አሳፍ ሀይሉ
– ኢትዮጵያ የብድር ክፍያዎቿ በአቅሟ ልክ እንዲስተካከሉላት እየወተወተች ነው።
– ተጨማሪ 2 ቢሊየን ዶላር ብድርም እንዲፈቀድላት በIMF ዙሪያ የተሰባሰቡ ቻይናና የአውሮፓ ሀያላን የተካተቱበትን የአበዳሪ ሀገራት እድር እየተማፀነች ነው።
– እስካሁን እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ ኢትዮጵያ በ30 ቢሊየን ዶላር ዕዳ ተዘፍቃለች።
– ዕዳቸውን በተቀመጠላቸው መርሀግብር ለመክፈል እንደማይችሉና ኢኮኖሚያቸው አዘቅት ውስጥ እንደሚገባ ከሚጠበቁትና፣ የአበዳሪዎቹን ዕድር እየተማፀኑ ካሉት 3 የአፍሪካ ደሀ ሀገሮች አንዷ ሆናለች።
– ከትናንትናው ዕለት ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአበዳሪዎቹ ጉባዔ ጋር ምሥጢራዊ የብድር ማራዘምና መልቀቅ ድርድር ላይ መሆናቸው ታውቋል።
– ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን፣ ኢንቬስትመንቷንና የዜጎቿን ደህንነት አውዳሚ የሆነ መጠነሰፊ ጦርነት እያካሄደች ነው።
– በሚሊየኖች ቁጥር ያላቸውንና በራሷ አቅም መመገብ የማትችላቸውን ረሀብተኛ ዜጎች እየፈጠረች ነው።
– ኢኮኖሚዋ አጠቃላይ fallout ውስጥ እንዳይገባ የብዙዎቹ አበዳሪዎች ሥጋት ነው።
– ወዘተ ወዘተ ወዘተ…
እነዚህ ሁሉ ዜናዎች ሶማሊያ ከመበታተኗ በፊት የተሰሙ ዜናዎች ናቸው። የአብይ አህመድ መንግሥት ሀገሪቱን ወደየት እየወሰዳት ነው? በአምልኮ የተጠመዱ ያገሪቱ ምሁራን ከእንቅልፋቸው መንቃት፣ ደፍረው ስለሀገሪቱ ከመንኮታኮት መውጫ መንገዶች መምከርና፣ አሁን በዚህ አሳሳቢ ወቅት ስለሚበጁት መፃዔ አስፈላጊ ተግባራት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማሰማት ያለባቸው ጊዜ የመሆኑ እውነታ ከብዙዎች በጭንቀት የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ናቸው!
በወያኔ-መራሹ የኢህአዴግ ማብቂያ ዘመን ያገሪቱን ኢኮኖሚ የሚመለከቱ እውነተኛና አስጊ መረጃዎች ሲወጡ ሲያስተባብሉ የነበሩ ባለሥልጣናት አሁንም በሥልጣናቸው መቀጠላቸውን ልብ ይሏል። በአሁኑ ወቅትም ሀገሪቱ ምዕራባውያኑን በልመና ደጅ እየጠናች፣ ከምዕራቡ ዓለም ጋር የምትቆራረጥበትን መንገድ የሚመክሩ ባለሥልጣናትና ምሁር ተብዬዎችም ተስተውለዋል። የብዙዎች ስጋት ኢኮኖሚው ጫናውን መቋቋም አቅቶት ሙሉ በሙሉ እንዳይፍረከረክ ነው።
እንግዲህ ዳግማዊ ሶማሊያነት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያችን ላይ ከፊታችን በቅርብ ርቀት የተደቀነ አስፈሪ አደጋ ሆኗል።
አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ወጪውና ተግባሩ ሁሉ ኢኮኖሚውን በቅጡ የተገነዘበ አይመስልም። አሊያም አውቆት ወደ አይቀሬው ውድቀት እየተንደረደረ ነው።
እውነታው ይኸው ነው። በቅርቡ ሁሉም ነገር ለሁሉም የሚታይ ስለሆነ ለብዙው የሆኗል-አልሆነም ሙግት ጊዜው የረፈደ ይመስላል።
እውነታው ይኸው ነው። በመንግሥት ሚዲያ የሚነዛው ዜና ሁሉ ግን ከዚህ እውነታ በተቃራኒው ነው። ምሳሌጨለመጥቀስ፦ ሰሞኑን በፋና ብሮድካስቲንግ የተላለፈ የመንግሥት መግለጫ በመላ ሀገሪቱ አቅም በላይ የሆነ የተከሰተ ረሀብ የለም ይላል።
ለማንኛውም መፍትሄው እውነታውን መካድ አይደለም። በቁጣ መወራጨት አይደለም። መሸበር አይደለም። ሳይቃጠል በቅጠል ነው።
ከምንም በላይ ለጦርነትም፣ ለኢኮኖሚው ቀውስም፣ ለረሀቡም፣ ኢንቬስትመንትን ለማስደንበሩም፣ ለብዙዎቹ ችግሮቻችን መንስዔ የሆነውን የፖለቲካ ችግር በሠላማዊ መንገድ አሁኑኑ ለመፍታት መጀመር ጊዜ የማይሰጠው እርምጃ መሆኑን ነው ዓለም ሁሉ ይህንን መገንዘብ እንዴት እንዳቃተን እጅጉን እየተገረመ እየወተወተን ያለው ነገር።
ፈጣሪ የተጋረደብንን ሁሉ ይግለፅልን!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ