>

አቢይ አህመድ የሆሊውዱ ወንደርላንድ ዓለም ኗሪ እንጂ የኢትዮጲያ አይደለም (ወንድወሰን ተክሉ)

አቢይ አህመድ የሆሊውዱ ወንደርላንድ ዓለም ኗሪ እንጂ የኢትዮጲያ አይደለም
*** ወንድወሰን ተክሉ***

 

*… የጨረባው_መንግስት_ግርግር
 
*… መልከጥፉን በስም ቢደግፉ መልከጥፉነቷን አይለውጠውም- በቢሊዮን ብር ውጪ የተንቆጠቆጠው  ድግስ የአቢይን የከሽፈ መሪነት ህይወት ዘርቶ ተቀባይነትን አያመጣም!
የጨቅላውና ጮርቃውን አቢይ አህመድ አጠቃላይ እሳቤን ስራንና ምኞቱን ስመለከት አሊስ በወንደርላንድ የሆሊውድ ፊልም (አንጀሊና ጆሊን ጨምሮ በርካታ እውቅ አክተሮች በመሪነት የተጫወቱት ፊልም) ያስታውሰኛል።
ወንደርላንድ የህልም ወይም የቢሆን ዓለም ተብሎ የሚጠራና በገሀዱ ዓለም የሌለ ዓለም እንደመሆነ መጠን ከእጽዋት አይነቶች አንስቶ ከረቂቅ እስከ ልሂቅ ፍጥረታት በሙሉ ፈጽሞ ያልታዩና ልዩ ዓይነት የሆኑ ፍጥረታት የሚረመሰመሱበትና ተዓምራዊ ኩነቶች እለታዊ የህወት ገጠመኝ በሆነበት ምናባዊ ዓለም ውስጥ እንዳለ ሰው አቢይ እመራታለሁ በሚላት ሀገራችን ሁኔታና እሱ ደግሞ መሪነቱን እያሳየበት ያለበት ሁኔታ ሰማይና ምድር ያህል የተራራቀ ከመሆኑ የተነሳ አቢይ ያለው በወንደርላንድ ዓለም ውስጥ ነው እንድል አድርጎኛል።
በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በጅቶ የተንበሸበሸ ድግስ በመደገስ «ኑና ንግስናዬን አድምቃችሁ እውቅና ስጡልኝ» በማለት የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር እንግዶችን በገፍ ጠርቷል።  የማእከላዊ አፍሪካ መሪ የነበረው ፊደል ቦካሳ በአንድ ወቅትና በዘመኑ (በ1980ዎቹ) የሀገሪቱ ዜጋ በአሰቃቂ ኋላቀርነትና ድህነት እየማቀቁ ባለበት ሰዓት እሱግን ቅልጥጥጥ ያለ ድግስ ደግሶ የንግስና ሰርገላውን የሚጎትቱ ፈረሶችን ሳይቀር ከቤልጂየም አስመጥቶ እራሱን «KING BOCASSA» ብሎ ሰይሞም እንደነበረ አይዘነጋም።
የዛሪይቱ ኮንጎ የያኔዋ ዛየር መሪ የነበረው ሞቡቱ ሴሴኮም ዛየራዊያን(ኮንጎያዊያን) በመሰረት ልማት እጦት እና እልም ባለ ድህነት በሚማቅቁበት ወቅት እሱ ግን በዚያን ጊዜው የገንዘብ መግዛት አቅም ከ$5.4ቢሊዮን በላይ ዶላር (5.4BILLION dollars $)ገንዘብ በግል አካውንቱ ውስጥ አጭቆ በፈረንሳይ በቤልጂየም በስዊዝ በሞሮኮ…….ወዘተ ባስገነባቸው ቤተመንግስቱ እየዞረ ይመነሸነሽ ነበር።
አቢይ አህመድ አሊ ዛሬ ድምጽ ሰርቆና ዘርፎም ይሁን ብቻ በ2016-2018 በተካሄደ ታላቅ ሕዝባዊ አመጽ እድል ተጠቅሞ ወደስልጣን ከመጣበት እለት አንስቶ ከአረብ ሀገራት በእያንዳንዳችን ስም (በኢትዮጲያ ስም የተወሰደ ብድርም ይሁን በልመና የተገኘ ነጻ ገንዘብ በእያንዳንዳችን ስም የተገኘ ገንዘብ መሆኑን ልብ ይሏል)  የሰበሰበን  ከ$6ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለቤተመንግስቱና ለጽህፈት ቤቱ ማስዋቢያ፣ ለስፍር ቁጥር የሌላቸው ፓርኮችና መናፈሻዎች ማስገንቢያ ሆጭ አድርጎ በማፈሰስ አለሙን የሚቀጭ የፋንታሲ FUNTASY ዓለም ኗሪ እና መሪ ይመስላል እንጂ በትንሹ ከ6.7ሚ ህዝብ በላይ በእሱ አገዛዝ ተፈናቅለው ለርሃብ የተጋለጡባትና በእሱ መሀይማዊ የፖለቲካ ፖሊሲ ምክንያት በአስርሺዎች የሚቆጠሩ የረገፉበት የእርሰበርስ ጦርነት ያስጨናቃት እና ኢኮኖሚያዊ ቀጥ ሊል አንድ ሀሙስ የቀራት ሀገር መሪ ፈጽሞ አይመስልም።
ከቀናት በፊት በተካሄደው በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድሮችን የመመስረቻ  ትርጉመ ቢስ ፕሮግራምን ጨምሮ ነገ ሰኞ 04-10-21 ለሚያሳውቀው መንግስት ተብዬ ምስረታው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መድቦ አዘጋጅ ኮሚቴ አቌቁሞ መጠነ ሰፊ የከበርቻቻ ድግስና አብለጭልጮ የደገሰ ሲሆን ይህንን ሁሉ ወጪ ለከንቱው ፕሮግራሙ ሲያውል የፕሮግራሙን ከንቱነትና የራሱንም ውስጠ ባዶነትን በብልጭልጭ ነገር ሸፋፍኖ ተቀባይነት ያለው ለማስመሰል መሆኑን ስለምናውቅ እኛ ኢትዮጲያዊያን መልከጥፉን በስም ቢደግፉ መልኴን አይለውጠውም ብለን በመተረት እንሳለቅበታለን እንጁ በጮርቃው ጨቅላዊና ኮልኮሌያዊ ድግስ የምንገረምም ሆነ አመለካከታችንን የምንለውጥ አይደለንም።
ይልቅስ የጨቅላው መጠን ያለፈ ሽርጉድ የሚያሳየንና የሚያረጋግጥልን ነገር ቢኖር የእሱን ፍጹም የለየለት Heartless መሆኑን ብቻ ሳይሆን የእሱን በግለ ምናባዊ የቢሆን ዓለም ውስጥ ያለ ሰው መሆኑን ቁልጭ አድርጎ  ያረጋገጠልን ሽርጉድ ሆኖ እንድናየው ነው ያደረገን እንጂ የምንቃወመው ግን ቢያንስ የመንግስትነትን ባህሪይ ያሟላ ጨቌኝ መንግስት እንኴን ብለን የምናየው አይደለም።
ለዚህም ነው አቢይ አህመድ አሊ በስልጣን መቀጠል የኢትዮጲያ ብሄራዊ ደህንነት ስጋት ምንጭ ነው የምንለውና በውድም ይሁን በግድ ስልጣኑን  መልቀቅ አለበት የምንለው።
እናም አንዳችም የሚመሰረት አዲስ የሚባል መንግስት በሌለበትና እራሱ የህወሃት ወራሽ ልጅ የሆነው ኢህአዴግ ቁጥር 2 በራሱ በህወሃታዊ ሕገ መንግስትና በህወሃታዊ አይዮሎጂ ሀገርና ህዝብ እያሰቃየ ያለ ሰው ብቁ ተፎካካሪዎቹን በእስር ተከርቸም አስገብቶ የህዝብን ድምጽ በጠራራ ጸሀይ በመስረቅ እራሱን የተመረጠ ለሚያስመስለው ጮርቃ ፈጽሞ የመንግስትነትን እውቅና የምንሰጠው ስብስብ አይደለምና ትግሉ ይበልጥ ተጠናክሮ ይጧጧፏል እንጂ መንግስት አለን ብለን ለአፍታም የምንዘናጋበት አይሆንም።
Filed in: Amharic