>

ሸገር አዲስ አበባ የነፃነት ቻርተር ይገባታልን? (ያሬድ ጥበቡ)

ሸገር አዲስ አበባ የነፃነት ቻርተር ይገባታልን?

ያሬድ ጥበቡ

 

*…. ዛሬ የትግራይ ባለሃብት ሲፈናቀል: ሲታሰር: ሲወረስ ታጨበጭባለህ:: ነገ ደግሞ ያንተ ተራ ነው:: ዛሬ ከከፍተኛ የሥልጣን እርከኖች አግልለውሀል: ነገ ደግሞ ከቤት ንብረትህ ያገሉሃል: በተለይ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆንከውን:: ዛሬ ለምን እስክንድር በግፍ በእስር እንደሚሰቃይ ጠይቅ:: አልገባህም እንጂ ላንተ ሲል ነው:: ባለውለታህ ነው:: አሳሪዎቹ በእስክንድር ትብብር በይሁንታም ይሁን በዝምታ በመተባበርህ የሚያደንቁህ አይምሰልህ: ይንቁሃል እንጂ::

ባለፉት 11 ወራት “እረ ይሄ ጦርነት አያዋጣም: የትግራይ ህዝብ ድጋፍ ያለውን ህወሓት ትግራይ ውስጥ መደምሰስ አይቻልም” ብዬ እንደ ነቢይ በመናገሬ ሳያፍሩ በወያኔነት የሚከሱኝ ተነስተዋል:: ይህን ፅሁፌን ያንብቡና የዛሬ አምስት አመት እነርሱ የት እንደነበሩ እስቲ ከህሊናቸው ጋር ሂሳብ ያወራርዱ::

 እኔ ወያኔን እንዲታረሙ ስሞግት እነርሱ የወይፈኑ ቆለጥ ይወርድ እንደሁ ብላ ሗላ ሗላው ቱስ ቱስ ትል እንደነበረችው ውሻ ከበረከት ሗላ ይከተሉ ነበር:: እነዚሁ ጉዶች ዛሬ እኔ ተኩስ ማቆም ስምምነት ተደርጎ የትግራይ ህዝብም ምግብና መድሃኒት በአስቸኳይ ይድረስለት  የትግራይ ታጣቂም ከአማራ ክልል ይውጣ ስል: “እንዴት ተደርጎ ወያኔ ፍፁም ሳይደመሰስ ድርድር የለም!” ብለው ሲፈክሩ ይሰማሉ::
 በመለስ አባባል “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው!” ዳሩ:እነርሱ አይዋጉ በገበሬ ልጅ ህይወት እንጂ የሚቆምሩት:: ከትናንት በስቲያ እንዳልኩት ይህ ጦርነት በብልፅግና ቲዮሎጂ ማእከልነት የሚመራ ነገር ግን በሁለቱም ወገን የተዋህዶ ክርስትና ወጣቶች የሚተራረዱበት ወንጀል ነው::

ተዋህዶ ንቃ: እርስ በርስህ አትጋደል:: በጦርነት በደከመው ገላህ ላይ የሚጫንብህን የኦሮሞ ብልፅግና የበላይነት አስብ:: ዛሬ የትግራይ ባለሃብት ሲፈናቀል: ሲታሰር: ሲወረስ ታጨበጭባለህ:: ነገ ደግሞ ያንተ ተራ ነው:: ዛሬ ከከፍተኛ የሥልጣን እርከኖች አግልለውሀል: ነገ ደግሞ ከቤት ንብረትህ ያገሉሃል: በተለይ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆንከውን:: ዛሬ ለምን እስክንድር በግፍ በእስር እንደሚሰቃይ ጠይቅ:: አልገባህም እንጂ ላንተ ሲል ነው:: ባለውለታህ ነው:: አሳሪዎቹ በእስክንድር ትብብር በይሁንታም ይሁን በዝምታ በመተባበርህ የሚያደንቁህ አይምሰልህ: ይንቁሃል እንጂ:: ስለናቁህም ነው ጀግናህን በቂሊንጦ ይዘው በምርጫ ተብዬው ግርግር የአዲስ አበባን አስተዳደር: የኦሮሚያ ክልልንና ፌዴራል መንግስቱን ጭምር የኦሮሞ ብልፅግና የወረረው:: አንዴ ከሥልጣን ካገለሉህ: ቀጥሎ ከንብረትየመገለልህ ጉዳይ የጊዜ ጉዳይ ነው:: ይመጣልሃል!

ከዛሬው ዕለት ከአምስት አመታት በፊት እንዲህ ብለህ ነበር ብሎ ማስታወሻ ላከልኝ:: እንብቡት: ትደመሙበታላችሁ
ሸገር አዲስ አበባ የነፃነት ቻርተር ይገባታልን?
 
የእሬቻ 2009 ጭፍጨፋን ለማውገዝ የዕለቱ ለት ከኢሳቱ ዲሬክተር አበበ ገላው ጋር መድረኩን የተካፈለው ጃዋር መሀመድ በአፋን ኦሮሞ ስለ ኦሮሞ የነፃነት ቻርተርና ሰለ ሽግግር መንግስት ተናገረው ተብሎ ተአማኒነት ባለው የዋዜማ ሬዲዮ ከተዘገበ ወዲህ የተነሳው ውዝግብ ሁላችንም ስናብላላው የቆየነው ነው ።  በወቅቱ የዋዜማን ዘገባ እንዳነበብኩ ጃዋርን ደውዬ መጠየቄንና የሰጠኝን ማብራሪያ እዚህ ግድግዳዬ ላይ መለጠፌም ይታወሳል ። ጃዋር በሶስቱም ቋንቋዎች እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ጉዳዮች (እንደ ታዳሚው ጆሮ)ያቀርባል የሚለው ስሞታ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከተነሳው ውዝግብ ይልቅ፣ የኦሮሞዎቹን የአትላንታ ጉባኤ የሚያስቆመው ምድራዊ ሀይል እንደሌለ ስለገባኝ፣ አዲስ አበባዬስ የነፃነት ቻርተር ሊኖራት ይገባታልን? የሚል መብሰልሰል ውስጥ ገባሁ ። ቢገባትስ የአዲስ አበባ ነው የሚሆነው ወይስ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ቻርተር? ብዬም አሰበኩ ።
 
የጎጃምና ጎንደር የገበሬ ልጆች በዩኒቨርሲቲ ቆይታዎቻቸው ወቅት በተለያዩ ካምፐሶች ውስጥ ከተማሩት የብሄረሰቦች ግንኙነት የተነሳ፣ ሁሌም የተናጠልና ብቸኛ የሆነው ህይወታቸው ከትግሬዎቹና ኦሮሞዎቹ ጋር ሲመዘን ጉዳቱ ገዝፎ እየታያቸው ሲመጣ እንደ አማራ መሰባሰብና ሁለት ሶስት እየሆኑ መምከር የሚገደዱበት ሁኔታ የተከሰተ ይመስለኛል ። አቅመ ቢስ ለመሆናቸውና መጎዳታቸው ደግሞ ህጋዊ እውቅና ያልተሰጠው የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ሰለባዎች ስለሆኑ መስሎ ተሰማቸው ። ይህ ስሜት ቀስ በቀስ ሲብላላ ከርሞ፣ እነዚህ ወጣቶች በግል የኮሌጅ ህይወታቸው ያዩት መገለል፣ በስፋትም የአማራ ብሄር እጣ መሆኑ ተገለፀላቸው ። ስለሆነም የአማራ ማንነታቸውን ይፈልጉና ይፈለፍሉ ገቡ ። አንዳንዶቹ የመገንጠል መብትን እስከመጠየቅ የሚሄድ ሀሳብ ላይ ተስማሙ ። ይህ ሂደትም ከወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ጋር ተዳብሎ ባለፉት ወራት በመገረምና በአድናቆት ያየነውን የአማራ ተጋድሎ ወለደ ። ይህ የኔ ንግርት ነው ። ሌሎች ትርክቶች እንደሚኖሩ እርግጠኛ ነኝ ።
 
ይህ የአማራ ተጋድሎ ግን አንድ ትልቅ ታሪካዊ ዳራም ፈጠረ ። የአማራ ብሄርተኝነትና ኢትዮጵያዊነት መፋጠጥ የሚገደዱበትን ሁኔታ ። ጎንደርና ባህርዳር  በተደረጉት ሰልፎች “የፈሰሰው የኦሮሞ ደም የኛም ነው” የሚል መፈክር መውጣቱና የበቀለ ገርባ ፎቶዎች መያዛቸው ያስቆጣቸው የአማራ ተጋድሎ ቄሮዎች ነበሩ ። በሌላ በኩል የአማራ ብሄርተኝነት መድረክ ላይ በመውጣቱና የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን የሚገዳደር ሆኖ መታየቱን፣ አንዳንዶች ግልግል ነው ብለውታል ። “ስለ ኢትዮጵያ ብሄርተኝነት አፋችንን በከፈትን ቁጥር የተደበቀ የአማራ ትምክህተኝነት ነው ከሚል ክስና ጥርጣሬ ነፃ አወጣን” የሚሉ ድምፆች ተሰምተዋል ። በግልፅም ባይሆን በጆሮ ሹክሹክታ ። የኦሮሞ ብሄርተኝነትም ይህን የፖለቲካ ሂደት በወንድማዊ መንፈስ የተቀበለው ነው የሚመስለው ። ኦሮሞ ብሄርተኝነት ወደመሃል ሲመጣና “በአድዋም በማይጨውም የተሰውት የኔ ፈረሰኞች ነበሩ፣ ኢትዮጵያን ለመረከብ ዝግጁ ነኝ” ሲል የአማራ ብሄርተኝነት መሀሉን ለቆ ወደዳር መሄዱ አልታወቀንም እንጂ ከታላቅ የመሬት መሰንጠቅ የማይተናነስ ፍፃሜ ነበር ። እንደ ሁሌውም ግን የኛ ነገር ምሁራኖቻችን ሳይዘጋጁ ሰልፈኛው ነው የሃገሪቱን እጣ የሚወስነው ።
 
በዘህ ሁሉ መሃል የኔይቱ አዲስ አበባ ዕጣዋ ምን   ይሆን ብዬ ማሰቤ አልቀረም ። 
ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ
ሃገርም እንደ ሰው ይናፍቃል ወይ? እያልኩ በመሸታ ቤት ክራር እንኳኳለሁ ። አዱ ገነት ናፍቃኛለች ። እንደ ናፍቆቴ ከሆነ ጃዋር በሰየመው “የፍፃሜ ጦርነት” ወቅት የሰላሌ ዘመዶቼን አሰልፌ በእንጦጦ በኩል መምጣቴ የማይቀር ነው ።
 ዱሮ “የፍፃሜ ጦርነት” የምንለው የላብአደሩን ተጋድሎ ነበር፣ ዛሬ የተገላቢጦሽ ሆኖ የኦሮሞ ጎበዝ አለቆች ተጋድሎ ስሙን ወርሶታል ።  ይሁን፣ ተሸነፍንም ሆነ አሸነፍን ቁም ነገሩ መታገላችን ነው የሚል እምነት አለኝ ። ቢያንስ የልጅ ልጆቻችን የሚዘክሩት ታሪክ እንተውላቸዋለን። “አያቶቻችን እምቢ ለመብቴ ብለው በ60 አመታት ውስጥ ሶስት አብዮቶች ቀስቅሰው በሁሉም ተሸንፈው በመጨረሻ እንጦጦ እግር ስር ደርሰው ተደመሰሱ” ቢሉ እመርጣለሁ። ወያኔ የሚባል አጋሚዶ ፈርተው ሲሸሹ አይሲስ የሚባል ዘንዶ ቀረጠፋቸው ከሚሉ ። 
 
ይህም ሆኖ ግን ጃዋር የሚለው “የፍፃሜ ጦርነት” አዲስ አበባዬን እንዴት ሊያደርጋት ነው? የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም የሚለው ሰይጣናዊ ሀረግ ህገመንግስቱ ውስጥ ሆን ብሎ ከተሰነቀረ ጀምሮ የአዲስ አበባ ነዋሪ ማንነቱ ያልታወቀ የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ ካርድ ሆኗል ። ወያኔ አዲስ አበባን የኦሮሞ ብሄርተኝነትን መከፋፈያ፣ ማባበያና እንቁልልጫ ማድረጊያ እቃ አድርጎት ሩብ ክፍለዘመን ሙሉ ሰብኳል ። በፀረ ወያኔው ተጋድሎ ሂደት፣ ወያኔ እድሜውን ያራዘመው በኦሮሞና አማራ ብሎም ኢትዮጵያ ብሄርተኝነቶች መሀል ፍጭትና መገዳደርን በመፍጠር መሆኑ ለሁሉም ግልፅ ስለሆነ ፣ የአዲስ አበባም የማንነት ጥያቄ መፍትሄ ያገኛል ብዬ አስባለሁ ። 
 
የኦሮሞ የነፃነት ቻርተርን ለማርቀቅ የዛሬ ወር አትላንታ ላይ ሲገናኙ፣ ይህን የአዲስ አበባን ሁናቴ ይመክሩበታል ብዬ አስባለሁ ። በእኔ አስተያየት አዲስ አበባ በኦሮሞዎች፣ በአማሮች፣ ጉራጌዎች፣ አረቦች፣ ኤርትራውያን፣ ግሪኮችና አርመኖችወዘተ ተመስርታ፣ ባለፉት አስር አመታት ደግሞ የትግሬዎች መሰረተ ልማት ታክሎባት አንድ ዘመናዊ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማእከል መሆን የቻለች የኢትዮጵያ ርእሰ ከተማ ወይም መዲና ናት ። አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ማእከል የመሆንዋን ያህል፣ ከኮሌጆቿ እቅፍ የኦሮሞንና የትግሬን ብሄርተኝነት የወለደች አመፀኛም ናት። የጋሼ አሰፋ ጨቦን አማርኛ ተውሼ ላሻሽልና አዲስ አበባ “የጋራ ቤታችን” ውስጣዊ መቅደስ ናት። ተንከባክበን ልንይዛት ይገባል ። 
 
የፖለቲካ ማእከሉን ትግሬም ያዘው ኦሮሞ፣ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር ያለ ኢትዮጵያ ብሄርተኝነት መቆምም ሆነ መጠንከር ስለሚቸግራት፣ ሁሉም የፖለቲካ ሀይሎች አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት inner sanctum
መቅደስ መሆኗን ቢቀበሉ ይጠቀማሉ እንጂ አይጎዱም ። ወያኔ ይህን ምክር 25 አመታት ሙሉ አልሰማም ብሎ አሁን የሚያድርበትን የዛፍ ላይ መኝታ ማየት ነው ።  በእኔ እምነት አዲስ አበባ ከብሄርተኛ ንቅናቄዎች ነፃ መሆን ይገባታል ። ነዋሪዋም ከኢትዮጵያዊነቱ ውጪ የዘር ማንነቱን የሚያሳይ መታወቂያ ካርድ ሊኖረው አይገባም ። በከተማዋ የ125 አመታት ታሪክ ሲዳቀል የኖረ የሰለጠነ ከተሜ በመሆኑም፣ ከዚህ ኮስሞፖሊታን ባህርዩ የሚመጥነው ብሄርተኝነት ኢትዮጵያዊነት ብቻ  ነው ። 
 
ኢትዮጵያዊነት አፋሩ፣ ሱማሌው፣ አማራው ወዘተ በፓስፖርቱ ላይ የሚያሳየው የዜግነቱ መታወቂያ ሳይሆን፣ ወይም የነዚህ የተለያዩ ትናንሽ ብሄርተኝነቶች የድምር ውጤት ሳይሆን፣ ራሱን የቻለ የሚንቦገቦግ ቃጠሎ ነው ። ሰው ከቀዬው ዘሎ ርቆ ሲያስብና ከዘሩ ውጪ ያለ ኢትዮጵያዊ መጎዳት ሲያንገበግበው ያኔ ኢትዮጵያዊ የሚሆን ይመስለኛል ። ይህን ስሜት ማክበርና የሚገባውን ቦታ መስጠት ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ። ማይጨው ላይ ዘምቶ ታሪክ የሰራው የሰላሌው አብቹ ኢትዮጵያዊ ነበር ። መተማ  ላይ የወደቀው ዮሀንስ ኢትዮጵያዊ ነበር ። እኔ መንደር እስካልመጡ ምን አገባኝ አላሉም ። የሃገር ሉአላዊነትን የሚረዳና ውድ ህይወቱን ለመስጠት የሚተጋ ጀግና ኢትዮጵያዊ ነው ። ይህን የመስዋእትነት ስሜት ማክበር ከተገቢ በላይ ነው ። ባለፉት 25 አመታትም ወያኔ ሲያጥላላውና ሲቀጠቅጠው የኖረው ሃገራዊ አርበኝነት ነው ። አትላንታ ላይ የሚመክረው የኦሮሞ የነፃነት ቻርተር ኢትዮጵያዊነትን ንቆ ሊያልፈው የሚችል ሳይሆን አክብሮ የሚገባውን መቀመጫ የሚለቅለት ሊሆን ይገባል ብዬ አምናለሁ። 
 
እኔ አጠቃላይ መንገድ ከማሳየት ውጪ አቅም የለኝም ። የአዲስ አበባ ቻርተር ምን ሊሆን እንደሚገባው ግን ይመለከተናል የሚሉ የከተማዋ ምሁራንና በህይወት የተረፉ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች ዝርዝሩን ሊያስቡበትና ፣ የማይቀረው የፍፃሜ ጦርነት የአዱ ገነትን በር ከማንኳኳቱ በፊት ለውይይት ሊጋብዙን ይገባል ። በተለይ በአዲስ ነገር፣ በዋዜማ፣ በዞን ዘጠኝ፣ በኢትዮ ቲዩብ ወዘተ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ወጣት ምሁራን ። ቦታችሁን ውሰዱ፣ ጊዜው የናንተ ነው ። አይዞን!
Filed in: Amharic