>

ግልጽ ደብዳቤ ለአቶ ኤርሚያስ ለገሰ...!!! (አበበ ገላው)

ግልጽ ደብዳቤ ለአቶ ኤርሚያስ ለገሰ…!!!
አበበ ገላው


ውድ ወገኖቼ፣ ከዚህ በታች ለአቶ ኤርሚያስ ለገሰ የጻፍኩት አይን ገላጭ ግልጽ ደብዳቤ እንዳያመልጣችሁ። ጉዳዩ የእኔና የኤርሚያ ብቻ ሳይሆን የጊዜውን ፖሊቲካ ግልጽ አድርጎ ያሳያል። አንብባችሁ ስትጨርሱ ኪሳራ ከተሰማችሁ ከፍተኛ ካሳ ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ፦) መልካም ሰንበት!
—-
ሰሞኑን በአንተ ላይ የመሰረትኩትን ክስ በተመለከተ ያው እንደ ተለመደው “በፓኬጅ” ጠርዘህ  የተዛባ መረጃ መልቀቅህ ባይገርመኝም እንደ ለመድከው አሁንም ህዝብ ስላሳሳትክ ብዥታውን ለማጥራት በይፋ አጠር ያለ ማስተካከያ መስጠቱ ተገቢ መሆኑ ስለተሰማኝ የሚከተለውን ለማለት ወደድኩ።
እንምታውቀው በዚህ ጉዳይ ላይ በተለያዩ ጊዜያት አራት ደብዳቤዎችን ጽፌልሃለሁ። እነዚም በኢሜይል የጻፍኩልህ ደብዳቤዎች ይዘታቸው ተመሳሳይ ሲሆን በአጭሩ መልዕክታቸው እኔን በተመለከተ መብቴን በመጣስና በመጋፋት ሚድያ ላይ ለህዝብ ያሰራጨሃቸውን አሳፋሪና ሃሰተኛ መረጃዎች በይፋ እንድታስተካል የሚጠይቁ ናቸው። ጉዳዩን ከፍርድ ቤት ውጭ መፍታት እንደምፈልግና አንተም እርምት አድርገህ ፋይሉን በሰላም እንድንዘጋው በተደጋጋሚ የጠየኩህ ሲሆን አንተ ግን በእብሪት የሰራሃውን ስህተት ለማረም ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርተሃል። እውነታው ይህ ሆኖ እያለ እራስህን ተበዳይ አድርገህ ለማቅረብ የተለያዩ ግዙፍ ሃይሎች ሴራ በአንተ ላይ የተሸረበ ለማስመሰል መሞከርህ ትዝብት ላይ ይጥልሃል እንጂ የውሸት ክምርህን ወደ አንዲት ቅንጣት እውነት አይቀይርልህም።
ዛሬ አንተ እንደምትለው ሳይሆን እኔ እርምት የጠየኩባቸው ጉዳዮች ሻቢያን፣ ግንቦት 7ን፣ የአብይን መንግስት፣ ጸረ አዲስ አበቤ ሃይሎች፣ የኦሮሙማ ቡድኖችና ሌሎች “በፓኬጅ” የሚናበቡ ሃይሎችን ያሳተፈ ጉዳይ ሳይሆን የሚመለከተው እኔና አንተን ብቻ መሆኑ ጠፍቶህ አይደለም። ይሁንና አላማህ እውነትን አዛብተህና እራስህን አግዝፈህ በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ሃይሎች ጦራቸውን አዝመተው እየተናበቡ ሊያጠፉህ የተነሱ አስመስለህ አቀረብከው። እንቁራሪት ዝሆን መሆን ሲያምራት ፈንድታ እስክትሞት እንዲህ ይወጣጥራታል። እራስን የማግዘፍ አባዜ መጨረሻው መፈንዳትና ኪሳራ እንጂ እንደምታስበው ለዘለቄታው አያተርፍም።
ሃቁን በጭስና በፉከራ ማፈንን ተወውና እስቲ ቆም ብለህ ቀላል በሆነ ቋንቋ እንነጋገር። እንደምታስታውሰው ያልተደበቀና የሌለ አደገኛ ሚስጥር ደብቄ የያዝኩ አስመስለህ በተደጋጋሚ በይፋ “ሚስጥሩ ይውጣ” የሚል ዘመቻ አድርገህ ጸሎትህ ሰምሮ የተባለው መረጃ ሲወጣና መልሶ በአንተ ላይ ሲባርቅ “ትንተና” ለመስጠት በሚል በመስከረም 2020 በቴድሮስ ጸጋዬ  ዩቲዩብ ቻናል ላይ ቀርበህ ሁለት ሰአት ያህል ጊዜ ወስደህ ታዳሚህን የውሸት ታሪኮችና የቡና ቤት ወጎች አጠገብከው።
በዚህም ጉባኤ ዋነኛው የጨበራ ትንታኔህ ኢላማ እኔ ነበርኩ። ታዳሚህና ጀሌህ የነገርከው ተረት ተረት እውነት መሰሎት ስሜቱን መቆጣጠር ያቀተው ሁሉ እኔን ሲራገምና ሲሳደብ ጸረ አማራ ሲለኝ አመሸ። እኔ ግን በአንተ እንጂ ውሸትን ተግቶ በስሜት በጦዘው ምስኪን ታዳሚና መንጋ አልፈረድኩም። ይሁንና ጉባኤው ከተበተነ በሁዋላ ከቅዥት ወደ ገሃዱ አለም መመለስ ተገቢ በመሆኑ የፈጠራው ትርክትና የሃሰት ተረቶችህ እንዲስተካከሉ መጠየቅ የግድ አስፈላጊ በመሆኑ የመጀመሪያውን ደብዳቤ እኤአ ሴፕቴምበር 2020 ላኩልህ። በመቀጠልም በተለያዩ ጊዜያት አራት ጊዚያት ያህል እርምት አድርገህ ጉዳዩን እንድንዘጋው በደብዳቤ ብጠይቅህም ፈቀደኛ ሆነህ ባለመገኘትህ ለአንተም ይሁን ለእኔ ወደ ማያዳላ ገለልተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ማቅረብ ተገቢ በመሆኑ ክሱ ፍርድ ቤት ደርሷል። ይህም ድንገት የመጣ ሳይሆን በጁላይ 17 በጻፍኩልህ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እርምት ለማድረግ ፍቃደኛ የማትሆን ከሆነ ያለኝ የመጨረሻ አማራጭ ጉዳዩን ወደ ህግ መውሰድ መሆኑን ግልጽ እድርጌልህ ነበር። በመሆኑም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የመራሃው ከእኔ ይልቅ አንተ ነህ።
እኔን መጉዳት አላማ ባደረገው በርዮት ሚድያ ዝግጅት ላይ ቀርበህ አስገራሚ ሊባሉ የሚችሉ የፈጠራ ክሶችን ኩሸቶችን ቀምረህ መደርደርህ በምስልም በድምጽም የሚገኝ መረጃ ስለሆነ አንተም ሆንክ እኔ ለማስታወስ አንቸገርም። እስካሁን ለመመለስ ግራ ያጋባኝ “ለምን?” የሚለውን ጥያቄ ብቻ ነው።  እርግጥ የራስህን አሳፋሪ ስህተት ለመሸፈን ፈጽሞ ያልደርሰብህን ሰውን ያለ አግባብ ማጥቃትና በሃሰት መወንጀል ከህወሃቶች የተማርከው ስሌትና ስልት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግተኝም።
ለማንኛውም ሻብያን፣ ኦነግን፣ ግንቦት 7ን ወይንም ጸረ አዲስ አበቤዎችን የማይመለከቱት የእኔ የአበበ ገላው የክስ ጭብጦች መሰረት ያደረጉት እውነታዎች  የሚከተሉት ናቸው፤
1ኛ/ በህወሃቱ መሪ   ደብረፂዮን ገብረሚኪያኤል ላይ በጃንዋሪ 2018 ያቀረብኩትን ሰፋ ያለ የምርመራ ሪፖርት በማጣጣል ደብረፂዮን ለምን ተነካብኝ በሚመስል መልኩ በግል ያጠቃሁት አስመስለህ ግለሰቡ ላይ ያቀረብኩት “ፐርሰናል” ጥቃት እንደሆነና እንደውም የእነ ደብረፂዮን የሌሎችን የግል ኢሜይል ሰብሬ እንደበረበርኩ መወንጀል ብቻ ሳይሆን መረጃ አለኝ ብለህ በአደባባይ ተናገርክ። የግለሰቦችንም ኢሜይል “ክራክ” ወንይም “ሃክ” እንደማደርግና ወንጀል እንደምፈጽም መረጃ መኖሩንም በድፍረት በሃሰት በአደባባይ መሰከርክብኝ። ስለሆነም የደብረጽዎንን ወንጀሎች ተከላክለህ እኔ ያልሰራሁትን ወንጀል ሰራቷል ብለህ የሃሰት ውንጀላ ይዘህ አደባባይ መውጣትህ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው አሳፋሪ ድርጊት በመሆኑ ማስተካከያ እንድታደርግ ጠይቄሃለሁ። ለእኔ ደብረፂዮን ትናንትም ዛሬም የኢትዮጵያ ህዝብ ቀንደኛ ጠላት ነው። አንተ ግን ለእነ ደብረፂዮን ወግነህ የእነርሱ ወንጀል ሲነሳ “እንደ ሚያንገሸግሽህ” ሃብታሙ አያሌው ሰሞኑን በምሬት ሲናገር እንደ ሰማሁት ሁሉ እኔንም መንገሽገሽህ ብዙ አልገረመኝም።
እኔ ያጋላጥኩት ደብረፂዮን የህዝብን አንጡራ ሃብት በአለም ዙሪያ በሚገኙ የቀይ መብራት ክልሎች (red light districts) እንዴት ያባክን እንደነበር ለማሳየት ለሰራሁት ልዩ ምርመራ መረጃው በዋነኛት በራሳቸው በህወሃቶች በተይም የአባይ ወልዱ ቲፎዞ በነበረው በገብረሚካኤል መለስ በኩል መውጣቱን ማወቅ ብቻ ሳይሆን እለታዊ ፕሮግራም ላይ አንተው በአንደበትህ የተናገርከው እኔም በመረጃ አስደግፌ የያዝኩት ሃቅ ቢሆንም በጠየኩህ መሰረት ምንም አይነት ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆንክም። በመሆኑም በሃሰት የኢሜይል መስበር ወንጀል እኔን በአደባባይ መክሰስህ ወገንተኝነትህ ከማን እንደሆነ የሚያጋልጥ እኩይ ድርጊት ነው።
ያም ሆነ ይህ ከዚህ ጋር በተያያዘ በስም ማጥፋትና በወንጀል ሊያስጠይቅ የሚችል የሃሰት ክስ በሚድያ ላይ ለህዝብ በማሰራጨትህ ከስሼሃለሁ።
2ኛ/ አንተው  እጅግ አጋነህ በጣም አስደንጋጭ ያልከውን ሚስጥር ደብቄ ያስቀመጥኩት ሳይሆን የኢንሳውን ኤንጂነር ማንነት በማያጋልጥ መልኩ እንደምታውቀው ለHuman Rights Watch ከፍተኛ ተመራማሪ ለነበረው ፊሊክስ ሆርን ሰጥቼው ማርች 2014 “They Know Everything We Do: Telecom and Internet Surveillance in Ethiopia” በሚል ርዕስ ባለ 145 ገጽ ሰፊ ሪፖርት ድርጅቱ መረጃውን መነሻ በማድረግ ሰርቶበታል። ይሄን ከፊሊክስ ሆርን ጋር ያደረግነውን በርካታ የኢሜይል ልውውጦች ጨምሮ በመረጃ ተገፎ እጄ ላይ ያለን ሃቅ ውሸት ነው ብለህ በተጠቀሰው ሚድያ ላይ ወጥተህ እውነተኛው “ሪፖርት” ሌላ ባለ 16 ገጽ ነው ያልከውን ፎርጅድ የሆነ ዶኩመንት ይዘህ ብቅ አልክ። አስደንጋጩ ጉዳይ ግን ባለቤትነቱ የእኔ የሆነን ዶኩዩመንት ቀያይረህና ፎርጅ አድርገህ በሃሰት ወነጀልከኝ። እውነታው ግን ባለ 16 ፔጅ ያልከው የሌለና ያልተጻፈ ሪፖርት እኔ ከኢንሳው ኢንጂነር ጋር ያደረኩት ቃለ ምልልስ ትራንስክሪፕት (የጽሁፍ ቅጂ) ሲሆን ፊሊክስ ሆርን ለእኔ በኢሜይል አስተርጉሞ የላከልኝ ሲሆን የዚህም እውነተኛ (ኦሪጂናል ኮፒና) አንተ ሪፖርት ብለህ የሌሉ ስሞች ጨምረህና ቀያይረህ አደባባይ ካቀረብከው ፎርጅድ ዶኩዩመንት ጋር ተያይዞ ወደ ፍርድ ቤት ተመርቷል። ለማስታወስ ያህል የእኔም ይሁን የHuman Rights Watch ፈቃድ ሳትጠየቅ ለስም ማጥፋት ስትል ብቻ  ፎርጅ ያደረከው ዶኩዩመንት ከ100 በላይ የእግሊዝኛ ስዋስው (grammar) ስህተት፣ የፊደል ግድፈትና (spelling errors) የስርአተ ነጥብ ስህተቶችን የያዘ “ሪፖርት” ስልሆነ ድፍረትህን ፍርድ ቤቱ ሳያደንቀው እንደማያልፍ እርግጠኛ ነኝ። ከዚህም ጋር በተያያዘ ሆን ብሎ ሰም ለማጠልሸት፣ በህዝብ ለማስጠላትና ተአማኒነትን ለማሳጣት እንዲሁም በሃሰት ለመወንጀል ፎርጅድ ዶኩዩምነት በማዘጋጀትና ህዝብ ለማሳሳት በማሰራጨትህ ጉዳዩን ፍርድ ቤት እንዲያየው በክሴ ጠይቂያለሁ።
3ኛ/ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርኩ ጊዜ ካስተማሩኝ መምህራን አንዱና በአሁኑ ጊዜ በቨርጂንያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ እና ማትስ መምህር የሆኑ አንድ ፕሮፌሰር የዛሬዋን የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በተመለከተ አንድ ኢሜይል ላኩልኝ። ይህም ማንም ሊያነሳው የሚገባው ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ታማኝነት (public integrity) የመፈተሽ ሃላፊነት ሚድያ ስላለበት በየጊዜው ጥቆማ ይደርሰዋል። ይህም የተለምደ ጉዳይ ነው።
በወይዘሮ ዳግማዊት ዙሪያ የተነሳው ጥቆማ አዲስ አልነበርም። ይሁንና በወቅቱ ለአዲስ አበባ ከንቲባነት ከታጩት ግለሰቦች መሃል መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ያለ ዳግማዊት ከንቲባ ለአሳር የሚል ዘመቻ ጀምረህ ነበር። ግለሰቧን አንዳንተ በቅርብ ስለማላውቃቸው አስተያየት ባልሰጥም የመጣው የሚድያ ጥቆማ ግን ትኩረቴን ስቦት ነበር። ጥቆማው ግለሰቧ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት መምህርና የድህረ ምርቃ ተማሪ በነበሩ ጊዜ የዛሬዋን በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑትን ዶክተር ትዝታ ሙሉጌታን የማስተርስ የመመረቂያ ጽሁፍ (Urban Poverty: A Comparative Analysis of Female and Male Headed Households in Addis Ababa: The Case of Woreda 2 and 28) ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ገልብጠው በማቅረባቸው ዩኒቨርሲቲው ጥፋታቸውን መርምሮ ከስራም ከትምህርት ገበታቸውም እንዲባረሩ ማድረጉን የሚያትተውን መረጃ ኮፒ ለአንተና ለሲሳይ አጌና ሰጠሁዋችሁ። ይሄም ጉዳይ ከሚድያ ስራ ጋር እንጂ ከሌላ የፖለቲካ ሴራ ጋር ተገናኝቶም አያውቅም።
አንተ በእርግጥ መረጃውን በወቅቱ አጣጥለህ እኔም ከእውነታው ይልቅ ከሴትዮዋ ጋር ስለነበረህ ወዳጅነት ስታወራ በትዝብት አልፌዋለሁ። ጉዳዩንም ሽፋን ላለመስጠት የወሰነው ከአንተ ተረት ጋር በተያያዘ ሁኔታ ሳይሆን እኔና ሲሳይ አጌና መክረን ጉዳዩ የቆየ ስለሆነ ሽፋን መስጠቱ ተገቢ ነው ብለን ስላላመንን እንጂ መረጃው ስህተት ስለነበር ወይን “ከሚኖሶታ ስለተላከ” አልነበረም፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የተዘጋ ፋይል እንደ አዲስ ከፍተህ ሚድያ ላይ ወጥተህ ልክ እኔ ሚኖሶታ ከነበሩ እንደነ ጃውር እይነት ግለሰቦች ዶኩመንት ተልኮልኝ (አንተም አይንህን በጨው አጥበህ ተመሳሳይ ቅጂ በፖስታ ደርሶኛል ብለሃል) የወይዘሮ ዳግማዊትን ስም ለማጠልሸት መንቀሳቀሴን እና ይሄንኑ ድርጊት ማስቆምህን አደባባይ ወጥተህ በድፍረት ተናገርክ። ደግነቱ እኔ እንደ እንተ የሴራ ፖለቲካ አይገባኝም፡፡ እንደ አንተ የሃስት ውንጀላ ከሆነ የግለሰቧን ስም ለማጠልሸት የተንቀሳቀስኩት የሃሰት ዶሴዎችን ይዤ በሌሎች ሰዎች እየተዘወርኩ ነበር። ይሁንና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተገኙ ዶኩመንቶችና እንዲሁም በውሳኔው ሂደት የተሳተፉ መምህራንና ሃላፊዎች በድጋሚ ያረጋገጡት ሃቅ ከአንተ ተረት ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣረሱ ናቸው። ይህም መረጃ በድምጽና በሰነድ ተዘጋጅቶ እጄ ላይ የሚገኝ ስለሆነ ለፍርድ ቤት ይቀርባል።
በመሆኑንም ይህንን የሃሰት ውንጀላ ለማስተካከል ፈቃደኛ ባለመሆንህ ፍርድ ቤት ጉዳዩን እንዲያየው ጠይቂያለሁ።
4ኛ/ ሌላው ከላይ ከተጠቀሰው ከወይዘሮ ዳግማዊት ጉዳይ ጋር በተያየዘ ያልከው አሳዛኝ ነገር እኔ አበበ ገላው የግለሰቧን ስም “በሃሰት ለማጥፋት” ተነሳስቼ የነበረው አማራ በመሆኗ እና ከንቲባ መሆን የሚገባው ኦሮሙማ ነው የሚል እምነት ስለነበርኝ ነው። በጣም ይገርማል! በጣምም ያሳዝናል!
አቶ ኤርሚያስ ሆይ! በጥቂቱም ቢሆን ባታውቀኝ ኖሮ እንዲህ አይነት አሳፋሪና ቆሻሻ ክስ ይዘህ አደባባይ መውጣትህ ባልገረመኝ ነበር። ይሄ በረከታዊ እኩይ ስሌትን ማንም አንተን የሚያውቅ ሰው ምን ውጤት ፈልገህ እንዲህ አይነት ቆሻሻ ክስ ይዘህ አደባባይ እንደወጣህ መገመት ይችላል። እኔ ማንም እንደሚያውቀው እንዲህ አይነት እርካሽና ዘረኛ ስሜትን የሚያስተናግድ ህሊናም ይሁን ልብ ስለሌለኝ ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ። በእርግጥ የወረወርከው ቆሻሻ ውዥንብርና ብዥታ ማፍጠሩ አልቀረም። በመሆኑም በተወለድኩበት ማህበረሰብ ላይ አድሎ እንደምፈጽም በአደባባይ ከታገልኩለትና ብዙ መስዋትነት ከከፈልኩለት የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ደግሞ ከአማራው  ህዝብ ጋር ለማቃቃር ዘግናኝ የሃሰት ውንጀላ ስላቀረብክና ለማረምም ፈቃደኛ ባለመሆንህ ይህንን እኩይ ጉዳይ ፍርድ ቤት እንዲያየው በክሴ ውስጥ አካትቼ አቅርቢያዋለሁ።
ዋነኛቹ ክሶች እነዚህ ሲሆኑ ከፍተኛ ሚስጥር ብዬ የያዝኩትን ጉዳይ ስላወጣህብኝ እንደጨነቀኝና ሌሎች ከክሶቼ ጭብጦች ጋር ተያያዥነት የሌላቸው ውሸቶችን አስጠርዘህና ሰበር ዜና አስርተህ በሚድያ ማስለቀቅህ ተጠያቂነት የሚባል ጉዳይ ስላለ ከአንተ አልፎ ለሚድያው ጥሩ አይሆንም። ብታምንም ባታምንም፣ ያንተ ያረጀና ያፈጀ ስታሊናዊ የውሸት የፕሮፓጋንዳ ስልት እኔ ላይ ፈጽሞ አይሰራም። የውሸትና የማዛባት ሱስና ልክፍት ዛሬ እንደምታየው አደባባይ ላይ እርቃን ያሰቀራል እንጂ ምንም ትርፍ አያስገኝም። አበበን በመንጋ አስጠላዋለሁ፣ አሰደብዋለሁ በሚል ቆሻሻ እሳቤ እራስህን ኪሳራ ውስጥ አትክተት። አንኳን አንተ ወያኔ ከእነ ሰራዊቱና ሙሉ ትጥቁ ብዙ አይነት የስም ማጥፋትን ጨምሮ ዛቻና ማዋከብ አድርጎ አልተሳካላትም፣ ወደ ፊትም ፈጽሞ አይሳካም።
እንግዲህ ከላይ የተጠቀሱት ክሶች እንደሚያሳዩት ሻቢያ፣ ኦሮሙማ፣ ግንቦት 7፣ ጸረ አዲስ አባቤ፣ የአብይ መንግስት ወይንም ሌሎች ሃይሎች በቅንጅት ሊሳተፉባቸው የሚችሉ ክሶች አይደሉም። ክስ የተመሰረተብህ የግለሰብን መብት በመጣስ የሃሰት መረጃ ሆን ብለህ ጉዳት ለማድረስ ለህዝብ በሚድያ አማካኝነት በማሰራጨትና ለማረምም ፍቃደኛ ባለመሆንህ ፍትሃዊ ያልሆነ ጥቃት በመሰንዘር ጉዳት ስላደረስክብኝ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም ተጨፈኑ ላሞኛችሁ የምትላቸውን በራሳቸው ፈቃድ እንደ መንጋ የሚነዱ የዋሆችን ለማጭበርበር መሆኑ ግልጽ ነው።
የካሳው ገንዘብ በዛብኝ ብለህም ብዙ አትጨነቅ። እንደምታውቀው እዚህ አሜሪካ እንኳን አንዲህ ከበድ ላለ ክስ ይቅርና ለተራ ጉዳይ በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ካሳ መጠየቁ የተለመደ ሲሆን ይህም የሚደረገው የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ለማሳየት ነው። ይህም ባይጠፋህም ልክ ክፈል ተብለህ ጉሮሮህ የታነቀ አታስመሰለው። ገና ተጀመረ እንጂ አላለቀም። ስለዚህም ተረጋጋ! ከሁሉም በላይ አስተውል።  የጥፋት ክብደት ለማሳየት ያህል እንጂ እንኳን በካሳ በብላሽም አበበ ገላው ከአንተም ይሁን ከሌላው ተከሳሽ አቶ ሊላይ ሃይለማሪያም ቤሳ ቤስቲ እንደማይፈልግ ልብህ ያውቀዋል። የሆነ ሆኖ “የቀድሞ” የህወሃት ሎሌዎች በአለቀ ሰአት ለምን እንደ ጠመዳችሁኝ ግራ ያጋባል? አንድ ወዳጄ “Once a Weyane, always a Weyane” ይል ነበር።
ለማንኛውም ለአንተም ይሁን ለእኔ ዋናው ጉዳይ እውነታን መቀበል እንጂ የእውነትን ፍላጻ በቀዳዳ የውሸት ጋሻ ለመመከት መውተርተር አይጠቅምም። ሁለታችንም የምንሟገተው አለቃህ በረከት ስሞን በቀጭን የስልክ መስመር ይዘውረው የነበረው አይነት ፍርድ ቤት ሳይሆን ለማንኛችንም ሳያዳላ ብያኔ የሚያሳልፍ ፍትህን የማያጓድል ፍርድ ቤት በመሆኑ ብዙ መርበትበትና ሰልፍ ማብዛት አያስፈልግም። ያንተን ውሸት እየጠጡ “ከጎንህ ነኝ” የሚሉ ምስኪኖች ግን ያሳዝናሉ። ለግዜው ነው እንጂ እነሱም የሚባንኑበት ጊዜው ደርሷል።
ለማጠቃለል ያህል፣ እንዳልከው በዚህ በምንኖርበት አገር “ያለ ገደብ” የመናገር ነጻነት አለ። ያለ ገደብ የምትለዋ ቃል ግን የሌሎችን መብት እስከ አልጣስክና እስከ አልተጋፋህ ድረስ ብቻ መሆኑን አብዛኛው ህግና ስርአት የሚያከብር ሰው ሁሉ ያውቃል። መብት እንዳለ ሁሉ ተጠያቂነትም አለ። አንተ ግን የአዲስ አበቤ አራዳ ነኝ ብትልም ገና ብዙ ነገር የተገለጠልህ አትመስልም። አስተሳሰብህ ሁሉ በዘመነ መለስና በረከት የተቸከለ መሆኑም ንግግርህም ይሁን ተግባርህ ምስክር ነው።
ህሊና ካለህ ለምን ብለህ እንድትጠይቅ የመጨረሻ ጥያቄ እንዳነሳ ይፈቀድልኝ። ከላይ የተዘረዘሩት እኔና አንተን ያወዛገቡን ጉዳዮች በሙሉ በትግል ሂደት እኔ የሰራሁዋቸውና ፋይሎቻቸው የተዘጋ ጉዳዮችን አደባባይ ይዘህ ወጥተህ በውሸት ክሶች እኔን ማጥቃቱና ተአማኒነት ለማሳጣት ስም ማጠልሸቱ ለምን አስፈለገ? አቶ ሊላይ አስገራሚ የስም ማጥፋት በከፈተብኝ ልክ በወሩ አንተ ደግሞ ከእሱ የባሱ የሃሰት ክሶችና ውንጀላዎችን ይዘህ ለምን አደባባይ ወጣህ? ያጋጣሚ ጉዳይ ነው ወይንስ ሌላ ያማናውቀው “ፓኬጅ” አለ? አገሬንና ወገኔን በብዙ ፈታኝ ውጣ ውረድ በማለፍ በሃቅ ማገልገሌ እንዴት አንተን በመሰለ “አገር ወዳድ” በሃሰት ውንጀላዎች ልጠቃ? መልሱን ለአንተው ትቼዋለሁ!
በተረፈ አንተም እኔም ያለንን እውነታ ሰብስበን ፍርድ ቤት መቅረባችን ተጠያቂነትን ለማህበረሰባችን ያስተማራል አንባገነናዊነትን ይገታል እንጂ ጉዳት የለውም። እንዳልከውም ልታስተምረኝና መቀጣጫ ልታደርገኝ አጋጣሚውን ለመጠቀም ቆርጠህ ስለተነሳህ ለመማርም ይሁን ቅጣቱን ለመቀበል ዝግጁ ነኝ። እስከዛው ግን እኩያህን ፈልግ። የከርሞ ሰው ይበለን!
Filed in: Amharic