>

.ለመሞት መኖር ወይስ ለመኖር መሞት...?!?  (ካሳሁን ይልማ)

ለመሞት መኖር ወይስ ለመኖር መሞት…?!?

                 ካሳሁን ይልማ

ጦርነት ውስጥ ነን። ዜጎች እንደቅጠል እየረገፉ ነው። በአሰቃቂ ሁኔታ የሚጠፋው የስው ልጅ ሕይወት ብቻ አይደለም።የሚቃጠለው ጊዜ፣ የሚወድመው ንብረት ብቻ አይደለም። በዚህ ሁሉ እልቂት የሚገነባው የመጠፋፋትና የበቀል ታሪክ ነው። ትውልድ ረግፎና ንብረት ወድሞ የሚገኝ ትርፍ ቢኖር በበቀል ደም የተነከረ ያው የተለመደው፣ ለዘመናት አብሮን የኖረው ድኽነት፣አርዛትና ሰቆቃ ነው።
ታዲያ ውጤቱ ይኼ እንደሚሆን እየታወቀ ወዴት ተሸጋገረ?
የጦርነቱ መንስኤ ኢህአዴግና ኢህአዴግ ናቸው።የዚህ ሁሉ ቀውስ ምንጭ በራሱ የጨዋታ ሕግና ሜዳ የተሸነፈው ህወሓት-ኢህአዴግና አሸናፊው ኦህዴድ-ኢህአዴግ ናቸው።ህወሓት አገልጋዮቹ ከነበሩት ኦህዴድ፣ ብአዴንና ደሕዴን እኩል መሆንን የባሪያ አገልጋይ እንደመሆን ቆጠረው።የነዚህ ድርጅቶች የስልጣን ሽኩቻ ለሁለት ዓመታት የብሔርተኛና የዘውጌ ብሔርተኛነት ካባ ለብሶ ወደ  “ተነስ፣ታጠቅ ዝመት” አዙሪት ተመለስን። ከ17 ዓመታት የጫካ ወንበዴነት ተነስቶ  ወደ 27 ዓመታት የቤተመንግሥት ወንበዴነት የተሽጋገረው ህወሓት ተመልሶ የጫካ ወንበዴ የሚለውን ቅጥያውን ተጎናጽፎ ገደል ለገደል እየተሹለከለከ ሕዝቡናን ሀገሪቱን አብሮ ገደል ሊጨምር ቆርጧል።በዚህም አሸባሪ የሚል መለያም ተሸልሟል።ነውም። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሁለት ጊዜ የወጋን የውጪ ወራሪው ፋሺስት ጣሊያን ነው። ኢትዮጵያን ሦስት ጊዜ በጠላትነት የወጋት ቡድን ቢኖር የውስጡ ጠላት ህወሓት ብቻ ነው። በሽፍትነት ዘመናቸው፣ ስልጣን ተቆና’ጠውና ከስልጣን ወርደው ኢትዮጵያን በጠላትነት የወጋት፣ከጠላቶቿ ሁሉ የተባበረ ቡድን የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ነኝ የሚለው ትህነግ ነው።
ትህነግ በአንድ በኩል “ትግሌ ከአቢይ አሕመድ፣አማራና ኤርትራ ጋር ነው” እያለ የሚያጠቃውና የሚገድለው መከላከያ ሠራዊቱን፣የአማራና፣አፋርን ሰላማዊ ሕዝብ ስለመሆኑ በድርጊቱ አስመስክሯል። በተጨማሪ የአማፂው ቡድን የፕሮፓጋንዳና ዋና የፖለቲካ ፊታውራሪዎች ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ፈርሳና ፈራርሳ ማየት እንደሚፈልጉ ደጋግመው በይፋ ገልጸዋል።በተግባርም በየእለቱ እያሳዩ ነው።ይህን ሀገር የማፍረስ እብሪትና ተልእኮ ለመከላከል በሚወሰደው እርምጃ በትግራይ የሚገኙ ሰላማዊ ዜጎቻችን ዋነኛ የጉዳት ሰለባ ለመሆናቸው ምርምር አይፈልግም።ስለዚህ፦
ሠላም፣ ድርድር‼
ድርድር በህወሓት መዝገበ ቃላት ምን ትርጉም አለው? ህወሓት በታሪኩ ድርድር የሚለውን የሠላም መንገድ የሚጠቀመው ለማዘናጊያና ኃይል መሰብሰቢያ አሊያም የተቀናቃኙን ግብአተ መሬት ለመፈጸም የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኑን ሲያረጋግጥ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል።ለዚህ 3 የታሪክ ኹነቶችን ለማስረጃ ማንሳት ይቻላል። ደርግ ውስጡ በጥቅመኛ ሀገር ሻጮች እየተፈረካከሰ መሆኑን ሲረዱ ሥርዓቱን ለማዘናጋት እነ አቶ መለስ ዜናዊና ስዩም መስፍን (ሁለቱም ሞተዋል) የወንበዴነት ዘመናቸው አብቅቶ በአሜሪካ፣ሱዳን፣ ግብጽና ሊቢያ የሚታገዘው ትግላቸው 4ኪሎ ሊያደርሳቸው መሆኑን ሲያወቁ በእነ ዶክተር አሻግሬ ይግለጡ የሚመራውን የደርግ መንግሥት ልኡክ ሮምና ለንደን ላይ እያገኙ ለይምሰል ለሠላም ይደራደሩ ነበር። ዶክተር አሻግሬ ይህን ጠቅለል አድርገው ሲያስቀምጡት  “የትህነግ አመራርም ሆነ አባላት ያላቸው የብልኽነት አመራር ሳይሆን የብልጠት አመራር ነው።ብልጠት ማለት ብልኽነት አይደለም። ብልጠት ከማጭበርበር በፊት የሚመጣ እንቅስቃሴ ነው” ብለዋል። ሁለተኛው፣ ከ100ሺህ በላይ ዜጎች ካስጨረሰው ጋሪዮሻዊው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማግስት ባደመን በምስኪን ዜጎች ደም በመቆጣጣሩ የተኩራራው ህወሓት በድርድርም እረታለሁ በሚል የአሸናፊነት ትምክህት አልጀርስ ላይ ከሻእቢያ ጋር ተደራድሯል። የወቅቱ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ስዩም መስፍን ዓይን ባወጣ ውሸት የቦርደር ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ ወሰነ ብለው በሕዝብ አደባባይ ቢያስጨፍሩም እውነቱ በተቃራኒው ሆኗል።የኮሚሽኑ አባላት የተባበሩት መንግሥታት፣አፍሪካ ህብረት፣አውሮፓ ህብረትና አልጄሪያ ባደመ የኤርትራ እንዲሆን ወስነዋል። የመጨረሻው የታሪክ ምስክር፣ህወሓት ከኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ጋር ያደረገው ድርድር ነው።ትህነግ ከኦብነግ ጋር የእንደራደር ጥያቄ አቅርቦ፣ የኦብነግ አመራሮችም አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተው ሠለም ለማምጣት ጅጅጋ ላይ ተገኙ። የትህነግ ወጥመድ ውስጥ በቀላሉ ገቡ። ሁሉም የኦብነግ ተደራዳሪዎች ጭካኔያዊ ግድያ ተፈጸመባቸው። የኦብነግ ፖለቲካዊ የዋህነት በዚህ ሰቅጣች ግድያ ብቻ አላበቃም። በ2004 ዓ.ም ህወሓትና ኦብነግ በኬንያ ሸምጋይነት ናይሮቢ ላይ ለ3ኛ ጊዜ ለድርድር ሊገናኙ ቀጠሮ ይዘዋል። ድርድሩ እንደመጀመሪያው ጅጅጋ ላይ አይደለም።የኦብነግ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ስሉብ አሕመድና ዓሊ ሁሴን የድርጅታቸውን ነጥቦች አሰናድተው የድርድሩን ቀንና ሰዓት  እየተጠባበቁ እያለ በንጋታው ራሳቸውን ማእከላዊ እስርቤት አገኙት። ሁለቱም አመራሮች በክፋት ስሩ ህወሓት ማዘናጊያ በሙስና በተጨማለቀው የኬንያ ደኅንነት ሰዎች ተመቻችቶ በወያኔ ደኅንነቶች ከናይሮቢ ታፍነው ተወሰዱ።ከህወሓት ጋር ድርድር ማለት በሬ ከአራጁ እንደሚውለው ነው። ለበለጠ መረጃ ደግሞ ኦነግን መጠየቅ ነው።
➢ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዴት ይታመኑ??‼
ዘመቻው ለጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ የሚደረግ መስዋእተነት አይደለም። ጠቅላዩ በኢህአዴግ የውስጥ “ለውጥ” ወደ ስልጣን በድንገት በመጡ ማግስት ጀምሮ ከአንደበተ ርቱእነታቸው በተጨማሪ ብዙ ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች ተወስደዋል። የፖለቲካ አስረኞችን መፍታት፣ ሽብርተኛ ተብለው ሀገራቸው እንዳይገቡ የታገዱ በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችና በርካታ ድርጅቶች ወደ እናት ሀገርቸው እንዲገቡ በር መክፈትና በክርስትና አና በእስልምና ኃይማኖቶች ውስጥ የነበሩትን መከፋፈሎች በስምምነት እንዲቋጩ ከፍተኛ የአስታራቂነት ሚና ተጫውተዋል።
ይሁን እንጂ በፍጥነት የሠላም ኖቤል ተሸላሚ የሆኑት መሪ የኢኒጂነር ስመኘው በቀለ መገደል፣የአብዮት አደባባዩ ፍንዳታ፣የቡራዩ የዘር ማፈናቅል፣የማያቋርጠው የመተከል የዘር ጭፍጨፋ እየመጣባቸው ላለው ሀገራዊ ግጭቶችና ቀውሶች በቂ ምልክት ሊሆናቸው አልቻለም። ከዚያ የአማራ ክልል አመራሮች ግድያ፣የሻሸመኔ ንዳድ፣የአጣዬና የወለጋና የጌዴኦ የዘር ጭፍጨፋና ማፈናቀል፣የታዋቂውና ተወዳጁ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተከታተሉ።
እነዚህ ተከታታይ ወንጀሎች ለበርካታ የሴራ ትንተና መፍለቅ መንስኤ ሆኑ። በመንግሥታቸው ላይ ያለውን እምነት እየሸረሸረው መጣ።የፖለቲካ አጋራቸው አቶ ለማ መገርሳ በድንገት ከጎናቸው መሰወርና ኋላም ተቀናቃኝ ሆነ መገኘታቸው ከተከማቹት መሰረታዊ ችግሮች ጋር ተደማምሮ መቀሌ ላይ ኃይሉን እያሰባሰበ ለነበረው ስልጣንና ዝርፊያ አይጠግቤው አንጋፋ የወያኔ ስብስብ የልብ-ልብ እየሰጠ መጣ። የደርግ ባላስልጣን የነበሩት ሌተናል ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታ ለመንግሥታቸው ዋናኛ ውድቅት “ለብዙ ዓመታት ተከማችተው በወቅቱና በጊዜው መፈታት ሲገባቸው በንቀትና በአክራሪነት ሳይፈቱ የቀሩ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ጉዳዮች ትልቁን ሚና ተጫውተዋል። ወቅታዊና ዓለምአቀፋዊ ሁኔታዎችም ውድቀቱን አፋጥነውታል።” ሲሉ ገልጸዋል።
ወቅታዊና ዓለምአቀፋዊ ሁኔታዎች‼
በዚህ በትረ መንግሥትም በሦስት ዓመታት ውስጥ የተከማቹት የውስጥ ችግሮች ሳይፈቱ ወቅታዊው ዓለምአቀፍ ሁኔታ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃራኒ የቆመ ይመስላል። “ምርጫ በሰላማዊ መንገድ ከተከሄደና ከተጠናቀቀ የምእራቡ ዓለም መንግሥታት ሳይወዱ በግድ እውቅና ይሰጣሉ”የሚል መላምት አስቀድሞ የነበረ ቢሆንም በአስደንጋጭ መልኩ መንግሥታቱ ምርጫው እንዳይካሄድ ጫና ከማሳደር አልፈው የቀውስ ትንበያ ማድረጋቸው ብዙዎችን አስገርሞ ነበር።እንዲያም ሆኖ ምርጫው በጦርነት መካከል ተካሄዶም ብልጽግና ፓርቲ ማሸነፉ ሲታወጅ የአቋም ለውጥ ያደርጋሉ ቢባልም ምእራባዊያኑ ጫናቸውን ይበልጥ ማጠናከር መርጠዋል። ይኼም ኢትዮጵያን ወደ እርስበርስ ጦርነት ከመራት ህወሓት ጎን በግላጭ ቆመው እስከመታየት ደርሰዋል።
በህወሓት የ27 ዓመታት የጭቆና እና አፈና ዘመን በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በአስርና ሃያ ሺህዎች በነቂስ ወጥተው በዲሲ በኒውዮርክና ለንደን የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደርጉ ተራ የሚባሉ ሚዲያዎች ሳይቀር የዜና ሽፋን ሳይሰጡ የዜጎች ብሶት ለአሜሪካ፣እንግሊዝ፣ለተባበሩት መንግሥታት የቁራ ጩኸት ሆኖ አልፏል። አሁን ግን ሰላሳ የማይሞሉ የወያኔ ደጋፊዎች ሰልፍ ሲወጡ ከሲ.ኤን.ኤን፣ ኒውዮርክ ታይምስ እስከ ቢቢሲ እንዲሁም ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ እስከ አውሮጳ ህብረት የሽብርተኛውን ድምፅ ያስተጋባሉ። ባልዋሉበት የአይን እማኝ ሆነው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን ወንጀለኛ አድርገው ይጽፋሉ፣ ይወተውታሉ፣ ያስጠነቅቃሉ።
የብልጽግና አስተዳደርም ልክ እንደቀድሞው ህወሓት-ኢህአዴግ ስራአት ሁሉ ካድሬ መር በመሆኑ የተፈጠረው የዲፕሎማሲ ኪሳራ እንዳለ ሆኖ ሀገሪቱ ለደረሰችበት ውጫዊ ጫና  ዋና መንስኤ የገዛ ውሃችን ነው። የአባይ ግድብን እንዳንገድብና፣ዘለዓለማችንን የፈረንጅ ምንደኛ ሆነን እንድንቀር መፈለጉ ወያኔዎች ያለሐሳብ የጦር መሳሪያ በገፍ እንዲቀርብላቸው፣የቴክኖሎጂ እገዛና ስልጠና ከጎረቤት እንዲያገኙ ወቅታዊው የፖለቲካ ሁኔታ አመቻችቶላቸዋል።ወያኔዎች ሽንፈት ሲከናነቡ ስለ ሰብአዊነት ሲሰብኩ የነበሩት ተቆርቋሪ  ምእራባዊያን የአሸባሪው ቡድን በአማራና አፋር ክልል ኢትዮጵያዊያንን በጅምላ እየገደለ፣እየዘረፈና እያወደመ ወረዳዎችን ሲቆጣጠር በቀን ሁለቴ ሳይቀር ዓለምአቀፍ ሚዲያዎች ሽፋን ከመስጠት አለፈው ወደ አዲስ አበባ እየገሰገሱ መሆናቸውን ሲዘግቡ በኢትዮጵያ ላይ ምን እየተካሄደ እንዳለ ለመገንዘብ በቂ ምልክት ነው።
ታዲያ አሁን ጦርነቱ የማን ነው??‼
ወያኔዎች ጥቅምት 24፣2013 ዓ.ም የሰሜን እዝ ላይ፣ የሽብርተኛው ቡድን ዋና መሪ የነበሩት ሴኮ ቱሬ ጌታቸው እንዳሉት የወሰዱት “መብረቃዊ ጥቃት” ከዚያም ወደጎንደርና ባህርዳር ያስወነጨፉት ሚሳኤሎች ጥቃት፤ በተለይም ህዳር 1፣ 2013 ዓ.ም ንጋት ላይ የትግራይ ልዩ ኃይል የአማራ ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎችንና የቀን ሠራተኞችን ከሌሊቱ 9 ሰዓት ጀምሮ በየቤታቸው እየገባ በግፍ መጨፍጨፉ እስከዛሬ ለዘለቀው የንጹሐን እልቂት መባባስና ቂም-በቀል ያፈራው ሠላም መጥፋት ማፋፋሚያ እሳት ሆኗል።
ይህ ግፍ አልበቃ ያለው ትህነግ ገና ከመሰረተ ፅንሰቱም መለያው የሆነውን ፀረ-ኢትዮጵያ ቅስቅሳውን ለመጀመር ጊዜ አልወሰደበትም። ሰንደቋን መሬት እየጎተቱ “ኢትዮጵያ ትውደም” እያሉ የኮሚኒስት ቀለማቸውን ከፍ አድርገው እያውለበለቡ ጦርነቱ ሕዝብ ከሕዝብ እንዲሆን ቅስቀሳ ማድረግን መርጠዋል።እነዚህ አበይት ምክንያቶች ተደማምረው መላውን ኢትዮጵያ አስቆጥተዋል።ዜጎች ለህልውናቸው ጨርቄን ማቄን ሳይሉ በነቂስ እንዲነሱ፣ ሕይወት ለመስጠት እንዲዘምቱ አስገድደዋል።
በተለይ በአማራና አፋር ክልል ወያኔዎች የፈጸሙት ግልጽ የዘር ጭፍጨፋና ውድመት ቡድኑ በእርገጥም ለትግራይ ሕዝብ የቆመ ሳይሆን የትግራይን ወጣት ከእናቶቻቸው እየነጠቀ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እናት ሀገርን የሚያደማ ሆኖ በተግባር መታየቱ የአማፂ ቡድኑን የነውር ታሪክ አላምን ብለው ሁለት ልብ የያዙና አውቀው ከተኙበት አልነቃ ያሉትን የህወሓት አስተዛዛኞችን ሳይቀር ያባነነ ሆኗል።
ስለዚህ ጦርነቱ የህወሓትና የኦዲፒ ብልጽግና የስልጣን ትግል መሆኑ ቀርቶ በኢትዮጵያ አፍራሽና በኢትዮጵያ አዳኝ መካከል እንዲሆን ተገዷል።ማለትም በተዘዋዋሪ ሕዝቡ ሀገር ለማዳን ከመንግሥት ጎን ተሰልፏል።ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ከ6 ዋራት በፊት “ጁንታውን” ድል እንደነሱ በኩራት መናገራቸውን ሕዝቡ ሳይዘነጋ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች እየተመመ ለመሙላት አላመነታም።ህወሓት ሱዳንና ቆላ ተምቤን ላይ በሙሉ ኃይሉ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጀ “ከSituation Room በቀጥታ የምናየው ጁንታ ተደመሰሰ” ተብሎ ትኩረቱ ችግኝ  ተከላ ላይ ሆኖ እንደነበር ይታወሳል።
➢አሻጥሩስ??‼
ክህደት የተፈጸመበት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ህወሓትን ድል ከነሳበት ትግራይ ምድር በአንድ ጊዜ ውልቅ ብሎ ለምን ወጣ? በዚያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የውጪ መንግሥታት የእርዳታ ኮሪደር ይከፈትልን የሚሉት ድርግን በጣሉበት የተለመደ መንገድ በእርዳታ ስም ጦር መሳሪያ ሊያስገቡ ነው። ይኼን አንፈቅድም!” የሚል መልእክት በቃለምልልስ ባስተላለፉ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ “ትግራይን የለቀቅነው ገበሬው እንዲያመርት፣ሠራዊቱ ከኋላው ተወጋ” በሚል አደናጋሪ ውሳኔው መነገሩ ብዙ ጥርጣሬዎችን አስነስቷል። በይፋ ያልተነገረ ወይም ሊነገር ያልተፈልገ ብዙ ምስጢር ይኖራል። ነገርግን ሕይወቱን ሳይሳሳ ለሀገሩ በሚገብረው የኢትዮጵያ ወታደር ላይ የሚፈጸም ደባ የተለመደ ነው። በወታደራዊ ብቃትም ሆነ በግዝፈት ለመላው አፍሪካ የሚያስፈራውን አብዮታዊ ሠራዊት ለሽፍቶቹ ሀገር ገንጣዮች ሲሳይ እንዲሆን ያደረጉት የደርግ ከፍተኛ አዛዦችና መኮንኖች እንደንበሩ ይታወሳል።በዝሆኖቹ ፀብ በተነሳው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ሠራዊት ለትርጉም አልባ ግብ እንዲማገድ የተደረገው በእብሪተኞ የጥቅም አጀንዳና ኃላፊነት በማይሰማቸው ከፍተኛ የጦርና የፖለቲካ አመራሮች ምክንያት ነበር። አሁን ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ ከ1970ዎቹ ጋር ይመሳሰላል። ከተማሪዎች አመፅና ዘውዳዊው ስራአት መገርሰስ ማግስት ሀገር እንዴት አንደሚመራ በማያውቁ የተለየዩ የፖለቲካ ቡድኖች መካከል ስክነት ጠፍቶና አንጃ ተፈጥሮ ለስልጣን ሲቫኮቱ ቀውሶቹ ተባብሰው የሲያድ ባሬን ሶማሊያ የልብ-ልብ ሰጥቶ ኢትዮጵያን በቀላሉ አንዲወርራት በር ከፍቷል። ዛሬም ሱዳን የውስጥ ውጥንቅጣችንን ተመልክታ ድንበራችንን ደፍራ ከመግባት አልፋ ልክ እንደያኔው የወያኔዎች የደኅንነት-መጠለያ (Safe Haven) ሆናለች።መሸሻ፣ መሸሸጊያ፣ማሰልጠኛ፣መወንጨፊያ ናት። ሶማሊያም ቢሆን ለወረራዋ ኦአልማና ግብ የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባርን ተጠቅማለች።ልዩነቱ ግብጽና ሱዳን ሙሉ ተልኳቸውን ለመፈጸም የተዘጋጀ የውስጥ ጠላት በቀላሉ አግኝተዋል። እነሱ መስዋእት ሳይሆኑ በትግራይ ደኻ ወጣቶች ሞት ጠላታቸው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሌት-ተቀን እየተጉ ነው።
የሲያድ ባሬን ወረራ ህወሓት፣ሻእቢያ ኦነግና መኢሶን ደግፈዋል። ደርግን ይጥልልኛል፣ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል ብሂል ለኢትዮጵያ ቆመናል የሚሉትን እነ ኢህአፓን ጭምር የሀገር መበተን እንዳያሳስባቸው የስልጣን ጥም አሳውሯቸው ነበር። ዛሬ በሚካሄደው ጦርነትም በውስጥና በውጪ ኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠው አደጋ የማያሳስባቸው የስልጣን ጥመኞች በሕዝባቸው አስከሬን ላይ ተረማምደውም ቢሆን 4 ኪሎ ለመግባት የሚከጅሉ ቡድኖች አሉ። በደርግ ዘመን ለገንዘብ ብለውና፣በእርስበርስ የስልጣን ሽኩቻ አልህ ተጋብተው የኢትዮጵያን ሠራዊት ጉድጓድ ምሰው ለወንበዴዎች አሳልፈው እንደሰጡት ጀነራሎች  አሁንም በሰሜን ተራሮች ላይ ጀግናው ወታደር ላይ አሻጥር የሚሰሩ አይጠፉም አሉ። እነዚህ ቅጥረኞች መጨራሻቸው እንደ ደርግ ባለስልጣናትና ወታደራዊ አዛዦች እንደሚሆን ታሪክ አስታዋሽ ይፈልጋሉ።እጣ ፈንታቸው በውርደት አስርቤት መማቀቅና ለማኝ ሊያደረጉት እንዳሰቡት ሠራዊት ለማኝ እንደሚሆኑ ከሕይወት ልምዳቸው ሀቁን ያካፈሉንና ለፈጸሙት ወንጀል ተፀጽተው “በማወቅ፣ በድፍረት፣ባለማወቅና በስህተት ለተፈጸሙት ደግሞ ሙሉ ኃላፊነትን በመውሰድ፣ በበኩሌ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እጠይቃለሁ።” የሚለውን የሌተናል ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታን ንሰሐ ማስታወስ ያስፈልጋል። ፍሰሐ ሠራዊቱ ላይ ስለተፈጸመው ሸፍጥ ሲያስታውሱ “አንዳንድ ጄነራሎች ‘ደርግ እንዲወድቅ የሚቻለንን ሁሉ ያህል ጥረት አድርገናል’ አያሉ በእስር በነበርንበት ጊዜ ሲናገሩ ሰምቻለሁ” ብለዋል በመጽሐፋቸው አብዮቱና ትዝታዬ። “እነሱ ከውድቀቱ የሚያመልጡ ይመስል!” ሲሉም የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ያክላሉ።
ስለዚህ ሀገር ለማፍረስ ሲል ለመሞት መኖር ከመረጠው ህወሓት ይልቅ ሀገሩን ከመፍረስ ለማዳን ሲል ለመኖር ሲል መሞትን ከመረጠው ሕዝብ ጎን መሆን ይበጃል።
Filed in: Amharic