አቻምየለህ ታምሩ
ምሑራን ነን ከሚሉን የያ ትውልድ የጎሳ ብሔርተኞች መካከል መዋሸቱ ሳያንሰው በተለያየ ጊዜ የሚዋሸው ነገር ርስ በራሱ ስለመጋጨት አለመጋጨቱ እንኳን ደንታ የማይሰጠው ዘባተሎ ፍጡር ቢኖር የፋሽስት ወያኔው “ምሑር” ፕሮፈሰር ገላውዲዮስ አርኣያ ከቀዳሚዎቹ መካከል ነው። ከሳምንታት በፊት በለጠፍሁት የራሱ የቪዲዮ ንግግር ላይ እንዳዳመጣችሁት የወልቃይትን ጉዳይ “ብዙ አጥንቸዋለሁ፤ ከኔ በላይ የሚያውቀው የለም” ስላለ ክርክር ለማድረግ ከአንድ ሜዲያ ጋር ለረጂም ጊዜ የተያዘ የክርክር ቀጠሮ አስይዞ ከኔ ጋር እንደሚከራከር ሲነገረው ክርክሩን ሰርዞ እንደፈረጠጠ ታስታውሳላችሁ። እሱ ራሱ “አቻምየለህ ከሚባል ትምክህተኛ ጋር መከራከር አልፈልግም” በማለቱ ክርክሩ ሳይካሄድ እንደቀረ በአንደበቱ ያረጋገጠበትን ንግግሩን ከታች በድጋሜ ተለጥፏል።
ከኔ ጋር መከራከር ባለመፈለጉ የተያዘለትን የክርክር ቀጠሮ መሰረዙን ከአንዱ የፋሽስት ወያኔ ልሳን ጋር በትግርኛ ቋንቋ ባደረገው ቃለ መጠይቅ ሲናገር የተሰማው የሲቲ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኒዮርክ “የታሪክና የፖለቲካ ሳይስን” መምርሁ ፕሮፈሰር ገላውዲዮስ አርኣያ ከሰሞኑ ደግሞ በሌላ የፋሽስት ወያኔ ሜዲያ ላይ የፊልም ባለሙያው ቴዎድሮስ ተሾመ የአሜሪካ ኮንግረስ አባልና በኮንግረሱ የአፍሪካ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ ለሆኑት ካረን ባስ ስለኢትዮጵያን ሁኔታ ባስረዳው ጭብጥ ዙሪያ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ምላሽ ለመስጠት ብቅ ብሎ የወልቃይትን ታሪክ በሚመለከት በተቃራኒ ወገን የሚከራከረው ሰው ማጣቱን ፕሮፈሰር እየተባለ የሚጠራበት የምሑርነት ማዕረግ ሳይከብደው ተቀደደ።
ይታያችሁ! ከሁለት ቀን በፊት በእንግሊዝኛ ቋንቋ በአንዱ የፋሽስት ወያኔ ልሳን ላይ ቀርቦ ባደረገው በዚህ ቃለ ምልልስ ላይ በወልቃይት ታሪክ ዙሪያ የሚከራከረኝ ሰው አጣሁ የሚለው ፕሮፈሰር ገላውዲዮስ አርኣያ ከወራት በፊት በሌላው የፋሽስት ወያኔ ልሳን ቀርቦ በትግርኛ ቋንቋ ባደረገው ቃለ ምልልስ በወልቃይት ታሪክ ዙሪያ እንዲከራከር ቀጠሮ ተይዞለት ክርክር የሚደረግበት ወቅት ደርሶ ከኔ ጋር እንደሚከራከር ሲነገረው ከሱ ጋርማ መከራከር አልፈልግም ብሎ የፈረጠጠውና እሱም ራሱ በአንደበቱ “አቻምየለህ ከሚባል ትምክህተኛ ጋር መከራከር አልፈልግም ብዬ የክርክር ቀጠሮውን ሰረዝሁት” ብሎ ሲናገር የሰማነው ገራሚ ፍጡር ነው።
ፕሮፈሰር ገላውዲዮስ አርኣያ የራሱን ውሸት ሪኮርድ የሰበረው በዚህ ብቻ አይደለም። በ2008 ዓ.ም. “የኢትዮጵያ ጠበቃ እንጂ የአንድ ብሔር አፈቀላጤ አይደለሁም” በሚል በድረ ገጽ በለቀቀው ጽሑፍ ገጽ 7 ላይ “ወልቃይትና ጸለምቲ በአፄ ኃይለሥላሴ ትእዛዝ በ1930 ዓ.ም. ከጎንደር እንዲስተዳደር፣ ቀጥሎም በ1957 ዓ.ም. ቤገምድርና ስሜን ተብሎ እንዲስተዳደር ተደርጓል።” ሲል ጽፎ ነበር። ይህን ያለው ፕሮፈሰር ገላውዲዮስ አርኣያ ሁሉ ከሁለት ቀን በፊት ደግሞ በእንግሊዝኛ ባደረገ ቃለ ምልልስ ወልቃይት ከትግራይ ተወስዶ ወደ በጌምድርና ስሜን እንዲካተት የተደረገው በ1948 ዓ.ም. ነው ብሎን አረፈው። ይህንን የፕሮፈሰር ገላውዲዮስ አርኣያ ውሸት የሚከተለውን ትር በመጫን በ2008 ዓ.ም. በድረ ገጹ ከለቀቀው ጽሑፉ ገጽ 7 ላይ ታገኙታላችሁ፤
የፋሽስት ወያኔ አፈ ቀላጤ ፕሮፈሰር ገላውዲዮስ አርኣያ ትናንትና የዋሸውን ውሸት ዛሬ ላይ በሚዋሸው ሌላ ውሸት የራሱን ውሸት ክብረ ወሰን በመስበር ፍላጎቱን የሚያሟላለትን ውሸት ሁሉ ያለ ስስት ሲፈጥር የሚውልና የራሱን ውሸት በአዲስ የራሱ ውሸት ሲያጣፋ የሚውል ቀዳዳ ነው። በሚያስተምርበት ዩኒቨርሲቲ ድረ ገጽ ላይ በ2008 ዓ.ም. ባሰራጨው የራሱ ጽሑፍ ወልቃይትና ጸለምቲ በአፄ ኃይለሥላሴ ትእዛዝ በ1930 ዓ.ም. በጎንደር እንዲስተዳደሩ እንደተደረገ እንዳልተቀደደ ሁሉ ዛሬ ደግሞ የትናንትና ውሸቱ ሳያሳፍረው ወልቃይት ወደ በጌምድር የተካተተው በ1948 ዓ.ም. ነው አለን።
በአንድ የአሜሪካን አገር በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ታሪክና ፖለቲካል ሳይንስ አስተምራለሁ የሚል ሰው ፋሽስታዊ ዓላማውን ለማሳካት ሲል ትናንት የዋሸውን ውሸት በዛሬ አዲስ ውሸት እያጣፋ እንዲህ የውሸት ክምር ሲቆልል ሲውል ከማየት በላይ ዝቅጠት የለም።
ግና ፕሮፈሰር ገላውዲዮስ ለማሰብ ፍቃደኛ ያልሆነ ተከታይ ስላለው ብቻ በአንድ ጉዳይ ላይ የራሱ የውሸት በማጠፍ ሌላ ውሸት በማምረት የራሱ የውሸት ሪከርድ እየሰበረ ትናንትና ሌላ ውሸት ዛሬ ደግሞ ሌላ ውሸት መቀደድን የፕሮፈሰርነቱ ግብር ቢያደርገው የሚቆልለው የትኛውም የውሸት ክምር ግን የወልቃይትን የታሪክ እውነት ሊሸነው አይቻለውም።
ከታች የተያያዘው ቪዲዮ ፕሮፈሰር ገላውዲዮስ አርቀኣያ የራሱን ውሸቶች በማጠፍ የራሱን የውሸት ሪከርድ የሰበረበትን በከፊል የሚያሳይ ነው። የቪዲዮን የመጀመሪያ ክፍል “አቻምየለህ ከሚባል ትምክህተኛ ጋር መከራከር አልፈልግም” ሲል ከወራት በፊት በትግርኛ የተናገረበት ነው። ከዚህ ንግግሩ ቀጥሎ “የወልቃይትን ታሪክ በሚመለከት በተቃራኒ ወገን የሚከራከረኝ ሰው አጣሁ” ሲል የራሱን የቀደመ ንግግር ያጣፋበት ቀደዳው ይገኛል። ከዚህ በመቀጠል ወልቃይት ወደ በጌምድር የተካተተው በ1948 ዓ.ም. መሆኑን ሲናገር ይደመጣል። በስተመጨረሻ ላይ በሚታየው ደግሞ በንግግሩ በ1948 ዓ.ም. ከትግራይ ተወስዳ ወደ በጌምድር እንደተካተተች የነገረን ወልቃይንት በ2008 ዓ.ም. “የኢትዮጵያ ጠበቃ እንጂ የአንድ ብሔር አፈቀላጤ አይደለሁም” በሚል በድረ ገጽ በለቀቀው ጽሑፍ ገጽ 7 ላይ “ወልቃይትና ጸለምቲ በአፄ ኃይለሥላሴ ትእዛዝ በ1930 ዓ.ም. ወደ ጎንደር እንዲስተዳደር ተደረገ” በማለት የጻፈውን የራሱ ጽሑፍ ነው።
ፕሮፈሰር ገላውዲዮስ አርኣያ በ2008 ዓ.ም. ያሳተመውን የራሱን ጽሑፍና ከሁለት ቀን በፊት የተናገረውን የራሱን ንግግር ስናገናኛቸው በ1930 ዓ.ም. ከትግራይ ተወስዳ ወደ በጌምድር የተካተተቸው ወልቃይት በ1948 ዓ.ም. ደግሞ ድጋሜ ከትግራይ ተወስዳ ወደ በጌምድር ተካትታ እናገኛታለን። እውነት እንደ ውሸት ብዙ መልክ የላትም። የፋሽስት ወያኔው ምሑር ፕሮፈሰር ገላውዲዮስ አርኣያ ስለ ወልቃይት የሚናገረውና የሚጽፈው በማስረጃ ሊረጋገጥ የሚችል እውነትነት ቢኖረው ትናንትና ስለ ወልቃይት ትናንትና የጻፈውና ዛሬ ስለወልቃይት የሚናገረው የተለያየና ብዙ መልክ አይኖረውም ነበር። ውሸትን በሕዝብ ላይ መክተብ ይቻል ይሆናል፤ ውሸትን ግን እውነት ማድረግ አይቻልም።
በስተመጨረሻም አሁንም ለአራተኛ ጊዜ እንዲህ እንላለን! ፋሽስት ወያኔ ባለፉት 30 ዓመታት በወረራ የያዛቸውን ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ አስመልክቶ ቢያንስ ላለፉት 1660 ዓመታት በአንድም የታሪክ ወቅት የትግሬ ሆነው እንደማያውቁ ፤ ይልቁንም ነበሩ ባለርስት አማራ እንደሆኑ በዋናነት የቀድሞ የትግሬ ገዢዎችና ከትግሬ የፈለቁ የኢትዮጵያ ነገሥታት የሰጡትን የታሪክ ምስክርነት ዋቢ በማድረግ ከ700 በላይ ማጣቀሻ (መጠቆሚያ) ተጠቅመን ውሸታውን ያረከሰ መጽሐፍ በማሰናዳት ለገበያ አቅርበናል። በመጽሐፉ የቀረበውን የታሪክ ሙግት አለኝ የሚለውን ማስረጃ አቅርቦ የተቸ አንድም የትግሬ ብሔርተኛ የለም።
መጽሐፍ ከመጻፍም አልፈን ፕሮፈሰር ገላውዲዮስ አርኣያ አለኝ የሚለውን ማስረጃ ይዞ በፈለገው መድረክ እንድንገናኝና በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት እንከራከር በአደባባይ ጠይቀን ነበር። ፕሮፈሰር ገላውዲዮስ አርኣያ ግን የሚከራከረው ከኔ ጋር እንደሆነ ሲነገረው ለክርክር የተያዘላቸውን ቀጠሮ ሰርዞ ፈረጠጠ። ፈርጥጦ ሲያበቃ ደግሞ ሳያፍር የወልቃይትን ታሪክ በሚመለከት በተቃራኒ ወገን የሚከራከረኝ ሰው አጣሁ እያለ ይቀደዳል።
ይህም ሆኖ እኛ ግን አሁንም ለአራተኛ ጊዜ እንጠይቃለን! ፕሮፈሰር ገላውዲዮስ አርኣያ ወልቃይት የትግሬ ወይም የትግራይ ነበር፤ የትግሬ መሬት ያለአግባብ ተወስዷል ብሎ የሚያምን ከሆነ ማስረጃውን ይያዝና ቢፈልግ ከዚህ በፊት ቀጠሮ ይዞለት በነበረውና ከኔ ጋር እንደሚከራከር ሲነገረው ጥሎ በፈረጠጠበት ሜዲያ፤ ቢያሻው በየጊዜው የራሱን የውሸት ሪኮርድ እየሰበረ በሚዋሽባቸው የራሱ ወገን ሜዲያዎች ላይ ቀርበን ስለ ወልቃይት የወሰን፣ የሕዝብ፣ የመልክዓ ምድርና የአስተዳደር ታሪክ በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት እንከራከር።
እኔ በበኩሌ ይህንን ክርክር በየትኛውም ፕሮፈሰር ገላውዲዮስ አርኣያ በሚመርጠው ሜዲያ፤ በማናቸውም ሰዓት ቀርቤ ለመሟገት ዝግጁ ነኝ! አንድ ሰው አወቀ የሚባለው የመረመረውን፣ ያጣራውን፣ ያረጋገጠውንና አለኝ የሚለውን እውነት ፊት ለፊት ይዞ ቀርቦ እንዲህ ለመሞገትና ለመከራከር ዝግጁ ሆኖ ሲገኝ እንጂ ፕሮፈሰር ገላውዲዮስ አርኣያ እንዳደረገው ከማን ጋር እንደሚከራከር ሲነገረው ፈርርጦ ከሄደ በኋላ የሚከራከረው እንዳጣ ለተከታዮቹ የሚዋሽና የሚናገረውን ማንም አይሰማም ብሎ በማሰብ በጓዳ በር ተደብቆ ሲሳደብ ሲውል አይደለም!