>
5:13 pm - Friday April 18, 6577

ሕወሓት እና ሌሎች .... (ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ)

ሕወሓት እና ሌሎች ….

ቴዎድሮስተክለአረጋይ

    በትግራይ ሁለት አይነት የፖለቲካ ቡድኖቾ አሉ ። ሕወሓትና ሌላው ። ሌላው ከሕወሓት በላይ አደገኛ ነው ። ሌላው ማለት በሕወሓት አክቲቪስትነት የጀመረና ከአክቲቪስትነት ያደገው ፖለቲከኛ ሲሆን ትግራይን እንገነጥላለን የሚለው ሲሆን ሕወሓት ማለት ደግሞ ለወቅታዊ ፖለቲካ ፍጆታ ምንም ቢል የትግራይን መገንጠል የማይደግፈው ሀይል ማለት ነው ። ለብዙዎቻችን ላይመስል ይችላል ። አክቲቪስቶቹን ያለመጠን ያሳደገና ባሳደጋቸው የተዋጠ ኃይል ነው ሕወሓት ማለት ። ሌላው ኃይል ትግራይን እንገነጥላለን እያለ የሚፈላበት ኃይልና ራሱ ያነደደውን እሳት ለማጥፋት የሚጥረው ኃይሎች ማለት ናቸው ሕወሓትና ሌላው ።
    ይህን ለመረዳት ሩቅ መሄድ አያስፈልግም ። የድርጅቱ ቁንጮና ቀማሪ አቦይ ስብሀት ነጋ ከጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ጋር ያደረጉትን ቃለመጠይቅ ማየት ብቻ ይበቃል ። በዚያ ቃለመጠይቅ ዳዊትና አቦይ ስብሀት ቦታ ተለዋውጠው ነበር ። ጋዜጠኛው ዳዊት የመገንጠልን አስፈላጊነትና ትግራይ እንደማንኛውም ክልል የተሰጣትን ተቀባይ መሆን እንደሌለባት ሲናገር ፖለቲከኛው ስብሀት ነጋ ግን የተረጋጋና ብዙዎቻችንን ያስደነቀ መልስ ነበር የሰጡት ። ( እባካችሁ ሊንኩ ያላችሁ አስተያየት መስጫው ላይ አስቀምጡልን ) በዚህ ወቅት ሀገር ከእርግማን ወጥቶ ይህን የመስማት ፍላጎት እንደሌለው አውቃለሁ ። እንግዲህ እያንዳንዳችን እንደ እያንዳንዳችን መኖር አለበት ። ያ ቃለመጠይቅ ለታሪክ ፍርድ ይቀመጥ ። ” ፍልስምና ፮ ” ን ለመስራት መቐለ በሄድኩ ወቅት የአቦይ ስብሀት ቃለመጠይቅ ተሳክቶ ቢሆን ከምጠይቃቸው አንዱ እነዚህኑ አክቲቪስቶች የተመለከተ ነበር ።
    እርግጥ ነው ሕወሓቶች እነዚህን ” ካልተገነጠልን ” ባዮችን ሙሉ በሙሉ አፋቸውን ማዘጋት አይፈልጉም ። የራሳቸው ትልልቅ የሚባሉ ሰዎችም ( ማን ወ/አረጋይ ነው የሚባሉት ? ) ስለመገንጠል ሲያነሱ አቧራውን በመፈለግ እንጁ እሱ የሕወሓት ፍላጎት ሆኖ አይደለም ። ጥያቄውን ማስቆም አቅቷቸውም አይደለም ። ሁሌም ሕወሓቶች ስጋት የመፍጠር ፖለቲካ ስልትን ነው ሲከተሉ የኖሩት ። ” ሌሎች ካልተገነጠልን እያሉ እኛ ነን ይዘን ያቆየነው ” ማለት ይፈልጋሉ ።
ሕወሓቶች ትግራይን መገንጠል ቢፈልጉ ጨዋታው ይህ ባልሆነ ። ለትግራይ ሕዝብም እዚያ የሚያደርስ ግድ የላቸውም ። እንደዚያ ቢያስቡ 30% የሚሆነውን ህዝብ እርዳታ ተቀባይ አድርገው ባላኖሩት ። የመንገድ ፣ የውሀ እጥረት ባልገጠመው ። ጉስቁልናው ጥግ ባልደረሰ ።
ነገ ሀገር የሚያደርጓትን ክልል እንዲህ ባልደቆሷት ነበር ። አመዛኞቹ የሕወሓት ባለስልጣናትና የትግራይ ሕዝብ የተዋወቁት ከአራት ኪሎ ሲባረሩ ነው ። ሕወሓቶች ትግራይን ከመገንጠል በላይ ኢትዮጵያን ማፍረስ የሚፈልጉ ይመስለኛል ።
Filed in: Amharic