>

ይድረስ ለ"ኢትዮጵያ ንጉሥ"...!!! (አሳዬ ደርቤ )

ይድረስ ለ”ኢትዮጵያ ንጉሥ”…!!!

አሳዬ ደርቤ እባላለሁ።

ከልጅነትዎ ጀምረው ሲመኙት የኖሩትን ዙፋን ከእጅዎ ውስጥ ያስገቡበትን ስልት እና ሥልጣንዎን የተመኘን ሃይል ከእግርዎ ስር የሚጥሉበትን ብልሀት አደንቃለሁ፡፡ ‹‹ቀንድ ያቆጠቆጠውን በድሮን ፣ ጭራ ያበቀለውን በሥልጣን›› እንዲል ‘መጽሐፈ ዙፋን’ ተቀናቃኞችዎን  አገልጋዮና ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጭ የሚያደርጉበትን ጥበብ አደንቃለሁ፡፡
ከዚህ ባለፈ ግን በሥልጣን ዘመንዎ በወገኔ ላይ የተፈጸመውን ግፍ ለመጻፍ ብሞክር፣ ‹‹መጤ ነህ›› የተባለ ይመስል ከጭንቅላቴ ተፈናቅሎ ፊቴ እና አንገቴ ስር የተጠለለ ጸጉሬ እንደ ንጹሐን ነፍስ ስለሚረግፍ ‹‹ዳውን ዳውን›› ከማለት ውጭ የምለዎት አይኖርም፡፡
ይልቅ ዳውን ዳውን ስል ምን ትዝ አለኝ መሰልዎት?
ትናንት ኤሬቻ በዓል ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡ እናም ከፊት ለፊቴ የቆሙ ጥቂት ወጣቶች ሥምዎን እየጠሩ ዳውን ዳውን ሲሉ ሰማሁና ክንዴን ሰቅስቄ ተቃውሟቸው ልጋራ ስል ‹‹ዳውን ዳውን ነፍጠኛ›› ማለት ጀመሩ፡፡ ያን ጊዜም ለተቃውሞ የጨበጥኩትን ክንዴን አውርጄ ከአካባቢው ጠፋሁ፡፡ ስቀልድ ነው ንጉሥ ሆይ! 😁
ጃል ሆይ (ማለቴ ጃን ሆይ)፡-
 በእርስዎ አማላይ ቃላት የተማረኩ ዜጎች በሰጡት ድምጽ የተመረጠ ቃላ’ባይ ፓርቲዎ ለቀጣይ አምሥት ዓመት ኢትዮጵያን ማፍረስ ወይም ማደስ የሚችልበትን እድል አግኝቷል፡፡ በበኩሌ ግን የፓርቲዎ ፌሽታና የሕዝቡ የዋይታ ዘመን መቀጠል የለበትም ብየ ስለማስብ የነገው በዓለ ሢመትዎ ላይ ከሹማምንትዎ ጋር እንዲህ ብለው ቃል ቢገቡ ደስ ይለኛል፡፡
‹‹ከጥይት የተረፈው ሕዝብ ፥ ርቦት እህል ውሃ ሲል
ለፓርክ፣ ለፓርቲ ምረቃ ፥ ድግስ ማሳመር ይበቃል፡፡
ቤተ-መንግሥቱ ቀርቶበት-
የሣር ጎጆውን ተነጥቆ- ሲሰደት የከረመን ሕዝብ፤
ዙፋን የያዘ ይመስል
‹‹ዳውን ነፍጠኛ›› እያሉ- ሰሚ አልባ ጩኸት ማነብነብ፤
ሰሜንን ለችግር ዳርጎ- ምዕራብ ላይ ፋብሪካ መትከል
አገርን እያዳከሙ- በሥሟ መቅጠፍ ይበቃል።
ሌላው ደግሞ ንጉሥ ሆይ፡- ከወራሪ መዳፍ ስር ጥለው የረሱት ሕዝብ ፓርቲዎን የመረጠው የእርስዎን ቃላት በመሸመደዱና ሕልምዎን በመውደዱ የተነሳ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ እርስዎ ግን ከፍቅር ይልቅ ብሔር የሚገዛዎት ይመስል ጦሩ ሲወጋ ፈጥኖ የደረሰዎለትን ሕዝብ ባላሰበው ጊዜ ለጥቃት ተዳርጎ ሲገደልና ሲፈናቀል ‹‹ሥራህ ያውጣህ›› ብለው ድምጽዎን አጠፉ፡፡
እኔ እምለው ክቡር ሆይ እልፍ አእላፍ ነፍስ ከያዙ ከተሞች ጋር የላሊበላ ቤተ መቅደስ ሕልውና በአሸባሪ ቁጥጥር ስር መውደቁ ካላስደነገጥዎት እርስዎ አገር የሚሉት ምኑን ይሆን?
በአገራቸው ውስጥ ከተፈናቀሉት ይልቅ ወደ ጎረቤት አገራት የሚሰደቱት የተሻለ ድጋፍና ክብር የሚያገኙ ከሆነስ መንግሥት ቀርቶ አገር አለኝ ማለት ይቻላል?
አሁንም ቢሆን ጃን ሆይ የእርስዎ ሥርዓትም ሆነ የኢትዮጵያ አንድነት እንዲቀጥል ከፈለጉ በዓለ ሲመትዎ በተፈጸመ ማግሥት ወራሪው ቡድን ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ በቸነፈርና በላውንቸር በመርገፍ ላይ የሚገኘውን ሕዝብ መታደግ ግድ ይለዎታል፡፡
ሌላው ደግሞ…
 ባለፉት ሦስት ዓመታት አገሪቱን ሲመሩ የነበሩት በአሸባሪው እቅድ እንጂ በእራስዎ እቅድ መሠረት እንዳይመስልዎ፡፡ በተለይ ደግሞ በ2013 ዓ.ም የፓርክ እቅድዎን ትተው ታንክ በመግዛት ከመቶ ቢሊዮን በጀት ጋር መቀሌ የከረሙት የጁንታውን የጦርነት እቅድ በመረከብዎ ነው፡፡ በቀጣይም የመጀመሪያ እቅድዎ ይሄን አውዳሚ ድርጅትና አስተምሕሮውን ማጥፋት የሚል ካልሆነ በቀር የአሸባሪውን የውድመት እቅድ በግልባጭ መቀበል እንጂ የእራስዎን የልማት እቅድ መጻፍ አይጠበቅብዎም፡፡  የእሱ የሤራና የተንኮል እቅድ ላይ “መከላከል” የሚል ተግባር  መጨመር ብቻ ይበቃዎታል፡፡ እናም ይህ እንዳይሆን ከፈለጉ ከምዕራቡ ማዕቀብ ይልቅ የሕዝብን ሐሳብና የአገርን ፍላጎት በማስቀደም በአሸባሪው ከፈን ላይ አገርዎን ማስቀመጥ ግድ ይለዎታል፡፡
በመጨረሻም…
ወዲ ዜናዊ  አንዱን እጠቅማለሁ ሲል የማንም ሳይሆን ባለፈበት የጥፋት ድርሳን እየተመራ አዲስ ነገር ሊሠራ ከሚያስብ መሪ ይልቅ ከቻለ ሕዝቡን፣ ካልቻለ እራሱን ለመሆን የሚጥር መሪ ከሕልፈት በኋላም ሕይወት አለው፡፡
ስለሆነም የተቀመጡበት የዘር ዙፋን ሰውነትዎንና ዜግነትዎን ቀምቶ ነገ የሚለብሱትን ከፈን እንዳያስረሳዎት ሰው ሆነው እርቃንዎን እንደተወለዱ ሁሉ ሰው ሆነው እንደሚሄዱ ያስቡ፡፡  ያን ጊዜ ጎዳና ላይ ከወደቀ ሕዝብዎ መሃከል የሚያስታውሱትና የሚያነሱት እንዲ ውድቀቱን የሚያረሳሱት ሕዝብ አይኖርም እያልኩ የቀጣይ የጠቅላይነት ዘመንዎ እንደባለፈው የሕዝብዎ ሕይወት እንዳይሆን እመኛለሁ፡፡
ለፓርቲዎ ደግሞ…
 የሕዝብ ጉርስ ሰብስቦ የፓርቲ ድግስ የማይደግስበት፣ በንጹሐን እልቂት ላይ ሥልጣኑን የማያጠናከርበት፣ አገር እያፈረሰ ቪላ የማይቀልስበት፣ የለቅሶ ድንኳን ውስጥ የማይደንስበትና የሁለት ፓርቲ አመራር ሆኖ የማይነግድበት ይሆን ዘንድ እመኛለሁ፡፡
Filed in: Amharic