>

የሰብዓዊ ዕርዳታን ከፖለቲካ ነፃ ማድረግ ይገባል....!!! (አወድ መሀመድ)

የሰብዓዊ ዕርዳታን ከፖለቲካ ነፃ ማድረግ ይገባል….!!!

አወድ መሀመድ

የፀጥታው ም/ቤት ለዛሬ ምሽት የጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ያለስምምነት መበተኑ ታውቋል። በኢትዮጵያ እና ሰሜን ኮርያ ጉዳይ ለመነጋገር የተጠራው ስብሰባ ምሽቱን በዝግ ተካሂዷል።
ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ የወቅቱ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ኬንያ በአምባሳደሯ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል እንዳስታወቀችው በስብሰባው ሀገራት በሁለቱም አጀንዳዎች ዙርያ የተለያየ አቋም በማንጸባረቃቸው የጋራ መግለጫ ለመስጠት አልተቻለም።
ኢትዮጵያ ህግ ተላልፈው በተገኙ የተመድ ተወካዮች ላይ የወሰደችውን እርምጃ በተመለከተ የምክር ቤቱ አባል ሀገራት ተመሳሳይ አቋም ሊይዙ ባለመቻላቸው ወደፊት ተጨማሪ ውይይቶችን ማድረግ ይገባል በሚል ስብሰባቸውን ቋጭተዋል።
የምሽቱን ስብሰባ በተመለከተ AFP ከዲፕሎማቲክ ምንጭ አገኘው ባለው መረጃ መሰረት ሩስያ እና ቻይና በምሽቱ የስብሰባ አጀንዳዎች ዙርያ ተጨማሪ ማጣራት ያስፈልጋል፤ በምክር ቤቱ ሥም የጋራ መግለጫ ለማውጣት አሁን ጊዜው አይደለም በሚል የአሜሪካና ሸሪኮቿን አቋም ሳይቀበሉት ቀርተዋል።
የወቅቱ የፀጥታው ም/ቤት ሰብሳቢ እና የኬንያ አምባሳደር ማርቲን ኪማኒ በስብሰባው ላይ ኢትዮጵያን በተመለከተ ከፀጥታና ደህንነት ጋር ተያይዞ ለሰብዓዊ ድርጅት ሰራተኞች ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባ፤ ግን ደግሞ እንደ ተመድ ያለ ዓለም አቀፍ ተቋም የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎችን ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነፃ ማድረግ እንደሚገባ” ከመተማመን ላይ ተደርሷል ብለዋል።
በፀጥታው ም/ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ሩስያ እና ቻይና ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው ነገር የአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ ነው፤ ጣልቃ መግባት አያስፈልግም የሚል የፀና አቋም እንዳላቸው ይታወቃል።(GMN)
Filed in: Amharic