>

ጦርነቱ ባስቸኳይ ይቁም!  (ከ ''ሰላም አሁኑኑ ማህበር'')

ጦርነቱ ባስቸኳይ ይቁም!

 ከ ”ሰላም አሁኑኑ ማህበር”


   

ባአገራችን ኢትዮጲያ በተለይም በሰሜን እንዲሁም በምእራብ፣ በደቡብ ያለው ጦርነት በቶሎ ባስቸኳይ መቆም አለበት። ባልፉት አስር ወራት የኢትዮጲያ ልጆች ደም በከንቱ እየፈሰሰ፣ የወጣቶች እምቡጥ ህይወት እየተቀጠፈ፣ የእናቶች እንባ እየረገፈ ነው። እንኳን በአገራችን ቀርቶ በሌሎች አገራት ይፈፀማል ያላልነውን እጅግ አስከፊ፣ አስነዋሪ፣ አሳፋሪ፣ አሳዛኝ ግፍና ጥፋቶች በእርስ በርስ ጦርነታችን ደርሷል። ከጠፋው ህይወት  የአካል ጉዳት በተጨማሪ በዜጎቻችን ስነ ልቦናን ለረዥም ግዜ የሚሰብር፣ ህይውታቸውን የሚረብሽ ሽብር እየተፈፀመ ነው።

በወንድማማቾች መካከል የሚፈሰው ደም፣ኢ-ሰበአዊ ጥፋት፣ ነውር፣ የንብርት ውድመትና ፣ የፕሮፕጋንዳ ጦርነት ወደ አስፈሪው ጨለማ እየወሰደን የአገራችንን ምሰሶና ማገር እየናደብን ነው። ይህ የእርስ በርስ መጠፋፋት ለማናችንም ሳይጠቅም የደሃውን ፣የምስኪኑን፣ ከፖለቲካውም ከስልጣን ፍትጊያው የሌለበትን ዜጎችን ህይወት እይቀጠፈ፣ እያፈናቀለ፣ ለርሃብ፣ እርዛትና  ሰቀቀን እየጣለ ነው።

በፖለቲከኞቻችን አለመግባባት የተፈጠርው ቀውስ፤ የህዝብ ፀብ እንድሆነ እይተነገርን የሚጠፋው ጥፋት ባስቸኳይ መቆም አለበት። ከዚህ የሚጠቀሙት መሳርያ የሚሸጡልን፣ የጦርነት የእልቂት ዜና እያስራጩ የሚቸረችሩትና ገንዘብ የሚለቅሙት፣ በንፁሃን ሞት የሚነግዱት  የስልጣን ነጋዴዎችን፤እንዲሁም የኛነታችን ሰላም፣ እድገት፣ ጥንካሬን የማይፈልጉ የውጭ ሓይሎችን ነው።

በአሁኑ ግዚያት ጦርነትን ስለማስቆም የሚሰማበት ግዜ ሳይሆን፤ በተፋላሚዎቹ ደጋፊዎች   የሚቀነቀነው ግፋ በለው፣ ቁረጠው፣ ግደለው፣ ማርከው፣ ደምስሰው አጥፋው የሚል የጥፋት ሽለላና መፍክር ነው። ለሞትና  ለጥፋት ገንዝብ የሚዋጣበት፣ ወጣቶች፣ ታዳጊ ልጆች ለሞት የሚሰለጥኑበት፣ ወደ ጦር ሜዳ የሚሄዱበት  ወቅት ነው። የሚፈሰው የራሳችን ወንድም እህቶቻችን ደም ነው። የምትደፈረው  የኛው እህታችን እናታችን ናቸው፤ የሚሞቱት ለጦረነት የሚማገዱት የኛው ልጆች ወንድም እህቶቻችን ናቸው።

የነበረንን ሁሉ አጥፍተን ምን ልንገንባ ነው? አገር ያለሰው እኮ አገር አይደለም::  አገር ማለት ሰው ሲኖርበት ነው። አገርን መውደድ ማለት የአገሩን ሰውን መውደድ ማለት ነው። ጦርነቱ በገፋ ቁጥር ወጣት ሴቶቻችን ባል አልባ፤ ህፃናት ወላጅ አልባ የሚያድርግ ፤ሲያድጉም ከፍተኛ የስነ-ልቦና  ጠባሳና ጉዳት የሚያደርስ ነው።

ይህ ጦርነት አሸናፊ የለውም። በጦርነቱ ተሸናፊዎች ሁላችንም ነን። ሟቾቹ ወንድሞቻችን እህቶቻችን፤የጠፋው የራሳችን ንብርት፣ ትምህርት ቤት፣ የጤና ተቋማት፣ የእምነት ቦታዎች እንዲሁም የኢኮኖሚ መሰርተ-ልማቶቻችን ናቸው። 

ከሰማይ እንደ እሳት የወረደው ክፉ መንፍስ በወንድሞቻችን ፖለቲክኞቻችን፣ መሪዎቻችን ልብ ገብቶ ለጦርነት፣ ለጭካኔ፣ ለሞት ፣ለጥፋት ሁላችንንም እየዳረገን ነው። የእምንት አባቶቻችን፣ ያገር ሽማግሌዎቻችን የተማሩ ቀና ሊቃውንቶቻችን ይህን ክፉ መንፍስ አገር ሲያፍርስ፣ ህዝብ ሲያጠፋ፣ አስንዋሪ ድርጊት ሲፈፀም ሊያውግዙ፣ ሊያስቆሙ ሊይስተምሩን  ይገባል። 

ጀግንነት ወንድም እህትን የቤት እንሰሳን  መግደል፣ መድፈር ማጥፋት ሳይሆን ጀግንነት ወንድም እህትን ከጥፋት ማዳን፤ ከጦረንት ማውጣት፣ አገርን ባህልን እምነትን ማዳን ነው። ለአገራችንና ለህዝባችን መኖር እንጂ መሞት የለብንም።  ”ላገራችን እንሞታለን” ሳይሆን ”ሰለ አገራችን  ስለ ህዝባችን ስንል እንኖራልን”  ነው ማለት ያለብን። ከሞትነውማ አገር ያለ ሰው ግኡዝ ባዶ መሬት ነው። 

በተቃራኒ ጎራ ቆማችሁ የምትገዳደሉ  ወንድም እህቶቻችን እባካችሁ ስለምትወዱት፣ ስለ ቆማችሁልት አላማ፣ ልጅ፣ ሰፈር፣ እምነት፣ ስትሉ ይሄንን ጦርነት አቁመን ችግራችንን ፣ ሃሳባችንን ያለጦርነት በሰላም በጠረጴዛ ዙሪያ እንወያይ። ዛሬ ጊዚያዊ ድል ብናግኝ ነገ ደግሞ ተሸናፊ ነንና ይህን የክፋት ድርጊት አቁመን በሰላም ጉዳዮቻችንን እንወያይ። ጦርነቱ ቢቀጥል ይብልጥ ሞት፣ ጥፋት ርሃብ፣ እርዛት፣ ለቅሶ ዋይታ ለመጪው ትውልድ ቂም በቀል  ማውርስ  ነው

በየትኛውም ወገን አመራር ላይ ያላችሁ የፖለቲካ ሹሞች፣ የጦር አበጋዞች፣የእምነት መሪዎች፣ ያገር ሽምግሌዎች፣ የሚዲያ ባለሞያዎች፣ ሙሁራኖች ሆይ፤ ይህ ጦርንት ሙሉ ለሙሉ ሳያጠፋን አገራችንን ሳያፈርስ  አሁኑኑ በቶሎ መቆም አለበት። የተዘጋው መንግድ ፣ የመብራት፣ የውሃ፣ ስልክ አገለግሎት መክፍት አለብት። ሰላማዊ የንግድ እንቅስቃሴ በቶሎ መጀመር አለበት። ባንኮች መክፈት አለባቸው።  ይህ የህዝብ አግልግሎት እንጂ የፖለቲክኞች ወይም ጦርኞች አግልግሎት አይደለም። በርሃብ፣ በምግብ እጦት እይተስቃዩ  ያሉ ወገኖቻችንን በቶሎ የምግብ መድሃኒት እርዳት  መድርስ አለበት።

ማእክላዊ መንግስትና ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ሆደ ሰፊ ሆኖ ስለ አገርና ህዝብ ህልውና ሲባል ጦርነቱን ለማቆም ታላቁን ድርሻ መወጣት አለበት። በፖለቲካ አምለካከታቸውም ወይም ተያያዥ ድርጊታቸው የታሰሩ ወገኖችን መልቀቅና  ለውይይት ማብቃት ይጠብቅበታል። ሌሎችም ባላንጣ ጦረኞች ለሰላም  ዝግጁ መሆን አለባችሁ። ሁሉንም ወገን ያሳተፈ ሰላማዊ ውይይት፣መግባባት መድርግ አለበት። አገራችሁን ህዝባችሁን የምትወዱ ወገኖች ሁሉ፤  አገርና ህዝብ ከስልጣናችህ ይበልጣሉና ስልጣናችሁን አጋሩ፤  አካፍሉ፤ ሁሉንም ለሚያስማማ ውሳኔ ተገዢ ሁኑ።

ተፋላሚ ወገኖች ለሰላም ጥሪ እምቢ ካሉ የኢትዮጲያ ህዝብ ጦርነት በቃኝ ማለት አለበት። ለርስ በርስ ጦርነት ለየትኛውም ወገን ወታደር ላለመሆን፣ ገንዝብ፣ስንቅ ላለመስጠት መቁርጥ አለበት። ጦርነቱ ይቁም ብሎ ሰላማዊ ሰልፍ፣ ፀሎት፣ ፆም ማድርግ ያስፍልጋል።

በመደብኛው መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም በማህብራዊ ሚዲያ  የምትሰሩ እንዲሁም ብዙ ተከታይ ያላችሁ ወገኖች፣ ተፅኖ ፈጣሪዎች ስለ አገራችሁና ስለ ህዝቡ ስትሉ የጦርነት ቅስቀሳና አፈቀላጤ ከመሆን ታቀቡ፤ ስለ ስላም አስፍላጊነት ና ጦርነቱ በቶሎ የሚቆምበትን ስራ እንድትሰሩ በእግዚአብሔርና በምትወዱት እንማፀናችኋልን። ስራችሁ የሚምዝግብና ሪክርድ የሚሆን ስልሚሆን ከወደፊት ተጠያቂነት ራሳችሁንም አድኑ። ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይብልጣልና። 

ራሳችንን ግጭት ራሳችን እናቁመው። የውጭ ሃይላት ሁሌም የራሳቸው ድብቅ ፍልጎት አለና፤ እኛ ከሰላም ውጪ የተደበቀ ፍላጎት የሌለን ኢትዮጲያንና ወዳጆች ጦርነትን በቃ እንበል። ከእንግዲህ  ልጆቻችን ወደ ት/ቤት፣ ዪንቨርስቲ እንጂ ወደ ጦር ካንፕ  ወይም ጦር ሜዳ መሄድ ያቁሙ።

በመካከልችን ያልውን ልዩነት፣ ያልጦርነት በሰላም ተነጋግርን እንፍታ። አንት ትብስ አንቺ ትብስ ተባብለን፣ ግምሽ መንግድ እየትጓዝን ፣ ሰጥቶ በመቀበል ዳር እንዳርሰው። በዚህ ሃሳብ የምንስማማ ወገኖች ሁሉ እንዲሁም  ትውልደ ኢትዮጲያን ፤ ሙሁራን፣ ዜጎች፣ በሚቅጥሉት ሶስት  ወራት  ከሁሉ  አስቀድመን ጦርነቱን እንዲቆም የምንችለውን ሁሉ እናድርግ። የጦርንቱ አጋፋሪዎቹ ላይ ጫና በማድርግ  ይህን የጥፋት ጦርነት እናስቁም። የእምነት አባቶች፣ያገር ሽማግሌዎች፣ ሙሁራኖች  የሚዲያ ሰዎች ስለ ሰላም፣ስለ መግባባት ስንል እጅ ለእጅ ተያይዘን ወድጥፋት እየሄደች ያለችውን አገራችንን ህዝባችንን  እናድን።

በጦርነቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑ  ብልፅግና ፓርቲ/ ማእክላዊ መንግስት፣ ሕወሃት/የትግራይ ክልል መንግስት፣ የኦርሞ ነፃንት ግንባር/ሰራዊት/ ”ሸኔ” ተብሎ የሚጠራውን ጨምሮ፣ የአማራ ና የአፋር ክልል መንግስታት፣ ሊሎች ጦርኞችን ሁሉ ጨምሮ እንዲሁም የኤርትራ መንግስት ላይ ወንድማዊ ጫና በማድርግ ይህን  እልቂት ቶሎ እናስቁም። ራሳችን ለራሳችን በምናድርገው ይህ መልካም ድርጊት አጋር የውጭ አገር መንግስታት ወይም ድርጅቶች  እርዳት ቢታከልበት መልካም ቢሆንም እነዚህ አገራት ወይም ድርጅቶች  ግን ምን አቅጣጫ መሆን እንዳለበት የምንወስነው ግን ራስችን ብቻ መሆን አለብን።

ይህን ታላቅ ጉዳይ ከዳር ለማድርስ በዚህ ሃሳብ የምንስማማ ወገኖች  ወግንተኝነት ሳይድርብን፣ አላማችን ጦርንቱን ባስቸኳይ ማስቆምና ወንድሞቻችንን በሰላምዊ መንግድ ችግራቸውን እንዲፍቱ ማመቻችት ስለሆነ በዚህ  አላማ የምታምኑና በሙሉ ፍላጎትና  ያልክፍያ፣ በችሎታችሁ በግዜችሁ፣ በገንዝባችሁ አስተዋፆ ለማድርግ የህሊናና የአገር እዳ ያለብን ወግኖች   እየተርዳዳን   “ጦርንቱ ይቁም፤  ሰላም አሁኑኑ” በሚል መሪ ቃል በቅርቡ በሚደርግ የማህበራዊ መድርክ ጥሪ ተስባስብን ይህን ጦርነት የምናስቆምበትን መከርን ወደ ወንድሞቻችን፣ ወደ ጦርንቱ አጋፋሪዎች ቀርበን ለመማፀን ብሎም  ህዝባችን  ጋ ለመድርስ እንችል ዘንድ ጥሪ እናድርጋለንና  በቅርቡ ለሚደርግ ጥሪ ነቅተው ይጠብቁ። 

ለዚህ መልካም ተግባር ለመሳተፍ የምትፈልጉ ወገኖች በምን መልክ ልትደግፉ እንድምትችሉ በመግልጽ በዚህ e-mail ይላኩልን።  Peacenowethiopia@gmail.com

 

እግዚአብሔር ይርዳን።

Filed in: Amharic