>

ከወያኔዎች ጋር ሂሳብ አወራርዶ ወያኔን ለዝንተአለሙ የመቅበር አስፈላጊነት....!!! (ክፍል 4 ) አንዳርጋቸው ጽጌ

ከወያኔዎች ጋር ሂሳብ አወራርዶ ወያኔን ለዝንተአለሙ የመቅበር አስፈላጊነት….!!!

(ክፍል 4 ) አንዳርጋቸው ጽጌ

ታሪክን በሚገባ ለፈተሸ፤ ኢትዮጵያ ግዛቷ ሲጠብና ሲሰፋ ለሺ አመታት በዘለቀው ፈታኝ ጉዞዋ፤ አንድ ላይ ሲንገታገቱ፣ ሲወድቁና ሲነሱ አብረው ከዘለቁ ጥቂት የተለያዩ ማህበረሰቦች መካከል በዋንኛነት የሚጠቀሱት አማሮችና ትግሬዎች ናቸው። በእምነት፣ በባህል፣ በትውፊት፣ በስነልቦና፣ በአካላዊ ቁመና፣ በአለባበስ፣ በአመጋገብ፣ በአኗኗር እንዲሁም በአመራረት ዘይቤ ይህ ነው የሚባል ልዩነት የሌላቸው እነዚህ ሁለት ማህበረሰቦች፤ በጋራ በመፈተን፣ በጋራ በመውደቅና በጋራ በመነሳት፣ እንደ ታላቅና ታናሽ ወንድማማቾች/እህትማማቾች (ማን ታላቅ ማን ታናሽ እንደሆነ አልተናገርኩም) ለረጅም ዘመናት በአንድ ላይ ኖረዋል። ስለ ሁለት ማህበረሰቦች የማንነት ተመሳሳይነት እንነጋገር ቢባል ከእነዚህ ሁለት ህዝቦች ይበልጥ የሚቀራረብ አይኖርም።
ሆኖም ግን “ወያኔ” የሚባል ድርጅት ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ አማራ የትግራይ ህዝብ ዋንኛ ጠላትነት ሆኖ ተፈረጀ። ይህ ፍረጃ በብዙ ሰው አእምሮ ውስጥ “ለምን?” የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ ይታወቃል። ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ስንል በተከታታይ ጽሁፎች ብዙ ነገሮችን ፈትሸናል። በመጨረሻም  ወያኔዎች ከኢትዮጵያ ታሪክ ኩነቶችን እየመዘዙ “በአማራ ተበድለናል” በሚል በትግራይ ህዝብ ውስጥ ያሰራጩት ትርክት፤ አይን ባወጣ ቅጥፈትና ይሉኝታቢስነት የተሞላ መሆኑን ማየት ችለናል። ቀጥለን የምንሸጋገረው ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በህይወት ያሉ ወገኖቻችን ምስክርነታቸውን መስጠት ወደሚችሉባቸው ጉዳዮች ይሆናል። የሂሳብ ማወራረዱ ስራም የሚቀጥለው በዚሁ አግባብ ይሆናል።
ወያኔ ከ1966 አም አብዮት መፈንዳት ጋር ተያይዞ የተመሰረተ ድርጅት ነው። መሪዎቹ፤ በእድሜም፣ በልምድም፣ በእውቀትም፣ እንጭጮች ነበሩ። በተለይ ወደኋላ ጎላ ብለው የወጡት፤ በወቅቱ ከ25 አመት እድሜ በታች ነበሩ። ከስብሃት ነጋ ውጭ 30 አመት እድሜ የነበረው መሪ አልነበራቸውም። በእድሜ የገፉ፣ ልምድና እውቀት የነበራቸው የትግራይ ተወላጆች ሙሉ በሙሉ ሃገር አቀፍ በሆኑ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ በስፋት የሚሳተፉ ነበሩ።
እንደ ኢህአፓ (ኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ) አይነቶቹ የ66 አብዮት ወደ አደባባይ ያወጣቸው ግዙፍ የፖለቲካ ድርጅቶች በርካታና ከፍተኛ የትግራይ ምሁራንን ያካተተ ነበር። ከዛም ተሻግሮ ወሳኝ የነበሩት ብዙዎቹ የድርጅቱ የአመራር ቦታዎች በትግራይ ምሁራን የተያዙ ነበሩ።
በኢህአፓ ውስጥ ሁሉም የኢትዮጵያ ምሁራን እና ወጣት ተማሪዎች ዘርን ሳይለዩ በመቶ ሽዎች እንደተሳተፉ እናውቃለን። በዛሬው የወያኔ የዘር መነጸር እንመርምረው ቢባል አብዛኛው የኢህአፓ አባላት የብሄረሰቦች ውህድ እና አማሮች ነበሩ። እነዚህ የኢህአፓ አባላት፤ የድርጅቱ ከፍተኛ መሪዎች አብዛኛዎቹ ትግሬዎች መሆናቸው አሳስቧቸው አያውቅም። ለእነዚህ መሪዎች ይሰጡት የነበረው ክብር፣ ፍቅርና ታማኝነት ወጣቶች የበቀሉበትን ማህበረስብ ቀናነትና የስብእና እድገት የሚያንጸባርቅ ነበር። እዚሁ ላይ በኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ዝነኛ የነበሩ በርካታ የተማሪ መሪዎች የትግራይ ተወላጆች የነበሩ መሆናቸውን እና አንዳንዶቹ በትግሉ ወቅት ለከፈሉት መስዋእትነት ተማሪው በጣኦት ደረጃ ያመልካቸው እንደነበር ማስታወሱ ተገቢ ነው።
ወያኔ ለአማራ ካለው ጥላቻ ይህን በከፍተኛ የትግራይ ምሁራን ሲመራ የነበረን ድርጅት፤ የአማራ ድርጅት፣ ትግርኛ ተናጋሪ ከፍተኛ መሪዎቹንም የሸዋ ትግሬዎች፣ የአማራ ቡችላዎች (ኩርኩር አምሃራ) የሚል ስም በመስጠት ነው ህወሃትን የመሰረተው። ኢህአፓ “ታላቂቱ ኢትዮጵያ (አባይ ኢትዮጵያ)” የሚል “አጭበርባሪ የአማሮች ድርጅት ነው” በማለት ወያኔ በትግራይ ውስጥ ሲያካሂድ የነበረውን ፕሮፓጋንዳ ሁላችንም እናስታውሰዋለን። “ታላቋ ኢትዮጵያ ባዮች እነዛ ብልጣብልጦች አሲምባ ተቀምጠው ለጭቁን ነን ባዮች፣ (“አባይ ኢትዮጵያ እቶም ተበለጽቲ አሲምባ ኮፍ ኢሎም ንውጽኡ በአልቲ” ) በትግራይ ገጠሮች በኢያሱ በርሄ የምትመራው የወያኔ የባህል ክፍል ከበሮ እየደለቀች ታጋዩን ስታስጨፍርበት የነበረ ሙዚቃ እንደነበር እናስታውሳለን።
ይህ የወያኔ አመለካከት፤ ውሎ አድሮ ከመላው ኢትዮጵያ የደርግን የቀይ ሽብር እርምጃ፣ እስራትና ሰቆቃ አምልጠው ትግራይ አሲምባ በሚባል ቦታ ላይ ተሰባስበው በነበሩ የኢህአፓ ታጋዮች ላይ ወያኔ ጦርነት እንዲያውጅ አድርጎታል። ከደርግ ጥይት በስንት መከራ ያመለጡ ወጣቶች በትግራይ ምድር በወያኔ ጥይት ያለቁት፣ ኢህአፓን “የአማራ ድርጅት” ብሎ በመፈረጁና  በአማራው ላይ ከቋጠረው ጥላቻ በመነሳት ነው። እግረ መንገዳችንን ወያኔ “የአማራ” የሚል ታርጋ ለሁሉም “ኢትዮጵያ” የሚል ስም ላላቸው የፖለቲካ ድርጅቶችና የኢትዮጵያ መንግስታት መለጠፍ ልማዱ ነው። ከየትኛው ብሄር ምሁርና ተማሪ ይልቅ በደርግ ጥይት ያለቀው የአማራ ምሁርና ተማሪ ሆኖ ሳለ ደርግ ሳይቀር ለወያኔ የአማራ መንግስት ነበር። ዛሬም ለወያኔዎች የዶ/ር አብይ መንግስት የአማራ መንግስት ነው። ወያኔ ለአማራ ህዝብ ያለው ጥላቻ ወደ እብደት እየመራው እንደሆነ ማስረጃው የኤርትራን መንግስትና ፕሬዚደንቱን ኢሳያስ አፈወርቂን ሳይቀር የአማራ አጀንዳ አስፈጻሚዎች አድርገው እነጻድቃን እና ጌታቸው ረዳ እየለፈፉ መሆኑ ነው።
ሃቅ ስለሆነ የምንነጋገረው፤ አማራው የሰዎችን ዘር ሳይመለከት፣ ሰዎች የቆሙለት አላማ ቀና ነው ብሎ እስካመነ ድረስ መሪነታቸውን ለመቀበል ችግር የሌለበት ህዝብ መሆኑን በተደጋጋሚ በታሪኩ ያሳየ ሲሆን ወያኔዎች ግን  ከሰው መልካምነት ይልቅ የዘሩ የትግሬ ጥራት የሚያሳስባቸው እንደሆነ ነው። ወያኔዎች ግን ሁሌም የራሳቸው ዘር የበላይነት ባልያዘበት፣ በዘር የመጠቃቀም እድል በማይፈጥርላችው  ማናቸውም የሰዎች ስብስብ ውስጥ በእኩልነት መሳተፍ የማይፈልጉና የማይችሉ ኋላቀር ፍጥረቶች ናቸው። ባለፉት 27 አመታት በተግባር የፈጸሙት ይህንኑ ነው። ከለውጡ በኋላም በእኩልነት ለመኖር የተፈጠረላቸውን መልካም አጋጣሚ መጠቀም አቅቷቸው የኢትዮጵያን ህዝብ አላስፈላጊ ወደ ሆነ ግጭት የጎተቱት ለዚህ ነው።
“ትግራይ ለትግሬዎች ብቻ” በሚል ብሂል ወያኔዎች ከትግራይ ምድር ወግተው ያስወጡት ኢህአፓን ብቻ ሳይሆን ሌላውን  ኢትዮጵያ በሚል ስም ሲንቀሳቀሰ የነበረውን ኢዲህን (ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት) ነበር። ሆኖም ግን ወያኔዎች ይህን አድርገው ከትግራይ ወጥተው በአማራ መሬቶች ውስጥ ያለምንም ይሉኝታ ለመንቀሳቀስ ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም። ወቅቱ የአማራ ህዝብ በደርግ ላይ የተማረረበት ወቅት ስለነበር፣ ወያኔዎችም “ያስመረረህን ደርግ በጋራ ታግለን እንጣለው” በማለታቸው የአማራ ህዝብ ከጥቂት አመታት በፊት ወያኔዎች “ትግራይ ለትግራይ ብቻ” በሚል ብሂል በአማራ ተወላጆች ላይ የፈጸሙትን ግፍ በማስታወስ ቂም ይዞ ወግዱ አትድረሱብኝ አላላቸውም። ቂም ያልያዘው ወያኔዎች እንደሚያስቡት እነሱ ስላሞኙት አልነበረም። አማራው የመቻል፣ የመታገስ፣ ለሰዎች ስህተት የራሱን ምክንያት በመደርደር ጥፋታቸውን የማሳነስ፣ “ስላልገባቸው ነው፤ ባያውቁት ነው። በሂደት ይማራሉ” የሚል የባህል መሰረት ያለው ህዝብ በመሆኑ ብቻ ነበር።  የቅርቡን ሳይሆን የሩቁን፣ ጠባቡን ሳይሆን ሰፊውን፣ መንደሩን ሳይሆን ሃገሩን እያሰበ፣ የአማራ ህዝብ ልጆቹን በታጋይነት ከወያኔ ጎን አሰልፎ፣ በጉልበቱና በሃብቱ እያገዘ፣ የወያኔን አቅም አጠናክሮ የደርግን ውድቀት በማፋጠን አዲስ አበባ እንዲገቡ አደረገ። ለእንዲህ አይነቱ የአማራ ህዝብ ቀና እና ወገናዊ ድጋፍ የወያኔ ምላሽ ምን ሆነ? (በነገራችን ላይ የአማራ ህዝብ ትብብር ባይገኝ ወያኔ እንኳን አዲስ አበባ መግባት አይደለም ነጻ አወጣሁት የሚለውን ትግራይ ይዞ የመቀጠል እድል እንዳልነበረው መገንዘቡ ተገቢ ነው። ወያኔ አዲስ አበባ የመግባቱን ሃቅ ከአማራ ህዝብ ትብብር ገንጥሎ ወርቅ በሆነው የትግራይ ጀግና ሰራዊቱ ተጋድሎ እንደሆነ ደጋግሞ ለራሱ በመናገሩና ራሱን በማሳመኑ ተከታታይ ለሆኑ ውርደቶች ራሱን አጋልጧል። አሁንም “በጀግኖች የትግራይ ተዋጊዎቼ አዲስ አበባ እገባለሁ” የሚል ቅዥት ውስጥ የወደቀው ወያኔ በታሪኩ ላገኛቸው ድሎች የአማራን ህዝብ ወሳኝ ሚና በመዘንጋቱ ነው።)
ሃተታ ላለማብዛትና ለሂሳብ ማወራረዱ እንዲቀል የአማራ ህዝብ ወያኔን አቅፎና ደግፎ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ካስገባ በኋላ በልዋጩ በወያኔ ለውለታው የተከፈለው በጥላቻ መርዝ የተለወሰ ክፍያ ምን እንደሚመስል በተራ ቁጥር እንዘረዝረዋለን።
1) በብዙ ሃገራዊ መስዋእትነት፤ ብዙ ዘመናትን ለግንባታ የወሰደውን፤ በህብረ ብሄራዊነቱ ወያኔ ከፈጠረው የራሱ መከላከያ ሃይል የላቀ የነበረውን፤ የኢትዮጵያን የመከላከያ ሃይል “የአማራ መንግስት መከላከያ ሃይል ነው” በሚል ሰበብ ሙሉ በሙሉ በማፍረስ፣ በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ከፍተኛ መስዋእትነት በመክፈል ሃገራዊና ህዝባዊ ግዴታውን ሲወጣ የነበረውን ሰራዊት በመበተን፣ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ የሰራዊቱን አባላት የጎዳና ተዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ፣
2) ወያኔ እራሱን ነጻ አውጪ፣ የብሄሮች፣ የቋንቋ፣ የእምነት እኩልነት አምጪ አድርጎ በማቅረብ፤ እንዲህ አይነቱን የእኩልነት ጥያቄ የሚጻረሩ አማሮች ናቸው የሚል የሃሰት ትርክት (የሃሰት ትርክት የምንለው በኢትዮጵያ ወስጥ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርአት እንዲዘረጋ፣ የቋንቋ፣ የእምነት የባህል እኩልነት በኢትዮጵያ እንዲሰፍን፣ ገባርነትና ጭሰኛነት እንዲወገድ ኢትዮጵያ ለሁሉም ዜጎቿ የምትመች የበለጸገች ሃገር እንድትሆን በኢትዮጵያ ታሪክ የአማራ ምሁርና ተማሪ የከፈለውን መስዋእትነት ያክል የሌሎች ብሄርና ብሄረሰቦች ምሁራን እና ተማሪዎች እንዳልከፈሉ ስለምናውቅ) በመላው ሃገሪቱ በሚገኙ ማህበረሰቦች ውስጥ በማሰራጨት፣ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ተበትኖ የሚኖረው አማራ፣ በሌሎች ወገኖቹ በጥላቻ አይን እንዲታይ፣ የአሰቃቂ ግድያዎች፣ የዘረፋ፣ የመፈናቀል ሰለባ እንዲሆን ማድረግ ነው። (እዚህም ላይ ቀደም ብሎ ኢህዴን በኋላ ብአዴን የሚል ስም የወሰደው የነታምራት ላይኔ ድርጅት ከወያኔ ጋር በመደመር ታሪክ የማይረሳውን ጸረ አማራ ድርጊት መፈጸሙን ማስታወስ ይገባል።) ይህ የግድያ፣ የዘረፋ፣ የማፈናቀል ድርጊት ወያኔ ስልጣን ከመያዙ ጥቂት አመታት በፊት ጀምሮ ከሰላሳ ለሚበልጡ አመታት የዘለቀ ሆኗል።
3) የአማራ ህዝብ በተገቢ ደረጃ በሃገራዊና በራሱ ክልል ጉዳይ ሳይቀር ትልቅነቱን እና ማንነቱን የሚመጥን ውክልና እንዳይኖረው በማድረግ፣ ከሃገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲገለል ማድረግ፤ ህገ መንግስቱ ሲረቅ ሁሉም ብሄረሰቦች ሲወከሉ የአማራ ህዝብ ያለ ውክልና እንዲቀር፣ ህገ መንግስቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በመላው ሃገሪቱ የሚኖሩ አማሮችን ሃገር አልባ፣ ንብረት አልባ፣ መብት አልባ ያደረገ መንግስታዊና ክልላዊ አወቃቀር እንዲኖረው  ማድረግ፤ ወያኔ የአማራ ህዝብ ላሳየው ቀናነት ከሰጣቸው እኩይ ምላሾች መካከል መጠቀስ የሚገባቸው ናቸው።
4) በጉልበት አስቀድሞ ወያኔ የያዛቸውን፤ ነባር የአማራ ህዝብ መኖሪያዎችን ህገ መንግስታዊ ሽፋን በመስጠት በአዲስ መልክ ለተደራጁ ክልሎች በማከፋፈል፣ የአማራ ህዝብ መልካምድራዊ አሰፋፈሩን በማጥበብ ብዛቱንና አቅሙን ማሳነስ፤ ወያኔ ወልቃይትና ራያን በትግራይ ስር ሲያካልል አላማው ትግራይ ነጻ ሃገር ስትሆን በምግብ ራሷን እንድትችል በሚል እሳቤ ብቻ ሳይሆን አማራውን የማዳከሚያ ስትራተጂ ጭምር ነው። መተከልም ወደ ቤንሻንጉል የተካለለው ወያኔ ለአማራ ካለው ጥላቻና የማዳከም እቅድ የተነሳ ነው።
5) ወያኔ በአካዳሚክ ተቋማት፣ በንግድ ስራ መስክ፣ ቁልፍ በሆኑ የፌደራል መንግስታዊ ስልጣኖች፣ በውጭ ሃገርና በአለም አቀፍ ድርጅቶችና ሌሎች ተቋማትና የስራ ዘርፎች ውስጥ ብቃትና ችሎታ ያላቸው አማሮች እንዳይገኙ፣ ቁጥራቸው እንዲመናመን ጥላቻን ነዳጁ አድርጎ በ27 አመታት የስልጣን ዘመኑ ሲሰራው የቆየ እኩይ ተግባሩ ነው። በ2002 አም እኔው ራሴ ባጠናሁትና በመረጃ አስደግፌ ባቀረብኩት ጥናት “የኢትዮጵያ” የሚል ስም በተሰጠው ምኑም ኢትዮጵያን በማይመስለው የመከላከያ ተቋም ውስጥ የሚገኙ 42 የክፍለ ጦር አዛዦች ውስጥ 41 የሚሆኑት ትግሬዎች ሲሆኑ አንድም አማራ የክፍለ ጦር አዛዥ እንዳልነበር ነው። ወያኔ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 42 መምህራንን በ1985 አም ሲያባርር ለምን የሚል ጥያቄ ላነሳነው ሰዎች በወቅቱ የወያኔ ጫማ መጥረጊያ ምንጣፍ የነበሩት እነታምራት ላይኔ፣ ዳዊት ዮሃንስና ተፈራ ዋልዋ የመሳሰሉ የኢህዴን መሪዎች የሰጡን ምላሽ “ትምክህተኞች አማሮች ስለሆኑ ነው” የሚል እንደነበር እናስታውሳለን። የአማራ ባለሃብቶች ጥንትም ብዙ ከማይሳተፉበት የንግድ እንቅስቃሴ ለማስወጣት፣ ለማቀጨጭ በወያኔ ያልተሸረበ ሴራ ያልተሰራ በደልና ግፍ የለም። እዚህ ግባ የሚባል ሃብት የሌለውን የአማራ ህዝብ ምክንያት በማድረግ ገበሬ መሬት የመሸጥ የመለወጥ መብት ሊኖረው ይገባል የሚለውን ሃሳብ መለስ ዜናዊ ሲቃወም “መሬቱን የሚገዙት አማሮች ይሆናሉና አይቻልም” የሚል እንደነበር ለወያኔዎች ልናስታውሳቸው ያስፈልጋል። በሂደት ግን መሬት የመንግስት ነው በሚል ሽፋን የሃገሪቱን ገበሬ ከመሬቱ ያፈናቀሉት የከተማና የገጠር መሬት ለጉድ የዘረፉት ወያኔዎችና ዘመዶቻቸው እንደሆኑ ይታወቃል።
6) ባላፉት 27 አመታት ወያኔ ጥላቻን መሰረት በማድረግ በአማራው ላይ  የፈጸመው ጥቃት፣ የአማራ ህዝብ ከተራ ባተሌዎቹ አንስቶ እስከ ከፍተኛ ምሁራኑ ከየትኛውም ብሄር ህዝብ በላይ በገፍ ሃገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ፣ በሰው ሃገር ተዋርደውና ባይተዋር ሆነው እንዲኖሩ አድርጓል። በተለይ እውቀት ተሞክሮ ያላቸው የአማራ ምሁራን በገፍ እንዲሰደዱ፣ በሃገር ውስጥ እንዲገለሉ በማድረግ ወያኔ በሃገር ደረጃ ብሎም በአማራ ክልል ህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ሃገሪቱም ሆነ ክልሉ ዛሬ ለሚገኙበት አሳዝኝ ደረጃ ዋናው ምክንያት መሆኑን ልብ ማለት ይገባል።
7) ወያኔ ስልጣን ሲይዝ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የነበረው የኗሪው የብሄራዊ ተዋጽኦ በደርግ ዘመን ተደርጎ በነበረው ጥናት መሰረት፣ 57 ከመቶው አማራ እንደሆነ የሚያሳይ ነበር። ይህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የከተማው አማራ ወያኔ ስልጣን ከያዘበት ከቀን አንድ ጀምሮ ጥርስ የተነከሰበት ሆኗል። “አዲስ አበባ ስገባ የሞቀ አቀባበል ያላገኘሁት ከተማው በአማሮች የተሞላ በመሆኑ ነው” የሚል ቂም ወያኔ ይዞ እንደነበር እናስታውሳለን። ወያኔ በ1997 አም ምርጫ በአዲስ አበባ ውስጥ ማንንም ማስመረጥ ባለመቻሉ፤ የዚህ ምርጫ ሽንፈት ምክንያት አማራው ነው ብሎ በማመኑ፤ ከ1997 አም ጀምሮ የአማራውን ቁጥር በከተማው ውስጥ ለማመናመን ብዛት ያላቸውን ትግሬዎች ሆን ተብሎ በተዘጋጀ ፖሊሲ አማካኝነት ከትግራይ እንዲፈልሱ በማድረግ፣ (ከራሳቸው ከወያኔ መሪዎች የሰማነው ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱ) የከተማ ቤቶችንና እና መሬትን የመንግስት የሚያደርገውን ህግ በመሳሪያነት በመጠቀም የቤት፣ የመሬት ባለቤቶች እንዲሆኑ አድርጓል። ነባር የከተማ ኗሪዎችን መሬታቸውን በመቀማት፣ በልማት ስም በማፈናቀል፣ የዘመናት የአብሮነት ህይወት የነበራቸውን የአንድ ሰፈር ሰዎች ከመሃል ከተማ በማንሳት ወደ ከተማው ዳርቻዎች በሁሉም አቅጣጫዎች በመበተን፣ ማህበረሰባዊ አቅማቸውን ለማዳከም ብዙ ነገሮችን ወጥኖ ተግባራዊ አድርጓል። ዛሬ ባለቤት አልባ የሆኑ ከ300 በላይ የሚሆኑ በግንባታ ላይ የሚገኙ ህንጻዎች የቆሙበት መሬትና ሌሎችም ግንባታቸው የተጠናቀቁ በሽዎች የሚቆጠሩ በከተማው እምብርት ላይ በወያኔና በሸሪኮቻቸው የተሰሩ ውድ ሆቴሎችና አፓርትመንቶች የቆሙት አዲስ አበባ ስትመሰረት ጀምሮ አያት ቅድመ አያቶቻቸው ከኖሩበት ቦታ በወያኔ ሆን ተብሎ እንዲፈናቀሉ በተደረጉ አማሮች ርስት ላይ ነው። “ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ” እንዲሉ በከተማው የብሄራዊ ተዋጽኦ 17 ከመቶ ድርሻ በመያዝ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የነበረው የጉራጌ ማህበረሰብም የአማራ (የነፍጠኛ) ተለጣፊ የሚል ታርጋ በወያኔ የተለጠፈለት በመሆኑ ቤት ንብረቱን የማጣትና የመፈናቀል ሰለባ ሆኗል። ወያኔ ሃጥያተኛ አድርጎ ላየው የከተማው አማራ የመጣው ቅጣት ከጉራጌው ውጭ ላሉት ወያኔ ጻድቃን አድርጎ ለሚያያቸውም የሌሎች ብሄረሰቦች የከተማ ኗሪዎችም አልቀረላቸውም።
8) ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች ካለቀውና ከተፈናቀለው አማራ በተጨማሪ ከ1997 አም ምርጫ በኋላ ወያኔ በወሰደው ሰፊ እመቃ በሚዛን ሲቀመጥ አሁንም ቢሆን ትልቁን የግፍ ገፈት የቀመሰው አማራው ነው። ቅንጅት ህብረ ብሄራዊ ድርጅት እንደሆነ እየታወቀ ወያኔ ቅንጅትን የአማራ “የነፍጠኛ” ድርጅት ብሎ በመፈረጅ በአማራ ክልል፣ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል የተካሄደው እመቃ በዋንኛነት በአማራ ማንነት ላይ ያነጣጠረ ነበር። በዚህ ወስጥ የቅንጅት አባላት የሆኑ የሌሎች ብሄረሰብ ተወላጆች አልታሰሩም፣ አልተገደሉም፣ አልተሰደዱም ማለት ሳይሆን ወያኔ ሁሉንም የቅንጅት አባላት የሚያይበት መነጸር በአማራ ጥላቻ የተቃኘ መሆኑን አንርሳ ለማለት ነው። ከዚህ አሳዛኝ ታሪክ ጋር በተያያዘ ከወያኔ ጋር በመተባበር ብዙ አሳፋሪ ስራ የሰሩ አማራዎችን ጨምሮ፤ ከተለያዩ ብሄረሰቦች የተውጣጡ ተላላኪዎች እንደነበሩ እያስታወስን በዝምታ የምናልፋቸው ዛሬ ወያኔ ሂሳብ ለማወራረድ የሚፈልገው ከነዚህ አካላትን ጨምሮ መሆኑን ስለተገነዘብን ነው።
9) ወያኔ እና ዘረፋ፤ በ2015 አም የተባበሩት መንግስታት፣ የቀድሞውን የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ታምቦ ኢምቤኬን በሊቀመንበርነት ሰይሞ፤  ከኢትዮጵያ እየተዘረፈ በሚወጣው ሃብት ላይ ባስደረገው ጥናትና በወጣው ሪፖርት ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ 30 ቢሊዬን ዶላር ከሃገሪቱ ተዘርፎ የወጣ መሆኑን ይገልጻል። ይህ ሃብት ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በውጭ መንግስታት ለሀገሪቱ ከተሰጠው 30 ቢሊዮን ዶላር ጋር መሳ ለመሳ መሆኑን ሪፖርቱ አስረድቷል። ይህን መረጃ ይዞ የወጣው ፍሮብስ የተባለው ታዋቂ የአሜሪካ መጽሄት ዘረፋው የተካሄደው የሃገሪቱን ስልጣን እና ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ በተቆጣጠረው ጠባብ የገዢ ክሊክ ነው በማለት በማያሻማ ቋንቋ አስቀምጦታል። ቁም ነገሩ ያለው ሪፖርቱ ላይ ሳይሆን ይህን አይነት አይን ያወጣ ዘረፋ ኢትዮጵያን ከመሰለ ደሃ ሃገር ላይ ማካሄድ ትርጉሙ ምን ያህል አስከፊ መሆኑ በሚገባ ከመረዳቱ ላይ ነው። ብዙ ሰዎች ይህ የተዘረፈ ገንዘብ፣ ስድስት የህዳሴ ግድብ እንደሚያሰራ ወይም በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ዩኒቨርስቲዎች እና ፋብሪካዎች እንደሚያስገነባ፣ ወዘተ በመግለጽ ሃገሪቱ በድህነት እንድትማቅቅ ዘረፋው እኩይ አስተዋጽኦ ያለው ለመሆኑ ለማስረዳት ሞክረዋል። ይሁንና እነዚህ ምሳሌዎች የወያኔን ወንጀል በደንብ ስለማያሳዩ ዘረፋውን በሰብአዊ ዋጋው መለካት አስፈላጊ ነው። በወያኔ ዘረፋ የተነሳ ስንት ህጻናት በቂ የምግብና የጤና እንክብካቤ ባለማግኘታቸው አለቁ? ስንት እናቶች በአቅራቢያቸው የማዋለጃ ስፍራዎች ባለማግኘታቸው ህይወታቸው አለፈ? ስንት ዜጎች በቀላሉ ሊፈወሱ ከሚችሉ በሽታዎች ወይም ሊድኑ ይችሉ ከነበሩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች መዳን ሳይችሉ ቀሩ? ስንት ቤተሰቦች በንጹህ የመጠጥ ውሃ ፣ በኤሌክትሪክ ፣ በትራንስፖርት አለመኖር፣ ኑሯቸው የስቃይና የመከራ እንዲሆን ተደረጉ? እነዚህ እና ሌሎች ጥያቄዎችን በማንሳት ነው፤ የወያኔን የዘረፋ የግፍ ለከት እውነተኛ ሚዛኑን መለካት የሚቻለው። ወያኔ በጥይት ደብድቦ የገደላቸውን፣ በየእስር ቤቱ እያጎረ ያሰቃያቸውን ዜጎች ቁጥራቸው በመቶሺዎች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናትን፣ ወጣቶችን፣ ጎልማሶችንና አረጋውያንን በቀጥታ በመዝረፍ  ህይወታቸው በመከራ የተሞላ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን የጅምላ እልቂት እንዲደርስባቸው ማድረጉን ያስታወሰው የለም። የወያኔ ዘረፋ፤ በረሃብ፣ በበሽታ፣ በሌሎችም በገንዘብ እጥረት የተነሳ በወያኔ ዘመን ላለቁ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የጅምላ እልቂት ዋናው ምክንያት ነው። የአማራ ህዝብ ደግሞ በወያኔ የጥላቻ አይን ተለይቶ የሚታይ በመሆኑ የዚህ የጅምላ ግድያ ዋና ሰለባ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ሂሳብ ማወራረድ ብለዋልና ሂሳቡ የሚያሳየው ይህንኑ ነው።
የጀመርነውን ክፍል ለመሰብሰብ
ወያኔ ከአማራ ጥላቻ በመነሳት በአማራ ህዝብና ከዛም አልፎ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያደረሰውን ጥቃትና ጉዳት ዘርዝረን መጨረስ አንችልም። ለጊዜው ለማሳያ ያክል እስካሁን ያልነው ይበቃል። ወያኔን የምንጠይቀው የዘረዘርነውን አንድ መቶኛ የሚሆን፤ አማራው በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸማቸውን እኩይ ድርጊቶች እንዲያቀርብ ነው። ማቅረብ እንደማይችል ግን እናውቃለን። በሚቀጥለውና በመጨረሻው ክፍል፣ ይህን ሁሉ ወንጀል በአማራ ህዝብ ላይ የፈጸመ እኩይ ድርጅት ከሶስት አመት በፊት በህዝብ ትግል ሲወድቅ ለመሆኑ ይህ ሁሉ በደል የተፈጸመበት የአማራ ህዝብ ምን አለ? የወያኔ ገዳዮቹን፣ ዘራፊዎቹንና አፈናቃዮቹን ምን ይደረጉ አለ? ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው ምላሽ የወያኔን እና የተባባሪዎቹን ይሉኝታቢስነትና አደገኛነት አጉልተው የሚያሳዩ ይሆናሉ። በመጨረሻው ክፍል ይህን ሃተታ ይዘን እንቀርባለን። እስከዛው በቸር እንገናኝ።
Filed in: Amharic