>

‘‘ኢትዮጵያ አፍሪካ እናት…’’ እንዴት?! (በዲ/ን ተረፈ ወርቁ)

‘‘ኢትዮጵያ አፍሪካ እናት…’’ እንዴት?!

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ


‘‘ኢትዮጵያ የአፍሪካ እናት ነች፡፡ እኛ አፍሪካውያን የኢትዮጵያ ቤተሰቦች ነን…፡፡’’ ባለፈው ሰኞ በመስቀል አደባባይ በተካሄደው የጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ በዓል ሲመት ላይ ከተገኙት አፍሪካውያን እንግዶቻችን መካከል አንዱ የነበሩት የኬንያው ፕሬዚዳንት እሁሩ ኬንያታ ካደረጉት ንግግር የተቀነጨበ ነው፡፡

በርግጥም ሀገራችን ኢትዮጵያ- ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች እናት መሆኗ በታሪክ መዛግብትና በታላላቅ ሰዎች አንደበት ደጋግሞ የተመሰከረለት ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካና ለጥቁር ሕዝቦች ታሪክና ሥልጣኔ፣ ቅርስና ባህል፣ ነጻነትና መብት ያደረጉትን ታላቅ ውለታ በተመለከተ በርካታ ምስክሮችን ማንሳት እንችላለን፡፡ ለአብነትም ያህል፤

ከመጽሐፍ ቅዱስ እስከ ቅዱስ ቁርኣን፣ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ መሐመድ፣ ከግሪካውያኑ ጠቢባን፣ ፈላስፋዎች እና የታሪክ ምሁራን ከሔሮዱተስ እስከ ሆሜር፣ ከጥቁር ሕዝቦች መብት ታጋዮች እና ፓን አፍሪካኒስቶቹ- ከማርከስ ጋርቬይ እስከ ዊሊያም ኤድዋርድ ቡርግሃርድ ዱ ቦይስ፣ ከጋናው የነጻነት አባት ከዶ/ር ኬዋሜ ንኩርማህ እስከ የኬንያው የነጻት አባት ጆሞ ኬንያታ፤

ከደቡብ አፍሪካው የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ እስከ ኦሊቨር ታምቦ እና ታቦ እምቤኪ፣ ከዚሙባቡዌው ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ እስከ ሴኔጋላዊው ሴዳር ሴንጎር… ወዘተ. ያሉ ታላላቅ ሰዎች- ሀገራችን ኢትዮጵያ ‘‘የአፍሪካ እናት’’፣ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ የአፍሪካዊነት/የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ እና ሥልጣኔ፣ ባህል እና ቅርስ፣ ነጻነት እና እኩልነት መሠረት መሆኑን ደጋግመው መስክረዋል፡፡

ይህን የታሪክ እውነት የፀረ-አፓርታይድ ታጋይ፣ የነጻነት አርበኛ እና የዓለም ሰላም ኖቤል አሸናፊ የሆኑት ኔልሰን ማንዴላ፣ Long Walk to Freedom በተባለ መጽሐፋቸው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት- ለደቡብ አፍሪካውያንና ለአፍሪካ ሕዝቦች የነበረውንና ያለውን ታላቅ ክብርና ስፍራ በተመለከተ እንዲህ ሲሉ ነበር በአጭር ቃል የገለጹት፤

‘‘Ethiopia always has a special place in my imagination & the prospect of visiting Ethiopia attracting me more strongly trip to France England & America combined, I felt I would be visiting my own genesis.’’

‘‘ኢትዮጵያ በልቤ ውስጥ ሁልጊዜም ልዩ ቦታ አላት፤ የፈረንሳይን፣ እንግሊዝንና አሜሪካንን በጥምር ከምጎበኝ ወደ ኢትዮጵያ ሄጄ ኢትዮጵያን መጎብኘት የበለጠ ይስበኛል፣ ትልቅ ደስታንም ይሰጠኛል፡፡ ይህም የራሴን [የአፍሪቃዊነቴን] የታሪክና የሥልጣኔ መሠረት የጎበኘሁና ያገኘሁ ያህል ሆኖም ይሰማኛል፡፡’’

ሀገራችን ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን ነጻነትና መብት፣ ለሰብአዊ ክብራቸውና እኩልነታቸው ካደረገችው ውለታዎች መካከል ጥቂቶቹን ለማንሳት እወዳለሁ፡፡   

ኢትዮጵያ በዓለማችን ሰላም እንዲሰፍን ከባለ ቃል ኪዳን አገሮች ማኅበር/League of Nations እስከ ተባበሩት መንግሥታት/United Nations መቋቋም ድረስ ብቸኛ አፍሪካዊትና የጥቁር ሕዝቦች ተወካይ በመሆን ደማቅ የሆነ አሻራዋን ያኖረች ናት፡፡ ሀገራችን የአፍሪካ ሕዝቦች ሰላም፣ አንድነትና የወንድማማችነት መስፈንና ብሎም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን/Organization of African Union፣ በኋላም የአፍሪካ ኅብረትን/African Union በማቋቋም ግንባር ቀደሙንና ትልቁን ሚና የተጫወተች ናት፡፡

‘‘ኢትዮጵያ ለእኛ ለአፍሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች እናታችን ናት፤ የነጻነታችን ትእምርት/Symbol የሆነች አገርም ናት፡፡ ስለሆነም አዲስ አበባ ‹‹የፓን አፍሪካን መዲና›› (የአፍሪካ አንድነት ከተማ) መባሏ ከዚህ ታሪካዊ ሐቅ ጋር የተያያዘ ነው…፡፡’’ (የናይጄሪያው ሳንዴይ ኦብዘርቨር/ጁላይ 23፣ 1972)

የጊኒ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሴኮ ቱሬ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር- ለአፍሪካ አንድነት ምስረታ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ያደረጉትን ታላቅ አስተዋጽኦና ሥራ በተመለከተ ሲናገሩ እንዲህ ነበር ያሉት፡-

… ኢትዮጵያዊ ታላቅ ሕዝብ ነው፡፡ ስለ አፍሪካ ነፃነት በጀግንነት የተዋጋ፣ ነፃነትም ቋሚ እንዲሆን፣ ሕዝቦቻችን ያለ ምንም የውጭ መንግሥታት ተቆጣጣሪነትና ጣልቃ ገብነት በተገቢ ሥልጣናቸው እየተመሩ የገዛ ራሳቸውን ዕድል እንዲመሩ ያላቸው ሥልጣን እንዲጠበቅላቸው የደከመ አፍሪካዊ ሕዝብ ነው …፡፡’’

ከ60 ዓመታት በፊት የኬንያው ‹‹የማኦ ማኦ›› ሕቡዕ ነጻ አውጭ ድርጅት መሪ የነበሩት ጆሞ ኬንያታ ለሰባት ዓመት ያህል በእንግሊዝ መንግሥት ታስረው ነበር፡፡ በወቅቱም የኢትዮጵያ መንግሥት ትምህርቷን በዩኒቨርሲቲ ትከታተል ለነበረችው ለጆሞ ኬንያታ ሴት ልጅ፣ በየወሩ ሁለት መቶ ሃምሳ የኬንያ ሽልንግ በኢትዮጵያ መንግሥት ጄኔራሌ ቆንሲሌ አማካይነት ይሰጣት ነበር፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያ ንጉሥ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ኬንያ ላይ ደርሶ ለነበረው ረሃብ ዕርዳታ የሚውል በኬንያ የብሪታንያ ተወካይ በነበሩት በሰር ሃምፍሬይ በኩል ሁለት መቶ ሃምሳ ሺኅ ሽልንግ ለኬንያ ዕርዳታ ልግስና አድርገዋል፡፡

የኬንያው የነጻት አባት ጆሞ ኬንያታ ከእስር እንደተፈቱ የሀገራችንን ውለታ በማሰብ ከሴት ልጃቸው ጋር በሀገራችን ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ነበር፡፡ በወቅቱም በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በቀድሞው የግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ልደት አዳራሽ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላደረጉላቸው ውለታ ምስጋናቸውን አቅርበው ነበር፡፡ ከዚህ ጽሑፍ ጋር ያያዝኳቸው ታሪካዊ ፎቶዎችም ይህንኑ የሚመሰክሩ ናቸው፡፡   

በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ለኬንያዊው የነጻነት ታጋይ ጆሞ ኬንያታ ብቻ ሳይሆን ለታንዛንያው የነጻነት አርበኛ ለጁለየስ ኔሬሬ ከኢትዮጵያ መንግሥት የወር ደመወዝ ተቆርጦላቸው ይከፈላቸው ነበር፡፡ ከዚህ የኢትዮጵያውያን ውለታ የተነሳም ታንዛናውያን ነጻነታቸውን ከተጎናጸፉ በኋላ የውጭ አገር ሰዎች ከታንዛንያ ሲባረሩ ስድስ መቶ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ቤተሰቦች ከኪሊማንጃሮ ተራራ አጠገብ በግብርና የመኖር መብታቸው ተጠብቆላቸው በክብር እንዲኖሩና ከአገር እንዳይወጡ ተደርጎ ነበር፡፡

በርካታ የአፍሪካ አገሮች በቅኝ ግዛት ቀምበር ስር ኾነው ይማቅቁ በነበሩበት ጊዜ ኢትዮጵያ እነዚህ አገራትና ሕዝቦቻቸው ነጻነታቸውን እንዲያገኙ በተለያዩ መንገዶች ስትረዳ ነበር፡፡ አፍሪካውያን በኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ነጻ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ፣ የኪስ ገንዘብ እንዲሰጣቸውና በተለያዩ የአገሪቱ ግዛቶችም ተደልድለው እንዲያስተምሩ ዕድል ተመቻችቶላቸው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡

በተጨማሪም አገራችን ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የነጻነት ታጋዮች ወታደራዊ ሥልጠና፣ ዕርዳታና ድጋፍ በማድረግም የበኩሏን ከፍተኛ የኾነ አስተዋጽኦ አድርጋለች፡፡ ለአብነትም ያህል የደቡብ አፍሪካው የነጻነት ታጋይ፣ ኔልሰን ማንዴላ፣ የዚምባቡዌው ሮበርት ሙጋቤና የበርካታ አፍሪካውያን የነጻነት ታጋዮች ወታደራዊ ሥልጠና በመስጠትና አስፈላጊ የኾነውን ዕርዳታ በማድረግ አፍሪካውያን ነጻነታቸውን ዕውን ማድረግ እንዲችሉ ትልቅ ሚና ተጫውታለች፡፡ ከኔልሰን ማንዴላ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠና ጋር ተያይዞም ጄ/ል ታደሰ ብሩ፣ ኮ/ል ፈቃዱ ዋኬኔ፣ ሻምበል ጉታ ዲንቃ የመሳሰሉ ጀግኖች ኢትዮጵያውን የሚታወሱ ናቸው፡፡  

በተመሳሳይም ኢትዮጵያ- የደቡብ አፍሪካው የኤ.ኤን.ሲ፣ የሞዛምቢኩ ሬናሞ፣ የናምቢያው ሰዋፖ ነጻ አውጭ ፓርቲዎች ከወታደራዊ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገርም በአዲስ አበባ ቢሮአቸውን እንዲከፍቱና ሕዝባቸውን መቀስቀስ እንዲችለ የሬዲዮ ሥርጭት እንዲኖራቸው በማድረግ በአፍሪካውያን የነጻነት ትግል ውስጥ የራሷ የኾነ ደማቅና ጉልህ አሻራን ትታለች፡፡ እንዲሁም የአንጎላ ቅኝ ገዢ ከሆነችውና ከአገራችን ጋር የረጅም ዘመናት ግንኙነት ከነበራት ከፖርቱጊዝ መንግሥት ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እስከማቋረጥ ድረስ የሄደችው በዚሁ ለአፍሪካውያን ነጻ መውጣት ከነበራት ትልቅ ፍላጎት የተነሳ ነበር፡፡

እንዱሁም ንጉሡ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ/የኢትዮጵያ መንግሥት ናሚቢያ ነጻነቷን እንድትጎናጸፍ ከነበራቸው ጥልቅ ፍላጎት የተነሳም ከላይቤሪያ ጋር በመሆን በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሁለት ጠበቆችን በማቆም ዘጠኝ ዓመታት ያህል ለናምቢያውያን ነጻነት ተሟግታለች፡፡

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውን ለአፍሪካ አገራት ነጻ መውጣት ካደረጉት ትግልና ካበረከቱት ትልቅ አስተዋጽኦ ባሻገርም የተባበረችና በልጆቿ ኅብረት የጸናች አፍሪካ ዕውን እንድትሆን፣ በመሪዋ በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ፣ በእነ ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ፣ በእነ ከተማ ይፍሩ፣ በእነ ክፍሌ ወዳጆ… በመሳሰሉ ወድ ልጆቿ አማካይነት አፍሪካ አንድነት ድርጅት/የአፍሪካ ኅብረት እንዲቋቋም ያደረገችው ታላቅ የኾነ አስተዋጽኦ በታሪክ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ እናም ሀገራችን ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን እናት መባሏ የሚገባት ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጭምር ያረጋገጠችው እውነታ ነው!!

 

ሰላም ለኢትዮጵያ! ሰላም ለአፍሪካ!!

Filed in: Amharic