>

መንግስት እንደትናንቱ እንዳያስብ! (ጌታቸው ሽፈራው)

መንግስት እንደትናንቱ እንዳያስብ!

ጌታቸው ሽፈራው
 የትህነግ ጉዳይ ቀይ መስመር ነው!
1) ከሕግ ማስከበር ዘመቻው በኋላ በየ መድረኩ የተደረጉ ያልተገቡ ድስኩሮች ሕዝባችን አዘናግተዋል። ትህነግ አፈር ልሶ እንዲነሳ ብዙ ስህተቶች ተሰርተዋል። አሁን መልሶ ማጥቃት ላይ ያለው መንግስት እንደባለፈው ካሰበ አደገኛ ነው። ትህነግ እንደባለፈው አያስብም። ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ አይቷታል። ባለፈው አመት ትህነግ አዲስ አበባ እገባለሁ እያለ ሲያስብ ለሌላው ጉዳይ ብዙም አልተዘጋጀበትም ነበር። አሁን ግን ትህነግ እንደዛ አያስብም። የከፋው ቢመጣስ ብሎ ያስባል። እንደባለፈው ተሸንፌ ጉድጓድ ውስጥ ብደበቅስ ብሎ ያስባል። መንግስት ትህነግን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን የከፋው ቢደርስብኝስ ያለ ትህነግ ምን ሊያደርግ ይችላል ብሎ ማሰብ አለበት። ራስን የከፋ ይገጥመኛል ብሎ በሚያስብ ትህነግ ቦታ አስቀምጦ ማሰለሰል ያስፈልጋል። ምን ሊያደርግ ይችላል? ብሎ ሳይንቁ እያንዳንዷን ነጥብ ማስቀመጥና መዘጋጀት ያስፈልጋል።
2) መከላከያ ሰራዊቱም አሁን የተለየ ነው። ትግራይ ውስጥ ያለ አግባብ ተጎድቷል። አሁን ሌላ እንዝላልነት አይፈልግም። ጥቅምት 24 ብቻ ሳይሆን ከዛ በኋላም ተመትቷል። በሕዝብ ማዕበል መትተውታል። አሁን ወደኋላ ወደፊት ከሚል መንግስትና አመራር ጋር መዛለቅ ይከብደዋል። በትህነግ ላይ ከሚወላውል አካል ጋር ጥል ውስጥ ይገባል። ከጎኑ የነበሩ ጓዶቹ በሕዝብ ማዕበል ተሰውተዋል። ተጎድተዋል። ጓዶቹ ሕዝብ አንመታም እያሉ በሕዝብ  ማዕበል ተጠቅተዋል። አገርህን የሚበትን ኃይል መጥቷል ተብሎ አዲስ ኃይል ሰልጥኗል። ይህ ኃይል ቃሉ እንዲጠበቅ ይፈልጋል። ጠላትህ ነው ያልከውን፣ እንደ ጠላት አይተህ እንድትመታው፣ እንዲመታ ይፈልጋል።
3) ሕዝብም የትናንትናው አይደለም። አማራና አፋር ክልል ላይ በተፈፀመ በደል ትህነግ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ካልተሸነፈ ሰላም አናገኝም ብሏል። የተፈናቃይ ካምፕ ውስጥ የነበሩ ንፁሃንን የጨፈጨፈ ኃይል ጋር የሚለሳለስ መንግስትን መልሶ ይገጥማል። ሰውና እንሰሳትን ሳይለይ የጨፈጨፈ ክፉ ጋር እደራደራለሁ ብሎ የሚያስብ መንግስት ቢኖር ሕዝብ ይተፋዋል። ይህን ያህል ያወደመ፣ የዘረፈ ቡድን ጋር ቁጭ እላለሁ የሚል አካል ካለ ሕዝብ ደመኛ ጠላቱ ያደርገዋል። ቄስ የገደለ፣ የቄስ ሚስት የደፈረ፣ ሲሰግዱ የነበሩ ደረሳዎችን የጨፈጨፈ፣ የ8 አመት ህፃንን ተሰብስቦ የደፈረ፣ ቤት ውስጥ አስከሬን የቀበረ፣ የተፀዳዳን ሰይጣን ቡድን ላቅርበው፣ ልየው የሚል አካል ጋር ሕዝብ ይጣላል። ይሄ ታውቆ ማደር አለበት!
 ከአራት ሚሊዮን በላይ የአማራ ሕዝብ ችግር ላይ በወደቀበት፣ በርካቶች በተጨፈጨፉበት፣ ብዙዎች በምግብና በመድሃኒት እጦት በሞቱበት፣ እየተሰቃዩ ባሉበት፣ እጅግ በርካቶች የንግድ ተቋማቸው ተዘርፎ፣ ተቋሞች ወድመው፣ መኖርያቸው ተራቁቶ፣ ሀብት ንብረታቸውን አጥተው በሚሰቃዩበት የመወላወልን መንገድ አንድ ስንዝር የሚራመድን ሁሉ ሕዝብ ይቀየመዋል።
4) የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢትዮጵያን ለማዳን ዋጋ እየከፈለ ነው። ልጆቹን መርቆ ሰጥቷል። ገበሬው እርሻውን ትቶ ዘምቷል። ባለሀብቱ ያለ የሌለ ንብረቱን እያወጣ ነው። እናቶች ስንቅ እያዘጋጁ ነው። ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን ወዲያ ብለው በአንድ ግንባር ተሰልፈዋል። ይህን ሁሉ የደከሙት ኢትዮጵያውያን ትህነግን ስለጠሉት፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሄ ለመስጠት ነው። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመንግስት ጎን የከረሙት፣ ሕዝብ  ከእነ በርካታ ችግሮቹ መንግስት ላይ ያለውን ተቃውሞ ለጊዜው ጋብ ያደረገው ትህነግ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተወግዶ የኢትዮጵያ ችግርነቱ ማብቃት አለበት ብሎ ስላመነ ነው።
5) ዓለም አቀፍ ማሕበረሰቡ መካከልም እየተቀየረ ያለ አካል አለ። ጎረቤት አገራት ትልሽ ለውጥ አሳይተዋል። ለበአል ሲመት ሳይሆን የመጡት ኢትዮጵያ ካለችበት ችግር ቀና ብትል ብለው ይመስለኛል። ለኢትዮጵያ ጠበቃ ሆነው የቀጠሉ አሉ። ምዕራባዊያን ሰበብ እየፈለጉ የሚፈጥሩት ሴራ ከድሮው የተሻለ እየታወቀ ነው። ኢትዮጵያ የምትሰማበት እድል እየተፈጠረ ነው። ቢያንስ ክፋት ባላሰቡት። በዚህ ወቅት መለሳለስ ዋጋ ያስከፍላል። ኢትዮጵያ እምነት የሚጣልባት አገር ለማፍረስ ላይ ታች የሚሉት ላይ ቆራጥ እርምጃ ወስዳ ውጋቷን ስታስታግስ  ብቻ ነው። አዲሱ መንግስት እየወጡ የሚዘላብዱ፣ ቲውተር ይሁን ጠላ ቤት ከራሱ አቋም ውጭ ወለም ዘለም የሚሉትን አደብ ማስገዛት አለበት። ካልሆነ ግን አንዱ ቲውተር፣ ሌላው ጠላ ቤት ወዘተ የሚዘላብዱት መንግስት የሕዝብን ልብ ትርታ ለመለካት የሚያደርገው ሆኖ ይቆጠርበታል!
6) በመወላወል ብዙዎችን ዋጋ አስከፍለናል። ኤርትራውያን ዋጋ ከፍለዋል። ከእኛ ጋር ተዳብለው ማዕቀብ ምናምን እየተባሉ የሚጨቀጨቁት በእኛ ችግር መሆኑ መታወቅ አለበት። ሕዝባችን ዋጋ እየከፈለ ነው። አሁንም ሌላ መወላወል፣ ሌላ ድልን ማግነን፣ ሌላ ትህነግን አቅልሎ ማየት፣ ሌላ የመድረክ ድንፋታ፣ ሌላ ስህተት የከፋ ዋጋ ያስከፍለናል። እንደ ትናንቱ ማሰብ በእጅጉ ይጎዳናል። ሁሉም ነገር ተቀያይሯል። ከአሁነ በኋላ የምንሰራው ስህተት ጉዳቱ እጅጉን የከፋ ነው።
7) የትግራይ ጉዳይም ተቀይሯል። አሁን ለአገርነት እየሰሩ ነው። በይፋ ኢትዮጵያ ጠላታችን ነች ብለው እየሰሩ ነው። ትህነግ የሚባለውን የዚህ ክፋት አስተባባሩ ማማሟት እስካልተቻለ ድረስ ቅስቀሳው ነገ ኢትዮጵያን አይምራትም።  ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሰለጠነው፣ ያን አስተሳሰቡን አውልቆ የሚጥለው ሲሸነፍ ብቻ ነው። እንደ ትናንቱ ሕዝብና ትህነግ ይለያያል የሚል ድስኩር ለኢትዮጵያ ቆይቶ የሚያቆስላት ፈንጅ እንጅ መድሃኒት አይሆንም። እነሱ ቆርጠው ሌላው ከወላወለ ዳግመኛ ኢትዮጵያ ትጠቃለህ፣ ሕዝቧ ስቃይ ይበዛበታል። ለዚህ ዳግም ስህተት የሚዳርግ መንግስት ላይ ሕዝብ መጀመርያ ፊቱን እንደሚያዞርበት መታወቅ አለበት!
*…. ትህነግ የኢትዮጵያ ደመኛ ነው!
 *…. ሁሉም ነገር መቀየሩን እንዳንረሳ!
*…. የትህነግ ጉዳይ ቀይ መስመር ነው!
ከሕዝብም፣ ከሰራዊቱም፣ ከወዳጅም ጋር መቀጠል የሚቻለው ቃልን በማክበር፣ ባለመናቅ ብቻ ነው! ጠላትን አደብ ማስገዛት የሚቻለው ሆኖ በመገኘት ነው!
ከትህነግ ጋር ባለ ግንኙነት የሚፈፀም ስህተት መዳኛ የሌለው ቀይ ስህተት ነው!
የኃይማኖት አባት ሆነ ፖለቲከኛ ባለሀብት ሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር በትህነግ ጉዳይ ውስጥ ውስጡን ሲሄድ ቢገኝ መጀመርያ የሚጋጨው በትህነግ እየተጎዳ ካለ ሕዝብ ጋር ነው! የሚጣለው ከኋላው ከተወጋው መከላከያ ሰራዊት፣ ኢትዮጵያ አትፈርስም ከሚል አገር ወዳድ፣ ልዩነቱን አሽቀንጥሮ በአንድ ግንባር ከተሰለፈ ኢትዮጵያዊ፣ ሁሉንም ነገር ለጦርነቱ ካደረገ አገር ወዳድ ጋር ሁሉ ነው!
 
Filed in: Amharic