>

ከአዲሱ መንግስት ምን ይጠበቃል (አልይ እንድሬ)

ከአዲሱ መንግስት ምን ይጠበቃል

(አልይ እንድሬ)


  ለ 25 ዓመት ያህል በህውሃት/ኢህአዴግ ታፍኖ የቆየው ህዝብ ለረጅም ጊዜ የተከማቼ ብሶቱን በኢትዮጲያ ጎዳናዎች ላይ ወጥቶ በመግለፅ በ2008 ዓ.ም ሀገሩን በተቃውሞ ድምፅ አጥለቀለቀው፡፡ ጠመንጃቸው እስካለ ድረስ ለህዝብ እልቂት ግድ የሌላቸው የህውሃት/ኢህአዴግ ባለስልጣናት ምርጫ ተጭበርብሯል በማለት በባዶ እጁ ተቃውሞውን ለመግለፅ የወጣውን ወጣት በ1997 ዓ.ም እንዴት እንደጨፈጨፉት በገሃድ ታይቷል፡፡ ከዛ ክስተት ወዲህ ለ11 ዓመት ያህል  በስልጣናቸው ላይ መቆየታቸው በ97 የፈፀሙት ጭፍጨፋ ሊፀፅታቸው ቀርቶ በልባቸው ውስጥ የማን አለብኝነት እብሪትን ገንብቷል፡፡ በ2008 ዓ.ም ተቃውሞ የወጣውን ወጣት በሚዲያ እየዘለቁ ልክ እናስገባቸዋለን ሲሉ መሰማታቸው ለህዝብ ያላቸውን ንቀትና እብሪት ክፉኛ አሳበቀባቸው፡፡ እንደተለመደው ታዛዥ ሰራዊታቸውን አሁንም (በ2008 ዓ.ም) ለተቃውሞ በወጣው ህዝብ ላይ አሰማሩት፡፡ ግን ሙላዕተ ህዝቡ በስርዓቱ ላይ ቆርጦ ተነስቷልና ሰራዊት አሰማርተው ጥይት ቢያዘንቡበትም ትግሉን አፋፍሞ ቀጠለ እንጅ የሚቀዘቅዝ አልሆነም፡፡ ልክ እናስገባቸዋለን የሚለው የእብሪት ቃል በአራቱም አቅጣጫ ያለውን የአገሪቱን ህዝብ ክፉኛ አስከፍቶታል፡፡ በተቃውሞው እንዲበረታ እና አንድ እነዲሆንም ረድቶታል፡፡ ተቃውሞው በየአቅጣጫው ተቀጣጠለ፡፡ ኦሮሚያ ላይ የተጀመረው ተቃውሞ አማራ ክልልንም አጥለቀለቀው፡፡ የአማራው ወጣት የኦሮሞው ደም የኔም ነው ብሎ ተነሳ እየደማ እና እየተሰዋም ቃሉን በተግባር አረጋገጠ፡፡  ጎንደር፣ባህር ዳር፣ወልደያ መርሳ፣ በህዝብ ቁጣ ተናወጡ፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች  ቤቶች ተቃጠሉ፣ አንዳንድ የህውሃት ደጋፊዎችም በቤት ውስጥ እንዳሉ ተቃጥለዋል (ለምሳሌ መርሳ)፡፡ ተቃውሞው እንደ ቋያ እሳት ሀገሩን ለበለበው፡፡ ልክ እናስገባቸዋለን እያሉ ሲፎክሩ የነበሩት የህውሃት ባለስልጣናት የሚይዙት የሚጨብጡት አጡ፡፡ማዕበሉ እንደማይቆም ቁርጡን አወቁት፡፡ህዝብን ገሎ መጨረስ አይቻልም ለካ!!፡፡ 97ን ጨምሮ በተለያዩ ዓመታት ህዝቡ በመንግስት ብልሹ አሰራር ላይ ያለውን ተቃውሞ ሲገልፅና ውድ ልጆቹንም የጥይት ሰለባ ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም በስርዓቱ ላይ ያለው የይሻሻላል የተስፋ ጭላንጭል ከህዝቡ ልቦና ውስጥ ጨርሶ የጠፋው በ2008  ዓ.ም ይመስላል፡፡ ልባቸው በእብሪት ለተደፈነው ህውሃቶች/ኢህአዴጎች ግን ወትሮም ቢሆን ህዝቡ የሰናፍጭ ፍሬ ለምታክል የይሻሻላልተስፋው ሲል እየተሸነፈላቸው እንጅ እያሸነፉት እንዳልሆነ የገባቸው አይመስልም፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ ልክ እናስገባቸዋለን ብለው በህዝብ ላይ ባልዛቱ ነበር፡፡ 

   የሆነ ሆኖ ለ27 ዓመት ያህል የኢትዮጲያን ህዝብ ንብረት ሲዘርፍና ሲበዘብዝ የኖረው ህውሃት በህዝብ ማዕበል ሲገፋ ቆይቶ በ2010 ዓ.ም ከስልጣን ወንበሩ ላይ ተንሸራቶ ወረደ፡፡ፓርላማው ተሰብስቦ እስከ ምርጫ ጊዜ ድረስ ዶ/ር አብይ አህመድን የኢትዮጲያ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰየመ፡፡ በየአምስት አመቱ የሚካሄደው ምርጫ በ2012 ዓ.ም ይካሄድ የነበረ ቢሆንም ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሆኖ በተከሰተው ኮቪድ-19 ምክንያት ሳይከናወን ቀረ፡፡ ህውሃት የኢትዮጲያን ሰራዊት ከድቶ በመውጋት ጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም በሀገሪቱ ላይ የከፈተው ጦርነትም ምርጫው እንዲራዘም የራሱን አስተዋፅኦ አበረከተ፡፡ በነዚህ ሁኔታዎች የተራዘመው ምርጫ ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ተከናወነ፡፡ እነሆ ዛሬ መስከረም 24/2014 ዓ.ም በምርጫ ውጤቱ መሰረት አዲስ መንግስት ተመሰረተ፡፡ የተፎካካሪ ፓረቲዎችንም ጭምር ያካተተ በመሆኑ አዲሱ የመንግስት ምስረታ ጥሩ ጅምር የታየበት ሂደት ነው፡፡ 

      ሊበታትኗት የሚጥሩ የውስጥና የውጭ ሴረኞችን ደባና ተንኮል ተቋቁማ ኢትዮጲያ ባካሄደችው ምርጫ መሰረት መንግስቷን መሰረተች፡፡ ይህ ትልቅ ድል ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ኢትዮጲያ ባለፉት ሶስት በተለይም በመጨረሻዎቹ ሁለት ዓመታት በርካታ ቀውስ ውስጥ (ጦርነት፣ በጦርነት ምክንያት የህዝብ እልቂትና መፈናቀል፣ከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣ወ.ዘ.ተ) የገባች በመሆኑ  ለእነዚህ ችግሮች የማያዳግም መፍትሄ ከመስጠትና የሀገሪቱን ሰላምና ልማት በአስተማማኝ ሁኔታ ፈር ከማስያዝና ከማረጋገጥ አኳያ ከአዲሱ መንግስት በቀጣይስ ምን ይጠበቃል? የሚለው ጉዳይ የትኩረት ነጥብ ነው፡፡ 

Filed in: Amharic