋት ወንጅል ሳይከሰስ፣ እኛ የምንከሰሰው በምን ሒሳብ ነው ብለው ቢሞግቱት ደግሞ፣ ኦሮሞና ትግሬ አይነካባት እንጅ የአማራ መጨፍጨፍ ላሜሪቃ ግድ አይሰጣትም ብሎ በድፍረት ይመልስላቸዋል፡፡  እዚህ ላይ ግን ዐብይ አሕመድ ነጥብ አለው፣ ምክኒያቱም ያሜሪቃ መንግሥት የሚያደርጋው ድርጊቶችና የሚያወጣቸው መግለጫወች ሁሉ፣ ለአማራ ሕዝብ ጉዳይ ግድ የሌለው ብቻ ሳይሆን ያሜሪቃን ጥቅም ለማስከበር የተነሳሳው በአማራ ሕዝብ ጉዳት ላይ እንደሆነ ያስመስሉበታልና፡፡    

የወልቃይትና የራያ ወደ ቀድሞ ቤታቸው ወደ አማራ ክልል መመለስ፣ ክልሉን በሁሉም ረገዶች የሁሉም ክልሎቸ የበላይ ኃያል (most powerful) አድርጎ፣ የዐብይ አህመድን የኦሮሙማ ሕልም፣ ሕልም ብቻ አድርጎ እንደሚያስቀረው ጥርጥር የለውም፡፡  ወያኔ ራያንና ሰሜን ወሎን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ባለበት ባሁኑ ወቅት፣ ከወያኔ ጋር ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የሚደረግ ድርድር፣ ውጤቱ ሊሆን የሚችለው ወያኔ ራያንና ወልቃይትን ወደ ትግራይ እንደገና መጠቅለል ብቻ ሳይሆን፣ ጥቅለላውን ሕጋዊ ማድረግ ነው፡፡  ይህ ከሆነ ደግሞ የአማራ ክልል ዕጣ እነዚህን ግዙፍና ለም መሬቶች ለዘላለም ተነጥቆ በእጅጉ የተዳከመ ክልል ከመሆኑ በሻገር፣ በቅርቡ በምትወለደው በዐባይ ትግራይ ሪፓብሊክ፣ በቅርቡ በሚመሠረተው በኦሮሞ አጼጌ እና በሱዳን ሙሉ በሙሉ የተከበበ የምሥራቅ አፍሪቃ አርመኒያ (The Armenia of east africa) መሆን ነው፡፡   ከወያኔ ጋር ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ፣ ይልቁንም ደግሞ ባስቸኳይ ድርድር እንዲደረግ ዐብይ አሕመድ ካሜሪቃ መንግሥት ጋር የሚመሳጠርበት ምክኒያት ይሄውና ይሄው ብቻ ነው፡፡  አለበለዚያ፣ ባስደናቂ ፍጥነት እየተደራጀና እየተጠናከረ ያለው የአማራ ሕዝብ፣ ለዐብይ አሕመድ የተከፈተለትን የዕድል በር ለዘላለሙ ጥርቅም አድርጎ ይዘጋውና የዐባይ ትግራይና የአሮሞ አጼጌ ሕልሞችን ለዘላለሙ ሕልም ብቻ ሁነው እንዲቀሩ ያደርጋቸዋል፡፡ 

መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic