>

ከ113 አመት በፊት የፊታውራሪ ተ/ሐዋርያት ከሩስያ መመለስና ከዳግማዊ ምኒልክ ጋር መገናኘት (ሲሳይ ተፈራ መኮንን)

ከ113 አመት በፊት የፊታውራሪ ተ/ሐዋርያት ከሩስያ መመለስና ከዳግማዊ ምኒልክ ጋር መገናኘት
ሲሳይ ተፈራ መኮንን

“አገሬ በጣም ናፍቃኛለች”
11 አመታት የኖርኩባትን፣ በት/ት ያደግኩባትን ሩስያን ትቼ ወደተፈጠርኩባት ኢትየጵያ ለመጓዝ በወዳጅ ዘመድ እምባ ታጅቤ በመርከቤ ላይ ተሳፈርኩ፡፡ በአውሮጳ ሰው የሚከበረው ያደገበት ት/ቤት የታወቀ ሲሆን ነው፡፡ እኔም በስመጥሩው የሚካዔል የመድፈኞች ት/ቤት ተምሬ የጨረስኩ ኢትየጵያዊ ተወላጅ መሆኔን ካወቁ በኋላ፣ በመርከቡ መናፈሻ የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች ወደ እኔ እየመጡ ሊያነጋግሩኝ ፈለጉ፡፡
አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች እየከበቡ በንግግሬ እየተደነቁ አፋቸውን እየከፈቱ ያዳምጡኛል፡፡ የፑሽኪን ዘመድ ሳይሆን አይቀርም ንግግር ያሳምራል እያሉ ይገረማሉ፡፡ ፑሽኪን በጣም የተመሰገነ የሩስያ ባለቅኔ ሲሆን አያቱ የሐማሴን ሰው ነው ይባላል፡፡ የፑሽኪን አያት በጦርነት በቱርኮች እጅ ተማርኮ ከአገሩ እንደወጣ ያነገራል፡፡ ከዚህ በኋላ ከቱርኮች አምልጦ ወደ ሩስያ በመግባት ጄነራል ለመሆን በቃ፡፡ ሚስት አግብቶም የፑሽኪንን እናት ወለደ፡፡
የጥንቷን ኮንስታንቲኖፕል የአሁኗን የቱርኮች ከተማ ኢስታምቡልን አልፈን እስክንድርያ ላይ ስንደርስ፣ ወንድሜን ሀብተ ማርያምን ለማጠያየቅ ከመርከብ ወረድኩ፡፡ ዘርቩዳኪል ከሚባል የግሪክ ነጋዴ ቤት ብጠይቅ ሀብተ ማርያም ወደ አገሩ ከተሳፈረ ቆይቷል አሉኝ፡፡ ወደ ጃፋ ተሻግሬ ኢየሩሳሌምን ለመጎብኘት በኋላም ወደ ካይሮ አልፌ ፒራሚዶችን ለመመልከት ተመኝቼ ነበር፡፡ ነገር ግን የግብጽ አረቦች የውጭ አገር ሰው ሲመጣ እንደጥገት በማየት የግድ ለማለብ ያስጨንቁታል፡፡ የሚከላከል ከሆነ ሊያጠቁት የሚፈልጉ ሲሆን ቆንሲል የሌለው ከሆነም መጠቃት አይቀርለትም፡፡
ከእስክንድርያ በፈረንሳይ መርከብ ወደ ጅቡቲ ተጓዝኩ፡፡ ቀይ ባህርን ስናልፍ ያገሬ ጠረፍ እየታየኝ ሰውነቴ ነቃ፡፡ ወደ አገሬ መቃረቤ ነው፡፡ ከአገሬ ስወጣ እውነት አልመሰለኝም ነበር፡፡ አሁንም ወደ አገሬ ተመልሼ ስገባ እውነት አልመሰለኝም፡፡ አገሬ በጣም ናፍቃኛለች፣ መቃረቤ እየተሰማኝ ሰውነቴ ሁሉ ተቀሰቀሰ፡፡ በጣም ነቃሁ፣ ራሴ ጋለ፣ ልቤ በሀይል እየነዘረ ስሜት በዛብኝ፡፡ በጀርባዬ ላይ ነርቮቼ ጅማቶቼ የሚበጠሱ መሰለኝ፡፡ እንቅልፍ እየወሰደኝም ሌሊቱን ሁሉ አይኖቼ ሳይከደኑ እንዳፈጠጡ አድራለሁ፡፡
በጅቡቲ ቆንስላ አቶ ዮሴፍ በደህና ተቀብለው መምጣቴን በስልክ ወደ አዲስ አበባ በማስታወቅ ወደ ድሬ ዳዋ አብረን መጣን፡፡ እቃዬን ለአቶ ንጋቱ አደራ ሰጠሁና ወደ ሐረር መጣሁ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ የሚያውቁኝ የሀረር እንደራሴ ፊታውራሪ በንቲ፣ ሐረር ላይ በደህና ተቀበሉኝ፣ በራስ መኮንን መቃብር ላይ አበባ አኖርኩ፡፡ ወንድሜ ሀብተ ማርያም ሰዎችና በቅሎዎችን ልኮልኝ መንገድ ለመንገድ እያደርኩ ወደ አዲስ አበባ በደህና ዘለቅኩ፡፡ ወንድሜ ገ/መድኅንን ጨምረሮ 30 የሚሆኑ ዘመዶቼ ሸንኮራ ላይ ተቀበሉኝ፡፡ ሸላ ላይ ከ15 አመት በፊት የተለየሁት ወንድሜ ሀብተ ማርያም በፈረስ ተቀምጦና 3 ፈረሰኞች አስከትሎ በታላቅ ደስታ ተገናኘን፡፡
አዲስ አበባ የገባሁ እለት የአገሬን ልብስ ለብሼ ነበር፡፡ በማግስቱ ዘመዶቼ የፈረንጅ ልብስ ያስከብርሃል፣ ያማራው ልብስ ያዋርድሃል፣ እያሉ መክረው አስለወጡኝ፡፡ ስለዚህ ሐዘን ተሰማኝ፣ የተወልዶዬን መምሰል አምሮኝ ነበር፣ ተሳቀቅኩ፡፡ ወንድሜ ቤት እንደገባሁ የስልክ ሹሙ በየነ ይመር መጥቶ፣ ገና ሳንተዋወቅ ተክለ ሐዋርያት እያለ በስሜ ጠርቶ ጃንሆይ/ምኒልክ አንተን ለማየት ቸኩለዋል፣ በቶሎ እንድትመጣ አለኝ፡፡
በማግስቱ ወደ ጊቢ/ቤተ መንግስት እንደ አውሮጳውያን ለብሼ ሄድኩ፡፡ ልብሴ ሁሉ ፓሪስ የተሰፋ ዘመናይ ነው፡፡ ወደ ጊቢ ስገባ እስከ ውስጠኛው በር ድረስ ከበቅሎ እንዳልወርድ ዘመዶቼ አስጠንቅቀውኛል፡፡ ገና ወደ በሩ ቀረብ ስል በረኛው ዞር በሉ እያለ በመጮህ መንገዱን አስለቀቀልኝ፡፡ እንደ አማራ ለብሼ ቢሆን ኖሮ መመታት አይቀርልኝም ነበር፡፡ በገዛ አገሬ ውስጥ ለመከበሪያዬ የሰው አገር ልብስ መከታ ስለሆነኝ ልቤ ተቃጠለ፡፡
ወደ ጓዳ በሚወስደው መንገድ እስከ ልጅ በየነ ጓዳ ድረስ ከበቅሎ ሳልወርድ ገባሁ፡፡ ደጃዝማች ባልቻ ከማረፊያ ጓዳቸው ብቅ ብለው ወደ ከተማው ያስተውላሉ፡፡ በሩቁ አውቃቸዋለሁ፡፡ በልጅነቴ በጅሮንድ ሲባሉም አይቻቸው ነበር፡፡ ከበቅሎ ሳልወርድ ሰላምታ ሰጠኋቸው፣ እሳቸውም ቀኝ እጃቸውን አስጠግተው ሰላምታ ሰጡኝ፡፡ ማን እንደሆንኩ ጠይቀው ከፈረንጅ አገር የመጣሁ አማራ መሆኔን ሲነግሯቸው ችላ አሉኝ፡፡ ይህም አስቀየመኝ፡፡ እኔ ግን አማራ ብቻ ሳይሆን ሱማሌና ደንከሌን ሳይም ደስ ይለኛል፡፡ ገዢዎች የሆኑት እነ ደጃዝማች ባልቻ ሁሉ ግን፣ የኢትየጵያ ተወላጅ የሆነውን ሰው ማክበር ለራሳቸው ውርደት የሚሆንባቸው ይመስላቸዋል፡፡
ጃንሆይ/ምኒልክ በሸክላው ቤት ውስጥ፣ በታችኛው ክፍል በበሩ ፊት ለፊት፣ በድንክ አልጋ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ካጥሩ ጊቢ ተቀምጦ የሚጠብቀኝ ልጅ በየነ ሲጠቅሰኝ፣ ሰተት ብዬ ወደ ጃንሆዬ አመራሁ፡፡ ዘንግ ይዘዋል፣ ካባ ለብሰዋል፣ ራሳቸው በሻሽ ተሸፍኗል፡፡ ወደኔ ያስተውላሉ፣ ዐይኖቻቸው ትላልቆች ናቸው፡፡ እግሮቼን በአንድነት አጋጥሜ፣ ራሴን ጎንበስ አድርጌ ሰላምታ ሰጠሁ፡፡ ጃንሆይም ራሳቸውን ጎንበስ አደረጉና ጠቀሱኝ፡፡ ገባሁ፣ ከበሩ ላይ ዘወር ብዬ እፊታቸው ቆሜ ተናገርኩ፣
ጃንሆይ ከአድዋ ዘመቻ እንደተመለስን፣ ጌታዬ አሳዳጊዬ ራስ መኮንን ወደ ሩስያ ሰደዱኝ፡፡ እዚያ ስማር ቆይቼ መሞታቸውን ሰማሁ፡፡ ይኸው በ11 አመቴ ተመልሼ ወደ አገሬ መግባቴ ነው፡፡ ጃንሆይ እኔን አያውቁኝም፡፡ እኔ ግን ንጉሴን ማወቅ የተገባኝ ነኝ፡፡ ስለዚህ ከማናቸውም ነገር በፊት እንደ አንድ ዜጋዎ ሰላምታ ላቀርብልዎ እፊትዎ ቆሜያለሁ፡፡ የመጣሁበት ጉዳይ ለጊዜው ይኸው ብቻ ነው በማለት፣ ወዲያው የባሰውን ጉዳይ ነገርኳቸው፡፡
የናቴ ናፍቆት በርትቶብኛል፡፡ አንድ ጊዜ አይቻት በቶሎ እመለሳለሁ፡፡፡ ከዚያ በኋላ የጃንሆይን ፈቃድ ለመፈጸም የተዘጋጀሁ ነኝ አልኳቸው፡፡ ደግ ነው ሂድና እናትህን አይተህ ተመለስ፣ በዝግታ እንነጋገራለን ብለው አሰናበቱኝ፡፡
እናቴንና ቤተሰቦቼን በካሰት ተመልክቼ ወደ አዲስ አበባ ከተመለስኩ በኋላ፣ ወደ አዲስ አበባ ገስግሼ ከደጃዝማች ተፈሪ/በኋላ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ/ ጋር ተገናኘን፡፡ ከሀረር ወደ ሩስያ ቶሎ ለመሄድ ጓጉቼ፣ ራስ መኮንን ተፈሪን ሳትስመው ትሄዳለህ? በማለት የተናገሩኝ ቃል ዘወትር ይታወሰኛል፡፡ ተማሪዎች ገና ከት/ቤት ስላልወጡ ጠበኩና ያን ጊዜ 15/16 አመት የሚሆነውን ደጃ/ተፈሪን አገናኙኝ፡፡ ጉንጩን ስሜ ጥቂት ተነጋገርንና ነገ እመጣለሁ ብዬ ተለያየን፡፡
ከአዲስ አበባ የተገዛ ጥቂት ገጸ በረከት ይዜ በማግስቱ ተገናኘን፡፡ በጊቢው ውስጥ ልጅ ኢያሱን፣ ልጅ ገብሩን፣ ልጅ ጌታቸውን ሲጫወቱ አገኘኋቸው፡፡ ስለማንተዋወቅ ዝም ብዬ አለፍኳቸው፡፡ እነሱም እያዩኝ ተጠቃቀሱና ተንሸካሸኩ፡፡ የት/ቤቱ ደወል ስለተደወለ ደጃ/ተፈሪ ለማግስቱ ጣይቱ ሆቴል ምሳ ሊጋብዘኝ በ6 ሰአት እንድንገናኝ ተቃጠርን፡፡ ያን ጊዜ 11/12 አመት የነበረው ልጅ ኢያሱና ልጅ ብሩም እንደኔው ለምሳ ተጋብዘው መጡ፡፡
ልጅ ኢያሱ ዐይን አፋር ነው፣ እኔን እንኳን ፊት ለፊት ለማየት ይፈራል፡፡ ልጅ ብሩ በመንቀባረር እንዳሻው ይናገራል፡፡ ሁለቱም እየደጋገሙ አባባ ይሙት እያሉ ይምላሉ፡፡ ደጃ/ተፈሪ ብዙ አይናገርም፣ አይምልም፣ ከንፈሮቹን ብቻ ፈገግ እያደረገ፣ ጥርሶቹ ሲታዩ ለገጹ ውበት ይሰጡታል፡፡ በእውቀቱም፣ በንግግሩም፣ ባኳኋኑ ሁሉ በጣም ደስ አሰኘኝ፡፡ ትልቅ ተስፋም አሳደረብኝ፡፡ ምሳችንን እየበላን ስለ አውሮጳ ኑሮዬ ጠየቁኝ፣ ባጭሩ ሁሉንም ገለጥኩላቸው፡፡
ወደ ጅማ አባጅፋር ጋ ለአደን በመሄድ ከጅሬን ወደ ጌራ የሚወስዱኝ አሽከሮችና አጋሰሶች ተሰጡኝ፡፡ ዝሆንና አንበሳ ገድዬ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ፡፡ ጃንሆይ ታመው ቆይተው ደህና ሲሆኑኑ በጅሮንድ ሙሉጌታ አገናኘኝ፡፡ እንደፊተኛው ቀን እሸክላው ቤት ውስጥ በፎቁ ላይ በድንክ አልጋ ተቀምጠዋል፡፡ ድምጻቸው ሰንፏል፣ አይናቸው ደክሟል፣ አነጋገሩኝ፡፡ አሳዘኑኝ፣ ሁለተኛ እንደማላገኛቸው ተረዳሁ፣ እሳቸውም ተረድተውታል፡፡
ጃንሆይ በሩሲያ ለ10 አመት የተማርኩት ት/ት ለሀገራችን ለዛሬው ጊዜ የሚሆን አይደለም፡፡ እንደገና ተመልሼ ትምህርቴን ለመቀጠል ቆርጫለሁ፡፡ መድፍ መስራት ባይቻለን እንኳን፣ ጠመንጃና ጥይት እዚሁ በአገራችን ማሰናዳት የምንችልበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ በእርስዎ እድሜ እንዲፈጸም ምኞቴ የጋለ ነው፡፡ ወደ መስኮብና ወደ ጀርመን ንጉሥ ደብዳቤዎች ያሰናዱልኝ፡፡ ወደ አካዴሚያ ገብቼ እንድማር አደራ ይበሏቸው፣ 3 አመት በት/ት ቆይቼ ተመልሼ እመጣለሁ አልኳቸው፡፡ ጃንሆይ ተገርመው እንዴት ብርታት ተሰጥቶሃል ልጄ! 10 አመት የተማርከው አንሶ፣ ዳግም 3 አመት ልትማር ትሄድ? አሉኝ፡፡
አዎን ጃንሆይ! በጥቂት ዋጋ የሚገኘው ት/ት ላገራችን ጠቃሚ ሊሆን አይችልም፡፡ እኔ የማስበው የዘለቄታውን ለሀገራችን በሙሉ የሚሆነውን እንጂ፣ የእለቱን ለራሴ ጥቅም ብቻ የሚሆነውን አይደለም፣ ብዙ መድከም ያስፈልጋል አልኳቸው፡፡ ማለፊያ ነው ሂድና ተማር፣ ስትመለስ ባቡሩም እዚህ ይገባና ለሁሉም ይመቸሃል፡፡ አሁን ግን እኔም እያመመኝ እንደድሮዬ መሆን አልተቻለኝም፡፡ ቀደም ብለህ ተወልደህ ወይም መኮንን ሳይሞት መጥተህ ቢሆን ብዙ ስራ እንሰራ ነበር አሉኝ፡፡ ይህን ሲናገሩ ድምጻቸው ሰለለ፣ ምራቃቸውን ዋጡ፣ እምባቸው አቀረረ፡፡ በጣም አሳዘኑኝ!!!
የሕይወቴ ታሪክ፣ ፊታውራሪ ተ/ሐዋርያት ተ/ማርያም፣ አአዩ ፕሬስ፣ ገጽ 144-170
Filed in: Amharic