አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ
የኢትዮጵያ መንግስት በውስጥ ጉዳዬ ላይ ገብተዋል፣ ከተፈቀደላቸው ዓላማና ተግባር ውጭ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል ያላቸውን 7 በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ግከለሰቦችን በ72 ሰአታት ውስጥ የኢትዮጵያን ግዛት ለቀው እንዲወጡ ሲል አዟል።
ይህንን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ “በኢትዮጵያ ውሳኔ ደንግጫለሁ” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ በአሸባሪው ህወሓት በርካታ ንጹሀን ሲገደሉ፣ ከ400 በላይ መኪናዎች በአሸባሪው ድርጅት ታግተው ሲቀሩ፤ አሸባሪው ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራሁ ነው ሲል ድምጻቸውን አጥፍተው አሁን ላይ መንግስት የአገር ሉአላዊነትን በተጋፉ የድርጅቶቱ ሰራተኞች ላይ እርምጃ ሲወስድ ደንግጫለሁ ማለታቸው ተገቢነት የጎደለው ነው ሲሉ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ተችተዋል።
አቶ አንዳርጋቸው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት አስተያየት፤ “አገር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚደነግጡት መቼ መቼ ነው?” ሲሉ ትዝብታቸውን ገልጸዋል።
አቶ አንዳርጋቸው፤ አሸባሪው ህወሓት በአንድ አገር ሉዓላዊ ሰራዊት ላይ የክልል መንግስት ጥቃት ፈጽሞ ንጹሀን ዩኒፎርም የለበሱ ወንድና ሴት ወታደሮች ሲጨፈጨፉ አንቶኒዮ ጉተሬዝ መደንገጣቸውን አልነገሩንም ብለዋል።
አሸባሪው ድርጅት ባደራጃቸው ገዳይ ቡድኖች ከ1000 በላይ ንጹሀን የአማራ ብሄር ተወላጆች በማይካድራ ሲጨፈጨፉ ዋና ጸሀፊው እንደደነገጡ አልነገሩንም ያሉት አቶ አንዳርጋቸው፤ በአፋር ጋሊኮማ የራሳቸው ድርጅት አባል የሆነው ዩኒሴፍ ሳይቀር ባጋለጠው ጭፍጨፋ ከ240 በላይ ንጹሀን ህጻናትና ሴቶች ጭምር በተጠለሉበት ሲጨፈጨፉ ጉተሬዝ ያሉት ነገር የለም።
አማራ ክልል ጭና ላይ በርካታ ንጹሀን በአሸባሪው ታጣቂዎች ሲጨፈጨፉ ዋና ጸሀፊው ድንጋጤ ብሎ ነገር አልተሰማቸውም፤ በቆቦ በአንድ ቀን ከ600 በላይ ንጹሀን መጨፍጨፋቸውን ሰምተው ዋና ጸሀፊው ድንግጥም ስለማለታቸው የተሰማ ነገር የለም ሲሉም ነው አቶ አንዳርጋቸው የዋና ጸሀፊውን አቋም የተቹት።
አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ፤ ከ30 ሚሎዮን በላይ ከሆነው ከአማራ ህዝብ ጋር ሂሳብ አወራርዳለሁ ብሎ በግልጽ ሲናገርና ወረራ ሲፈጽም አንቶኒዮ ጉተሬዝ መደንገጣቸውን አልነገሩንም፤ መንግስት ሀምሌ ወር ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች ከአሸባሪው ህወሓት ጋር አብረው እየሰሩ ነው፤ ከዚህ ድርጊታቸው ካልተገቱ እርምጃ እወስዳለሁ ብሎ ሲያስታውቅ በሰራተኞቻቸው ድርጊት ዋና ጸሀፊው አላፈሩም፤ አልደነገጡም ነው ያሉት አቶ አንዳርጋቸው።
የእርዳታ እህል ይዘው ወደ ትግራይ ክልል ከገቡ 400 መኪናዎች ውስጥ የተመለሱት 38 ብቻ ናቸው፤ ምግብ ለማድረስ መኪና ተቸገርኩ ብሎ ድርጅታቸው አቤቱታ ሲያቀርብ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ምንም አለማለታቸውን ያስታወሱት አቶ አንዳርጋቸው፤ መንግስት ከተደጋጋሚ ማሳሰቢያና መስጠንቀቂያ በኋላ ሰባት የእርሳቸው ድርጅት ግለሰቦችን ስላልተገባ ድርጊታቸው አገር ለቃችሁ ውጡ ሲል ግን አንቶኒዮ ጉተሬዝ ደንግጠዋል፤ መደንገጣቸውንም በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል፤ ይህ የእርሳቸውንም ሆነ የድርጅታቸውን ሚዛን የለሽነት ያሳብቃል ነው ያሉት።
“ለመሆኑ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የሚደነግጡት መቼ መቼ ነው?” ሲሉ የሚጠይቁት አቶ አንዳርጋቸው፤ ከዋና ጸሀፊው አቋም ተነስቶ ለዚህ ጥያቄ መልሱ “አሸባሪው ህወሓት የተጎዳ ሲመስላቸው አብዘተው ይደነግጣሉ፤ አብዝተውም ይጮሃሉ” የሚል ብቻ ነው ሲሉ ተችተዋል።
በአስቴር ኤልያስ