የክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ የትንቢተ ቃል!!!
ዘላለም ጥላሁን
“…አሁን በይፋ የሚደረጉትን አንዳንድ ነገሮች ስመለከትና እንዲሁም በይፋ በየመድረኩ የሚደረጉትን አንዳንድ ነገሮችን ስሰማ በኔ አስተያየት የኢትዮጵያ ህልውና አስጊ ሁኔታ ላይ ቆሞ የሚገኝ ይመስለኛል::
ይህን የምልበት ምክንያት ዛሬ ራሳቸውን በልዩ ልዩ የነፃነት ግንባር የሰየሙ ቡድኖች “የህዝቦች የራስን እድል – እስከነፃነት በራሳቸው የመወሰን መብት ” ለተባለው ድንጋጌ : የተሳሳተ ትርጉሜ ሰጥተው : የራሳቸው ነፃ መንግስት እንዲኖራቸው ..ያሰቡት ሀሳብ ፍፃሜ የሚያገኝ ከሆነ ይህ ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የማይጣጣም ሆኖ ስለሚታየኝ ነው::
“የህዝቦች የራሳቸውን እድል እስከ ነፃነት..”የሚለው ድንጋጌ በነፃነት ግንባሮች የተሰጠው ትርጉሜ የተሳሳተ ከመሆኑም ሌላ : እንደ ኢትዮጵያ ብዙ ነገዶችና በነገዶችም ውስጥም ብዙ ጎሳዎችና ንኡስ ጎሳዎች በሚኖሩባት አገር: በቃል የሚነገረውን ያክል በግብር መተርጎሙ ቀላል ሳይሆን ሊወጡት የማይቻል ገደል ነው::
በተጎራባች አገሮች መካከል ያለው የወሰን :የወንዝ ክፍፍል :የጎሳዎችና የንኡስ ጎሳዎች አስተዳደር .የሚያስነሱት ዘልአለማዊ ሁከትና ጦርነት : ለሀገርና ለልማት ሊውል የሚገባውን ሀብትና ጉልበት እየበላ ሁልጊዜ አደህይቶና ሰላምን አሳጥቶ የሚኖር በመሆኑ : የሚሸሹት እንጂ እንኩዋንስ ሊይዙት የሚቀርቡት አይደለም::
…
ይህ ንኡስ አንቀፅ ተፈፃሚነቱ ለሽግግር መንግስቱ እድሜ ብቻ እስከሆነ ድረስ የሚፈጥረው ችግር ቢኖር ጎልቶ ላይታይ ይችል ይሆናል:: አሁን ወደሚረቀቀው ቋሚ ህገመንግስት የሚተላለፍ ከሆነ ግን :በየነገዳቸው ህዝብ ላይ ስልጣን መያዝ ለሚፈልጉ ሁሉ በር ከፋች ሁኖ: መጨረሻው ለማይታይ ሁከትና ጦርነት መንስዔ ሊሆን ስለሚችል :ህገመንግስቱን ለማርቀቅ ሀላፊነት የተጣለባቸው ክፍሎች አጥብቀው ሊያስቡበት የሚገባ ይመስለኛል:: ተመሳሳይ ህገመንግስት በነበሩዋቸው አገሮች: በሶቭየት ህብረትና በእነ ዮጎዝላቢያ ዛሬ የደረሰውም ትምህርት ሊሆነን ይገባል”
መጋቢት 19,1985 ዓ.ም: አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያደረጉት ንግግር
(ምንጭ: ኢትዮጵያዊነት: መፅሄት:1985)