የምርጫ መታዘብ ሁኔታ ላይ ከኢሰመጉ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
መስከረም 23 ቀን 2014 ዓ.ም
መግቢያ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ በርካታ እንቅስቃሴዎችን ሲያደረግ መቆየቱ ይታወሳል። ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች መካከል በቅድመ ምርጫ፣ በድምጽ መስጫ ዕለትና ድህረ-ምርጫ ወቅቶች ያለውን አጠቃላይ የምርጫ ሒደት መታዘብ፣ የመራጮች ትምህርት እና በምርጫ ወቅት የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታን ክትትል
ማድረግ ቀዳሚዎቹ ናቸው። ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ምርጫ በተከናወነባቸው በአብዛኛዎቹ የምርጫ ክልሎች ላይ ከ500 በላይ ታዛቢዎችን በማሠማራት የምርጫ መታዘብ ግኝቱን የመጀመሪያ ደረጃ (ቀዳሚ) መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡
መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ምርጫ ባልተከናወነባቸው በቀሪ የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ የተደረገ ሲሆን፤ በእነዚህ የምርጫ ክልሎች ላይ ኢሰመጉ ከ140 በላይ ታዛቢዎችን አሠማርቷል፡፡ የምርጫ መታዘብ ግኝቱን የመጀመሪያ ደረጃ መግለጫ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት አጠናቆ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ ሲሆን፤ የሰኔውን ምርጫ ጨምሮ ጥቅል
የመታዘብ ግኝቱን በመጪዎቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ይፋ እንደሚያደርግ ያስታውቃል፡፡
በሶማሌ እና በሐረሪ ክልሎች ባሉ ሁሉም የምርጫ ክልሎች እንዲሁም በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ባሉ የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ ተከናውኗል፡፡ ኢሰመጉ በቅድመ-ምርጫ ወቅት በሶማሌ ክልል እና በደቡብ ክልል ካፋ ዞን፣ ቦንጋ ከተማ እና በሶማሌ ክልል፣ ፋፈን ዞን፣ ደንዳማ ወረዳ፣ ኮሌጂ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ በመገኘት በገጽ ለገጽ ስልጠና ከተለያዩ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ለተውጣጡ መራጮች የመራጮች ትምህርት የሰጠ ሲሆን፤ አምስት የተለያዩ የራዲዮ መልዕክቶችን በሶማሌኛ ቋንቋ በማዘጋጀት ዜጎች በእውቀት ላይ የተመሰረት ምርጫ እንዲያከናውኑ የሚረዱ መረጃዎችን አስተላልፏል፡፡ እንዲሁም በአማርኛ እና በሶማሌኛ ቋንቋ የተዘጋጁ በራሪ ጽሁፎችም የመራጮች ትምህርት ከተሰጠባቸው መንገዶች መካከል አንዱ ነው፡፡